World News

Goolgule.com: “ቄሮ አልሸባብ” ነው – ህወሓት!

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Wednesday, 10 January 2018

“ቄሮ አልሸባብ” ነው – ህወሓት!

 
  • “ስድስት ሚሊዮን ወጣት በጠላትነት ፈርጀህ ማንን ልታስተዳድር ነው?” ለማ መገርሳ

ህወሓት/ኢህአዴግ በኢትዮጵ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በምሥራቅ ሐረርጌ “ቄሮ” በመባል የሚታወቅ ሕገወጥ እንቅስቃሴ እመረምራለሁ፤ ለፍርድ አቀርባለሁ ብሎ ዝቷል። “አመራሩ ብቃት የለውም” በማለት ራሱን የገመገመው ህወሓት/ኢህአዴግ ብቃት አልባነቱን ተገንዝቦ ራሱን ከሥልጣን ማግለል ሲገባው አሁንም የማሰርና የማሰቃየት ግፉን በስፋት ለመቀጠል በዕቅድ ለመቀንቀሳቀስ ማሰቡን ነው በዚህ ዜና የገለጸው።

የኢትዮጵያ ወጣቶችን በሥራ በማሰማራት ለአገር እንዲጠቅሙ ከማድረግ ይልቅ “አደገኛ ቦዘኔ” በማለት ሲፈርጅና ሲስር የነበረው ህወሓት አሁን ደግሞ በኦሮሞ ወጣቶች “ቄሮ” ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ለመሰንዘር ጎራዴውን እየሳለ ነው። ግፉ የበዛባቸው ወጣቶች ታላቁ ሩጫ በተካሄደበት ባንድ ወቅት ላይ “አደገኛ ቦዘኔ ራሱ ወያኔ” በማለት ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

“ማዕከላዊን እዘጋለሁ፤ ለአገራዊ መግባባት ሲባል እስረኞችን እፈታለሁ” በማለት በአደባባይ የለፈፈው ህወሓት/ኢህአዴግ “ቄሮ” ላይ ዘመቻ በመክፈት በርካታ ማዕከላዊ ለመክፈት ማቀዱንና በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችን ለማሰቃየት መወሰኑን ይፋ አድርጓል። ይህንኑ የህወሓትን ሃሳብ የሚደግፉ አቀንቃኞቹ “ቄሮ” ማለት “አልሸባብ” ነው፤ እንደ አልሸባብ መታየት አለባቸው እያሉ ነው። የሁለቱም ቃል ትርጉም “ወጣት” ማለት ነው።

በቄሮ ላይ የተነሳውን ዘመቻ አስመልክቶ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ ባልደረቦች መርጋ ዮናስና አርያም ተክሌ ያጠናቀሩትን ከዚህ በታች አቅርበናል።

የፌዴራል ፖሊስ የ“ቄሮ” ምርመራ በኦሮሚያ ክልል 

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሐረርጌ ዉስጥ በሚንቀሳቀሰው “ቄሮ” በመባል በሚታወቀው የወጣቶች ቡድን ላይ ምርመራ እንደጀመረ የሀገር ዉስጥ ዘገባዎች አመልክተዋል።

የአሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ዳንዳኣ ኮሚሽኑ ይህን ሥራ መጀመሩን የሚያሳይ ምንም መረጃ እንዳልደረሳቸዉ ይናገራሉ።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገባው በእንቅስቃሴው ዉስጥ ቄሮዎቹ ብቻ ሳይሆኑ የአካባቢ ሚሊሽያዎች፣ ፖሊሶችና የወረዳ አመራሮች እንደተሳተፉ ይጠቅሳል። ኮሚሽኑም “ቄሮ” እንዴት እንደተደራጀና አላማዉም ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ ዘገባዉ አክሎበታል። የ“ቄሮ” እንቅስቃሴ የመከላከያና የፌዴራል ፖሊስ አባላትን ተልዕኮ አስተጓጉሏል፤ በአካባቢዉ ስጋት ፈጥሯል መባሉም እንደምክንያት ተቀምጧል።

የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምሕርና የበየነ መረብ (ኢንተርኔት) ፀሐፊ ስዩም ተሾመ ግን ወጣቶቹ ለማህበረሰቡ ጥያቄ መልስ ለማስገኘት የሚታገሉ እንደሆኑ አስረድተዋል። የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር የወጣቶቹን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ጥናት ላይ እንደሚገኝ አቶ ስዩም ይናገራሉ። ምክንያቱም አዲሱ የክልሉ መስተዳድር ወደ ስልጣን የመጣዉ ወጣቱ ትዉልድ ወይም “ቄሮ” በፈጠረዉ ጫና አማካኝነት በመሆኑ ባይ ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ የዛሬ ሁለት ወር ገደማ በድርጅታቸዉ በኦሕዴድ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር “እኛ የፈጠርነዉ ወጣት ትዉልድ ስራ ስላጣ ብቻ ነዉ ወይስ ሌላ ጉዳይ ስላለ ነዉ የጠላን?” በማለት ተሳታፊዎቹን ጠይቀው እንደነበር ይታወሳል። ያኔም ስለ “ቄሮ” ያላቸዉን አስተያየት እንደሚከተለው ገልጸው ነበር።  “ቄሮ ቄሮ ቀሮ፣ እሺ ቄሮ ምንድነዉ? ቄሮን ጠላት አድርጋችሁ ታያላችሁ። ቄሮ ማለት ወጣት ማለት አይደል በአፋን ኦሮሞ? ቁጥሩ በተለይ እየጨመረ ያለውን ስድስት ሚሊዮን ወጣት በጠላትነት ፈርጀህ ማንን ልታስተዳድር ነው? እኛ ሁላችንም እዚህ አንቆይም። የፓርቲዉን አላማ የሚያስቀጥሉት ወጣቶቹ ናቸዉ” ብለው ነበር።

በአሮሚያ ክልል በፍትህ ቢሮ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ዳንዳኣ “ቄሮ” የማሕበረሰቡ ወሳኝ አካል ስለሆነ እነዚህን ወጣቶች በማግለል ወይም እንደ ወንጀለኛ በመፈረጅ እድገትና ሰላም ማምጣት እንደማይቻል የክልሉ መንግስት እንደሚረዳው ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

እንደ አቶ ታዬ አስተሳሰብ፣ ቄሮ የሚባል የወጣት ቅንጅት በምሥራቅ ሐረርጌ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በክልሉና በሀገሪቱ የሚንቀሳቀስ ቡድን ነው። የሕግ በላይነት በየትም ቦታ ሊከበር እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ታዬ እስካሁን ቄሮ ተደራጅቶ ወንጀል አለመፈጸሙን አረጋግጠዋል።

የድምጽ መልዕክቱ ከዚህ በታች ይገኛል።

Audio Player

 

 

 

(ምስል፡ የቄሮና የአልሸባብ ምልክቶች ከኢንተርኔት የተወሰዱ)

 
 

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events