World News

Goolgule.com: “የስብሃት ማፊያ ቡድን” – ህወሓት መፍረስ፤ EFFORT መወረስ አለበት

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Wednesday, 26 December 2018

 

ህወሓት – ጨቋኝ ቡድን ወይስ ወራሪ ጠላት?

1) ጨቋኝ ቡድን እና ወራሪ ጠላት

አንድ መንግሥት በሚመራው ህዝብ ላይ እንዲህ ያለ በጭካኔ የተሞላ ግፍና በደል የሚፈፅም የፖለቲካ ቡድን አምባገነን ወይም ጨቋኝ ብቻ ሊባል አይችልም። የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና አንድነት በሚያፈርስ መልኩ ዘረፋና ሌብነት የሚፈፅም ቡድን ሙሰኛ ወይም በዝባዥ ብቻ ሊባል አይችልም። እንደ ህወሓት በሰው ልጅ ላይ ጨካኝ እና በሀገሩ ላይ ዘራፊ የሆነ መንግስት ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። አብዛኞቹ አምባገነን መንግስታት በዜጎች ላይ ግፍና በደል የሚፈፅሙት የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር በሚል ሰበብ ነው። ስለዚህ በዜጎች ላይ ጨቋኝ እና ጨካኝ ቢሆኑም ለሚመሩት ሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት በፅናት የሚታገሉ ናቸው። በሌላ በኩል ለሚያስተዳደሩት ሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ደንታ-ቢስ የሆነና በዜጎች ላይ በጭካኔ የተሞላ ግፍና በደል የሚፈፅም መንግሥት ከአምባገነንና ጨቋኝ ይልቅ “የውጪ ወራሪ ኃይል” የሚለው የተሻለ ገላጭ እና ትክክል ነው።

የሀገርን ሉዓላዊነት በመድፈር የመጣ ወራሪ ኃይል ለሀገሪቱም ሆነ ለህዝቡ አይጨነቅም። ምክንያቱም ለሀገሪቱ ሉዓላዊነትና ነፃነት የሚጨነቅ ቢሆን ኖሮ ሲጀመር ወረራ አይፈፅምም። ከዚህ በተጨማሪ ለሀገሪቱ ዜጎች ተቆርቋሪና ወዳጅ ቢሆን እንኳን ህዝቡ የወራሪዎቹን ወዳጅነትና ተቆርቋሪነት አይሻም። ከዚህ አንፃር ህወሓት በዜጎች ላይ የጭካኔ ተግባር የሚፈፅም ቢሆንም እንደ ሌሎች ጨቋኝና አምባገነን መንግሥታት በሚያስተዳድረው ሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ ፅኑ አቋም የለውም። ለዚህ ደግሞ ለኤርትራ የተሰጡት የአሰብ ወደብ እና ባድመ፣ ለሱዳን የተሰጠው የጎንደር፥ መተማ መሬት፣ በብድር ዕዳ ምክንያት የሀገሪቱ ሉዓላዊ ሃብትና ንብረት አደጋ ላይ የወደቀበት አግባብ፣… ወዘተ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በሌላ በኩል ህወሓት የውጪ ወራሪ ኃይል ነው እንዳይባል የኢትዮጵያ የታሪክና የስልጣኔ እምብርት ከሆነችው ትግራይ የመጣ የፖለቲካ ቡድን ነው። ታዲያ የሀገር ዘራፊና ከሃዲ፣ ለዜጎች ጨካኝና ጨቋኝ የሆነ ቡድን ምንድነው?

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ “A Political History of the Tigray People`s Liberation Front 1975-1991” በሚል ርዕስ በፃፉት የሶስተኛ ዲግሪ ሟሟያ ጥናታዊ ፅሁፍ የህወሓትን መስራቾች እና ቁልፍ የሆነ የአመራርነት ሚና የነበራቸውን ሰዎች ስምና የህይወት ታሪክ በአጭሩ ገልፀዋል። ከህወሓት መስራቾች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ስሁል አየለ ነው። ይህ ሰው ገና በ14 አመቱ የአጎቱን እግር በመከተል ፋሽስት ኢጣሊያን ለመታገል ወደ ጫካ የገባ፣ በ1950ዎቹ አጋማሽ በቀዳማይ ወያነ ትግል የተሳተፈ፣ ለሁለት የምርጫ ዘመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኖ አገልግሏል። በመጨረሻም በቀድሞ የአፄ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ተማሪ ከነበሩ 7 የትግራይ ተወላጆች ጋር በመሆን የትጥቅ ጀምሯል።

ከስሁል ጋር የትጥቅ ትግል ከጀመሩት ተማሪዎች፤ አጋዚ ገሰሰግደይ ዘራፂዮንአስፋሃ ሀጎስአረጋዊ በርሄስዩም መስፍንአባይ ፀሓዬ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር አረጋዊ በፅሁፋቸው የትጥቅ ትግሉ መስራች ያልሆኑ ነገር ግን ህወሓት ውስጥ ወሳኝ የሆነ የአመራርነት ሚና ከነበራቸው በሚል ሶስት ሰዎችን ይጠቅሳል። እነሱም፡- ሙሴ ተክሌ፣ ስብሃት ነጋ እና መለስ ዜናዊ ናቸው። የትጥቅ ትግሉ በተጀመረ ጥቂት ዓመታት ውስጥ አዛውንቱ ስሁል አየለ በሽፍታዎች ተገደለ፣ ወጣቱ አጋዚ ገሰሰ በደርግ ወታደሮች ተገደለ፣ እንዲሁም ከኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር ጋር በነበረው ቆይታ ጠቃሚ የውጊያ ልምድና ችሎታ የነበረው ሙሴ ተክሌ በውጊያ ላይ ሲመራው ከነበረ የህወሓት ታጣቂ ቡድን ከጀርባ በተተኮሰ ጥይት ተገደለ።

2) ወደ ነፈሰበት የሚነፍሱት ስዩምና አባይ

በህወሓት ውስጥ የትግራይ ማርክስት-ሌኒኒስት ሊግ – ትማሌሊ (Marxist-Leninist League of Tigrai – MLLT) የሚል የተለየ ቡድን መመሥረቱን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባትና ግጭት ሶስት የድርጅቱ መስራቾች፤ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ድርጅቱን ጥለው በመውጣት ተሰደዱ። እንደ አረጋዊ በርሄ አገላለፅ፣ ትማሌሊ ከተመሠረተ በኋላ ከህወሓት መስራቾች ውስጥ የቀሩት ስብሃት ነጋ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አክራሪ ብሔርተኛ አመላካከት ያለው ስዩም መስፍን እና ወደ ነፈሰበት የሚነፍሰው ወይም የራስ አቋም የሌለው አባይ ፀሓዬ ናቸው።

የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን ዓለም ባድመ ለኢትዮጵያ ተወሰነች ብሎ ህዝብ ካስጨፈረ በኋላ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ግን ለኤርትራ መወሰኑ ይታወሳል። ለኤርትራ የተወሰነበት መሰረታዊ ምክንያት የስዩም መስፍን አቅምና ብቃት ማነስ ነው። ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ በተካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ የባድመ እና አካባቢው ነዋሪዎች ስም ዝርዝር በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የመረጃ ቋት ውስጥ ይገኛል። ባድመ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኗን ለማሳየት የባድመ ነዋሪዎችን ስም ዝርዝር ይዞ መሄድ ብቻ በቂ ነበር። ስዩም መስፍን ባድመ የኢትዮጵያ አካል መሆኗን ለማሳየት ያቀረበው በ1900 ዓ.ም (እ.አ.አ.) በአፄ ሚኒሊክ የተፈረሙ የድንበር ስምምነቶችን ነበር። በእንዲህ ያለ የድንቁርና ደረጃ ላይ የሚገኝ ግለሰብ የህወሓት መስራችና አንጋፋ መሪ ይባላል።

በተመሳሳይ በ1993 ዓ.ም ህወሓት ለሁለት ሲከፈል አባይ ፀሓዬ በመጀመሪያ ከእነ ተወልደ ቡድን ጋር የነበረ ሲሆን የእነ ተወልደ ቡድን ሲመታ ይቅርታ ጠይቆ ወደ መለስ ቡድን መመለሱ ይታወሳል። ይህ የአባይ ፀሓዬን ትክክለኛ ባህርይ ያሳያል። ከዚህ በተጨማሪ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ በኦሮሚያ ለተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ግንባር ቀደሙን ሚና የተወጣው አባይ ፀሓዬ መሆኑ አይካድም። ትላንት፣ ዛሬም ሆነ ነገ አባይ ፀሓዬ በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ሃሳብና አስተያየት በሰጠ ቁጥር ህወሓት አንድ ነጥብ ይጥላል። ስለዚህ የህወሓት መስራቾች በሙሉ በሞትና ስደት ከትግሉ ሲወጡ ድርጅቱ በሁለት ሰዎች ቁጥጥር ስር ወደቀ። እነሱም ስብሃት ነጋ እና መለስ ዜናዊ ናቸው።

ከህወሓት ወደ ትማሌሊ – ከታጋይነት ወደ ማፊያነት!

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው፣ በ1970ዎቹ አጋማሽ አከባቢ ዋናዎቹ የህወሓት መስራቾች በሞትና ስደት ተለይተው አባይ ፀሓዬ እና ስዩም መስፍን ብቻ መቅረታቸውን ተመልክተናል። ከእነዚህ አንፃር ሲታይ መለስ ዜናዊ የተሻለ የትምህርት ዕድል ግንዛቤ እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። በመጀመሪያ መለስ ዜናዊ የህወሓት የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ የነበረው አባይ ፀሓዬ ምክትል ሆኖ ሲሰራ ነበር። ትግሉን በተቀላቀለ ሁለተኛ አመት ከእነ ስዬ አብረሃ ጋር ምክትል የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ተመርጧል። በድርጅቱ ውስጥ ተፅዕኖ መፍጠር የጀመረው በህወሓት ውስጥ ትማሌሊ የተባለ ሌላ ድርጅት ከተመሰረተ በኋላ ነው። ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ መለስ ዜናዊ ከስብሃት ጋር በመሆን ተቀናቃኞቹን በማስወገድ የህወሓት ሊቀመንበር፣ ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ለመሆን በቅቷል።

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በጥናታዊ ፅሁፋቸው፣ መለስ ዜናዊ መጀመሪያ ላይ አክራሪ ብሔርተኛ ነበር። በትማሌሊ ምስረታ ወቅት ወደ ዓለም አቀፍ ኮሚኒስትነት የተቀየረ ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ ከማዖዊስት ሶሻሊዝም ወደ መንግስት መር ካፒታሊዝም የአቋም ለውጥ ማድረጉን በመጥቀስ ወጥ የሆነ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንደሌለው ይገልፃሉ። ከትማሌሊ ምስረታ እና ድርጅቱ ከሚከተለው የትግል አቅጣጫ ጋራ በተያያዘ በመለስ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በማዳፈን፣ እንደ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ያሉ መስራቾችን በማስወገድ የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሆን፣ እንዲሁም በ1993 ዓ.ም የመለስ ቡድን አሸናፊ እንዲሆን ያስቻለው ስብሃት ነጋ ነው።

በመሰረቱ ስልጣን ማለት በራስ ፍላጎትና ፈቃድ የመወሰን ነፃነት ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ ውስጥ በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ የመወሰን ነፃነት የነበራቸው ስብሃት ነጋ እና መለስ ዜናዊ ናቸው። ሌሎች የህወሓት አመራሮች እና አባላት በራሳቸው ፍላጎትና ፈቃድ ቀርቶ በድርጅቱ ደንብና መመሪያ መሰረት የመወሰን ነፃነት የላቸውም። ከራሳቸው ህሊና እና ከድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ይልቅ ለስብሃት እና መለስ ዜናዊ ፍላጎትና ምርጫ ተገዢ መሆን አለባቸው። ለዚህ ደግሞ ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ ከእነ ስብሃትና መለስ የተለየ አቋምና አመለካከት የነበራቸው እንደ ግደይ ዘራፂዮን፣ አስፋሃ ሀጎስ እና አረጋዊ በርሄ ያሉ የህወሓት መስራቾች ዕጣ-ፈንታን እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

በአጠቃላይ ህወሓት ውስጥ እንደ ስዩም መስፍን እና አባይ ፀሓዬ ለመለስ ዜናዊ ታዛዥና ተገዢ ካልሆኑ በስተቀር መጨረሻቸው ስደት ወይም እስራት ይሆናል። ነገር ግን ያለ ስብሃት ድጋፍና እርዳታ መለስ ዜናዊ እንደ እነ አረጋዊ በርሄ ያሉ የድርጅቱን መስራቾች በማስወገድ የህወሓት ሊቀመንበር መሆን፣ እንዲሁም እንደ እነ ስዬ አብርሃ ያሉ አቻዎቹን በማሰር እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ መቀጠል አይችልም ነበር። ስለዚህ የህወሓት አባላትና አመራሮች ለመለስ ዜናዊ ተገዢና ታዛዥ የሆኑት በስብሃት አማካኝነት ነው። መለስ ዜናዊ ደግሞ በህወሓት/ኢህአዴግ ሊቀመንበርነት ለመቀጠል ከፈለገ ለስብሃት ነጋ ተገዢና ታዛዥ መሆኑ የግድ ነው።

ነገር ግን የህወሓትን ታሪክ በቅርበት የሚከታተሉ ምሁራንና የድርጅቱ የቀድሞ አመራሮች ስብሃት ነጋ በህወሓት የትግል ታሪክ ውስጥ በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ ሚና እንደሌለው ይገልጻሉ። በእርግጥ ከደርግ ውድቀት በኋላ በህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ውስጥ የረባ ሥልጣን አልነበረውም። ይሁን እንጂ ከደደቢት እስከ ቤተመንግስት ድረስ የህወሓት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትር የስልጣን እድሜ የሚወሰነው በዋናነት በስብሃት ነጋ ፍቃድና ምርጫ እንደነበር ግልፅ ነው። ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ስብሃት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ስለነበረው የአመራርነት ሚና እና ተፅዕኖ የሚከተለውን አስፍረዋል፡-

“Woldesilassie Nega (Sibhat). A TPLF CC member since 1976 was born in a village called Adi-Abune near Adwa where his father was a fitawrari who owned substantial farmlands. Sibhat claims to be a descendant of a legendary warrior known locally as Wa’ero, who is said to have owned large tracts of land in the district of Adwa. In this sense he was filled with ‘feudal sentiments’, which earned him the nickname ‘feudal intriguer’. He finished high-school in Meqele and studied agricultural economics at H.S.I.U. He joined the Front at Dedebit and was an ordinary member until he was elected to the leadership at the Fighters’ Congress in 1976. He showed to be strongly ethno-nationalist, and organized likeminded individuals around himself and considers any ‘Amhara’ as his enemy. His relations with the other people in the Front are reputed to be clannish and nobody knows what tangible political or military contribution he had in the struggle; but, as Tecola W. Hagos (1995: 8) rightly put it, indeed he ‘is the ‘Exchequer’ of the TPLF’.” A Political History of the Tigray People`s Liberation Front 1975-1991

ከላይ ከተጠቀሰው የዶ/ር አረጋዊ በርሄ ፅሁፍ ውስጥ “Exchequer” የምትለዋ ቃል ከደደቢት እስከ ቤተመንግስት ባለው የህወሓት ታሪክ ውስጥ የስብሃት ትክክለኛ ሚና ምን እንደነበር በግልፅ ትጠቁማለች። “Exchequer” የሚለው ቃል በአጭሩ የዘውዳዊ መንግሥትን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት የሚቆጣጠር ማለት ነው። በዚህ መሰረት በህወሓት የትግል ታሪክ ውስጥ የስብሃት ድርሻና ሚና የድርጅቱን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት መቆጣጠር እንደነበር መገንዘብ ይቻላል። ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ የስብሃትና መለስ ዜናዊ ቡድን የህወሓት መስራቾችን በማስወገድ የድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በበላይነት ለመቆጣጠር ችሏል። ስለዚህ ከትማሌሊ ምስረታን በኋላ ባለው የህወሓት የትግል ታሪክ መለስ ዜናዊ የድርጅቱን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሲመራ፣ ስብሃት ነጋ ደግሞ የድርጅቱን ፋይናንስ በማስተዳደር ደርግን ተገዳድረዋል። ይህ ጥምረት ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጋር በመሆን የደርግን መንግስት ከስልጣን በማስወገድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት መቆጣጠር ችሏል። በቀጣይ ክፍል የስብሃት-መለስ ቡድን እንዴት ወደ ማፊያ ቡድንነት እንደተቀየረ በዝርዝር እንመለከታለን።

“የEFFORT” ትክክለኛ ባለቤት እና የህወሓት ዋና አለቃ ማን ነው?

እንደ ፖለቲካ ድርጅት ህወሓት ገና ከአመሰራረቱ ጀምሮ የተለየ ሃሳብና አመለካከትን የመታገስ ሆነ የመቀበል ልማድና ባህል የሌለው አክራሪ ድርጅት ነው። በዚህ ረገድ ከህወሓት መስራቾች አንዱ የሆነው የአለምሰገድ/ሀይሉ መንገሻን ጉዳይ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። በቀድሞ የሃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ጥበብ ትምህርቱን አቋርጦ የትጥቅ ትግሉን የጀመረው አለምሰገድ ሁልግዜ ከድርጅቱ አመራሮች የተለየ ሃሳብ የማንጸባረቅ ልማድ ነበረው። በዚህ ምክንያት በ1976 ዓ.ም (እ.አ.አ.) በተካሄደው የመጀመሪያው የታጋዮች ጉባኤ ላይ በአመራርነት ሳይመረጥ ቀረ። የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው የትጥቅ ትግል ከጀመሩት የህወሓት መስራቾች ውስጥ በአመራርነት ሳይመረጡ የቀሩት አለምስገድ መንገሻ እና አስፋሃ ሀጎስ ብቻ ናቸው። ከህወሓት አመራሮች እና አባላት የሚደርስበት ጫና እና ግፊት እያየለ በመሄዱ አቶ አለመስገድ መንገሻ ከአንድ ዓመት በኋላ ድርጅቱን ለቅቆ ተሰደደ። አቶ አስፋሃ ሀጎስ ደግሞ ከትማሊሌ ምስረታ በኋላ እ.አ.አ. በ1985 ዓ.ም ድርጅቱን ለቅቆ በስደት መኖር ጀመረ።

በመጀመሪያው የህወሓት ጉባኤ ላይ በአመራርነት የተመረጡትም ቢሆን ተመሳሳይ እጣ ነው የገጠማቸው። ቀድሞ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ የነበረውና በመጀመሪያው የታጋዮች ጉባኤ ላይ ከተመረጠ በኋላ እ.አ.አ. ከ1976 – 1979 ዓ.ም የህወሓት ዋና ሊቀመንበር፣ እስከ 1986 ደግሞ የድርጅቱ የወታደራዊ ኮሚቴ ሃላፊ ሆኖ ያገለገለው አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በትማሌሊ ምስረታ በኋላ በስብሃትና መለስ ቡድን ድርጅቱን ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል። በተመሳሳይ እስከ ትማሌሊ ምስረታ ድረስ (1978 – 1985) የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የነበረው አቶ ግደይ ዘራፂዮን በተመሳሳይ ምክንያትና መንገድ ድርጅቱን ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል። ገሰሰው አየለ (ስሁል) እና ዘሩ ገሰሰ (አጋዚ) ትግሉ በተጀመረ የመጀመሪያ አመታት መገደላቸው ይታወሳል።

በዚህ መልኩ ስብሃት ህወሓትን በሊቀመንበርነትና ምክትል ሊቀመንበርነት ሲመሩ የነበሩ የድርጅቱን መስራቾች በማባረር የሊቀመንበርነት ቦታውን የ28 ዓመት ወጣት ለነበረው መለስ ዜናዊ አስረከበው። ከመስራቾቹ ውስጥ የቀሩት ለመለስ ዜናዊ ታዛዥ እና አገልጋይ የሆኑት ስዩም መስፍን እና አባይ ፀሓዬ ናቸው። ድርጅቱን ለቅቀው በወጡት መስራቾች ምትክ በአመራርነት የተሾሙት እና በድርጅቱ ውስጥ የሚቆዩት ለመለስ ዜናዊ ታዛዥና ተገዢ ከመሆን አንፃር ባሳዩት አፈፃፀም ነው። ስብሃት ታዛዥና አጎብዳጅ በሆኑ ሰዎች ዙሪያቸውን ካጠረ በኋላ እንደ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ አገላለፅ የህወሓት “Exchequer” ሆነ። ይህ ማለት ስብሃት የህወሓት ፋይናንስ ኃላፊ ሆነ ማለት ግን አይደለም።

በእርግጥ ስብሃት ነጋ የህወሓት ፋይናንስ ኃላፊ የነበረውን (አስፋሃ ሀጎስ?) ድርጅቱን እንዲለቅ ካደረገ በኋላ ምትኩ ለመለስ ዜናዊ ታዛዥና ለእርሱ ተገዢ የሆነ አመራር መድበዋል። ስለዚህ ስብሃት የህወሓት ፋይናንስ ኃላፊ ሳይሆን የድርጅቱን የፋይናንስ ገቢና ወጪ በበላይነት የሚቆጣጠር ነበር ማለት ነው። በሌላ በኩል የህወሓትን የፖለቲካ አቅጣጫና እንቅስቃሴ የሚመራውን የህወሓት ዋና እና ምክትል ሊቀመንበሮች በማስወገድ የሚፈልገውን ግለሰብ እንዲሾም አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪ እ.ኢ.አ. በ1993 ዓ.ም ህወሓት ለሁለት ሲከፈል ለመለስ ዜናዊ ስልጣንና መመሪያ ተገዢ አልገዛም ያለውን ቡድን አከርካሪ በመምታት ረገድ ቁልፍ ሚና እንደነበረው ይታወቃል።

በዚህ መሰረት ስብሃት ነጋ ከህወሓት ሊቀመንበሩና ሌሎች አመራሮች ኋላ ተቀምጦ የድርጅቱን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ላይ የመዘወር ስልጣን እንዳለው መገንዘብ ይቻላል። ስለዚህ ስብሃት ነጋ የድርጅቱን የፋይናንስ ገቢና ወጪ የሚቆጣጠር ወይም የፖለቲካ አደረጃጀትና እንቅስቃሴ የሚመራ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ህወሓትን እንደ ትልቅ የቢዝነስ ኩባኒያ ብንወስደው፤ ስብሃት ነጋ የኩባንያው ባለቤት ሲሆን መለስ ዜናዊ ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ (CEO) ነው። የተቀሩት የህወሓት አባላት እና አመራሮች በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የድርጅቱ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ናቸው።

የህዝብ እንደራሴ በነበረው አቶ ገሰሰው/ስሁል አየለ እና ሰባት (7) የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካኝነት የትግራይን ህዝብ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የራስን እድል በራስ የመወሰን ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማረጋገጥ የተመሰረተው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከመስራቾቹ ፍቃድና ይሁንታ ወደ ትማሌሊ ተቀየረ። በዚህ አማካኝነት ህወሓት ከተቋቋመለት ዓላማና ግብ ውጪ በአንድ ግለሰብ ፍላጎትና ቁጥጥር ስር ወደቀ። የደርግ መንግስት መውደቅን ተከትሎ ህወሓት ከትማሌሊ ወደ ¨EFFORT” ተቀየረ። እንደ አንድ ፖለቲካ ድርጅት የዜጎችን መብትና ፍትህ ከማስከበር ይልቅ የስብሃትን ገቢና ትርፍ ለማሳደግ የሚንቀሳቀስ የቢዝነስ ድርጅት ሆነ። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የድርጅቱ አባላትና አመራሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ¨የEFFORT” ወኪልና ሠራተኞች ሆኑ። በዚህ የቴሌቪዥን ቃለ-ምልልስ እንደተናገረው ለስብሃት ¨EFFORT የማን ነው?” የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች የተማሩና የሚያስተውል አዕምሮ ያላቸው መሆኑን ይጠራጠራል። (https://www.youtube.com/watch?v=zmLJNcRMOPE)

ስብሃት ነጋ በቃለ-ምልልሱ እንደገለጸው ¨በEFFORT” ስር ያሉት ድርጅቶች በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሰረት የተመዘገቡ የኢንዶውመንት ድርጅቶች ናቸው። የድርጅቶቹን መነሻ ካፒታል ህወሓቶች ከውጪ ያመጡት ሃብት ነው። በመሆኑም ሲፈልጉ ታንዛኒያ ወይም ሌላ የውጪ ሀገር ማድረግ ሲችሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናቸውን ጠቅሷል። የህወሓት “Exchequer” እንደመሆኑ መጠን የEFFORTን መነሻ ካፒታል ከየት እንዳመጡት በግልፅ የሚያውቀው ስብሃት ነጋ ብቻ ነው። በህወሓት አማካኝነት በሰበሰቡት ገንዘብ በተቋቋሙት የኢንዶውመንት ድርጅቶች ላይ ህወሓት ምንም ዓይነት ድርሻ ሆነ ባለቤትነት እንደሌለው በመጥቀስ፣ በEFFORT ላይ ባለቤትነት ሊኖረው የሚችለው የትግራይ ህዝብ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል።

ይሁን እንጂ ባለፈው አመት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ የEFFORT ድርጅቶችን በአክሲዮን መልክ ወደ ህዝብ ስለማስተላለፍ መወያየት ሲጀምር ስብሃት ድርጅቱ የግል አንጡሯ ሃብቱ እንደሆነ፣ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በራሱና በቤተሰቦቹ ስም ተመዝግቦ እንደሚገኝና ይህን ሃብት ለትግራይ ህዝብ አዘዋውር ብሎ ማንም ሊጠይቀው እንደማይችል ተናግሮ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱ ይታወሳል። በመጀመሪያ የEFFORT ድርጅቶች መነሻ ካፒታል የተገኘው በስብሃት አማካኝነት ነው። ሁለተኛ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የEFFORT ሃብት በስብሃት ስም ተመዝግቦና ገቢውም በእርሱ የባንክ ሂሳብ ገቢ መደረጉን በራሱ ስብሃት ተናግሯል። በዚህ መሰረትEFFORT” ዋና ባለቤት የትግራይ ህዝብ፣ ህወሓት ወይም ሌላ አካል ሳይሆን ስብሃት ነጋ ነው

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ከትማሌሊ ምስረታ በኋላ ህወሓት በስብሃት ፍላጎትና ፈቃድ የሚመራ ድርጅት ሆኗል። ከህወሓት ሊቀመንበር ጀምሮ ያሉትን አመራሮች ለእርሱ ጥቅምና ፍላጎት ተገዢና አገልጋይ እንዲሆኑ በማድረግ ድርጅቱን የግላቸው አድርገውታል። ስለዚህ ስብሃት የህወሓት አባልና አመራር ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ህወሓት ስብሃት የዘረጋው ድርጅታዊ መዋቅርና የሰው ኃይል አደረጃጀት ነው። ይህን ካደረገ በኋላ፤ በአስከፊ ድርቅ ምክንያት ለተራበው የትግራይ ህዝብ ከውጪ የተለገሰ የእርዳታ ገንዘብ፣ በአክሱም ከተማ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተዘረፈ ገንዘብ፣ ከደርግ ሰራዊትና የመንግስት ድርጅቶች የተዘረፈ ሃብትና ንብረት፣ እንዲሁም ምንጩ በግልፅ ያልታወቀ ገንዘብን በማሰባሰብ “EFFORT” የተሰኘ ትልቅ የንግድ ኩባኒያ አቋቁሟል። ስለዚህ ስብሃት EFFORT ባለቤት እና የህወሓት አለቃ። በአጠቃላይ EFFORT እና ህወሃት አንድ ላይ የስብሃት ማፊያ ቡድን ሊባል ይችላል።

የማፊያዎች ስልት ወንጀል መስራት እና ወንጀለኞችን ማበረታታት ነው!

ሀገርና ህዝብ የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት የፖለቲካ ቡድን በተወሰነ ደረጃ የሚታወቅ የተግባር መርህና አቋም ሊኖረው ይገባል። ህወሓት ግን በግልፅ የሚታወቅ ድርጅታዊ መርህና አቋም የለውም። በመሆኑም በቀጣይ ሊወስድ የሚችለውን የተግባር እርምጃ ሆነ ሊያደርግ የሚችለውን የአቋም ለውጥ ማወቅና መገመት አስቸጋሪ ነው። ባለፉት ሦስት አመታት የሀገራችን ህዝብ ሆነ የዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የህወሓትን የተግባር መርህና እርምጃ ለመገመት ያላደረጉት ጥረት የለም። ሆኖም ግን ሌላው ቀርቶ የህወሓት አመራሮችና አባላት የድርጅታቸውን አቅጣጫና እርምጃ በእርግጠኝነት ማወቅ ሆነ መገመት የሚችሉ አይመስለኝም። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የትግራይ ሆኑ የኢትዮጵያ ልሂቃን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህብረሰብ የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪና ዓላማ በግልፅ ማወቅ አለመቻላቸው ነው።

እንደ አንድ የፖለቲካ ቡድን ህወሓት የራሱ የሆነ አቋምና መርህ፣ ዓላማና ግብ፣ የወደፊት አቅጣጫና ዕቅድ አለው። እነዚህ ነገሮች ከሌሉት ህወሓት እንደ ድርጅት ራሱን በራሱ መምራት ሆነ የትግራይ ክልልና ህዝብን ማስተዳደር አይችልም። እንደ አንድ ድርጅት ወይም ቡድን የህወሓት ዓላማና ግብ፣ የሚከተለው አቅጣጫ እና በተግባር የሚመራበት መርህ ምንድነው? ይህን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ከተቻለ የህወሓትን ትክክለኛ ባህሪ እና የወደፊት እርምጃ በእርግጠኝነት ማወቅና መገመት ይቻላል። ስለዚህ ከህወሓት ጋር የሚደረገው ማንኛውም ግንኙነትና እንቅስቃሴ በተጨባጭ በግልፅ በሚታወቅ መርህና አቅጣጫ ላይ የተመሰረተ ይሆናል።

በግልፅ ተለይቶ የሚታወቅ ዓላማና የተግባር መርህ ከሌለው የፖለቲካ ቡድን ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት ያልተጠበቀ ውጤት ያስከትላል። ለምሳሌ የደርግ ውድቀትን ተከትሎ በተቋቋመው የሽግግር መንግስት ውስጥ ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ እንደነበሩ ይታወሳል። ከዚያ በኋላ ባሉት አስር አመታት ውስጥ የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ እነዚህን የፖለቲካ ፓርቲዎች በወታደራዊ ጉልበትና ፖለቲካዊ አሻጥር ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል። በወቅቱ ብዙዎች የችግሩ መንስዔ የኢህአዴግ አገዛዝ አምባገነንነት እንደሆነ ሲገልጹ ነበር።

በ1997ቱ ምርጫ የኢህአዴግን አምባገነንነትና ጭቆና በነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማስወገድ የተደረገው ሙከራ በምርጫ ማጭበርበር፣ እስራትና ግድያ ሳይሳካ ቀረ። ከዚያ በኋላ ባሉት አስር አመታት የኢህአዴግ ጭቆና እና አምባገነንነት ወደ የህወሓት የበላይነት የሰፈነበት የአፓርታይድ ስርዓት ተቀየረ። ባለፉት ሦስት ዓመታት የታየው ለውጥ የመጣው የመንግስታዊ ሰርዓቱን ትክክለኛ ባህሪና እንቅስቃሴ በግልፅ መለየት በመቻሉ ነው። አሁን ያለው ለውጥ የመጣው የሀገራችን መሰረታዊ የፖለቲካ ችግር ከኢህአዴግ አምባገነንነት እና ጭቆና ይልቅ የህወሓት የበላይነት እና አፓርታይድ እንደሆነ በመለየትና በዚህ ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ ንቅናቄ ማድረግ በመቻሉ ነው። የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ የተዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት ከሞላ-ጎደል ወድቋል። በመሆኑም የህወሓትን የበላይነት እና ሌብነት ማዕከል ባደረገ መልኩ የተደረገው ህዝባዊ ንቅናቄና ትግል ዓላማውን አሳክቷል። ይሁን እንጂ የህወሓት የበላይነት ያበቃው በፌደራል መንግስቱ ውስጥ እንጂ በትግራይ ክልል ላይ ከቀድሞ በበለጠ መልኩ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በእርግጥ አብዛኞቹ የህወሓት አባላትና አመራሮች ወደ መቀሌ በመሄድ መሽገዋል። ነገር ግን በህወሓት የአፓርታይድ ዘመን በተለያዩ ጎሳዎች፥ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መካከል የተዘራው ጥላቻና ቂም፣ አለመተማመን እና ጥርጣሬ በየትኛውም ግዜና አጋጣሚ ወደ ግጭትና ብጥብጥ ሊቀየር ይችላል። በዚህ ረገድ የቀድሞ የህወሓት ጄኔራሎች እና ባለስልጣናት፣ የፀጥታና ደህንነት ኃላፊዎች ያላቸውን ልምድና የሙያ ዕውቀት በመጠቀም በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል የእርስ-በእርስ ግጭትና ብጥብጥ እንዲነሳ በማድረግ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋሉ።

በሌላ በመንግሥት ኃላፊዎች፣ ተቋማትና ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት በመፈፀም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማናጋት በፈጸሙት ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች የትግራይ ክልልን መደበቂያ ያደርጋሉ። በመሆኑም የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ህወሓት ዋና እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲደረግ አይፈቅድም። በአንፃሩ የክልሉ ነዋሪዎች የሚያነሱትን የማንነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በኃይል ለማዳፈን ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል። በመሆኑም የትግራይን ክልል ጨምሮ በሀገር-አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ በዘላቂነት ማስቀጠል፣ በዚህም የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት በሚደረገው ጥረት ህወሓት ዋና እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል።

ህወሓት በፌደራል ስርዓቱ ላይ የራሱን የበላይነት ለማረጋገጥ የዘረጋውን የአፓርታይድ ስርዓት ለመታገል እና ለማስወገድ ያስቻለው ስልት ከዚህ በኋላ አዋጭ አይደለም። ምክንያቱም በፌደራል ደረጃ የነበረው የህወሓት የበላይነት ከሞላ ጎደል አብቋታል። ከዚህ በኋላ ህወሓት የለውጡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚጠቀመው ስልት የወንጀል ተግባራትን በመፈፅም እና ለወንጀለኞች መሸሸጊያ በመሆን የህግ የበላይነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ማስተጓጎል ነው። በትግራይ ክልል የለውጥ ጥያቄን በኃይል በማፈን እና በሌሎች ክልሎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋል። ከዚህ በኋላ የህወሓት ስልትና ተግባር ወንጀል በመስራት እና ወንጀለኞችን በማበረታታት የተጀመረውን ለውጥ ማስተጓጎልና መቀልበስ ይሆናል።

በዚህም መንግስትና ዜጎች ለውጡን ከማስቀጠል ይልቅ ፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴዎችን በመከላከል ላይ እንዲወጠሩና በሂደት በለውጡ ተስፋ እንዲቆርጡ ማድረግ ነው። የጸረ-ለውጡ እንቅስቃሴ እየተጠናከረ ሲመጣና የዜጎች ሰላምና ደህንነት፣ እንዲሁም የሀገሪቱ አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ መንግስትም በጸረ-ለውጡ ኃይሎች ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል። ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ለውጡን ለማደናቀፍ የሚደረገው ጥረት በፀረ-ለውጡ ወገን ላይ እልቂት ከመጋበዝ የዘለለ ፋይዳ የለውም። ይህን ተከትሎ ጸረ-ለውጡን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚወስደው የኃይል እርምጃ መንግስትን ይበልጥ አምባገነን ያደርገዋል። የለውጡን ደጋፊዎች ወደ ጦርነት ከማስገባት እና መንግስትን አምባገነን ከማድረግ በዘለለ የጸረ-ለውጡ ኃይል ተመልሶ ስልጣን የመያዝ ዕድል የለውም። ይህ ልክ እንደ ጸረ-ለውጡ ኃይል በፍፁም የማይቀየር ሃቅ ነው።

“EFFORT” የማፊያ ቡድን ንብረት ስለሆነ መወረስ አለበት!

“የስብሃት ማፊያ ቡድን” አስመልክቶ ከላይ ባሉት ርዕሶች ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ መቀሌ ላይ የመሸገው ህወሓት በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማስቀጠል እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ዋና እንቅፋት ሆኖ ይቀጥላል። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የብሔር ግጭትና ብጥብጥ በማስነሳት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ያደርጋል። በተለይ በትግራይ ክልል ደግሞ ምንም ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይጀመር እንቅፋት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ የስብሃት ማፊያ ቡድን ለኢኮኖሚ እድገት እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዳይኖር ዋና ማነቆ ነው።

በመሠረቱ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ዘላቂነት የሚኖረው በኢኮኖሚው ዘርፍ ስር-ነቀል ለውጥና ማሻሻያ ሲደረግ ነው። ምክንያቱም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋለውን ህገወጥ አሰራርና የጥቅም ትስስር ማስወገድ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት ማቅረብ የግድ አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችና ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ የጉምሩክና ታክስ አስተዳደር፣ የመሬት፥ ብድርና የውጪ-ምንዛሬ አቅርቦት፣ የቢዝነስ ማበረታቻና ድጋፍ አሰጣጥ ረገድ የሚስተዋለውን አድሏዊ አሰራር መቀየር ይኖርበታል።

በተለይ ደግሞ ለአዳዲስ ኢንቨስተሮች እና ሥራ ፈጣሪዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግላቸው ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸውና ድጋፍና ማበረታቻ እየተደረገላቸው ያሉት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች ናቸው። በዚህ ረገድ በተባበሩት መንግሥታትና የዓለም ባንክ ድጋፍ የተሰሩ ጥናቶች፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ምሁራን የተሠሩ ጥናቶች ለአዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች (entrepreneurs) እና ድርጅቶች ዕድገትና መስፋፋት ዋና ማነቆ የሆነባቸው የመንግሥት ድጋፍና ማበረታቻ ከሚደረግላቸው ትላልቅ ድርጅቶች ናቸው።

በጥናቱ መሰረት ከጀማሪ እና መካከለኛ ደረጃ ያሉ የቢዝነስ ድርጅቶች ከመሬት፣ ብድርና የውጪ ምንዛሬ አንፃር የተሻለ አቅርቦት እና ድጋፍ ከሚደረግላቸው የመንግስት ድርጅቶች (State-owned enterprises) እና የኢንዶውመንት ድርጅቶች (party-affiliated endowments)፣ እንዲሁም የውጪ ድርጅቶች ጋር ኢፍትሃዊ ውድድር ውስጥ መግባታቸው ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል። በሌላ በኩል እ.አ.አ. በ2009 ዓ.ም በዓለም ባንክ የተሰራ ጥናት የግል ቢዝነስ ተቋማት በመንግስት አሰራር፥ ሙስና እና የተንዛዛ ቢሮክራሲ፣ ከጉምሩክና ታክስ አስተዳደር፣ በመሬት፥ ብድርና የውጪ-ምንዛሬ አቅርቦት፣ እንዲሁም በመንግስት ማበረታቻና ድጋፍ አሰጣጥ ረገድ የሚገጥሟቸው ችግሮች ለመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች አሳሳቢ አለመሆናቸውን አረጋግጧል።

በዚህ መሰረት በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እና በመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች መካከል መሰረታዊ የሆነ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በህወሓት/ኢህአዴግ የተዘረጋው የኢኮኖሚ ስርዓት ከፓርቲና የመንግስት ፖለቲካ ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው። በዚህ ረገድ “Tilman A. (2010)” የተባለ ጀርመናዊ የስነ-ምጣኔ ምሁር “Industrial policy in Ethiopia” በሚል ርዕስ የሰራውን ጥናት በግል የቢዝነስ ድርጅቶች እና በመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶች መካከል የሚስተዋለው ልዩነት የፖለቲካዊ ስርዓቱ ውጤት እንደሆነ ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ እርስ በእርስ የተጠላለፉ ናቸው፡-

“…business and politics are still strongly entwined in Ethiopia. State-owned enterprises (SOEs) still dominate many manufacturing industries and service sectors, and party-affiliated endowments have taken many of the business opportunities left for private engagement. To date Ethiopia is clearly anything but a predatory state whose government pillages the economy. … Power constellations may change, those who have vested interests in SOEs and endowment-owned enterprises may gain political influence, and political power shifts may force political leaders to compromise on their development agenda.” Tilman A. (2010): Industrial policy in Ethiopia / Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010. − (Discussion Paper / Deutsches Institut für Entwicklungspolitik ; 2/2010) ISBN 978-3-88985-477-3

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ የመንግስት ድርጅቶች የማምረቻና አገልግሎት ኢንዱስትሪውን በበላይነት የተቆጣጠሩ ሲሆን የኢንዶውመንት ድርጅቶቹ ለግል ድርጅቶች የሚሆነውን ዘርፍ ተቀራምተውታል። እስካሁን ድረስ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኪራይ ሰብሳቢ እና ጥገኛ ከመሆኑም በላይ የፖለቲካ ለውጥ በሚኖርበት ግዜ የመንግስትና ኢንዶውመንት ድርጅቶቹን የፖለቲካ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሚጠቀምባቸው ይገልፃል። ለአዳዲስና ጀማሪ የሆኑ አነስተኛና መካከለኛ የግል ቢዝነስ ተቋማትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻለው የመንግስት እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች በኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅዕኖ መቀነስ እና/ወይም ማስወገድ ሲቻል ነው።

ከላይ በተገለጸው መሰረት በህወሓት መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት የልማት ድርጅቶችን በመንግስት ቁጥጥር ስር ያደረገው የሀገርና ህዝብ ሃብትን ያለ ከልካይ ለመዝረፍ እንዲያመቸው ነው። የኢኮኖሚ እድገቱን ለማስቀጠል እና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ኢንዶውመንት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዘዋወር አለበት። ይህ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በበላይነት ለመቆጣጠር በሚከተሉት ስልት ምክንያት በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖ መግታት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ የሚታየውን የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ያስቀራል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ኢንዶውመንት ድርጅቶች ወደ ግል ሲዘዋወሩ በምርት ዋጋና ጥራት ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን የገበያ ስልት ይቀይሳሉ። በመሆኑም ምርቶቻቸውን ለአካባቢው ማህብረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርባሉ። በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪና ትርፋማ ስለሚሆኑ ለአካባቢው ማህብረሰብ ሆነ ለሀገሪቱ አሁን ካለው በተሻለ ሁኔታ ተጨማሪ የሥራ እድል ይፈጥራሉ። እነዚህን ድርጅቶችን ወደ ግል በማዘዋወር መንግስት ለመሰረተ-ልማት ግንባታ የሚሆን ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛል። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ትእምት (EFFORT) ያሉ የኢንዶውመንት ድርጅቶችን በመውረስና ወደ ግል ማዘዋወሩ የህወሓት ባለስልጣኖች እያገኙት ያለውን ያልተገባ ጥቅም ያስቀራል። ይሁን እንጂ እነዚህ ድርጅቶች የስብሃት ማፊያ ቡድን የግል ንብረት ናቸው።

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚደረገው ጥረት የስብሃት ማፍያ ቡድንን ከማስወገድ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ህወሓት በፌደራል መንግስት ውስጥ የነበረውን የስልጣን የበላይነት ሲያጣ በፌደራል የመንግስት የልማት ድርጅቶች አማካኝነት በሀገርና ህዝብ ላይ ሲፈፅም የነበረው ቅጥ ያጣ ዘረፋና ሌብነት መጋለጡ ይታወሳል። በመሆኑም ይህ የማፊያ ቡድን ወደ መቀሌ ሲሄድ ከስልጣኑ በተጨማሪ ዘረፋና ሌብነቱ ቀንሷል። ሆኖም ግን የትእምት (EFFORT) ኢንዶውመንት ድርጅቶች እስካሉ ድረስ የፋይናንስ ምንጩ አይደርቅም። የስብሃት ማፊያ ቡድን ከእነዚህ ድርጅቶች የሚያገኘውን ገንዘብ ወንጀል ለመፈፀም እና ወንጀለኞችን ስፖንስር ለማድረግ ይጠቀምባታል። የትእምት (EFFORT) ድርጅቶችን በዚህ ማፊያ ቁጥጥር ስር ሆነው እንዲቀጥሉ መተው የተጀመረውን ለውጥ እንዲቀለበስ የመፍቀደ ያህል። እነዚህ ድርጅቶች ከህወሓት እጅ እስካልወጡ ድረስ ለውጡን፤ ማስቀጠል ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት አይቻልም። በአጠቃላይ የዶ/ር አብይ አመራር ትእምትን (EFFORT) ካልወረሰ ህወሓትን ሰዶ-ሲያሳድድ ይኖራል።

ማጣቀሻዎች

UNCTAD (United Nations Conference on Trade and Development) (2004): An investment guide to Ethiopia: opportunities and conditions, Geneva, March

World Bank (2007a): Ethiopia: accelerating equitable growth: country economic memorandum, Washington, DC

Zerihun, A. (2008): Industrialisation policy and industrial development strategy in Ethiopia, in: T. Assefa (ed.), Digest of Ethiopia’s national policies, strategies and programs, Addis Ababa: Forum for Social Studies, 239−281

World Bank (2009): Ethiopia: towards the competitive frontier: strategies for improving Ethiopia’s investment climate, Washington, DC

Tilman A. (2010): Industrial policy in Ethiopia / Tilman Altenburg. – Bonn : DIE, 2010. − (Discussion Paper / Deutsches Institut für Entwicklungspolitik ; 2/2010) ISBN 978-3-88985-477-3

በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ሌብነት ለተጠረጠሩ የመንግስት ሃላፊዎች ይቅርታ ማድረግ ችግር አለው?

የደርግ መንግስት ዘወትር “ሀገር ገንጣዮች፥ ወንበዴዎች፥ ሽፍታዎች፥…” ሲላቸው የነበሩት ህወሓቶች በመጨረሻ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን ተቆጣጠሩ። ከዚያ በኋላ ብዙዎች የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የሚያራምደው የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በተለያዩ ብሔር ተወላጆች መካከል ግጭት ያስነሳል፣ ሀገር ያፈርሳል፣… ወዘተ ሲሉ ትኩረት ሰጥቶ የሰማቸው አልነበረም። በ1997 ዓ.ም የኢህአዴግ አምባገነንነትን በምርጫ ከህዝብ ጫንቃ ላይ ለማውረድ የተደረገው ጥረት ብዙዎችን ለእስራት፣ ስደትና ሞት ዳርጓል።

ባለፉት ሦስት አመታት የህወሓት የበላይነትን ለማስወገድ በተደረገው ትግል አብዛኞቹ የህወሓት አመራሮችና አባላት ከአዲስ አበባ በመሸሽ መቀሌ መሸጉ። በመቀጠል በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በከፍተኛ የዘረፋና ሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩ አባላትና አመራሮችን ለፌደራሉ መንግስት አሳልፎ ላለመስጠት መዛትና ማስፈራራት ጀመሩ። በዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ የሆነ ግፍና በደል የፈፀሙ፣ ሀገርና ህዝብን በጠራራ ፀሐይ የዘረፉ ሌቦችን በህግ ቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ በትግራይ ህዝብ ላይ የተቃጣ ንቀት እንደሆነ ይገልፃሉ። ሆኖም ግን የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የህወሓት አመራሮች እና አባላት የተከሰሱበት ወንጀል እንኳን በተግባር ለመፈፀም በጆሮ ለመስማት የሚዘገንን ኢሰብዓዊ ድርጊት ነው። ከዚቺ ደሃ ሀገር ላይ የዘረፉት ገንዘብ ለመቁጠር የሚከብድ ነው።

በሌላ በኩል የትግራይ ክልላዊ መንግስት እና የህወሓት ደጋፊዎች በወንጀል የተጠረጠሩትን ሰዎች ከህግ ተጠያቂነት ለመከላከል የሄዱበት ርቀት በጣም ያሳፍራል። የህወሓት ተቃዋሚ ወይም ገለልተኛ የነበሩ ልሂቃን ውስጥ አንዳንዶቹ “ለምን ህወሓቶች ብቻ ይከሰሳሉ?” በሚል ሰበብ የተከሳሾች “የብሄር ስብጥር ተመጣጣኝ” ሊሆን ይገባል ሲሉ ይሰማል። አንዳንዶቹ ደግሞ “ዘመኑ የይቅርታና ምህረት ነው” እስከተባለ ድረስ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከባድ ዘረፋ ለተሰማሩ ሰዎች ጭምር ይቅርታና ምህረት ሊደረግ ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። ይሁን እንጂ በተለይ በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለተከሰሱ ሰዎች የዶ/ አብይ መንግስት ሆነ ሌላ አካል ይቅርታና ምህረት የማድረግ መብት ሆነ ስልጣን የለውም።

በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጠረጠሩት ሰዎች ላይ በአቃቤ ህግ በኩል የከሰሳቸው የሀገሪቱ መንግስት ሳይሆን የመብት ጥሰት የተፈፀመባቸው ዜጎች ናቸው። ስለዚህ ከከሳሾቹ ፈቃድና ይሁኝታ ውጪ ማንም ቢሆን ለእነዚህ ተከሳሾች ምህረትና ይቅርታ ማድረግ አይችልም። የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመባቸው ሰዎች ለተከሳሾች ይቅርታና ምህረት እንዲያደርጉላቸው ከተፈለገ በቅድሚያ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። በዜጎች ላይ የፈፀሙት አሰቃቂ ግፍና በደል፤ በችሎት ፊት የሚያምኑትን አምነው፣ የሚቃወሙትን ክስ በማስረጃ ተከራክረው ውድቅ ከተደረገ በኋላ ይፈረድባቸው ወይም ይፈረድላቸው። በዚህ መሰረት ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ተከሳሾች ለፈፀሙት ጥፋት ተጠቂዎችን ይቅርታ በመጠየቅ የህሊና እረፍት ማግኘት ይችላሉ። እነዚህ ሰዎች ለፍርድ ሳይቀርቡ፣ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ለፈፀሙት ወንጀል የጥፋተኝነትና ጸጸት ስሜት ሳይሰማቸው ይቅርታና ምህረት መጠየቅና ማድረግ በከሳሾች ላይ ተጨማሪ በደልና ግፍ መፈፀም ነው።

በሌላ በኩል በከባድ የዘረፋና ሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩትን ሰዎች በፌደራል አቃቤ ህግ በኩል የከሰሰው የኢትዮጵያ መንግስት ነው። በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩት ሰዎች በመንግስት የተጣለባቸውን ስልጣንና ሃላፊነት በመጠቀም በሀገር ሃብት ላይ ከፍተኛ ዘረፋና ሌብነት ፈፅመዋል። ይህን የወንጀል ተግባር የፈጸሙት ደግሞ በአብዛኛው ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው። የተጠረጠሩበት ከጉቦና ያልተገባ ጥቀም ባለፈ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገትና ሉዓላዊነት፣ እንዲሁም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የዘረፋና ሌብነት ተግባራት ነው። ስለዚህ እነዚህ ተጠርጣሪዎች ለፍርድ ሳይቀርቡ ከቀሩ ወይም ይቅርታና ምህረት ከተደረገላቸው የህግ በላይነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ አይቻልም።

በዚህ መሰረት በከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና የዘረፋና ሌብነት ተግባር የተጠረጠሩ የመንግስት ኃላፊዎችን ለፍርድ አለማቅረብ የሀገሪቱ አንድነትና ሉዓላዊነት እና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለአደጋ ያጋልጣል። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሀገርና ህዝብ ማስተዳደር ይሳነዋል። በዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ እድገት እና የፖለቲካ መረጋጋት አይኖርም። ለዚህ ደግሞ በወንጀል የተጠረጠሩት የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ከዚህ ቀደም የዘረፉትን ሃብት እና በመንግስት ስራ ላይ ያላቸውን ልምድና ግንኙነት በመጠቀም መንግስት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ሰርገው በመግባት ዳግም “የማፊያ መንግስት” (Mafia State) ይመሰርታሉ።

በእርግጥ ብዙዎች “የማፊያ መንግስት” (Mafia State) ሲባል እውነት ላይመስላቸው ይችላል። ነገር ግን ባለፉት 27 አመታት ውስጥ የህወሓት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት ለምን በዜጎች ላይ ጨካኝና ጨቋኝ እንደሆኑ፣ በሀገር ሃብት ላይ ከፍተኛ የዘረፋና ሌብነት ተግባር እንደፈፀሙ ከተለመደ ግምትና መላምት የዘለለ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ሲፈፀም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ዘረፋ ከህዝብ የተሰወረ ሚስጥር ሆኖ አይደለም። ከዚያ ይልቅ አብዛኞቹ የሀገራችን ልሂቃን በህወሓት መሪነት የተዘረጋውን መንግስታዊ ስርዓት ትክክለኛ ባህሪና ዓላማ መገንዘብና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ መስጠት ስለተሳናቸው ነው።

የህወሓት መሪዎችና አባላት ትላንት ሲያደርጉት የነበረው በደልና ዘረፋ፣ ዛሬ እያደረጉት ያለውን እና ነገ ላይ የሚያደርጉትን ለመገመት ስለ ማፊያ መንግስት ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል። ይህ ሲሆን የህወሓት/ኢህአዴግ አገዛዝ ትክክለኛ ባህሪና ዓላማ ምን እንደሆነ፣ አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ከባድ የሆነ ዘረፋና ሌብነት የፈጸመብትን መሰረታዊ ምክንያት፣ እንዲሁም በቀጣይ የሚከተለውን አቅጣጫና የሚወስደውን እርምጃ በግልፅ መገንዘብና መገመት ይቻላል። በቀጣይ ክፍል ስለ ማፊያ መንግስት በዝርዝር እንመለከታለን።

ስዩም ተሾመ

የአዘጋጆቹ ማስታወሻ፤ ይህ ጽሁፍ በስድስት ክፍል ተከፋፍሎ የወጣ ሲሆን ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ለራሱ እንዲመቸው አድርጎ በአንድ አትሞታል። በጽሁፉ ውስጥም የተለወጡና የተሰረዙ ቃላትና ዓርፍተ ነገሮች ይኖራሉ።


6ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 6 - ERi-TV Documentary

Dehai Events