World News

የአንዳርጋቸው መጽሃፍ!

Posted by: Semere Asmelash

Date: Wednesday, 11 September 2019

የአንዳርጋቸው መጽሃፍ!



የአንዳርጋቸው መጽሃፍ!

ተስፋዬ ገብረአብ  11-9-2019

አዲሱን የአንዳርጋቸው መጽሃፍ አንብቤ ጨረስኩት። እናም ከሁለት ቀናት በፊት አጭር አስተያየቴን በኢሜይል ላኩለት። የላክሁለትን ባካፍላችሁ ምንም አይላችሁ።

ሰላምታ Andy!

"እኛም እንናገር" ን አነበብኩት።

ምን እንደምልህ አላውቅም። የተተራመሰ ነገር ውስጥ ገብቻለሁ። መጽሃፉ ከግማሽ በላይ እውነት ነው። እራስህንም አልማርክም። ብዙ ቦታ ማንበቤን እያቁዋረጥኩ ስቄያለሁ፣ አዝኛለሁ፣ ገርሞኛል። ቀደም ሲል ከኢትዮጵያውያን ኢሊት እንዲህ አይነት መጽሃፍ አላነበብኩም። ስምህ አንዳርጋቸው ባይሆን ኖሮ፣ በአማራነት ባትታወቅ ኖሮ፣ መስዋእትነት ያልከፈልክ ቢሆን ኖሮ እነ አጅሬ እንደ ፋሲካ በሬ ቅርጫ ያደርጉህ ነበር። አሁንም ቢሆን እየተናነቃቸው እንጂ ስሜታቸውን ተፈታትነሃል።

በኦሮሞ እና በአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ ብዙ የተፋለሱ መረጃዎች አይቻለሁ። ሆኖም በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ በቁዋፍ ያለ እንደመሆኑ የሚያጦዙ ነጥቦችን ማንሳት አያስፈልግም ብዬ አምናለሁ።

የኤርትራን ጉዳይ ብዙ አንስተሃል። በጣም ጠቃሚ ነጥቦች አሉ። ከጥቂት በላይ እውነቶችን በድፍረት ጽፈሃል። በዚህም ተደንቄያለሁ። "ኤርትራ እና ዱላ" በሚለው ምእራፍ ግን ሙሉ በሙሉ ከአንተ ትንታኔ በተቃራኒው ነኝ።

ኤርትራን "ማንም ቅኝ ገዢ ጠፍጥፎ የሰራት አገር" ብለህ መግለጽህ እውነት አይደለም። ኤርትራን በዚህ መልኩ መግለጽ ካንተ ብእር የሚጠበቅ አልነበረም። ይህ አባባል ለጅቡቲ እንኩዋ አይሰራም። ኢትዮጵያ ራስዋ የት ነበረች? ከምኒልክ በፊት ኢሉ-አባቦርን ረግጦ የሚያውቅ፥ ከሃይለስላሴ በፊት ቀይባህርን በአይኑ አይቶ የሚያውቅ አንድ ንጉስ እስኪ ጥራልኝ? የኢትዮጰያ ታሪክ እየተባለ የሚነገረው አብዛኛው የፈጠራ ድርሰት መሆኑን የምታውቀው ነው። ለብሄራዊ ኩራት ሲባል ተረቱ እንደ እውነት ቢቀጥል አይጎዳም ይሆናል። እኛው ለእኛው ግን መቸም ያው እንተዋወቃለን።

ወደፊት በወደብ ምክንያት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል እልቂት የሚያስከትል ጦርነት ሊካሄድ እንደሚችል መግለጽህም ከእውነታ የራቀ ነው። ገራሚ አባባል ነው። እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ ከዚህ በሁዋላ የኤርትራን አንድ ጠጉር መበጠስ የሚችል ሃይል አይኖርም። የሚሻለው በሰላም ተከባብሮ፣ በአፍሪቃ ቀንድ ደረጃ ተጋግዞ መኖር ብቻ ነው።

በተቀረ አሪፍ መጽሃፍ ጽፈሃል። ትውልድን የሚያደናግር ነገር ባያጣውም በጥቅሉ ተነባቢ ነው። በተለይ ስለ ቤተሰብህ የጻፍከው መሳጭ ታሪክ ነው።

ሁለተኛውን ክፍል ለማንበብ እጠብቃለሁ። ይህን የመሰለ ልባዊ አስተያየት መስጠቴ ጉዋደኝነታችን ላይ ክፍተት እንደማይፈጥር ተስፋ አደርጋለሁ።

ወዳጅህ!






EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events