World News

DW.com: የሕወሃት አመራር የኃይል አሰላለፍ

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Thursday, 30 August 2018

August 30, 2018

ከኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ በኋላ ሕወሀት ውስጥ ሁለት ኃይል መፈጠሩን የፓርቲው አንጋፋ ታጋይ ገለጹ። የቀድሞ የማዕ/ኮሚቴ አመራርና የኢትዮጵያ ሃገር መከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹም ሌተና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንኤ ለዶቼቨለ እንደተናገሩት፣ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ የማይደግፈው ኃይል በሕዝቡ ውስጥ ሥጋት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:46

የትግራይ ሕዝብ እና ሕወሃት አንድ ነው የሚለውን አባባል ሕዝቡን የሚያሳንስ እና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት የሚቃወሙት ሌተና ጄኔራል ጻድቃን አባባሉ ሥልጣኑን አጥቷል ያሉት ቡድን ወደ ቀድሞው አፈናው ለመመለስ እና የፈጸማቸውን የተለያዩ ጥፋቶች ለመደበቅ የሚጠቀምበት ሥልት ነው ብለዋል :: በሕወሃትም ሆነ በኢሕዲግ አመራር ውስጥ የለውጡ ተቀናቃኝ ሲሉ የገለጹት ኃይል ዳግም ሥልጣን ላይ ከወጣ ለትግራይም ሆነ ለመላው አገሪቱ አደጋ እንደሚሆንም አስጠንቅቀዋል :: 

ከሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለውጡ በፊት የነበረው የኢሕአዲግ አስተዳደር ፖለቲካዊ ችግሮችን በሃይል የሚፈታ የሕዝቦችን ዲሞክራሲያዊ መብት የገፈፈ እና ከፍተኛ ጭቆና የሚፈጽም ነበር ሲሉ የቀድሞ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር እና የኢትዮጵያ የሃገር መከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹም ሌተናት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ገልጸዋል :: የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይን ወደ ሥልጣን መምጣት በአገሪቱ አንዣቦ የነበረውን አስፈሪ የፖለቲካ ቀውስ እና የሥጋት ደመና የገፈፈ እንዲሁም የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በመሆኑ ለውጡን በእጅጉ እደግፈዋልሁም ብለዋል :: 


በተለይ በትግራይ ጭቆና አፈና እና የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እጅግ የከፋ ነው፣ ሕዝቡ በሕወሃት አመራሮች እግር ተወርች ታስሯል የሚሉት አንጋፋው የሕወሃት የቀድሞ አመራር ሌተናት ጄኔራል ጻድቃን ነጻነት እና ለውጥ ሲናፍቅ የኖረው የትግራይ ሕዝብ ፖለቲካዊ ለውጡን ተከትሎ ከሌላው ኢትዮጵያዊ እኩል የምንጠቀምበት ጊዜ መቷል የሚል ትልቅ ተስፋ እንደነበረው ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አልፎ አልፎ የሚታየው ሕዝቡንም ከአመራሩ ጋር በጅምላ የመፈረጅ እንቅስቃሴ ለውጡን በስጋት እና በጥርጣሬ እንዲመለከት እያስገደደው መቷል በማለት ተናግረዋል :: ለውጡን አይደግፍም ያሉት ኃይልም ይህን አጋጣሚ እየተጠቀመበት መሆኑንም ገልጸዋል :: 

/
-በትግራይ መንግሥት እና ፓርቲ ባልተለየበት የመንግሥት አወቃቀር ሥርዓት ሕዝቡ ከፍተኛ መከራ እና ግፍ እየደረሰበት በመሆኑ ድርጅቱ አስቸኳይ የፖለቲካ ሪፎርም እንደሚያስፈልገው ጄኔራሉ አስታውቀዋል :: የትግራይ ሕዝብ በተለይም ወጣቱ ለውጡን የሚፈልገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይን ከመደገፍ አንጻር ብቻ ሳይሆን የፍትህ ሥርዓት እንዲነግስ እና የሕዝቡን መብት የሚያስጠብቁ ነጻ ተቋማት እንዲፈጠሩ የግድ ስለሚያስፈልግም ነው ብለዋል::
ሌተናት ጄነራል ጻድቃን የትግራይ ሕዝብ እና ሕወሃት አንድ ናቸው እየተባለ በአንዳንድ ወገኖች ስለሚነሳው አወዛጋቢ ጉዳይም ፈጽሞ አንድ አለመሆናቸውን ነው የገለጹት :: 


አዲሱ የመንግሥት አመራር በደንብ መልኩን አውጥቶ አለመግለጹም ሆነ የለውጥ ሂደቱን ተከትሎ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዚህ በኋላ የሚከተሉት የፖለቲካ መስመር ጥርት ብሎ አለመታየቱ ስጋት እንደፈጠረባቸው ጄነራሉ አልሸሸጉም :: አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታየው አለመረጋጋትም እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ 

አርያም ተክሌ
 


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events