Dehai

ግልጽ ደብዳቤ ለኣቶ ግዛው (ኢሳት)

Posted by: Tecle Berhe

Date: Tuesday, 08 December 2020

ግልጽ ደብዳቤ ለኣቶ ግዛው

ኢሳት

ላንተ ኣይነቱ በገለማ ኣስተሳሰብ ለተላቆጠ ሰው ሰላምታና ክብር መስጠት የማያስፈልግ ቢሆንም፥ ከሓበሻ የትሕትና ባህል ጋር ላለመጣላት እንደምን ሰነበትክ እልሃለሁ።

ሕዳር 22 ቀን 2013 ዓ/ም ፥ በተላለፈው “ዕለታዊ” የኢሳት ፕሮግራም ላይ፥ በወያኔ ጥቃት ወደ ኤርትራ ላፈገፈጉት የሰሜን እዝ ኣባላት በኤርትራ በኩል ስለተደረገላቸው ድጋፍ፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ኣቢይ ኣሕመድን የፓርላማ ሪፖርት መሰረት በማድረግ ኣስተያየት እንድትሰጥ፥ መርሓ ግብሩን ይመራ የነበረው ኣቶ ወንድምኣገኝ ከሎንዶን በጠየቀህ ግዜ፥ “የኤርትራውን በሚመለከት ለሲሳይ ልተውለት” በማለት ወደ ተለመደው መዘላበድህ ገባህ።

ጌታው
“የኤርትራውን ጉዳይ ለሲሳይ ልተውለት “ማለት ምን ማለት ነው። ያንተን እንጭጭ ኣሽሙር ለመረዳት እኮ መዋእለ ህጻናት የሚውል እምቦቃቅላ መሆን ብቻ በቂ ነው። ሲሳይ እኮ ጉዳዮችን ኣስፍቶ የሚያይ፥በሓቀኛ ጋዜጠኛነት ስነምግባር የታነጸ ብትምክሕትና በትዕቢት ያልተበከለ ስለሆነ ነው ኤርትራውያን ለኢትዮጵያውያን ወንድሞቻቸው ያላቸውን በጎ ኣስተሳሰብና፥ በታሪክ ውስጥ ብተደጋጋሚ በተግባር የተመሰከረውን የኤርትራን ድጋፍና ኣበርክቶ፥ በልበ ሙሉነት የሚገልጸው እንጂ፥ ኣንተ በኣሽሙር ልትሸረድደው እንደፈለግከው የኤርትራ ቅጥረኛ በመሆኑ ኣይደለም ። ኣንተ ግን ከህልምህ ገና ያልነቃህ፥ የገዥነት ሸጋታ ኣስተሳሰብ ያደቆነህና በሽምግልና ዕድሜህም ያቄሰህ ስለሆነ ፥ ስለ ኤርትራ ስትጠየቅ ጸሓይ የሞቀውን ሐቅ ለመናገር እንኳ ድፍረት ኣጥተህ ኣንደበትህ የሚዘጋው።

ጌታው
ምንም እንኳ ዲሞክራሲ፥ፍትሕ፥ እኩልነት እያልክ ብታላዝንም፥ ገና ሕዝቦችን በተለይም ደግሞ የኤርትራን ሕዝብ እንደስምህ ዳግም ገዝተህ ለማንበርከክ የምትቋምጥ ቅዠታም መሆንህን በዚህ ድርጊትህ በማያወላዳ ሁኔታ ኣረጋገጥህ። እንኳንስ ብዕውቀትና በሐቅ ጠበል ውስጥ፥ በኣሲድም ውስጥ ቢነክሯችሁ የማትነጹ ፥ ኣንተና ኣንተን የመሰሉ ትምክሕተኞችና ተስፋፊዎች ተከታታዩን ኤትዮጵያዊ ትውልድ ካለዕዳው ዕዳ እያሸከማችሁ፥ ኢትዮጵያን የማያባራ ስቃይና መከራ ግዳይ ኣድርጋችሁ መቆየታችሁ በጣም ያሳዝናል። በተለይ ዛሬ ከዚህ በላይ የሚያሳዝነው፥ በኤርትራና በኢትዮጵያ ላይ በወያኔ ሰበብ ለዓመታት ኣንዣቦ የቆየው የጦርነትና ያለመተማመን ጨለማ ተገፎ፥ የፈነጠቀው የሰላምና ብሎም የዕድገት ብርሃን ይበልጥ ደምቆ እንዲታይ የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች ተስፋ ባሳደሩበት ወቅት ፥ ኣንተ ደግመህ ደጋግመህ ይህንን ተስፋ ለማጨለም መርዝ መርጨትህ ነው።

ከሁለት ሳምንት በፊት በተላለፈ ዕለታዊ ፕሮግራም ላይ የዕለቱ ኣርእስት በሌሎቹ ጋዜጠኞች (በመሳይ፥ ብወንድማገኝ፥ ፋሲል፥ ሲሳይና ጴጥሮስ) በጥሩ ሁኔታ ተገባዶ ካበቃ በህዋላ “የኣንድ ደቂቃ ዕድል ይሰጠኝ” ብለህ እንደእርጎ ዝንብ ጥልቅ በማለት በልብህ ውስጥ ተዳፍኖ ገና የሚያብከነክንህን ትዕቢት ግላጭ በማውጣት ኤርትራን በሚመለከት የሰጠኸውን ኣስተያየት ያስታውሷል። “ወያኔን በጋራ ከጣልን በህዋላ፥ ከኤርትራ ጋር የምናወራርደው ሂሳብ ኣለ” በማለት የተፋኸውን መርዝ ኣልረሳነውም። በወቅቱ በሓቀኛው ጋዜጠኛ ሲሳይ ኣገና ተገቢው መልስ የተሰጠህ እንኳ ቢሆንም ፥ እኔም ትንሽ ልበል፡ ግን መሃል ላይ ኣንዲት የኢትዮጵያ ኣበው ኣባባል ትዝ ስላለችኝ እንዳልረሳት እንዲሁም ለመዝናኛም ትሆነን ዘንድ ልጠቃቅሳት።

ያምርብኛል ብዬ ጎራዴ ብገዛ
እሱም ወዘወዘኝ ኣሽሟጣጩም በዛ!!

ጌታው ኣቶ ግዛው! ኣንተም እርጅና ባንቋቋው ወገብህ ላይ ጎራዴ ገዝተህ ታጠቅና “ከኤርትራ ጋር ጦር እማዘዛለሁ”’ ብለህ “ዘራፍ” በል። መዘባበቻና መሳለቂያ ከመሆን ግን ኣታልፍም፤ ኣንተን ተጠናውቶ ኣልለቅም ያለህ ትዕቢትና የገዥነት ፍላጎት ግዜ ኣልፎበታል! ታሪክ ተቀይሯል። ደግሞ “ከኤርትራ ጋር የማወራርደው ሂሳብ ኣለኝ” ብሎ ነገር! ቁቅም ከፈስ ተቆጠረች ኣሉ። ድንቄም!!!

የኤርትራ መንግስት ወይም ሻዕብያ ዛሬ ብቻ ሳይሆን፥ ገና ከጨቅላነት ዕድሜው ጀምሮ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን በሚመለከት በጎና በቅንነት መንፈስ ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ሲከተል ቆይቷል። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ካንተና ኣንተን ከመስሉ ደካሞች ውዳሴ፥ ምስጋናና ምርቃት ለማግኘት ኣይደለም። በፕሮግራሞቹ ላይ ካሰፈራቸው ዓበይት ዓላማዎቹ ኣንዱ እንዲሁም ጥርት ያለ ራእዩ ስለሆነ ነው። ያንተን ደካማ የመገንዘብ ደረጃ በሚመጥን መልኩ ኣንዳንድ ለዚህ መታያ የሆኑ ስራዎችን ላስቀምጥ።

ኣኣምሮህ ብትምክሕት ስብ ተሸፍኖ ረስተኸው እንዳይሆን እንጂ፥ “ኣባሉ ነበርኩ” ለምትለው የእሕኣፓ መሪዎች፥ ካለው ኣካፍሎ፥ ኣብልቶ፥ ኣጠጥቶ፥ ኣሰልጥኖና መሳርያ ኣስታጥቆ ኣሲምባ ድረስ የሸኘ እኮ ሻዕቢያ ነው። በየመድረኩ ለፍትሕና ለእኩልነት እንታገላለን ብለው የተነሱ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ድርጅቶችን ብተመሳስይ መልኩ ያስተናገደም እሱ ሻዕብያ! ኤርትራ በተለይ በወያኔ ለተሳደዱ፥ ለተገፉ ወዘተ ኢትዮጵያውያን በኣካባቢያችን ብቸኛዋ ጥላና ከለላ እንደነበረችና፥ በዚህም ሰበብ የከፈለችውን ውድ ዋጋ ካንተ በስተቀር የሚረሳ ኢትዮጵያዊ ያለ ኣይመስለኝም።

ብትጥቅ ትግሉ ወቅት፥ ሻዕብያ በኣእላፍ የማረካቸውን ኢትዮጵያውያን ወታደሮች ፥ ከታጋዮቹ እኩል ኣብልቶ ኣጠጥቶ ኣልብሶ፥ ያልተማረውን ኣስተምሮ ለሃገራቸውና ለወገናቸው ያበቃ መሆኑ ኣንተን የመሰለ ትምክሕተኛና ተስፋፊ ለማመን ያስቸግረው ካልሆነ በቀር በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚመሰክሩት ሓቅ ነው። ሻዕቢያ ይህንን ሲያደርግ ደግሞ “ከኢትዮጵያ ገዥ መደቦች ጋር እንጂ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ቅራኔ የለንም፥”ከሚለው ኣቋሙ በመነሳት እንጂ፥ በማንም ተገዶ ኣልነበረም። እነዚህን ሓቆች በሚመለከት በቅርቡ ማሞ ኣፈታ በተባለ ኢትዮጵያዊ “ኣንቱ በእናት” በሚል ርእስ እንዲሁም ኣጠቅላይ ግንዛቤ ለማግኘት ቢረዳህ ኢትዮጵያዊው ምሁር ዓብዩ ብርሌ (ጌራ) ‘በሀገር ፍቅር ጉዞ” በሚል የጻፏቸውን መጻሕፍት እንድታነብ እግረ መንገዴን ልጠቁምህ እፈልጋለሁ።

ጋሬጣ ሆኖ የቆየውን የወያኔን መደምሰስ ተከትሎ፥ በኤርትራና ኢትዮጵያ መካከል ከለውጡ በህዋላ የተፈጠረውን ስለማዊና በጋራ መተሳሰብ ላይ የተመሰረተውን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጎለብትና ፥ ኣንተና መሰሎችህ እንደምታስቡት ኤርትራ ለኢትዮጵያ ስጋት ሳትሆን የክፉ ቀን ወዳጅ መሆኗን የሚያረጋግጡ ዓበይት ግብራዊ እርምጃዎች በከፍተኛ ፍጥነት ይወሰዳሉ። ዕድሜውን ሰጥቶህ፥ የትምክሕተኛነት ዓይነ-ጥላህን ገልጦ ለማየት ያብቃህ።

በመጨረሻ፥ በነዚያ ታጋይ በሆኑ ጋዜጠኞች በነመሳይ፥ ፋሲል፥ ጴጥሮስ ወንድማገኝና ሲሳይ ወዘተ ጥረት ብዙ መሰናክሎች ታልፈው፥ ኢሳት ያተረፈው ተወዳጅነት፥ ባንተ ሰበብ እንዳይሸረሸር ስጋቴን ለመጥቀስ እወዳለሁ። በውስጥ ጉዳይ መግባት ሆኖ እንዳይቆጠርብኝ እንጂ፥ ኣንተን ከገበታው ቢያርቁህ የተሻለ ይመስለኛል፤ ምነው ቢሉ ቆማጣን ቆማጣ ካላሉት ገብቶ ይፈተፍታልና!!

በል ጌታው፥ ምናልባት ትንሽ ግንዛቤ ቢኖርህ ከሚል ወንድማዊ ኣስተሳሰብ የኤርትራን ሓቆች ቀለል ባለ መንገድ ኣቅርቤልሃለሁ። የኤርትራ ሓቅ ገብስ ነው። ቢሻህ እንደቆሎ ቆልተህ፥ ኣለያም እንደበሶ በጥብጠህ መልሰህ መላልሰህ ከስክሰው፤ ቢጠቅም እንጂ ኣይጎዳም።

ሰላምና ብልጽግና ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ሕዝቦች!


ተክሌ በርሄ
27 ህዳር 2013

ታሪኽ ቅድድም ብሽግለታ ካበይ ናበይ | The history of cycling and transformation of the sport in Eritrea - ERi-TV