Dehai News

(አማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት) ከኤርትራ የእርሻ ሚኒስቴር በየደረጃው የተውጣጡ 12 ምሁራንን ያካተተ የኤርትራ ልዑክ በአማራ ክልል የሚገኘውን የቆጋ የመስኖ ግድብ ጎበኘ፡፡

Posted by: Semere Asmelash

Date: Tuesday, 10 December 2019

Amhara Mass Media Agency
10 December 2019 

ከኤርትራ የእርሻ ሚኒስቴር በየደረጃው የተውጣጡ 12 ምሁራንን ያካተተ የኤርትራ ልዑክ በአማራ ክልል የሚገኘውን የቆጋ የመስኖ ግድብ ጎበኘ፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረው ሠላም ዘርፈ ብዙ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እንደሚጠቅምም ጎብኚዎቹ ተናግረዋል፡፡

የቆጋ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት በምዕራብ ጎጃም ዞን ሜጫ ወረዳ የተለያዩ አትክልት እና ፍራዎችን በማልማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቱ ከ10 ሺህ በላይ አርሶ አደር ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እያደረገ ሲሆን 7 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ለክልሉና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ልማት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ከኤርትራ የእርሻ ሚኒስቴር በየደረጃው የተውጣጡ 12 የመስኖ ልማት መሐንዲሶች እና ባለሙያዎች የፕሮጀክቱን ሁለንተናዊ አደረጃጀት በመጎብኘት ተሞክሮዎችን መውሰድ ችለዋል፡፡ ከጎብኚዎች መካከል አቶ ገብረመስቀል ተወልደ ‹‹በጉብኝቱ የውኃ አጠቃቀም ስልት፣ በተለይ የቦይ ዝርጋታው እና የአርሶ አደሮች የውኃ አጠቃቀም እና አደረጃጀት የተሻለ ሆኖ በማግኘቴ ልምድ ቀስሜያለሁ›› ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ለአርሶ አደሮቹ የገበያ ትስስር በመፍጠር የተለያዩ ሰብሎችን እንዲያለሙ ቢያደርግ የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርገው አቶ ገብረመስቀል መክረዋል፡፡

አቶ ገብረመስቀል ‹‹የኤርትራ ኢኮኖሚ 80 በመቶ ግብርና ነው፤ ስለዚህ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስስ ወንዝ ስለሌለን እያንዳንዷን የውኃ ጠብታ በመጠቀም ነው እያለማን የሀገራችንን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የቻልነው›› ብለዋል፡፡ ለጉብኝቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በሀገራቸው ላይ ያሉ ያህል እንደተሰማቸውና በሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት እንደተደሰቱም ተናግረዋል፡፡

‹‹ድሮ በእኛ መካከል ተከስቶ በነበረው ግጭት በርካታ የሰው ሕይወት አልፏል፤ ብዙ ንብረትም ወድሟል፡፡ ይህ በጣም ያሳዝናል፤ ስለዚህ ሁለቱም ሀገራት ይህን ማካካስ የሚችሉት የተለያዩ ተሞክሮዎችን በመለዋወጥ ሁለንተናዊ ዕድገታቸውን በማፋጠን ነው›› ያሉት ደግሞ አቶ ኢዮብ ገብረመስቀል ናቸው፡፡ ‹‹አሁን የጎበኘነው የግብርና ልማት እንቅስቃሴን ነው፤ ወደፊት ሁለቱም ሀገራት ግንኙነታቸውን በማዳበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት የሚያጋጥሟቸውን ክፍተቶች ሊሞሉ ይገባል›› ብለዋል አቶ ኢዮብ፡፡

ኤርትራ “ገርሰት” እና “ከርከበት” የተባሉ ሁለት የመስኖ ግድቦች አሏት፡፡ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ በማግኘት በስድስት ወራት ውስጥ 30 አነስተኛ ግድቦችን በመገንባትም ውኃን በማጠራቀም እያለማች ትገኛለች፡፡ እያንዳንዱ ግድብ ከ100 ሺህ እስከ 300 ሺህ ሜትር ኪዩብ ውኃ መሸከም እንደሚችሉ ከጎብኚዎቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮም የኤርትራ ጎብኚ ልዑክ አባላት የሰጡትን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ገልጧል፡፡

ዘጋቢ፡- ብሩክ ተሾመ



EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events