Dehai

ለምን ይረሳል?

Posted by: Brhane Woldu

Date: Friday, 26 February 2021


የወያነ መሪዎች በውርደት ለተጎነጩት የሞት ጽዋ ጠንቅ የሆነውን የእብደት እርምጃ በሰሜን እዝ ላይ የወሰዱት ምን ሆነው ነው? እስከዚህ ድረስ ከሃዲዎች ናቸው ወይ?

ከዚያስ በኋላ በማይካድራ ጀሌዎቻቸውን ኣሰማርተው ምንም በደል ያልፈጸሙ ንጹሐንን ሲጨፈጭፉስ ትንሽ ሰብዓዊ ርህራሄ የላቸውም ወይ? የሚሉና ሌሎችም መሰል ጥያቄዎችን በመገረም የሚያነሱ ሰዎች ኣልታጡም፥

በተጨማሪም ገና የወያኔነት እብደት ያልለቀቃቸው ኣብዛኛዎቹ በውጭ ኣገር የሚቀመጡ ደቀ መዛሙርቶቻቸውና ነጭ ቅጥረኞቻቸው ሰለ ወያነ የምናውቀውን ሓቅ ሊያስረሱን፥ ዓለምንም ይህንን ሐቅ እንዳያይ በሓሰት ኣቧራ ሊያሳውሩት ሲፍጨረጨሩ ይደመጣሉ::

ከላይ ጠቀስ ያደርግኋቸውንና መሰል ጥያቄዎችን በገራገርነት ለሚያነሱ ኣንዳንድ ሓቆችን ለማስታወስ፥ ገና በቅዠት ውስጥ ሆነው የባጥ የቋጡን የሚለፈልፉትን  ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ደግሞ ለማያቃችሁ ታጠኑ ለማለት ለምን ይረሳል? የሚል ኣርእስት ማንሳትን መርጫለሁ።

የሰሜን እዝ በትግራይ ለዓመታት ከህዝቡ ጋር የኖረ፥ ብዙ ደግ ስራዎችን የሰራ፥ ኣብሮ የበላ ኣብሮ የጠጣ፥ የተወዳጀ ወዘተ መሆኑ የታወቀ ሆኖ ሳለ የወያነ መሪዎች በውድቀተ ሌሊት ባልታሰበ ሰዓት በጥይት ደበደቡት፥ በካራ ቀሉት፥ በሳንጃ ዘለዘሉት፥ ሴት ወታደሮችን ሳይቀር ጡት ቆረጡ፥ ብዙዎችን ኣሰልፈው በሲኖ-ትራክ ጨፈለቋቸው፤  በዚህ አረመኒያዊ እርምጃ የወደቁትን የሰራዊቱን ኣባላት ሬሳ፡ ኣፈር ሰስተውለት ቀብር ሳይፈጽሙለት ለሰማይ ኣሞራ፥ ለዱር ኣራዊት ሰጡት። ይህ ዓይነቱ ክህደት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ስለሆነ ግርምት የሚፈጥር ነው። የዚህ ክህደት ፈጻሚዎች የወያነ መሪዎች መሆናቸው ከግምት ሲገባ ግን ሁኔታው የተፈጠረው ግርምት ኣቅም ያጣል። ምነው ቢሉ የዚህ  ጭፍጨፋ መሪዎችና ፈጻሚዎች ይህን መሰሉ ክህደትና ኣረመኔነት ዛሬ ሳይሆን ገና ከጥንቱ ከጠዋቱ ወያነ” ብለው የተጠመቁበት መለያ ጠባያቸው ስለሆነ። 

በትጥቅ ትግሉ ወቅት ከነሱ ድርጅት በተጨማሪ በትግራይ ይንቀሳቀስ በነበረው “ተጋድሎ ሓርነት ትግራይ በተባለው ድርጅት የኣመራር ኣባላት ላይ የተጠቀሙበት ማዘንጋትና ግድያ ለዚህ ተጠቃሽ ኣብነት ስለሆነ የሚረሳ ኣይደለም፡ ለምንስ ይረሳ?

የወያኔ መሪዎች የዚህን ድርጅት ኣመራሮች ልዩነታችንን ለመፍታት በሰላም እንወያይ ብለው ከጋበዙና ተባብሮ ለመስራት የተስማሙ ሆነው ከቀረቡ በኋላ ስምምነቱ የተጻፈበት ቀለም እንኳ ሳይደርቅ ኣዘንግተው ወዲያው ስምምነቱ በተደረገበት ሌሊት በተኙበት መርዶ ነጋሪ እንኳ ሳይተርፍ በጥይት ቆሏቸው። በግፍ የተጨፈጨፉት እነዚያ የትግራይ ልጆች፥ ለፍትሕና ለእኩልነት ብለው መስዋእት ለመክፈል በረሃ የወረዱ፥ ምናልባትም አንዳንዶቹ የወያነ መሪዎች ኣብሮ ኣደጎች ወይም የትምህርት ቤት ጎደኛሞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከእሳቤ ሲገባ የወያነ መሪዎችን ክህደት የሚያገዝፍ፥ የኣረመኔነታቸውንም ገደብ ኣልባነት የሚያረጋግጥ ነው።

እነዚህ ከሃዲዎች እኤኣ 1998 / በኤርትራ ላይ ጦርነት ኣውጀው ሻዕቢያን ለማጥፋት ያደረጉት ከንቱ ሙከራስ ለከሃዲነታቸው ተጨማሪ መታያ መሆኑ የሚረሳ ነወይወታደራዊ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ሀ፥ሁ ብሎ ያሰለጠናቸው፡ በደርጉ ሊቀመንበር በኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም ኣገላለጽ መሳርያ መታጠቅ ብቻ ሳይሆን ሱሬ መታጠቅም ያስተማራቸው፥” የኢትዮጵያን ህዝብ የዘመናት ፍትህና የእኩልነት ሕልም እውን ያደርጋሉ፥ ብሎም ለኣካባቢያችን ሰላምና እርጋታ ያበረከታሉ በሚል ተስፋ እንኮኮ ብሎ  ኣራት ኪሎ ቤተ መንግስት  ዙፋን ላይ ያስቀመጣቸው ሻዕቢያ መሆኑ የኣደባባይ ምስጢር ነው።

የወያነ መሪዎች የማያቁት ቤተ መንግስት ገብተው በጥጋብ ሆዳቸው ቆርዝዞ ሃይል በተሰማቸው ግዜ፡ በኢትዮጵያ ኣንጡራ ሃብት ይህ ነው የማይባል የጦር መሳርያ፥ ዘመናዊ ተዋጊ ኣውሮፕላኖች ታንኮች ወዘተ ሸምተወ ኣኣላፍ ሰራዊት ኣታለውና ኣስገድደው በማሰለፍ፥ ሻዕቢያን ደምስሰው የኤርትራን ህዝብ ኣንገት ለማስደፋት በማለም ጦርነት ኣወጁ። እነዚህ ሰዎች የበሉበትን ወጭት ሰባሪ ያጎረሳቸውን እጅ ነካሶችና በክህደት የተላቆጡ መሆናቸውን ዳግም ኣጉልተው ኣሳዩ።

በእውር ድንብር በመሩት 3 ዙር ጦርነት በኣእላፍ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች ረገፉ፥ በኢትዮጵያ ኣንጡራ ሃብት የተሸመተው መሳርያም በገፍ ወደመ ተማረክ። ባጠቃላይ ሲታይ ይህ ከንቱ ሙከራቸው የሞታቸውን ጽዋ መጎንጨት የጀመሩበት ቀዳማይ ምዕራፍ ከመሆን ኣልፎ ያስገኘላቸው እርባና ባይኖርም፥ የከሃዲነት ጠባያቸውን ያጎላ ታሪካዊ ምዕራፍ ስለሆነ የሚረሳ ኣይደለም። ለምንስ ይረሳ።

በወቅቱ በማያምኑበት ጦርነት ተማግደው  ወደፊት ግባ” እይተባሉ ከኋላ  የራሳቸው ወገን ጥይት ጭምር እየተርከፈከፈባቸው በየፈፋውና በየሸንተረሩ የወደቁትን የኢትዮጵያ ወጣቶች  የሚሰቀጥጥ  እልቂት በሚመለከት፥ እልቂቱን በዓይናቸው ባዩ የውጭ ጋዜጠኞች ሳይቀር ሲጠየቁ በወቅቱ የወያነ ቃል ኣቀባይ የነበሩት ቅንጡ እምቤት ያያችሁት ሬሳ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊ ይሸታል እንዴ? በማለት የሰጡት መልስ በገዛ ሰራዊታቸው ላይ የፈጸሙት በፌዝ የተሸኘ ክህደት መሆኑን የሚረሳ ኣለወይ? ለምንስ ይረሳ?

ሌላው ዛሬ ብዙዎች በመገረም የሚያነሱትና መልስ ያጡበት የሚመስለው በማይካድራ በወያኔ ጀሌዎች የተፈጸመው የሰላማዊ ሰዎች ጭፍጨፋ ነው። እነዚያ እንኳንስ የጦር መሳርያና ኣርጩሜም ያልያዙ ሰርቶ ኣደሮች ዘራቸው እየተቆጠረ፥ ማምለጫና መፈናፈኛ በሌለው ሁኔታ ተከበው በቆንጨራና በፋስ ተጨፈጨፉ፥ በካራ ታረዱ፥ በገመድ ታንቀው በስቃይ ኣለፉ፤ ይሄ በኣተገባበሩ ከሩዋንዳው እልቂት ጋር የሚመሳሰልና የሚወዳደር ጭፍጨፋ እንኳንስ ወገንና በሩቅ የሰማውን ሰብዓዊ ህሊና ያለውን ፍጡር ሁሉ ያንገበገበና እዬዬ” ያሰኘ  ነው። ለመሆኑ የወያነ መሪዎች  ሰብዓዊ ፍጡሮች ናቸው ወይ? የሚል የግርምት ጥያቂ ማስነሳቱ ኣልቀርም፤ ይህ የማይካድራው እልቂት  የወያነ መሪዎች ድንገት የጠባይ ለውጥ ኣምጥተው የፈጸሙት ኣይደለም። መሰል ግፍና ጭፍጨፋ ኣፈር ፈጭተው ያደጉበት፥ የጎለመሱበትና ያረጁበት ስለሆነ። እነዚህ ሰዎች በስልጣን ዘመናቸው ያልተነገረ እንጂ ያልፈጸሙት ጭፍጨፋና እልቂት ስለሌለ። የማይካድራውም የዚሁ ተቀጥያ ስለሆነ። እስኪ ይሄን ኣባባሌን ከብዙ በጥቂቱ በኣንዳንድ ሐቆች ላስደግፈው።

ሰላማዊ ሰዎች ታስረው ከነህይወታቸው ለጅብ ተሰጥተው እንዲሞቱ ተፈረደባቸው!” ስለማዊ ሰዎች ታስረው ጉድጓድ ውስጥ ኣንዲገቡና ቁሻሻና ኣይነ ምድር በላያቸው ላይ እየተደፋ ቀስ በቀስ እይተሰቃዩ እንዲሞቱ ተደረገ” የሚል ነገር ሲነገር ጆሮኣቸውን የማያምኑና፥ በዓለማችን እንዲህ ይደረጋል እንዴ?” ብለው የሚገረሙ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በወያኔ የጭቆና ቀንበር ስር ለተሰቃየው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህ ግፍ እንግዳ ነገር ኣይሆንበትም። በኣገሩ - በሶማሌ ክልል፥ ዓብዲ ኢለ የተባለ የሚያውቀው ሰው፡ በወያኔ መሪዎች ትእዛዝ  ለኣንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ፥ ብሎም ለብዙ ዓመት ከፈጸመው የግፍ ግፍ በጥቂቱ  መሆኑን ጠንቅቆ ስለሚያውቅ። ይልቅዬስ  ይህ ኣሰቃቂ ግፍ፥ በጣም የሚገርመው ደግሞ ትናንት ትናንት በማይካድራ የተፈጸመው የሚዘገንን ጭፍጨፋ የኣደባባይ ምስጢር ሆኖ ሳለ፥ በወያነ ዶላር የሰከረ ምናምንቴ ነጭና ዓለም ኣቅፍ ድርጅቶች” ተብዬዎቹ ስለዚህ ኣሰቃቂ ግፍና ጭፍጨፋ ኣንድም ቀን ትንፍሽ ሳይሉ፡ ዛሬ ሓሰት በየእለቱ እየፈበረኩ  ለወያነ ጥብቅና መቆማቸው ነው። በዚህም ኣጸያፊ ድርጊታቸው ከጥቅማቸው በቀር ቅንጣት ታህል ርህራሄ የሌላቸው ሰው ው በላዎች መሆናቸውን እያረጋገጡ ነው። ከነዚህ ሓቅና ፍትሕ የሚጠበቅ ኣይደለም። ከእባብ ዕንቁላል እርግብ ለስሆነ፥ ስለዚህ የወገኖቹ መጨፍጨፍ የሚያንገበግበውና፥ ማንኛውም ህሊና ያለው ሰው ኣቅሙ በፈቀደለት እነዚህን ቅጥረኛ ኣረመኔዎች ጉዳቸውን እያጋለጡ እርቃነ ስጋቸውን ማውጣት ሰብኣዊና ታሪካዊ ግዴታው ነው።

ቀደም ሲል በተጠቀሰው ወያኔ በኤርትራ ላይ ያካሄደውን ጦርነት ተከትሎ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበሩት ኤርትራውያን ላይ፡  ቤተሰብን መለያየት፥ ኣቅመ ኣዳም ያልደረሱ ህጻናትን ከወላጆቻቸው ነጥለው ለብቻቸው እስከማባረር የደርሰውን ግፍ የኢትዮጵያ ህዝብ በጎረቤቶቹ ላይ ሲፈጸም ያየውና ያነባበትም ስለሆነ ይህ የወያነ መሪዎች ግፍና በደል እንዳይረሳ ኣስታውሸ ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳልገባ ላልፈው መርጫለሁ።  የጠላትን ሐይል ወደ ውስጥ ኣስገብቶ ለመደምሰስ በኤርትራ በኩል በተደረገው ስልታዊ ማፈግፈግ የወያነ ሰራዊት ለጊዜው በያዛቸው ከተሞችና ገጠሮች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የሰራቸው ግፎች በተለይ ደግሞ የኤርትራን ታጋዮች መቃብር እየቆፈረ ኣጥንታቸውን በመበተን የፈጸመው ክእምነትና ከባህል ውጭ የሆነ ኣጸያፊ ተግባር ማንኛውም ኤርትራዊ ሁሌም የማይረሳው መሆኑን ግን ላስታውስ እፈልጋለሁ።

የንጹሐንን ደም ምሱ ኣድርጎ ኣልጠግብ ያለው ወያነ፥ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ለኣንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተቀብሯል። ቀንደኛ መሪዎቹና ከፍተኛ የጦር ኣበጋዞቹ ከየተደበቁበት ጉድባ እየተለቀሙ በፍትሕ ፊት ሲቆሙ እያየናቸው ነው። ኣንዳንዶቹም ከወደቁ ወዲያ መንፈራገጥ ለመመላለጥ  እንዲሉ፥ ለማምለጥ ሲሞክሩ የጥይት እራት ሆነዋል። ያንን ስሜቱን መቆጣጠር እስኪያቅተውና ስሩ እስኪገተር ዘራፍ ሲል የነበረውን ስዩም መስፍንን ያስታውሷል።(ሙት ኣነሳሁ፥ ተገድጀ ነው።)

ኣዎን ወያነ ዳግም ላይመለስ ለዝንተ ዓለሙ ኣሸልቧል። እነዚያ በየውጭ ሃገሩ የወያነን ስኳር መላስ የለመዱ እንጭጮች ይህ ሓቅ መራራ ቢሆንባቸውም ዋጥ ኣድርገው፥ ወያነን ወግነው በፈጸሙት በደል ተጸጽተው ንስሐ በመግባት ሕዝባቸውን እንደመካስ፥ ወያነን ከሞት  ያስነሱት ይመስል ከንቱ ሲውተረተሩና፥ የባጥ የቋጡን ሲዘላብዱ ይሰማሉ።

እነዚህ ቅምጥሎች በቀጣይ ኡኡ” የሚሉበትና ኣጉልተው ለማሳየት የሚሞክሩት የኤርትራ ሰራዊት ትግራይን ወረረ የሚል ነው። እነዚህ ሰዎች ድራግ” የሚሉትን የነጮቹን ሱረት እየለበለቡ ነው መሰለኝ የሚለፈልፉት፤ ምክንያቱም ትናንት ትናንት ያሉትን ሲረሱ ምን ልበል።ትናንት ትናንት ኤርትራ ሰራዊት የሚባል የላትም ጠበንጃውን እየጣለ በገፍ ወደ ትግራይ እየተሰደደ ነው፥ የቀረውም ቢሆን የመዋጋት ልምድ የለውም ስለዚህ ከተፈለገ ኣንድ ጥይት ሳንተኩስ ወደ ኣስመራ እንገባለን” ኣላሉንም እንዴ? ኣንዳንድ የወያኔ እፍታ ማማሰያ ላሾችም አረ ኣንድ ጥይት ሳንተኩስ ነው ጥርሳችንን እየፋቅን ኣስመራ የምንገባው” እያሉ ሲያጫፍሩ ተደምጠዋል። ይህ እንግዲህ የኣጭር ግዜ ትውስታ ነው፥ ልንረሳው ኣንችልም ለምንስ እንረሳዋለን፤ ታድያ የኤርትራ ሰራዊት ወረረን፥ ጉድ ኣረገን” ብሎ ማላዘንን ምን ኣመጣው?

ወያነ ላለፈው ሁለት ዓመት ተኩል የጦርነት ዝግጅት ያደረገው የማንን ጎፈሬ ለማበጠር ወይስ ማንን ቅቤ ለመቀባት ነበር? ሚስጥራዊ ሰነዳቸው እንደሚያረጋግጠው የሰሜንን እዝ ባላሰበው ሰዓት ኣዘንግቶ መምታት፥ ከተበታተነ በኋላ ጎንደርንና ወልድያን መቆጣጠርና ኣዲስ ኣበባን መያዝ ከዚህ ጋር መሳ ለመሳ  ወደ ኤርትራ በመዝለቅ ኣስመራን መያዝ ኣልነበረም እንዴ? ታድያ ይህንን: የትናንቱንም እንድንረሳ ነው የሚፈለገው? ኣንረሳውም፥ ለምንስ ይረሳል?

ወረቀት ላይ የተነደፈው የጦር እቅድ መሬት ላይ ሲወርድ ግን ጸንቶ ሊቆም ኣልቻለም። የሰሜን እዝ በርካታ ኣባላቱ ቢጎዱም፥ በዚህ ሳይደናገጥና ሳይበተን ወዲያውኑ ዳግም ተደራጅቶ በተበዳይነት ቁጭት ገጠማቸው። ያበጡትን ያህል ኣስተነፈሳቸው፤ በሶስት ሳምንትም የግብኣተ መሬታቸው ፍጻሜ ሆነ። ፊኒታ!!!

ያ ሁሉ ድንፋታ የተሰማበት ፥ ዶላሩ በቢሊዮን የተከሰከሰበት፥ ያዙኝ ልቀቁኝ የተባለበት የወያነ የጦርነት ድግስ እንዲህ በኣጭር ግዜ ተርመጥምጦ እንዳልነበር ሲሆን ደጋፊዎቻቸው ቅዠት ውስጥ ገቡ፤ ኣእምሮኣቸውም ተነካ። ዛሬ የሚያሰሙት ኡኡታና መዘላበድ፥በየምዕራብ ሃገራቱ ኣደባባይ ላይ መንደባለል  የዚህ ውጤት ነው።ይህ እብደታቸው ምን ያህል ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማየት ኣንዳንድ ጭብጦችን እንዳክል ኣንባቢ ይፍቀድልኝ።

በቅርቡ በመቀሌ በተደረገ የመንግስት ሰራተኞች ስብሰባ ላይ፥ ኣንዲት የወያነ ምልምል ወይዘሮ በሰጠችው ኣስተያየት “በስሜን እዝ ላይ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ሓሰት ነው” ስትል ተሰማች። ሴትዮይቱ በተካነችበትና በወያነ በሰልጠነችበት ተዋናይነት፥ ተበዳይ በመምሰል ኣፍንጫዋን እየነፋች እጠቅሳለሁ “ይህ ሁሉ የተፈጸመው የትግራይ ህዝብን ኣንገት ለማስደፋት ነው እንጂ በሰሜን እዝ ላይ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ሓሰት ነው። እኔ ሰሜን እዝ መምሪያ ኣካባቢ ነው የምኖረው ጥቃቱ ተፈጸመ በተባለበት ሌሊት ኮሽታም ኣልሰማሁ ለጥ ብዬ ነው ያደርኩት” በማለት ምንም ሳታፍር ተናገረች። እሷ ስትተኛ ወደ በድንነት የሚቀይራት በሽታ ካለባት ምሕረቱን ይላክላት፤ እራሳቸው የጭፍጨፋው ፈጻሚዎች ዘመዶችዋና መሪዎችዋ ይህንን የፈጸምነው ብ45 ደቂቃ ውስጥ ነው እያሉ፥ የዛሬውን ኣያድርገውና ሲዘባነኑ ሴትዮይቱ ተኝታ ወደ በድንነት ተቀይራ ይሆን?  ይህን ዓይነቱን ክህደት ምን ይሉታል? ደግሞ በካሜራ ፊት በህዝብ ስብሰባ ላይ።  ባላሰቡት ሁኔታ በጥይት ተቆልተው፥ በገመድ ታንቀው፥ በሳንጃ ተዘልዝለው፥(እሷን በመሰሉ ሴቶች ላይ ጭምር) መስዋዕትነት በከፈሉ የኢትዮጵያ ልጆች ላይ ማላገጥና መሳለቅና ንቀት ስለሆነ የሕግ ገደብ ሊበጅለት ይገባል። ይህንን ከመናገር መብት ጋራ የሚያያይዘው ጉዳይ የለም። ኣፍንጫን እስከ መምታት ከተደረስ የዲሞክራሲ መብት የሚባል ነገር የለም። ይህንን መሰሉ በንቀትና ኣይን ባወጣ ሓሰት ላይ የተመረኮዘ ኣስተያየት ስራውን በጀመረው ከመቀሌ በሚሰራጨው የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ መዘውተሩ ደግሞ ይበልጥ የሚገርም ነው። “ስልጠና ተሰጣቸው” የተባሉት ጋዜጠኞች በውጭ ኣገር ካሉት ዲጂታል ወያኔዎች ጋር እየተናበቡና እየተቀናጁ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር ህዝቡን በመንግስት ላይ ለማነሳስት የሚሰሩት ስራ ስለሆነ፡ መንግስት ያንን “ወያኔ ወያኔ” የሚሸት ጣብያ ማጽዳት ይገባዋል። እነዚህ ጋዜጠኞች ሳይሆኑ ለወያነ ካድሬነት ኣድረው፡ ትናንት ሲደልቁት የነበረው የጦርነትና የእልቂት ከበሮ የሚረሳ ኣይደለም ለምንስ ይረሳ።

ሌላው በዚህ ጽሑፌ ላይ ላነሳው የፈለግሁት የስዬ ኣብርሃ ጉዳይ ነው። ሰውዬው ከ 3 ወራት በፊት መቀሌ ላይ ተገኝቶ “የትግራይ ህዝብ ጦርነት ባህሉ ነው። ኮር ደምስሶ ኮር መፍጠር፥ ብርጌድ ደምስሶ ብርጌድ መገንባት እንችልበታለን” በማለት የተናገረውን የምንረሳው ኣይደለም። ቃላት እየመረጠ፥ እየተዘባነነ፥ እንደ ኣንበሳ ጎምለል ጎምለል እያለ። ከዚህ በፊት በውርደት ያባረሩትን ጓደኞቹን  “እኔም ከጎናችሁ ኣለሁ”” በማለት ሲያጋግል ቆይቶ፥ ውጊያው ከመጀመሩ በፊት ላጥ ብሎ በሱዳን በኩል በመውጣት ቦስቶን ኣመሪካ ላይ ታየ። 

እሱ እንዳለው ወያነ እንኳንስ ጦርነት ባህሉ ሊሆን ቀርቶ የጦርነትን “ሀሁ” የማያውቅ የደደብ ስብሳቢ መሆኑ በተጋለጠበት ውጊያ ኣፈርድሜ  ከበላና፥ መሪዎቹም ተዝረክረክርከው ከጠፉ  በኋላ ስዬ ኣብርሃ “እዩኝ እዩኝ ያለውን ያህል ደብቁኝ ደብቁኝ “ እንደማለት መድረክ ላይ ወጥቶ “ የተባበሩት መንግስታት ወደ ትግራይ ገብቶ ያድነን” ብሎ ሲማጸን ተሰማ። እንዴ! ሰውዬው ለመሆኑ በስንት ኪሎ ጨው ነው ዓይኑን የታጠበው? ይቅርታ ይደረግለኝ እንጂ፥  ይህ ኣይናውጣ ባደገበት ቤተሰብ ውስጥ ለመሆኑ “ይሉኝታ” የሚባል ነገር ነበር ወይ ብዬ ለመጠየቅ ተገድጃለሁ። በህይወቱ ውስጥ ያሳየው የእስስትነት ጠባይ ከእንሰሳዋ በላይ  ስለሆነብኝ እኮ ነው ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት። በመጨረሻ “በኣመሪካ የተንደላቀቀ ኑሮህን ትተህ፥ ቡላ ገበርዲንህን ኣውልቀህ፡ ቁምጣ ሱሬ  ለብሰህ በረባርሶ ጫማህን ተጫምተህ ወደ ትግራይ ዝለቅና ፈራርሶ ትቢያ የሆነውን የወያነ ኮር፥ ክፍለ ጦርና ብርጌድ እንዴት ዳግም እንድሚፈጠር ኣሳየን! ለኛም ትምህርት እንዲሆነን!” የሚል ምክሬን ሰጥቸ ልሰናበተው።

የነስዬና መሰሎቹ መንጨርጨርስ እሺ! ምክንያቱን ላብራራ ሞክሬኣለሁ።  እነ ማርቲን ፕላውትን የመሰሉ ነጭ ኣጭባዎች ኣያጋበቻው ገብተው መፈትፈት፡  እንዲሁም እነሱ የሚያጎርሷቸውን ሓሰት እያላመጡ ሉኣላዊቷን ሃገር ኢትዮጵያን በውስጥ ጉዳይዋ ውስጥ ገብተው “ይህን ኣርጊ ይህን ኣታድርጊ” የሚል ትእዛዝ ለመስጠት የሚዳዳቸው “ዓለም ኣቀፋዊ ድርጅት” ተብዬዎችስ ጉዳይ  ምንድነው ሚስጥሩ ? ለሚለው ትንሽ ልበልና ጽሑፌን ልቋጭ።

ይህ ጉዳይ 7ኛ ክፍል ስማር የኣማርኛ ኣስተማሪያችን  ያስነብበን የነበረው “ተረት ተረት የመሰረት” የምትል በሃዲስ ኣለማየሁ የተጻፈች መጽሓፍ ትዝ ኣለችኝ። በመጽሓፍዋ ውስጥ ከሰፈሩት ቁምነገር ኣዘል ተረቶች ኣንዱ “የጅብ ፍቅር እስኪቸግር “የሚል ነው፤ ተረቷ በኣንድ ኣገር ውስጥ የከብት በሽታ ይገባና ከብቱን ሁላ ይጨርሰዋል፡  ስጋ በሌው ኣውሬ ሁሉ ጥጋብ በጥጋብ ይሆንና፥ ጅብ ከኣህያ ጋር ትዳር ይመሰርታል። ኣብረው ሲኖሩ ቀስ በቀስ የከብት በሽታው ያበቃል፡ የሚሞት ከብት ይጠፋል፥ ኣያ ጅቦ ይራብና ያቺን በጥጋቡ ግዜ ያገባትን ኣህያ “ውይ ለካስ ኣህያ ነሽ ብሎ ይሰልቅጣታል። እነዚህም ከወያኔ ጋር የያዛቸው ፍቅር የጅቡን ዓይነት ነው፤ እስኪቸግር ነው። ወያነ ከኢትዮጵያ ካዝና እየመነተፈ ይረጭላቸው የነበረው ዶላር ቀስ በቀስ እያለቀ ሲሄድ የሚያበቃ ነው። እነዚህ “እራስን መሸጥ” በሚል ባህል ውስጥ ያደጉ ነጫጭባዎች፥ የለመዱት የወያነ ዶላር እየነጠፈ ሲሄድ “በጨረታው ኣንገደድም”ብለው ሽል እንደሚሉ የታወቀ ነው። የሚከፍላቸውም ካገኙ ያዋረዱትን ለማወደስ፥ ያንኳንሰሱትን ለማድነቅ ወደኋላ የማይመለሱ ኣይናውጣዎች መሆናቸው የነገው ታሪክ የሚመሰክረው ነው። ዕድሜውን ይስጠን።

ይህ የነጮቹንና ዓለም ኣቀፍ ድርቶች ሴራና ደባ ኣዲስ ነገር እንዳልሆነ፡  በኣመሪካ መሪነት በኣውሮጳ ተባባሪነት በወያነ ጋሻ ጃግሬነት በኤርትራ ላይ ሳያባራ የዘነበ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲገነዘቡልኝ ለማስታወስ እፈልጋለሁ።

ኤርትራ  “ልኡላውነቴን ፥ የውሳነ ነጻነቴን ኣላስደፍርም፥ የሃያላኑ መሳርያ ኣልሆንም ወዘተ” የሚለው በመርህ ላይ የተመረኮዘ ጽኑ ኣቋምዋ፥ በኣፍሪካ ላሉ ሌሎች ሃገሮች የምዕራብ ሃገራትን የበላይነትንና ኣውቅላችኋለሁ ማለትን ያለመቀበል “መጥፎ ምሳሌ” ሰለሚሆን መቀጨት ኣለበት ተባለ። ለዚህ እከይ ተግባርም ወያነ ታጨ። በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እርዳታው፥ ብድሩ በያይነቱ ፈሰሰለት፥ የወያኔ መሪዎች በየዓለም ኣቀፍ መድረኩ ተወደሱ።  በምዕራባውያኑ ለመጋለብ ወገባቸውን ኣመቻቹ። ባንጻሩ በኤርትራ ላይ ሴራውና ደባው ተዝጎደጎደ። ወያነ በኤርትራ ላይ ካካሄደው ጦርነት በኋላ ባድመን በሚመለከት ሄግ ላይ በተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን  የተሰጠው ውሳኔ ተተግብሮ በኣካባቢው ሰላም እንዳይሰፍን ሁሉም ዓይነት ጫናና እንቅፋት እንዲፈጠር ተደረገ።

“ኤርትራ ለሶማሌው ኣልሸባብ እርዳታ ታደርጋለች፥ በኣትዮጵያም ግንቦት 7ና ኦነግ የመሳሰሉትን በግብረ ሽበራ የተፈረጁ ድርጅቶች ትደግፋለች ተባለ። ከዚህም በተጨማሪ በኤርትራ ወስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ፥የሰው ዘር የማጥፋት ወንጀል፥ የሴቶች መደፈር ወዘተ ይፈጸማል” የሚለው የሓሰት ክስና ውንጀላ መልኩን በተለያየ መንገድ እየቀያየረ ተዥጎደጎደ። የኤርትራንና የመሪዋን ስም ለማጠልሸት ሌት ተቀን ተሰራ፤ እንዳንድ የጎረቤት ሃገሮች መሪዎችም በወያነ ተታለውን ተገደው በዚህ ሴራ ውስጥ እጃቸውን እንዲያስገቡ ተደረገ።ይህንን ዘመቻ ብቋሚነት እንዲያካሂዱ “ልዩ” ኮሚተዎችና ፥ ራፖርተሮች በዓለም ኣቀፍ ደረጃ ተቋቋሙ። ኤርትራ በዚህ ሁሉ  ተፈትና ኣልበገር ስላለች፥ ኢኮኖሚዋን ኣሽመድምዶ ለመጣል የኢኮኖሚ ኣገዳ ተጣለባት፥ በተጨማሪም በመሪዎችዋ ላይ የጉዞ እገዳ ተጨመረበት።

የኤርትራ መንግስትና ሕዝብዋ ግን በዚህ ኣልተደናገጡም። የኤርትራ መንግስት እጁን ለመጠምዘዝ ኣላመቻቸም። የሃገሩን ሉኣላዊነትና የውሳነ ነጻነቱን ባለማስደፈር፥ ይህንን ዓለም ኣቀፍ ታርጋ የተለጠፈበትን በኣመሪካ መሪነት በኣውሮፓ ተባባሪነት በወያነ ኣሽከርነት በቀጣይ የተሸረበ ሴራና ደባ ከስሜታዊነት ርቆ በጥንቃቄ እየገመገመ፥የዚህ ሁሉ ሴራ ግዳይ (ሆስቴጅ) ሳይሆን፥ በቆፈሩለት ቦይ ሳይፈስ በቆራጥነት መከተ። የኤርትራ ሕዝብም በያለበት በተለይም ወጣቶች የተወለዱበት ወይም ያደጉበት ሃገር ሕግ የሚፈቅድላቸውን ዕድል በመጠቀም ፔቲሽን በማቅረብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ በሶሻል ሚድያውም ይህንን ደባ በማጋለጥ ወዘተ ተመሙ።

ያ ምዕራባውያኑ የደከሙበት፡ ብዙ ሚሊዮን ዶላር ያፈሰሱበት ኤርትራን ከዓለም ነጥሎ የመደምሰስ ውጥን ኣልተሳካም። በታማኝ ኣሽከርነት የተማመኑበትም ወያነ ኣልጎበዘላቸውም። ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የለውጥ ሃይል ተመቶ ተሽመደመድ፤ ከቤተ መንግስት ተባሮ እየተውተረተር መቀሌ ገባ፥ እነሆ ዛሬ ደግሞ በለኮሰው እሳት ተለብልቦ፥ በማሰው ጉድጓድ ተቀበረ። ለታማኙ ኣሽከራቸው ሞት የነጮቹ እዬዬ ተስተጋባ። የሚገርመው ደግሞ ከሞቱ ያስነሱት ይመስል፥ የሴራው ክታብ እየተከተበ ነው። “በትግራይ ሰብኣዊ መብት እየተረገጠ ነው፥ ሴቶች እየተደፈሩ ነው የዘር ማጥፋት ወንጀል እይተፈጸመ ነው” የሚለው የሰለቸና የተለመደ እሮሮም እየተሰማ ነው። ወኔውና ተሞክሮው ስላለ ግን የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግስታት ሕዝባቸውን ኣሰልፈው ይህንንም ሴራ እንደሚያበራዩት እውቅ ነው። ሴራውና ደባው ያስነሳው ኣቧራ ይጠራል፤ የጋራ ትብብሩ ብሎም ወደ ብልጽግናና እድገት ወደ ኣካባቢያችን ሰላምና እርጋታ የተጀመረው ጉዞ እንቅፋቱ ተወግዶለታልና ይቀጥላል።

በመጨረሻ ለዚያ ማርቲን ፕላውት ለሚሉት ቀበዝብዛ የምታስተላልፉልኝን ኣንድ መልእክት ትቼ ልሰናበታችሁ። ከዚህ በፊት በወያነ ኣይዞህ ባይነት የኤርትራን መንግስት ስም እያነሳ የባጥ የቋጡን ሲዘላብድ ደሙ የፈላበት ኤርትራዊ ወጣት በሎንዶን ኣደባባይ ያከናነበውን ሓፍረት ኣስታውስ በሉት፡፡ የኣበሻ ቁጣ ፊትን የበሰል ቲማቲም ነው የሚያስመስል።

በሌላ ጽሑፍ እስክንገናኝ በቸር ይግጠመን!

ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላምና ብልጽግና!!!

ተክለ በርሄ

   

 


ታሪኽ ቅድድም ብሽግለታ ካበይ ናበይ | The history of cycling and transformation of the sport in Eritrea - ERi-TV