Dehai

Goolgule.com: በአዲስ አበባ የተወረረው መሬት፣ ባለቤት አልባ ቤቶችና ሕንጻዎች ይፋ ሆኑ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 28 January 2021

በአዲስ አበባ 1 ሺሕ 338 ሄክታር መሬት አሁንም በወረራ ተይዞ እንደሚገኝ አስተዳደሩ አስታወቀ። የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ በህገወጥ መሬት ወረራ ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

ወይዘሮ አዳነች በዚህ ጊዜ እንዳሉት በአዲስ አበባ ካሉ 121 ወረዳዎች ውስጥ በ88ቱ የመሬት ወረራ ተፈጽሟል።

በአጠቃላይ በከተማዋ 1 ሺህ 338 ሄክታር መሬት የተወረረ ሲሆን በተደረገው የህንጻ ቆጠራ 322 ህንጻዎች እና ቤቶች ባለቤት አልባ መሆናቸውን ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል። ወይዘሮ አዳነች በዚህ ጊዜ እንዳሉት በአዲስ አበባ በህገወጥ መንገድ 21 ሺህ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህገወጥ መንገድ ተይዘው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቤቶች ውስጥ 15 ሺህ 891 ቤቶች የባለቤትነት መረጃ አልቀረበባቸውም። 850 ቤቶች ደግሞ ዝግ ሆነው ሲገኙ 4 ሺህ 530ዎቹ ደግሞ ባዶ ሆነው መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ዝርዝር ማብራሪያው እንደሚከተለው ነው፦

– በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ 13,389,955 ካሬ ወይም 1,338 ሄክታር መሬት በህገወጦች ተይዟል። በከተማዋ ካሉ 121 ወረዳዎች በ88ቱ ወይም በ73 % በሚሆኑት ላይ ወረራ ተፈፅሟል።

– በአጠቃላይ ባለቤት አልባ በሚል የተለዩ ህንፃዎች በድምሩ 322 ሲሆኑ የቦታ ስፋታቸው 229,556 ካሬ ነው። ከነዚህ ውስጥ ግንባታቸው የተጠናቀቁት 58 ሲሆኑ 125፣ 409 ካሬ ላይ ተገንብተውና ተከራይተው ያሉ ነገር ግን ባለቤት ነኝ የሚል አካል መረጃውን እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ማቅረብ ባለመቻላቸው ባለቤት አልባ ሆነው ተገኝተዋል።

– ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ እንዲሁም ባለቤታቸው ያልታወቁ ህንፃዎች ብዛት በድምሩ 264 ሲሆኑ ስፋታቸው ደግሞ 104,147 ካሬ ላይ ያረፉ ቤቶች እና ህንፃዎች ናቸው። እነዚህ ቤቶች በተለይ በየካና በላፍቶ ክ/ከተሞች ላይ በአንድ አካባቢ መሬት በመውረር ግንባታ የተገነባባቸው ናቸው።

የኮንደሚኒየም ቤቶችን በተመለከተ፦

– በህገወጥ መንገድ የተያዙ የጋራ መኖርያ ቤቶች በጠቅላላው 21,695 ሲሆኑ 15, 891 የጋራ መኖሪያ ቤቶች መረጃ ያልቀረበባቸው ናቸው።

– 4530 ባዶ የሆኑ ፣ 850 ዝግ የሆኑ ፣ እና 424 በህገወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው ይገኛሉ።

– በዕጣ ሳይሆን በተለያዪ አግባቦች ወደ ተጠቃሚው ግለሰቦች የተላለፉ ደግሞ 51,064 ቤቶች ተገኝተዋል፡፡

– በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው ባለዕጣዎች ስም ዝርዝር እና በመስክ በተገኘው የተጠቃሚዎች የስም ዝርዝር መሀከል ልዩነት ያላቸው ቤቶች 132,678 እንደሆኑና 18,423 ቤቶች ደግሞ የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው ናቸው። በእነዚህ ቤቶች የሚኖሩ ግለሰቦች መረጃቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም መረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ በመሆናቸው ቤቶቹ በህገወጥ መንገድ የተያዙ መሆናቸውም ታውቋል።



ያልተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች በተመለከተ፦

28 ብሎክ ማለትም ከ782 እስከ 842 የሚሆኑ ቤቶች እና የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች (ኮሚናል ) ደግሞ 83 ሳይገነቡ መቅረታቸውን ተገልጿል።

በፌደራል እና በአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች በተሰራው የኦዲት ውጤት መሰረት በአጠቃላይ ላልተገነቡ ህንፃዎች የቦርድም ሆነ የስራ አመራር የውሳኔ ቃለ ጉባኤ አልተገኘም።

ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ፥ ምንም እንኳን መረጃ ባይገኝም ለግንባታው ክፍያ አልተከፈለም ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር በኦዲት ጥናቱ ማመልከቱን ገልፀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚተዳደሩ 150 ሺህ 737 የቀበሌ መኖሪያ እና ንግድ ቤቶች አሉ፡፡ ዛሬ ይፋ በሆነው ጥናት ተደራሽ መሆን የተቻለው 138 ሺህ 652 የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን እንደሆነ ተገልጿል።

በከተማዋ 10 ሺህ 565 የቀበሌ ቤቶች በቁልፍ ግዥ፣ ሰብሮ በመግባት ፣ እና በሌሎች ህጉ  ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ እንደተያዙ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።

በጥናቱ ተደራሽ ከተደረጉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ፡-

1ኛ. 7,723 ቤቶች ውል በሌላቸው (ህገወጥ) በሆኑ ሰዎች ተይዘዋል፡፡

2ኛ. 2,207 የቀበሌ ቤቶች ወደግል የዞሩ፣

3ኛ. 265 በሶስተኛ ወገን የተያዙ፣

4ኛ. 164 ኮንደምንየም በደረሳቸው/የራሳቸው ቤት ባለቸው ሰዎች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው ታውቋል።

5ኛ. 137 ለመኖሪያነት የሚያገለግሉ የቀበሌ ቤቶች በሽያጭ ወደ ግል የተላለፉ፤

6ኛ. 1 ሺህ 243 ታሽገው/ተዘግተው የተቀመጡ፣

7ኛ. 5 ሺህ 43 የፈረሱ፤

8ኛ. 180 አድራሻቸው የማይታዎቁ/የጠፉ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዳሉ ተረጋግጧል፡፡

የቀበሌ ንግድ ቤቶችን በተመለከተ፦

በአጠቃላይ የንግድ ቤቶች ብዛታቸው 25,096 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በህገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ የንግድ ቤቶች ብዛት 4,076 ናቸው።

1ኛ. 1 ሺህ 70 የንግድ ቤቶች ውል የሌላቸው ነጋዴዎች እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ተለይቷል

2ኛ. 2 ሺህ 451 የቀበሌ የንግድ ቤቶች ከአንድ በላይ የንግድ ቤት በያዙ 1,086 ነጋዴዎች እንደተያዙ ተለይቷል

3ኛ. 376 የቀበሌ ንግድ ቤቶች ደግሞ በተከራይ ተከራይ በሶስተኛ ወገን መያዛቸው ተለይቷል፣

4ኛ. 179 የታሸጉ የንግድ ቤቶች እንዳሉ ተለይቷል፡፡ (መረጃው የተጠናቀረው ከፋና፤ የአዲስ አበባ ፕሬስና ቲክቫህ)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


6ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 6 - ERi-TV Documentary

Dehai Events