World News

(ኤፍ ቢ ሲ) ጠ/ሚ ኃይለማርያም የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹምን አግኝተው አነጋገሩ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Monday, 08 January 2018

ጠ/ሚ ኃይለማርያም የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹምን አግኝተው አነጋገሩ

8-1-2018

ጠ/ሚ ኃይለማርያም የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹምን አግኝተው አነጋገሩ
አዲስ አበባ፣ (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሱዳን መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም የሆኑትን ሌተናል ጀነራል ኢማድ አልዲን አዳዊን በፅህፈት ቤታቸው አግኝተው አነጋገሩ።
ኢታማዦር ሹሙ ከፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተላከን መልዕክት አድርሰዋል።
ኢትዮጵያ የሱዳን ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን የገለጹት ሌትናል ጄኔራሉ፤ አገራቱ በቀጣይ የጋራ ትብብራቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
አንዱን አገር የሚያጋጥም ፈተና ሁለቱን አገር እንደሚጎዳ ገልጸው፤ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመግታት የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የሁለቱ አገራት የአብሮነት ስሜትና የትብብር መንፈስ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ መገንባት ከጀመረ ወዲህ እየተጠናከረ መምጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ዴሊቨሪ ዩኒት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብረሃ ለኢዜአ ተናግረዋል።
በዛሬው ውይይትም ይህ ትብብር ወደ ተሻለ ደረጃ የሚሸጋገርበት ሁኔታ ላይ እንዳተኮረ ገልጸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኢትዮጵያ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የሁለቱን አገራት ብሔራዊ ጥቅምና የቀጠናውን ጥቅም ለማስከበር በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ በጋራ የሚያደርጉትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አገራቱ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አቶ ዛድግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያና ሱዳን ወዳጅነታቸውን በየጊዜው በማጠናከር ላይ ሲሆኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ባሳለፍነው ዓመት መጋቢት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት አገራቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ውህደት መፍጠር፣ ለጋራ ሰላም አብሮ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
 
በቅርቡ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን በሱዳን ጉብኝት ማድረጋቸውን እና አንካራ ወታደሮቿን የምታሰፍርበት ደሴትን ከካርቱም ማግኘቷን ተከትሎ የቀይ ባህርና አካባቢው ፖለቲካ የተለየ ሙቀት ውስጥ መግባቱን የሚገልፁ ወገኖች አሉ።
የቱርክ እና የሱዳን ስምምነትንም ተከትሎ ግብፅ በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ድጋፍ የተወሰኑ ወታደሮቿን ወደ ኤርትራ መላኳ ነው የሚነገረው።
ቀደም ብላ በግብፅ የሚገኙ አምባሳደሯን የጠራችው ሱዳን ባለፈው ቅዳሜም ከኤርትራ ጋር የምትዋሰንበትን ድንበር መዝጋታን ገልፃለች።
እነዚህ ወቅታዊ አካባቢያዊ ጉዳዮች በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና በኢታማዡር ሹሙ ውይይት ወቅት ስለመነሳታቸው የተገለፀ ነገር የለም።

foto van Office of the Prime Minister-Ethiopia.

foto van Office of the Prime Minister-Ethiopia.



EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events