World News

(ኤፍ ቢ ሲ) የኢሕአዴግ ምክር ቤት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Thursday, 18 April 2019

የኢሕአዴግ ምክር ቤት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ

አዲስ አበባ ፣ (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ምክር ቤት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መደበኛ ስብሰባውን አጠናቀቀ።

ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ሀገራዊ የለውጥ ሂደቱ ያለበትን ደረጃና የተከናወኑ የፖለቲካና የድርጅት ስራዎችን አፈፃፀም ገምግሟል።

በዚህም ባለፈው አንድ አመት በተለይም 11ኛው የኢሕአዴግ ጉባኤ ከተካሄደበት መስከረም ወር ጀምሮ የጉባዔውን ዋናዋና ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች መሰረት በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ያስቻሉ ተጨባጭ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን ምክር ቤቱ በዝርዝር ተመልክቷል።

የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ የተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መኖራቸውን እንዲሁም እህት እና አጋር ፓርቲዎች እያደረጓቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች በመልካም ጅምርነት የገመገመው ምክር ቤቱ፥ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ በሀገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ እንዳለው ገልጿል።

ኢህአዴግ የቃል ኪዳን ሰነዱን አክብሮ በመንቀሳቀስ ሃላፊነቱን በተሟላ መልኩ እንዲወጣ አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን፥ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ህገ መንግስቱንና የሀገሪቱን ህጎች አክብረው በሰላማዊ የሀሳብ ትግል ብቻ በመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ውስጥ ያለባቸውን ሃላፊነት ተረድተው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪውን አስተላልፏል።

ከፖለቲካዊ ስራዎች አንፃርም የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲና የአመራር አንድነት ላይ በስፋት በመወያየት፥ በእህት ድርጅቶችና በአመራሩ መካከል የሚታየውን መጠራጠር በመፍታት የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክሯል።

ከዚህ አኳያም መታረምና መስተካከል ያለባቸው ነጥቦች ላይ ፍጹም ነጻ በሆነ መንገድ ሀሳብ እንዲንሸራሸርና በመጨረሻም ሃገርንና ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ጉዳዮች ላይ መግባባት መደረሱንም ምክር ቤቱ ለጣቢያችን በላከው መግለጫ አመላክቷል።

በኢኮኖሚው መስክ የተወሰዱ የእርምት እርምጃዎች ሀገራዊ የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን በማስተካከል ረገድ በጎ ሚና ነበራቸው ያለው ምክር ቤቱ፥ በተለይም ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱን በማሳደግ በኩል ትርጉም ያለው ስራ መሰራቱን ጠቅሷል።

በዚህ መስክ መሻሻሎች እየታዩ ቢሆንም ከፍተኛ የስራ አጥነት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እና የብድር ጫና መዋቅራዊ መፍትሄ ለመስጠት መረባረብ ይገባል ብሏል።

የወጣቶችን የተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተለይም የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት ስራዎች ቢሰሩም ከችግሩ ስፋት አንጻር ከለውጡ በሚገባው ደረጃ አለመጠቀማቸውንም ምክር ቤቱ አንስቷል።

በተጨማሪም የወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ጥያቄ አለመመለሱን የጠቀሰው ምክር ቤቱ፥ የወጣቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ በቀሪ የበጀት አመቱ ወራት ልዩ ሃገራዊ አጀንዳ እና የርብርብ ማዕከል እንዲሆን ወስኗል።

በየአካባቢው የሚታዩ ከመልካም አስተዳደርና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት የተጀመረውን የማሻሻያ ስራ አጠንክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ በፀጥታና ፍትህ ስርዓቱ ላይ የተካሄደው ማሻሻያና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በሀገሪቱ ላይ አንዣቦ የነበረውን የመበታተን አደጋ በመቀልበስ ሀገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ የላቀ ሚና ነበረውም ብሏል ምክር ቤቱ።

ይሁን እንጅ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ያሉ ክፍተቶች መታረም እንዳለባቸውና ለግጭት እና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች ተለይተው በአስቸኳይ መታረም ይገባቸዋል ብሏል።

መንግስትም ህግን የማስከበር ቁልፍ ሃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንደሚገባውም የጋራ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፥ ከዚህ አኳያ ክልሎች እና የየአካባቢው መዋቅር የየራሳቸውን ህገ መንግስታዊ ግዴታ እንዲወጡም አቅጣጫ አስቀምጧል።

ባለፉት ጊዜያት በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ላይ በጥልቀት የተወያየው ምክር ቤቱ፥ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመስለ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባም ገልጿል።

ከጎረቤት ሀገራት ጋርም መልካም ወዳጅነት መመስረቱንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብር እየተካሄደ ነው ያለው ምክር ቤቱ፥ በተለይ ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ ጋር የተጀመረው ግንኙነት ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስር የሚያጠናክሩ ዕድሎችን መጠቀም በሚያስችል መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወስኗል።

የኢሕአዴግ ምክር ቤት ለውጡ ሰፊና ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዲቀጥል ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ፍትህን እንዲሁም ሀገራዊ አንድነትንና ሀገራዊ ክብርን ማረጋገጥ የድርጅቱ ቀዳሚ ተልዕኮዎች መሆናቸውንም አስገንዝቧል።

በመሆኑም እስካሁን የተመዘገቡ ስኬቶችንና ድሎችን የሚያሰፋና ጉድለቶችን የሚያርም እንቅስቃሴ በጊዜ የለንም መንፈስ መፈፀም እንዳለባቸውም አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከዋና ዋና ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ አውታሮች ግንባታ አንጻርም እስካሁን የተመዘገቡ ውጤቶች እንደተጠበቁ ሆነው በቀጣይ በተለይም ለመስኖ ልማት ከሚሰጠው ትኩረት ባሻገር በቀሪ ወራት በመኸር ስራ ላይ መረባረብ ይገባል ነው ያለው።

በተጨማሪም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማነቃቃት መረባረብ እንደሚገባም አሳስቧል።

ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በተያያዘም ሀገራዊ ለውጡንና ትሩፋቶቹን እንዲሁም ያሉበትን ተግዳሮቶች በተመለከተ በስፋት መዘገባቸው፥ ሀገራዊ አንድነት በማምጣት ረገድ አወንታዊ ሚና እየተወጡ መሆኑን ገምግሟል።

ሚዲያው ዜጎች ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ መሆኑም በአዎንታ የሚታይ ለውጥ ነው ብሏል ምክር ቤቱ።

ሆኖም ከታሪክ ትምህርት በመውሰድ ተልዕኮን ለማሳካት የሚያግዙ መልዕክቶችን ከመቅረፅ ይልቅ ባለፉት ጉድለቶች ላይ ብቻ በመንጠልጠል ብሶትን የማራገብ አዝማሚያ በቀጣይ መታረም እንደሚገባው አሳስቧል።

ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ማህበራዊ ሚዲያው እየተጫወተ ያለው አዎንታዊ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ዴሞክራሲውን የማቀጨጭ ሚናው እየጎላ መምጣቱንም ነው በመደበኛ ስብሰባው የገመገመው።

ከዚህ አንጻርም ከለውጡ ጋር በተዛመደ መልኩ የሚታረምበት አካሄድ መከተል እንደሚገባው አመላክቷል፤ የጥላቻ ንግግሮችን በህግ አግባብ መከላከል አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት በመጥቀስ።

ምክር ቤቱ ለውጡ አሁንም ህዝባዊ መሰረት ይዞ እንዳይጓዝና ከተቻለም እንዲቀለበስ የሚጥሩ ሃይሎች የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውንም ገምግሟል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ጽንፈኛ ብሄርተኝነት፣ ስርዓት አልበኝነት እና የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ፈተናዎች የሃገራዊ አንድነት ችግሮች በመሆናቸው፥ በተባበረ ክንድ በመፍታት ለውጡን በማስቀጠልና በማስፋት ከለውጡ በተቃራኒ ያሉ አስተሳሰቦችንና ተግባራትን መግታት ወቅቱ የሚጠይቀው ቁልፍ ተልዕኮ መሆኑንም አስምሮበታል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ሰነድና ሪፖርት ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኃላ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው ሲሆን፥ የድርጅቱ አመራር፣ አባላት፣ አጋር ድርጅቶች፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበራትና ህዝቦች የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪውን አስተላልፏል።





7ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 7 - ERi-TV Documentary

Dehai Events