World News

Goolgule.com: የአብዲ ኢሌይ መጨረሻ ሲጀምር

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Thursday, 05 July 2018

 

የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት (ሒውማን ራይትስ ዎች) በዛሬው ዕለት (ጁላይ 4) “እንደ ሞቱ ሰዎች ነን፤ የሶማሊ ክልል በሚገኘው የዖጋዴን እስር ቤት የሚካሄደው ስቅየትና ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች” “We are Like the Dead’: Torture and other Human Rights Abuses in Jail Ogaden, Somali Regional State, Ethiopia” በሚል ርዕስ የ88 ገጽ ዘገባ አውጥቷል።

ዘገባው ፍጹም ጭከናና መረን የለቀቀ የማሰቃየት፣ አስገድዶ የመድፈር፣ ቶርቸር የማድረግ፣ እና የማዋረድ ተግባራትን በታሳሪዎች እንዴት እንደሚፈጸም የሚያትት ሲሆን ይህም ለታሳሪዎች የቤተሰብ ጥየቃን፣ ከጠበቃ ጋር የመገናኘትን እንዲሁም ምግብ እስከ መከልከል የደረሰ እንደሆነ ያስረዳል። እስር ቤቱ የሚመራው በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ሞሐመድ ኦማር ወይም በቅጽል ስሙ አብዲ ኢሌይ በሚታዘዘው ልዩ ፖሊስ ሲሆን አብዛኛዎቹ እስረኞች የተከሰሱት ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግምባር (ኦብነግ) ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ነው። ሌሎችም የተቃዋሚ ቡድን አባላት በዚህ አስርቤት የሚገኙ ሲሆን አብዛኛዎቹ መቼም ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ያልቀረበ እንደሆነ በሪፖርቱ ተመልክቷል።

የሪፖርቱ ዋና አቀናባሪና በሒውማን ራይትስ ዎች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን “አዲሱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ/ር የደኅንነት ሰዎች ኢትዮጵያውያንን ማሰቃየታቸውን ቢያምኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ግፍ እየፈጸሙ ለፍርድ ሳይቀርቡ እና ተጠያቂ ሳይሆኑ የመቅረትን ባህል (እስከ ጥግ) ሊዋጉት ይገባል” ብለዋል። ሲቀጥሉም “በዖጋዴን አስር ቤት ውስጥ የሚፈጸመው አሰቃቂ ተግባር በተመለከተ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፣ ሌሎች የሶማሊ ክልል ባለሥልጣናትና ልዩ ፖሊስ ላይ ፈጣንና ግልጽ ምርመራ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል።

ዘገባው የተጠናቀረው ወደ 100 የሚጠጉ ሰዎችን በማነጋገር ሲሆን ይህም የደኅንነት ሰዎችን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና 70 በእስር ቤቱ ታስረው የነበሩ እንዲሁም እኤአ ከ2011 እስከ 2018 በዖጋዴን እስር ቤት የተፈጸመውን በሰነድ የተደገፈ ማስረጃ መሠረት በማድረግ ነው።

ከታሣሪዎች አንደበት (ስማቸው ለደኅንነታቸው ተቀይሯል)፤

አብዱሳሌም፣ ዕድሜ 28፤

“ለሦስት ዓመታት በእስር በቆየሁባቸው ጊዜያት በፍጹም ጭለማ ውስጥ ለብቻዬ ታስሬ ነው የነበርኩት፤ ማታ ሲሆን ሊያሰቃዩኝ  ያወጡኝ ነበር፤ (የእስር ቤት ኃላፊዎች) ብዙ ነገሮችን ፈጽመውብኛል፤ የብልቴን የዘር ከረጢት በኤሌክትሪክ አቃጥለውኛል፤ በሽቦ ካሰሩኝ በኋላ በላስቲክ ውስጥ በርበሬ (ሚጥሚጣ) በራሴ ላይ አድርገው (አፍነውኛል)፣ በጣም እንዳልጮህ አፌን አስረውታል፤ ቀን ቀን በጣም ትንሽ ምግብ ይሰጡኛል፤ አንድ ዳቦና አንዳንዴ ጥቂት ወጥ ያለበት፤ በዚሁ ኦጋዴን እስር ቤት የነበረችውን ሚስቴን አስገድደው ደፍረዋታል፤ የኔ ያልሆነ ልጅም እዚያው ወልዳለች”።

ሌሎቹን እስረኞች ለማስፈራራት ታሳሪዎች በእስረኛው ሁሉ ፊት ዕርቃናቸውን ተደርገው ተገርፈዋል፣ ተደብድበዋል፣ ሌሎች አሣፋሪ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ተደርገዋል።

ሆዳን፣ ዕድሜ 30፤

“በየምሽቱ ሰዎችን ሲገርፉ፣ ሲደበድቡ እሰማለሁ፤ ብዙ የሰቆቃ ጩኸትም እሰማለሁ፤ ጠዋት ላይ ሰዎች በክፍሌ ደጃፍ ቁርስ እየበሉ በቀስታ ባለፈው ማታ የተፈጸመውን አንስተው ያወራሉ፤ ‹ትላንት ማታኮ እከሌን እና እከሌን እኮ በድብደባ ተገድለዋል፤ እገሊትና እነገሊት ደግሞ ተደፍረዋል፣ ተደብድበዋል› ይላሉ፤ በየጠዋቱ የሞቱትን ወይም ወደ ክፍላቸው ያልተመለሱትን እንቆጥራለን፤ ነገ የኔ ተራ ይሆን በሚል በየቀኑ በማያቋርጥ ፍርሃት ውስጥ እንኖራለን”።

ፋጡማ፣ ዕድሜ 30፤

“እጃችንን የፊጥኝ በገመድ ያስሩና ከአናቴ በላይ ከፍታ ባለው የውሃ ገንዳ ውስጥ ይደፍቁናል፤ በአንድ ጊዜ በገንዳው ውስጥ 10 ሰዎች ያደርጋሉ፤ … የተለመደውን ጥያቄ ‹ከኦብነግ ውስጥ ማንን ታውቂያለሽ? እንዴት ነው የምትረጂያቸው?› በማለት ይጠይቁናል፤ አንዳንዶቹን ከውሃው ሲያወጧቸው ምንም አይንቀሳቀሱም፤ ሞተው ይሆን እኔ አላውቅም”።

ዓሊ፣ ዕድሜ 32፤

“ሲመሽ ግምገማ ይጀመራል፤ ይህንን ታሳሪዎች ናቸው እርስበርሳቸው የሚያደርጉት፤ ሲነጋ ለጠባቂዎቹ ሪፖርት ይቀርብላቸዋል፤ ብዙ የካደ በጣም ይሰቃያል፤ ጥሩ የተናዘዘ ቅጣቱ ይቀንስለታል፤ ጥፋተኛ መሆኑን በደንብ ያመነ በግምገማው ወቅት ብዙዎች ያጨበጭቡለታል፤ ነገርግን አላምንም ያለ እዚያው ካባሱ (የእስረኞች አለቃ) ይደበድበዋል”።

ሞሐመድ፣ ዕድሜ 28፤

“በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዕርቃናቸውን ሆነው አይቻለሁ፤ ማታ ነበር ደግሞ ይዘንብ ነበር፤ ውጭውም ጭቃ ነበር፤ ከክፍላችን እንድንወጣ አድርገውን ነበር፤ ልብሳችንን እንድናወልቅ ነገሩን፤ ከዚያም ጭቃው ላይ እንድንከባለል አደረጉን፤ ከዚያ አንዳንዶቻችን ወደየክፍላችን ዕርቃናችንን ተወሰድን፤ ሌሎቹ ደግሞ አንዱ የሌላውን ብልት በመያዝ በመስመር እንዲሄዱ ተነገራቸው፤ ወደ ክፍል ከተወሰድን በኋላ እንድንወጣ አይፈቀድልንም፤ ይህንን ክስተት ጠባቂዎቹ እየሳቁ ፎቶ ያነሳሉ”።

አብዲራህማን፣ ዕድሜ 31፤

“ሁልጊዜ አንዳችን ሌላችንን እንድናዋርድ ይነገራናል፤ ከሁሉ የከፋው የተከሰተው ግን አንድ ቀን በርከት ያልን እስረኞችን አመጡንና አንዳችን ሌላችንን እስንሞት እንድንደበድን ነገሩን፤ ለዚህም የብረት መደብደቢያ ሰጡን፤ እምቢ ካልኩ ራሴን መግደል እንዳለብኝ ተነገረኝ፤ እምቢ የሚሉትን ራሳቸው ይደበድቡናል – የከፋው ግን የሚደርስብን የስነልቦና ቅጣት ነው”።

ዓይና፣ ዕድሜ 30፤

“እኔ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ የተወለዱት ህጻናት በሙሉ ከሌሎች ሴት እስረኞች ከተደረገላቸው በስተቀር አንዳቸውም ምንም የባለሙያ ዕገዛ አልተደረገላቸውም፤ እኔ ራሴ መውለጃዬ ሲቃረብ (የሕክምና ዕርዳታ) እንዲደረግልኝ ጠይቄ ነበር፤ ልዩ ፖሊሱ የመለሰልኝ ‹ልጁን ሽንት ቤት ጨምሪው፤ ምንም አይጠቅሙን፤ ምክንያቱም ካደጉ በኋላ የኦብነግ ደጋፊ ነው የሚሆኑት› በማለት ነበር፤ ለመውለድ ወደ ሆስፒታል እንድወሰድ ስጠይቅ ሳቁብኝ፤ ተጨማሪ ውሃ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ ከለከሉኝ፤ ስለዚህ እዚያው እስር ቤት ውስጥ ወለድኩ፤ ሴቶቹ ስለታም ብረት ስለነበራቸው ዕትብቱን ቆረጡልኝ ከዚያም አሠሩልኝ”።

ዓሚና፣ ዕድሜ 34፤

“የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን ለመመርመር ሲመጣ ከበድ ያለ ጉዳይ ያላቸውን አወጧቸው፤ አዳዲሶቹን ተዋቸው፤ ከተደበቁት ሰዎች አንዷ ነበርኩ፤ ወደ ጋርባሳ ወታደራዊ የጦር ሠፈር (ሚሊታሪ ካምፕ) ነበር የተወሰድነው፤ ለመጀመሪ ጊዜ እዚያ ለሰባት ቀን ተቀምጬ ነበር፤ አረጋውያን ሴቶችን፣ ፊታቸው ላይ የተመቱትን፣ ወይም ቁስል ያለባቸውን ወይም ህጻናት ልጆች ላቸውን በሙሉ አውጥተዋቸው ነበር”።

አብዲ በቅርቡ ከኢጋድ ኃላፊነቱ በቀጭን ደብዳቤ በፍጥነት ከተባረረው ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር አለምሰገድ አብርሃ፤ ፎቶ ምንጭ ኢንተርኔት

“አንድ ጊዜ በሰዉ ሁሉ ፊት መሬት ላይ ዕርቃኔን እንድተኛ አደረጉኝ፤ ከዚያም ጭቃ ላይ እንድንከባለል በማድረግ በዱላ ደበድቡኝ ነበር” ይላል ለአምስት ዓመት ያለ አንዳች ክስ የታሰረው የ40 ዓመቱ ሆዳን። “አንድ ቀን አንድ አዛውንት ሰው ከሴት ልጁ ጋር ዕርቃኑን እንዲቆም አደረጉት … በሌሎች እስረኞች ፊት እንዲህ ስትደረግ ኃፍረት ይሰማሃል”።

ታሣሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ከፍተኛ የልዩ ፖሊስ አባላት በእስረኛው ላይ ቶርቸር (ስቅየት)፣ አስገድዶ መድፈር፣ ምግብ መከልከል እንዲፈጸም የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም በማሰቃየቱና አስገድዶ በመድፈሩ ላይ ይሳተፋሉ። በእስር ቤቱ ውስጥ የእስረኛው ቁጥር ከመጠን በላይ መሆን፣ ከዚያ ጋር ቴይዞ የሚፈጸመው ስቅየት፣ ምግብና ውሃ ክልከላ፣ ከንጽህና ጉድለት ጋር የተያያዙ በሽታዎች እንዲከሰቱ በማድረግ ለበርካታዎች ሞት ምክንያት ሆኗል።

እርጉዝ እስረኞች ልጆቻቸውን በዖጋዴን እስር ቤት ወልደዋል፤ አንዳንዶቹም አስገድዶ ከመድፈሩ ጋር በተያያዘ የተፀነሱ ናቸው። ሴት እስረኞች ልጆቹን በሚወልዱበት ጊዜ ተገቢ የጤና እንክብቃቤ ቀርቶ ውሃ እንኳን እንዳላገኙ ልጆቹንም በእስር ክፍላቸው እንደወለዱ ይናገራሉ።

ልዩ ፖሊስና የክልሉ ኃላፊዎች ተጠያቂነት

የዛሬ 10 ኣመት አካባቢ የኦብነግን ጥቃት መልሶ ለማጥቃት በሚል የህወሃት ሠራዊት በዖጋዴን እጅግ አሰቃቂ የመብት ጥሰቶችን ፈጽሟል። ልዩ ፖሊስ የሚባለው የተቋቋመው ከዚህ በኋላ ነበር። ይህ በህወሓት አደራጅነት የተቋቋመው የጭከና ቡድን በአብዲ ኢሌይ መሪነት በተደጋጋሚ በሶማሊ ክልል ግፍ ሲፈጽም ቆይቷል። ከዚህም አልፎ በኦሮሚያ ክልል ሰርጎ በመግባት በመቶዎች የሚቆጠሩ ገድሏል፤ አንድ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ደግሞ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ አድርጓል።

ሒውማን ራይትስ ዎች እንደሚለው የሶማሊ ክልል ልዩ ፖሊስ መታደስ አለበት ከፍተኛ አመራሮቹም ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽን እኤአ በ2011 በበርካታ ጊዜያት የኦጋዴንን እስር ቤት ጎብኝቶ ነበር። ይህንን ተከትሎ ተቀናበረ የሚባለው ሪፖርት ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም፤ ለደረሰው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት የተወሰደ ካለ ምን ዓይነት እርምጃ እንደተወሰደ ምንም የተነገረ ነገር የለም።

ፎቶ፤ አብዲ ኢሌይ ከህወሓት “ጄኔራሎች” ጋር፤ ከኢንተርኔት የተገኘ

ነገር ግን በርካታ የቀድሞ እስረኞች እንደሚሉት ኮሚሽኑ ወደ እስር ቤቱ ሲመጣ በግልጽ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሚታወቁ በርካታ ህጻናትና እርጉዝ ሴቶች በምሥጢር ክፍል እንዲደበቁ ተደርገዋል፤ ወይም ከእስር ቤቱ ወጥተው ወደ ሌላ ስፍራ ተወስደዋል። ሌሎች ደግሞ ለኮሚሽኑ ምን ማለት እንዳለባቸው በኃላፊዎች ተነግሯቸዋል፤ ይህንን ችላ ብለው በግልጽ የተናገሩ አሰቃቂ የአጸፋ ቅጣት ተቀብለዋል።

ስለዚህ በኦጋዴን አስር ቤት የሚፈጸመውን በተመለከተ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰት የሚመረምሩ ኤክስፐርቶች ያሉበት የፌዴራል ኮሚሽን ጠ/ሚ/ሩ ማቋቋም አለባቸው፤ ይህ ምርመራ ሥልጣንን እና የሥራ ደረጃን ሳይሌ መካሄድ አለበት ይላል የዘገባው መረጃ። “በኦጋዴን እስር ቤት የሚፈጸመውን ግፍ በቸልታ ልናየው የሚገባ አይደለም” ይላሉ ፊሊክስ ሆርን፤ “ዶ/ር ዐቢይ ስቅየትን በአደባባይ መኮነናቸውን መቀጠል አለባቸው፤ ከዚህም በተጨማሪ በኦጋዴን እስር ቤት የሚፈጸመውን በተመለከተ እርምጃ በመውሰድ ስቅየትን በማስቆም ተጠያቂነትን ተግባራዊ እንደሚያደርጉ በግልጽ ማሳየት ይገባቸዋል” ብለዋል።

ይህ የግፍ ቁልል የተከማቸበት ዘገባ፤ በኦጋዴን እስር ቤት ግፍና ስቅየት በመፈጸምና በማስፈጸም ተዋናኝ የሆኑትን የፌዴራሉ መንግሥት የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌንና ሌሎች ከፍተኛ የሶማሊ ክልል ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ የሚያደርግ ነው።

ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

ከዚህ በፊት ጎልጉል፤ የድረገጽ ጋዜጣ ያቀናበረውን እና “ኦጋዴን፤ የኢትዮጵያ [የህወሃት] ድብቅ ኃፍረት” በሚል ርዕስ የታተመውን እዚህ ላይ ማንበብ ይቻላል።

(የመግቢያ ፎቶ፤ Satellite image of Jail Ogaden, Jijiga, Ethiopia, recorded on May 27, 2016. © CNES 2018 – Airbus DS 2018; Source Google Earth. All other pictures credit, HRW)


6ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 6 - ERi-TV Documentary

Dehai Events