World News

Satenaw.com: የሕወሓት መግለጫ፡ “የሌባ ዓይነ ደረቅ!”

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Friday, 15 June 2018

(መንግስቱ አሰፋ)

 

ከሁሉም በፊት

፩. የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በትላልቅ የሕዝብ ተቋማት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማዞር እንዲሁም በኢትዮ ኤርትራ የድንበር ውዝግብን ለመፍታት የአልጄርስን ስምምነት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመቀበል፣ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔም ለመተግበር ያስተላለፈው ውሳኔ እጅግ ከባድ ጥንቃቄ የሚጠይቅ፤ ምንአልባትም መካሄድ የነበረባቸው ድርድሮች፣ ምክክሮች እና ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም የሕዝብ ግንኙነትና ግንዘቤ መፍጠር ዙሪያ ያልተሠራበት ጉድለት መኖሩን የብዙኃኑም ሀሳብ ነው። በተጨማሪም በግንባሩ አሠራር መሠረት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሳይሆን ምክር ቤቱ ነው ትላልቅ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፈው።

ከነዚህ የአሠራር ክፍተቶች በስተቀር ሁለቱም ውሳኔዎች በመርኅ ደረጃ ብዙኃኑን ያስማማል።

፪. የተቃውሞ ሰልፍ በትግራይ

እነዚህን ውሳኔዎችን በመቃወም በጥቂት የትግራይ አካባቢዎች (ኢሮብ እና ባድመ) የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። የሰልፈኞቹን መሠረታዊ ሥጋቶችን መካድ አይቻልም። ውሳኔው እንደ ሀገር ብቻ ሳይሆን ቤታቸው ይገባል፣ ንብረትታቸውን እና ጎረቤት ቤተሰው ይለያል (ቢያንስ ዋስትና/ማረጋገጫ አልትሰጣቸውም)። ዜግነት ያስቀይራል (ቢያንስ ማረጋገጫ አልተሰጣቸውም)። ስለዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ቢያደርጉ አያስገርምም።

ነገር ግን የችግሩ (ውሳኔው) ጀማሪ እና ፈጻሚ የሆነውን የጊዜውም አመራር ሆነ ድርጅትና ግለሰቦች አለማውገዝ ተቀባይነት የለውም። እነዚህ ሰዎች ሕግ ብለበት ሀገር መከሰስ እና መቀጣት የነበረባቸው( ያለባቸው) ናቸው።

፫. ወደ ሕወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ መግለጫ እንምጣ

ሀ. የኢሕአዴግን ውሳኔ (የትኛውም ድርጅታዊም ሆነ ሀገራዊ) እጃቸው አለብት። ይሄ ሊሰመርብት ይገባል። ትላንት አዲስ አበባ ላይ ዶልተው፣ ገፋፍተው፣ አጨብጭበውና ፈርመው ካጸደቁ ብኋላ መቀሌ ተመልሰው ውሳኔውን መንቀፍ አሻጥር ነው። ማኅበራዊ መሠረታቸው እየተናድ ባለብት ጊዜ በሕዝበኝነት ሥም አድሃሪነትን (reactionary) ማሳየት ነው። እየተካሄደ ያለው የለውጥ እርምጃ የማታ ማታ እንደማይሆንላቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለዚህ አሁን ብዙ ብልጣብልጥነት እና መዘውር (maneuvers) የበዛበት አቋም መያዝ ከዚህ የዘለለ ትርጉም የለውም። ይሄ ኢሕአዴግን የማታ ማታ ከዴሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ጋር ያፋታል። ምክንያቱም ከሁልቱም መሆን አይቻልም፤ ኢሕአዴግን ከድርጅታዊ መርኅ ውጪ ሠራህ እያሉ በተመሳሳይ መግለጫ ደግሞ ዉሳኔውን የሚቃወም አቋም መያዝ ግራ ነው።

ለ. ከፍ ሲል ደግሞ የሕዝብን ደምጽ እንስማ በሚል ይስሙላ እራሳቸው የዉሳኔው አካል የነበሩበትን ጉዳይ መቃወም የራሳቸውን በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሉ የተሸረሸረውን ቅቡልነት ማገገሚያ አሻጥር ነው። ይህን ደግሞ በግልጽ ቋንቋ ተናግረዋል። ውሳኔውን የትግራይ ሕዝብ እና ሌላው ኢትዮያጵያዊ ቢቃወም ችግር የለዉም። የዛሬ 20 ዓመት አላስፈላጊ ውጊያ ያዋጉን፣ ከዚያ ደግሞ በደርድር ነገሩን ከማርገብ ፈንታ ውሳኔውን የተቀበሉት፣ ወሳኔውን የተቃወሙ የራሳቸው ግንባር አባላትን ያባረሩ፣ ያሰሩ እና ከሃገር ያስወጡት ተመሳሳይ ግለሰዎች ዛሬ ተከርብተው መቃወም ምን ይሉት ሕዝበኝነት ነው?

ሐ. አንዳንድ ከኢሕአዴግ መርኅ ውጪ የሆኑ አሠራሮች እና አካሄዶች ስለተባለው ጉዳይ፥ የትኛው ነው? ይሄ ግልጽ ነው። “ተሓድሶው” አንዳንድ ክልሎች ላይ ይሕወሓትን ጣልቃ ገብነት ውሃ አስበልቷል። ለሕወሓት የማያጎበድድ የክልል አመራሮች ተነስተዋል። ኮንትሮባንድ ቀንሷል፣ down down Woyane የሚሸቱ ትርከቶች የብዙኃንን ጆሮ እንደሳበው በአንዳንድ የክልል አመራር ልብ ውስጥ ደግሞ ራዕይ ሆነው ፍሬ ሊያፈሩ ነው። ይሄ ቢያሳስባቸውና ሌላ አሻጥር ቢያሸርብ ምንም አይገርምም። በዚህ የወዮልኝ ለቅሶ ግን ትግራዋይ ተጎዳ፣ ተጠላ በሚል ተራና ርካሽ ፕሮፓጋንዳ እንደገና ልንሰራራ ባይነትን መስማት እና ማመን ዘመን ያለፈበት የሟች ለራስ ለቅሶን የመሲሕ ነፍሰአድን ሕማማት አድርጎ መቀበል ነው።

መ. ነባር ታጋዮች እውቅና እንዲሰጣቸው

ምን ጎደለባቸው? ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጡረታ ያሰነበቱአቸው ያነባር ታጋዮች በወሳኔው (በጡረታ መሰናበትን) ደስ እንዳለስኛቸው ተናግረው ነበር። በሌላ በኩል ድግሞ እንደውም ዘግይቷል የኔ ጡረታ፤ “ወዲ 84 ዓመት እየ” ብለው የተናገሩም ነበሩ። ሌላው ቢቀር የሃገሪቱ የጡረታ የእድሜ ጣሪያ 65 ዓመት ነው መሰለኝ። አንደኛ፦ ጡረታውን መቃወሙ ሕጋዊ መሠረት የለውም (ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን እና ዶክተር ዳኛቸው አሰፋን ያለ እድሜ ያሰናበቱት ሰዎች መሆናቸ ልብ ይሏል)። ሁለት ነባር ታጋዮች ደግሞ በራሳቸው ፍቃድ የለቀቁ ናቸው (የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጄንሲ እና የብረታብረት እና እንጂነሪንግ ኮርፖሬች ዳይሬክተሮች)። ምን ክብር ነው የጎደለባቸው?

ለምን እንደዚ እንደሚሉ ልንገራችሁ። The best defense is a good offense ይባላል። እነዚህ ነባር ታጋዮች በእጅጉ በሙስና፤ የትላልቅ መሠረተ ልማት ፕሮጅክቶችን ገንዘብ ያለቅጥ ለረጅም ዓመታት ሲመዛብሩ የኖሩ ናቸው። አቶ አባይ ጸሓየ በስኳር ኮርፖሬሽን፣ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው ደግሞ በ2010 ዓ.ም. ብቻ የ9 ቢሊዬን ብር ጥፋት በብረታብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፈጽመው ነው በሰላም እየኖሩ ያሉት። አቶ ጌታቸው አሰፋ የብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን ደም እጁ ላይ ነው። ከኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ1992 እ.ኤ.አ. ጀምሮ የ 37000 ወጣቶች በኦኔግ ሥም ታፍነው ተውስደው እስካሁን የት እንዳሉ አይታወውም። ለእነዚህ ሰዎች የጎደለባቸው ነገር ቢኖር ተገቢው ቅጣት ነው። ክብር አንሶባቿል ማለት the best defence is a good offence ወይም በሃገሬው ብሂል የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያውልቅ ነው። እነዚህን በታጋይነት ተርጋ ወሽቆ የማትረፍ የነፍስ አድን ጥሪ ነው። ማንም አይሸወድ።

ሠ. ብትግራይ እና በድርጅታችን ላይ የሚደረግ የጥላቻ እና የመምታት ዓላማን መታገል.

ይህም ተመሳሳይ ትግራይን ከኢትዮጵያ የማጣላትና የመለየት ሥራ ነው። ማንም ጤነኝል ሰው ተራ ትግራዋይን፣ ኦሮሞን፣ አማራን፣ ኮንሶን የሚጠላበት አንዳች ምክንያት አይኖረውም። ሲጀምር ሰውን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መውደድን እና አብሮ መኖርን ከፖለቲካ ድርጅት እና ፖለቲከኛ ተማሩ ያለን ማን ነው? በፍላጎት ሰውን እና ድርጅትን የሚጠላው ማን ነው? ከፋፋይ የፖለቲካ አጀንዳን የሕልውና መሠረት እና ይሕይወት ጥሪው አድርጎ የሚኖረውን ሕወሓትን የፍቅር አብዮተኛ ያረገው ማን ነው? ወይስ አብዮታቸው ዓይነቱ በአንድ ቀን ስብሰባ ተቀየረ?
ይልቁንስ ትግራዋይ ውንድሞቻችን ለነሱ ያለንን ኢትዮጵያዊ ፍቅርና አክብሮታችንን ከሕወሓት ባይሰሙ ጥሩ ነው፤ እኛ አልላክናቸውምና። የወልቃይት ጥያቄም በዚሁ ማእቀፍ እየተወገዘ ነው። ያው የተለመደው ነው ለማለት ነው።

ለትግራይ የቆመ “ሕዝባዊ ወያነ” ቢሆን ለምን አመራሩ በአዲስ ፊት አይተካም? ለምን EFFORT የጥቂት ግለሰቦች ሀብት ሆነ? ሥሙ “ትካል እግር ምትካል ትግራይ” (ትእምት) አይደለም እንዴ? የማንን እግር መልሶ አቋቁሞ ያውቃል? በተሰውት ታጋዮች ሥም መነገድስ ልነ ስሑል፤ ለነቀሺ ገብሩ፤ ለነአሞራው፤ ለነአተኽልቲ፤ ለነሓየሎም ውርድትና ስድብ አይሆንም ወይ?

ደርግ ከትግራይ ወድቆ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሕወሓት መራሹ የኢሕአዴግ መንግስሥት ባለፈው ሩብ ምዕተ-ዓመት በሌሎች ክልሎች የፈጸመው ግፍ መቼም ቢሆን ታሪክ አይረሳውም። ይህንን ድርጅት ዝም ብሎ አምኖ መከተል በተመሳሳይ ልክ የታሪክ ተወቃሽ ከማድረግ አልፎ በቅርቡ በሚፈጸመው የዚ ድርጅት ግብዓተ መሬት ቀን ያስተዛዝበናል።

ረ. የአመራር ምደባ አልተመቻቸውም

የው ወይዘሮ አዜብ መስፍን ናቸው። በሕወሓት የተገፉ አንጃ። ከድርጅታቸው ሚእከላዊ ኮሚቴ፣ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ከEFFORT ያባረሩአትን ግለሰብ በፌዴራል ደረጃ የትልቅ ኮርፖሬሽን (METEC) አመራር ቦርድ አድርጎ መሾም እንዲያስታቸው አይጠበቅም። ሌሎቻችንም ተቃውመናል ነገር ግን ለተለየ ምክንያት። ሌላው መሰኛነታቸውን (የው/ሮ አዜብ) ሲቃወም ሕወሓት ግን ስለ ፖለቲካቸው ነው። ምክንያቱም እነሱ ስለ ሙስናና ብልሹ አሠራር ለመናገር ፍላጎትም ሞራልም አይኖራቸውም።
ሰ. አስቸኳይ የኢሕአዴግ ስብሰባ እንዲጠራ ጥሪ አቀረበ

ያው ስብሰባው ላይ እንደግና ለመደራደር ነው። ይህ ድግሞ ከዚህ በፊት በተደረጉ የኢሕአዴግ ስብሰባዎች ላይ ያለመግባባቱ ልክ አቶ ሺፈራው ሽጉጤ እንዳሉት “እምንት” ወይም አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት “ጥቂት የሀሳብ ልዩነቶች” ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ ያደርጓል። ይልቁንም ላልተወሰነ ቀናት የሚያፋጃቸው፤ ምናልባትም እየተደረጉ ያሉትን የለውጥ ጭላንጭል ላይ አሮጌ ኢሕአዴጋዊ ውሃ ለመቸለስ የሚሞከርበት ስብስባ የሚያስጠራ የሀሳብ ስምጥ ሸለቆ ነው ያለው።

ማጠቃለያ.

፩. ሕወሓት ለሕልውናው ሰግቷል። እየተደረገ ያለው ለውጥ ለሱም ሆነ ለአሮጌው የሕወሓት ኢሕአዴግ ቀን እየጨለመ ነው። ትግራይን የኢትዮጵያ ሰሜን ኮሪያ ለማድረግም ደፋ ቀና እያለች ነው። አክራሪ የአግዓዚያኑ ንቅናቄና ሻዓቢያንም መርሳት ተገቢ አይደለም።

፪. ኢሕአዴግ በመርኅ ደረጃ ተዳክሟል፣ ተከፋፍሎአል፣ የርዕዮተ ዓለም ኪሳራ ገጥሞታል። የሕወሓት የበላይ ክንዶች ዝለዋል። በአዳዲስ አመራሩ ለውጥ ፈላጊነትና በነባር ታጋዩ ቆሞ ቀርነት መካከል የተውጠረው ርዕዮተ ዓለም የግንባርነት ነገሩንም እርግፍ አደርጎ ትቶውህደት በመፈጸም ወደ አንድ ሀገራዊ ፓርቲ የመሸጋገር ዓላማም አንግቦ ለቀጣይ ሕልውናው ሁነኛ መፍትሄ ማፈላለግ ባለበት ጊዜ ላይ ነው ያለው። በዚህ ጊዜ ያልተለመደውን በሀገራዊ ጉዳይ ላይ በውሳኔ አለመካተታቸው ሕይወሓትን ያሳሰበው የአጋር ድርጅቶች ነገር ነው። ለምን አሁን? አብዲ ኢሌ አለ። ብጥብጥ በየቦታው እየተቀሰቀሰ ነው። ለምን አሁን? የሚመዘዝ ካርድ ይኖር ይሆን? የአቶ ሺፈራው ሽጉጤ ደኢሕዴን፣ የአብዲ ኢሌው ሶሕዴፓ እና ሶማሌ ልዩ ኃይል……ማን ያውቃል? ያልጠረጠረ…….ነው ነገሩ።

ባጠቃላይ በተለመዱ ሴራዎች የተሞላ መግለጫ ነው። ለሕዝብ ንብረትም ለኢትዮ ኤርትራ ሰላም እና መረጋጋት እንቅፋት ሊሆን የሚችል አቋም የተያዘበት፣ የሀገሪቱን የጽጥታ እና የሰላም እንዲሁም በሕዝቦች መካከል ላለው አንጻራዊ መተማመን አደጋን የጫነ፣ ለምስራቅ አፍሪካ የሰላም ሁኔታ መፍትሄን የሚያጨናግፍ አቋም የተንጸባረቀብት ነበር።

የሌባ ዓይነ ደረቅ።

 

7ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 7 - ERi-TV Documentary

Dehai Events