World News

Dahabshiil long banner 728x90
Eritrea for mobile viewing

(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አደረገ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Tuesday, 05 June 2018

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አደረገ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ውሎ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ይፋ አድርጓል።

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዛሬው ስብሰባው ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሏን፣ ይህም ዕድገት ከፍተኛ መነቃቃትንና ተነሳሽነትን በመቀስቀስ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር ዕድል መፍጠሩን፣ በአንፃሩ ደግሞ በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ያሉ መሆኑን በጥልቀት ገምግሟል። 

እንዲሁም ባለፉት 2 ዓመት ተኩል የወጭ ንግድ አፈፃፀም ከታቀደው በታች በመሆኑ በዚህ ረገድ ያለውን ውስንነት ለመፍታት የግብርናና ኢንዱስትሪ አምራች ዘርፍን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በተለይ የወጭ ምርቶች ላይ መረባረብ እንደሚጠይቅ አጽንኦት ሰጥቶታል።

የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ማስፋት፣ የገቢ መሰብሰብ አቅም ማሳደግ፣ የኑሮ ውድነት ችግርን ማቃለልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ኮሚቴው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ገምግሞ ቀጣይ የአፈጻጸም አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በዚህም መሰረት የስካሁኑን ፈጣን ዕድገት ይበልጥ ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም በተሻለ የኤክስፖርት አፈፃፀም ለመድገም ከአሁኑ የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠኑ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አምኖበታል።

በዚህም መሰረት ፈጣን ዕድገቱ ዜጎችን አካታች በሆነ መልኩ ግለቱን ጠብቆ እንዲቀጥል የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች በሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው ወስኗል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለረጅም ጊዜያት በሀገራቸው ልማት ለመሰማራት ያላቸውን ምኞት በማረጋገጥና የዕድገቱን ፍጥነት ይበልጥ ለማስቀጠል እንዲሁም እውቀትና የውጭ ምንዛሪ ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሃብቶች በዕድገታችን ላይ ተገቢውን አዎንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ውሳኔዎችን አሳልፏል።

እነዚህም መሰረት፦ 

• በመንግስት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክሲዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ፤

• እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች እና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግስት ይዞ ቀሪው አክሲዮን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች እንዲተላለፍ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አቅጣጫ አስቀምጧል።

አፈፃፀሙም የልማታዊ መንግስት ባህሪያት በሚያስጠበቅ፣ የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ፤ ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲሲፒሊን ተግባራዊ እንዲደረግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል።

የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ አቅርቧል።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ህይወት ሊጠፋ ችሏል፤ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ የመኖሪያ ቀዬ ማፈናቀሉ መግለጫው አስታውሷል።

በሁለቱ ሀገራት መሃከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱም ሀገራት ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፤ በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩንም በመግለጫው ተብራርቷል።

በድምሩ ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፤ በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ መቆየቱን አንስቷል።

ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ መፈጠሩን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በመግለጫው አንስቷል።

የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት 20 አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም ያለው ማእከላዊ ኮሚቴው፥ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል ብሏል የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው።

“እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም” ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሄ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው ብሏል።

ይህን ባለማድረጉም በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዋል ብሏል መግለጫው።

“የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን” ያለው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው፥ “በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን” ብሏል በመግለጫው።

በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን በመግለጫው አረጋግጧል።

የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጠይቋል።

Dm eri tv subscribe

HDRI Publishers: Book Release - ህያው ደብሪ A Book Hailed As A Game Changer in Eritrean Modern Poetry