World News

Goolgule.com: ጥያቄው አሁንም ግልጽ ነው!

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Friday, 05 January 2018

ጥያቄው አሁንም ግልጽ ነው!

 

ያለ ሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) በማለት የሰየመ የአሸባሪ ወንበዴዎች ቡድን አሁንም የውንብድና ተግባሩን እየፈጸመ ይገኛል። ይህ በዓለምአቀፋዊ የአሸባሪዎች መረጃ ቋት ውስጥ በአሸባሪነትየተመዘገበ ድርጅት በነጻ አውጪ ስም ሕዝብ ሲጨፈጭፍ፣ ሲያዋርድ፣ ሲያስር፣ ከአገር ሲባርር፣ ሲያፈናቅል፣ … የኖረ ድርጅት አሁንም በዚሁ ተግባሩ ቀጥሏል።

ዓላማ ብሎ የተነሣለትን አገር ማፍረስ የተቃወሙ፣ ሃሳባቸውን በሰላማዊ መንገድ የገለጹ በሙሉ አሸባሪ፣ ጸረ ልማት፣ ጸረ ህዝብ፣ … በማለት ሲገድልና ሲያሰቃይ ኖሮ አሁን ደግም “አላሰርኩም” ሲላቸው የነበረውን እስረኞች “እፈታለሁ” ብሏል። ይህ በህወሓት/ኢህአዴግ ስለተነገረው መግለጫ ጥቂት ነጥቦች ብቻ እናንሳ፤

በመጀመሪያ ኃይለማርያምና ጓደኞቹ በኢትዮጵያ ስም እና ስለ ኢትዮጵያ እየተናገሩ ኢትዮጵያን የሚወክል ሳይሆን የራሳቸውን “ጨርቃ ጨርቅ” ከኋላቸው አሰልፈው የወጡት ኅሊናቢሶች ናቸው። “የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” የሚሉትን “ባለ ሰማያዊ ኮከቡን ባንዲራ” መድረኩ ላይም ይሁን ከኋላቸው ያለማድረጋቸው ንግግራቸው ስለኢትዮጵያ ሳይሆን ስለፈጠራቸው ህወሓት እንደሆነ በጉልህ የመሰከሩበት ነው።

ለዓመታት በመንግሥት ስም ሆነው ሲገድሉና ሲያስሩ፤ ከሟቹ መለስ ጀምሮ እስከ ኃይለማርያም ድረስ በአገር ውስጥና በውጪ “በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም” ሲሉ ቆይተው ዛሬ ከየት ያሰሯቸውን “የፖለቲካ እስረኞች” አምጥተው እንደሆነ ባታወቅም “እንፈታለን” ማለታቸው እስካሁን ያሰሩት በሙሉ የፖለቲካና የኅሊና እስረኛ መሆኑን በራሳቸው አፍ ያመኑበት ማስረጃ ነው።

ሲቀጥል እነዚህኑ “እንፈታቸዋለን” ያሉትን እስረኞች እንፈታለን ያሉት እንደ “መንግሥት” በመሆን ወይም የመንግሥት ሥራአስፈጻሚ አካል በመሆን ሳይሆን ኢህአዴግ በሚሉት ድርጅታቸው ስምና ውክልና ነው። አገሪቱ ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚባል ጠቅላይ ሚኒስትር አላት ሲሉ የኖሩትን ያህል እርሱ እንደ መንግሥት ወኪልነቱ በአገሪቱ አስተዳደር ስም ሆኖ አለኝ በሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ መናገር ሲገባው መግለጫው የተሰጠው በድርጅት ስምና ዓርማ ነው።

ይህንን ሁሉ ሕዝብ ሲያስሩ የኖሩት “ሕገመንግሥቱን ለመናድ በማሰብ” እና “ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በማሰብ ሲንቀሳቀሱ” ያገኘኋቸው “አሸባሪዎች ናቸው” በማለት ነበር። ስለዚህ ክሱ ሁሉ የተፈጸመው “በተከሳሹ”ና በ“መንግሥት” መካከል ነበር ለማለት ይቻላል፤ የበርካታ ክሶች ማስረጃ የሚመላክተው ይህንኑ ነው። ስለዚህ አሣሪው “መንግሥት” (ሥራ አስፈጻሚው) ነበር ቢባል ሐሰት አይሆንም። አሁን ግን “እፈታለሁ” የሚለው ያሰራቸው “መንግሥት” ሳይሆን ህወሓት/ኢህአዴግ ነው። በሌላ አነጋገር የታሰሩትም ሆነ ታስረው የተፈቱት፣ የሞቱት፣ የተሰደዱት፣ ወዘተ ወገኖቻችን በሙሉ ይህ ሁሉ መከራ የደረሰባቸውና የሚደርስባቸው ከህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ስሙም መሆን ስላልቻሉ ነው ወደሚለው ድምዳሜ በቀላሉ መድረስ ይቻላል። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ራሱ ህወሓት/ኢህአዴግና መግለጫው ነው!

ይህ በድርጅት ስም በገሃድ የተነገረ መግለጫ ግልጽ ሆኖ ሳለ የምዕራብ ሚዲያ ተቋማት በሙሉ ኃይለማርያም እንደመንግሥት ወኪልነቱ እስረኞችን እፈታለሁ አለ በሚል ዜናውን መሥራታቸው ትዝብት ላይ የሚጥል ብቻ ሳይሆን የሙያ ስነምግባር የጎደለው ሆኖ አግኝተነዋል። በዚህ ድርጊት የአሜሪካና የጀርመን ድምጽ ሬዲዮኖች መሳተፋቸው እርምት ሊወስዱበትና ይቅርታ ሊጠይቁበት የሚገባ ነው እንላለን።

ይህ በአደባባይ የተሰጠ መግለጫ “እስካሁን ድረስ በአገራችን ላይ ለደረሰው ግፍ ማነው ተጠያቂ?” ለሚለው በጥሩ ማስረጃነት መቅረብ የሚችል ነው። ከዚህም ሌላ አራቱ ስዎች በአንገታቸው ላይ የመታነቂያ ገመድ እያስገቡበት እንደሆነ ራሳቸው ተረድተውታል ለማለት እንጠራጠራለን። የተናገሩትን በአጭሩ ለማስቀመጥ፤ “የተቃወሙንን፣ ከእኛ ጋር የማይስማሙትን፣ የፖለቲካ አመለካከታቸው ከእኛ የተለየውን በሙሉ ስንገድል፣ ስናስር፣ ስናሰቃይ፣ ከአገር ስናባርር፣ ወዘተ የነበረው እንደ መንግሥት የአገሪቱን ኅልውና አደጋ ላይ የጣሉ አሸባሪዎች በመሆናቸው ሳይሆን ለህወሓት/ኢህአዴግ አሜን ብለው እጅ እየነሱ መገዛት ያልፈለጉትን ሁሉ ነው። ስለዚህ የጸረ ሽብር ሕግ የሚል በማውጣት የቻልነውን ያህል ገድለናል፤ አስረናል፤ አዋርደናል፤ ከአገር አባርረናል፤ ይህንንም እንደ መንግሥት ፈጽመናል፤ ለዚህ ማስረጃ እንደ መንግሥት ያሰርናቸውን እንደ ድርጅት ለመፍታት መወሰናችን ብቻ ሳይሆን ይህንንም በአደባባይ በማስረጃ እንዲደረግ መወሰናችን ውስጣዊ ዴሞክራሲያዊ አሠራር መጀመራችንን ያሳያል። ሌላው መታወቅ የሚገባው ጉዳይ ባስፈለገ ጊዜ በየትኛውም ቦታ ነፍሰበላ አሳሪዎች መሆናችንን እንዲመሰከርብን የሚያስችል ማስረጃ እየሰጠን ነው። መጪው ጊዜ ከኢህአዴግ ጋር ጥቅጥቅ ጨለማ ነው”።

ህወሓት/ኢህአዴግ የቱንም ያህል ባህታዊ መስሎ ቢቀርብም ቀበሮነቱን ግን ሊክደው የማይችል ተፈጥሮአዊ ባህርዩ መሆኑን ራሱ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ጠንቅቆ ያወቀው ጉዳይ ነው። ከ26 ዓመት ውሸትና ማጭበርበር በኋላ አሁንም “ኑ ላታልላችሁ” ማለት በረሃ ተወልዶ ያደገ “አራዳነት” ካልሆነ እብደት ነው የሚሆነው። ህወሓት/ኢህአዴግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በቃህ ብሎታል። በኢሬቻ በዓል ላይ “down down woyanne” እንዳለው ወጣት ህወሓት መውደም ነው ያለበት።

ጥያቄው አሁንም ግልጽ ነው! የሕዝብ ጥያቄ “የህወሓት የበላይነት ይቁም” የሚል ነው!!

 

EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events