World News

BBC.com: እስራኤል አፍሪካዊያን ስደተኞች እንዲወጡ አዘዘች

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Wednesday, 03 January 2018

እስራኤል አፍሪካዊያን ስደተኞች እንዲወጡ አዘዘች

3 ጃንዩወሪ 2018
Image copyright AFP

የእስራኤል መንግሥት በአስር ሺህዎች ለሚቆጠሩ አፍሪካዊያን ስደተኞች ሃገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ካልሆንም እስር እንደሚጠብቃቸው ማስጠንቀቂያ አውጥቷል።

ስደተኞቹ እሰራኤልን በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ለቀው ለመውጣት ከተስማሙ 3500 ዶላር ይሰጣቸዋል ተብሏል።

በአማራጭነትም ወደሃገራቸው ካልሆነም ወደሌላ ሦስተኛ ሃገር የመሄድ ምርጫም ቀርቦርላቸዋል።

ነገር ግን ከቀነገደቡ በኋላ እስራኤል ውስጥ ለመቆየት ከወሰኑ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ስደተኞቹን ማሰር እንደሚጀምሩ ባለስልጣናቱ አስጠንቅቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ይህ አወዛጋቢ ዕቅድ ዓለም አቀፍና የእስራኤል ህግን የሚቃረን ነው ብሏል።

የእስራኤል መንግሥት ግን ስደተኞቹ እንዲመለሱ የሚደረገው 'በፈቃደኝነትና' ሰብአዊ ክብራቸውን በጠበቀ መንገድ ነው ይላል።

ይህ ማስጠንቀቂያ ሕፃናትን፣ አረጋዊያንን፣ በባርነት ተይዘው የነበሩትንና የሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑትን ስደተኞች አይመለከትም።

የእስራኤል የፍልሰትና ሥነ-ሕዝብ ባለስልጣን ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ጊዜ 38 ሺህ ''ሰርጎገቦች'' ብለው የጠሯቸው ስደተኞች በእስራኤል ውስጥ እንዳሉና ከእነዚህ መካከልም 1420ዎቹ በእስር ቤቶች ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

የእስራኤል መንግሥት ''ሰርጎገቦች'' የሚለውን ቃል ከሕጋዊዎቹ የድንበር መግቢያዎች ውጪ ወደ ሃገሪቱ የገቡ ሰዎችን ለማመልከት ይጠቀምበታል።

አብዛኞቹ ስደተኞች ኤርትራዊያንና ሱዳናዊያን ሲሆኑ ወደእስራኤል የመጡት ከሚደርስባቸው ማሳደድና ከጦርነት ለማምለጥ እንደሆነ ቢናገሩም ባለስልጣናት ግን የተሻለ ኑሮ ፈልገው የመጡ እንደሆኑ ያምናሉ።


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events