World News

(ኢዜአ) የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝት የአገሮቹ ግንኙነት ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ ያስችላል

Posted by: Semere Asmelash

Date: Monday, 30 December 2019

የፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጉብኝት የአገሮቹ ግንኙነት ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ ያስችላል


(ኢዜአ)የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ጉብኝት የሁለቱ አገሮች የህዝብ ለህዝብ፣ የምጣኔ ኃብትና ፖለቲካ ግንኙነት ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ የሚያስችል ነው ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ተናገሩ።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከቀናት በፊት በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደሚሉት ይህ ጉብኝት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ጨምሮ የአገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር  ህጋዊ መሰረት እንዲይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታን ይፈጥራል።

ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ ጦርነትም ሰላምም በሌለበት መንገድ ተቋርጦ የነበረው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ወደስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሰላማዊ እልባት አግኝቷል።

ይህም ዓለምን ያስደመመና ተራርቀው የነበሩ የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች መልሶ ያገናኘ ተግባር ነው ብለዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደህግ ማዕቀፍ ለመቀየር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አገሮቹ በምጣኔ ኃብት፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ዘርፎች ያላቸው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ህጋዊ ማዕቀፍ ሊኖራቸው እንደሚገባም አንስተዋል።

ለዚህ ደግሞ የሰሞኑ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የስራ ጉብኝት መልካም አጋጣሚ መሆኑን በመግለጽ።

የቋሚ ኮሚቴው አባል አቶ አዲስ ከበደ በበኩላቸው ኢትየጵያ በመሪዋ አማካኝነት ለምስራቅ አፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ጉልህ ሚና እየተጫወተች መሆኑን ያነሳሉ።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጉብኝቶች ማድረጋቸው አገሪቷ በሌሎች አገሮች ዘንድ ያላትን እምነት የሚያጠናክርና ተፈላጊነቷን የሚጨምር ነው ብለዋል።

በአገራቱ መካከል በተፈጠረው ሰላማዊ ግንኙነት ሳቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተደጋጋሚ በኤርትራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ወደኢትዮጵያ ሲመጡ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

በሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር የተወያዩ ሲሆን በአዳማ፣ ቢሺፍቱና ዱከም የሚገኙ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንም ተመልክተዋል።

ሁለቱ መሪዎች በአዲስ አበባ አዲስ ለሚገነባው የኤርትራ ኤምባሲ ህንፃ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

ena.et

6ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 6 - ERi-TV Documentary

Dehai Events