World News

Goolgule.com: ኢህአዴግና እነለማ ከ“ምን ይዤ ልመለስ?” እስከ “መግለጫ” ማጽደቅ!

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Tuesday, 02 January 2018

ኢህአዴግና እነለማ ከ“ምን ይዤ ልመለስ?” እስከ “መግለጫ” ማጽደቅ!

January 2, 2018 08:10 pm By

ህወሓት የሚዘውረው ኢህአዴግ ከሁለት ሳምንታት በላይ ስብሰባ አድርጎ “መግለጫ” ያለውን “ቀጭን ትዕዛዝ” በማውጣት ተጠናቋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በለውጥ አራማጅነት ሲጠቀሱ የነበሩት እነለማ መገርሳ “መግለጫውን” አብረው አጽድቀው ወጥተዋል። “የጨለንቆን ፍጅት የፈጸመው ማነው?” የሚለውም ደፋር አጀንዳ አብሮ የሞተ ጉዳይ ሆኗል። “ምን ይዤ (ወደ ሕዝቤ) ልመለስ?” በማለት ወደስብሰባው የገቡት ኦህዴድና ብአዴን “የተቀናጁ ተጨማሪ እርምጃዎች” እወስዳለሁ (መግደሌን እቀጥላለሁ) ለሚለው የህወሓት “መግለጫ” ይሁንታቸውን ሰጥተው ወጥተዋል።

የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ከወር በላይ ስብሰባ በማድረግ የደቆሰውና የፈጨውን በተስፈኞቹ ብአዴንና ኦህዴድ ላይ በመድፋት በድንፋታ ኢህአዴግ የሚለውን የድርጅቱን ሥራ አስፈጻሚ መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁ ከራሱ ከአገዛዙ የሚዲያ ተቋማት ተነግሮናል። የድርጅቱ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ሲጀመር በርካታ ነገሮች ሲባሉበት ቆይተዋል። በድርጅቱ ውስጥ የተፈጠረው አለመግባባት፤ የመካከለኛና የበታች አመራሩ መክዳት፤ የእነ ለማ እና ገዱ አፈንግጦ መውጣት ህወሓትን ለብቻው ያስቀረዋል፤ ድምጽ ያሳጣዋል፤ … የተባሉ ተስፋዎችና ምኞቶች በተለይ ከዳያስፖራው በኩል ሲወራበት፣ ሲተነተንበት የቆየ ጉዳይ ነበር። እነ ለማ ወደ ስብሰባው የገቡት በምን መልኩ ነበር?

ኦህዴድና ብአዴን – “ምን ይዤ ልመለስ?”

የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ሲጀመር የነበረው መንፈስ ቴዲ አፍሮ ለስደተኞች “ምን ይዤ ልመለስ ወደእናቴ ቤት?” በሚለው የዘፈን ድባብ ነበር። ለጊዜው “ዝምታን” ከመረጠው ደኢህዴን በስተቀር በጉባዔው ላይ የተገኙት ብአዴንና ኦህዴድ ከሕዝባቸውና ከበታች ካድሬው የተላኩት መልዕክት ስለነበር በስብሰባው ላይ መገኘታቸው “ምን ይዤ (ወደ ሕዝቤ) ልመለስ?” በሚል ጥያቄ የተሞላ ነበር። ኃይለማርያም ከኃላፊነቱ ሲነሳ ኦህአዴን ሊቀላቀል ይችላል የተባለለት ደኢህዴን የብአዴንን ቦታ በመውሰድ ለህወሓት ባለውለታነቱን ለማሳየት የተዘጋጀ ሆኖ ነው ስብሰባው የተጀመረው። በሌላ ጎራ “በጨለንቆ በተፈፅመው የጅምላ ግድያ በስተጀርባ ማን ነው ያለው?”፤ “ኢትዮጵያዊነት ደማችን ነው”፤ “ተቀላቅለናል”፤ “ሠርገኛ ጤፍ”፤ ሙሽራ አበባ፣ ቡሄ ዳቦ፣ … ሲሉ የነበሩት በአንድ ወግነው ስብሰባው በመጀመሩ ብዙ የለውጥ ቀቢጸ ተስፋዎችና ሲከፋም ቅዠቶች ተተንብየውለት የተጀመረ ስብሰባ ነበር።

ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ከዚህ በፊት ባተማቸው የዜና ዘገባዎች ኦህዴድ መከፋፈሉን፣ መክዳቱን፣ ብአዴን መከተሉንየህወሓት/ኢህአዴግ የገጠር መዋቅር መፍረሱንከመካከለኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታች ካድሬ ድረስ ለው አመራር በኦህአዴድና ብአዴን ላይ ማመጹን ወዘተ መዘገቡ ይታወሳል።

በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ የታየው ህዝባዊ ተቃውሞ አነሳሱም ሆነ አካሄዱ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች “የእኛ ትግል ነው” ለማለት እንደሞከሩት ሳይሆን የሕዝብ ትግል ነበር። ከሕዝብ የመነሳቱ ማስረጃዎች ብዙ ቢሆኑም በተለይ ግን ከዚህ ሁሉ ግድያ፣ አፈና፣ ጭከና፣ … በኋላ ዓመጹ እስካሁን አለመብረዱ ቀዳሚ ማስረጃ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘ ህወሓት/ኢህአዴግ “ጥልቅ ተሃድሶ”፣ “በጥልቀት መታደስ”፣ ወዘተ እያለ ቢለፍፍም ውጤቱ በጥልቀት መበስበስ ሆኗል

ካድሬው ከሕዝብ የወጣ በመሆኑና እያንዳንዱ ካድሬ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በአገሪቱ ውስጥ ካለው መድልዖ፣ የሃብት ክምችት ልዩነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ዘረኝነት፣ ግድያ፣ አፈና፣ … ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለችግሩ ቅርብ ነው። ከቀበሌ፣ ከወረዳ፣ ከዞን፣ አመራር ጀምሮ ወደላይ ያለው ሠንሠለት እንደ ዱሮው ተያይዞ የሚሄድና ትዕዛዝ በተዋረድ የሚቀበል መሆኑ ከቀረ ዓመታት ተቆጥረዋል። ለዚህም ነው ኢህአዴግ በተደጋጋሚ ኦህዴድን ሲፐውዝ የቆየው፤ ብአዴንንም እንዲሁ። በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ካድሬዎች ከድርጅቱ እንዲሰናበቱ ተደርገው በምትካቸው አዳዲስ ቢገቡም ከሰው ለውጥ በስተቀር ችግሩ ግን አንዲትም ቅጣት ወደ መፍትሔ ሲሄድ አልታየም። ህወሓት/ኢህአዴግ ግን አሁንም በጥልቀት እየታደስኩ ነው ይላል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትና ኪሣራ ያስከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅ፤ በርካታ “የመታደስ” ተግባራት ተከናወኑ ቢባልም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደተነሳ ሕዝባዊው ተቃውሞው ወዲያውኑ ቀጥሎ ታይቷል። ይህም የትግል እንቅስቃሴው የሕዝብ መሆኑን ባንድ መልኩ ያሳየ ሲሆን በሌላ ደግሞ ኢህአዴግ እጅግ የሚኮራበት የአምስት ለአንድ ጥርነፋ በምንም መልኩ በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ለመሥራት ያልቻለ ለመሆኑ ማስረጃ ሆኖ የሚቀርብ ነው። እንደ አሠራሩ ከሆነ ጥርነፋውን ተግባራዊ የሚያደርግው ካድሬው ነው። ከዚህ መዋቅር አልፎ በየዕለቱ በበርካታ አገሪቱ ክፍሎች የአደባባይ ትዕይንቶች መካሄዳቸው የኦህዴድንና ብአዴንን መክዳት በጉል ያመላከተ ነው።

የአገሪቱ ችግር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በ“ጥልቅ ተሃድሶ” እና በመሳሰሉ ድሪቶዎች ለመሸፋፈን የሞከረው ህወሓት/ኢህአዴግ ችግሩ የመጣበት ከሕዝቡ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቀዋል። ሕዝቡ በበታች አመራሩ በተለይም በካድሬው በኩል በተደጋጋሚ ለድቃይ ድርጅቶቹ ኦህአዴድና ብአዴን ችግሩን ሲያቀርብ ቆይቷል። የድርጅቶቹ አመራሮች በየቦታው ህዝቡን ሲያነጋግሩ የሚሰሙት ምሬትና ምላሽ የናፈቀው ጥያቄ የዕዝ ሠንሠለቱን ጠብቆ እስከ በላይ አመራሩ ደርሷል። ሕዝብ በዓመጽ ላይ መሆኑን፣ በሚሊዮን የሚቆጠር አባል አለኝ እያለ ኢህአዴግ የሚኩራራበት መዋቅር ዋጋቢስ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ እንደሚያስፈልገው በገሃድ የተሰማና የታወቀ አጀንዳ ነው።

በመሆኑም የሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ ከመጀመሩ በፊት በተለይ ኦህአዴድና ብአዴን በካድሬው በኩል ሕዝብ የላካቸውን አጀንዳ ይዘው ነበር የገቡት። ስብሰባው ሲጠናቀቅ የህወሓት/ኢህአዴግ ምላሽ የታወቀ ቢሆንም ለኦህአዴድና ለብአዴን ግን የጥያቄና የጭንቀት ወቅት ነበር። ለጭቆናው፣ ለበደሉ፣ ለግድያው፣ ለአፈናው፣ ለኑሮው ውድነት፣ ለህወሃት ተስፋፊነት፣ ለሽበባው፣ ለግፉ፣ ወዘተ “ምን ይዤ ወደ ሕዝቤ ልመለስ?” የሚል ነበር። በተለይ እነ ለማ ሰሞኑን ከተወደሱበት ኢትዮጵያዊነት ስብከት አኳያ ጥያቄው የውጥረቱ ሙቀት እንዲጨምር ያደረገ ሆኗል።

ለ“ምን ይዤ ልመለስ?” የህወሓት ምላሽ!

ኦህዴድ “ጀግኖ” በህወሓት ላይ “በጨለንቆ በተፈፅመው የጅምላ ግድያ በስተጀርባ ማን ነው ያለው?” በሚል መግለጫ ያወጣ ጊዜ “የፌዴራል” በማለት የጠራውን ህወሓት በክልሉ የሚያካሂደውን ጣልቃገብነት አውግዞ ነበር። ይህ አቋሙ ከሌሎች “ኢትዮጵያዊነት” እና “ሠርገኛ ጤፍ” ስብከቶች ጋር ተዳምሮ “ህወሓት አለቀለት” ያሰኘ “ሰበር ዜና” ሆኖ ከርሞ ነበር። በተሌ በዳያስጶራው ሚዲያ “ተንታኞች” የተራቀቁበትና “አዋቂዎች” የፖለቲካ ቅዠታቸውን ያብራሩበት የኦህዴድ በተለይም የበላይ አመራሩ አካሄድ ከብአዴን “እምቢባይነት” ጋር ተዳምሮ ሥራ አስፈጻሚው ሲሰበሰብ ህወሓት “እምነት የማይጣልበት” ተብሎ በድምጽ ይካዳል ተብሎም ነበር።

የህወሓት ተስፋፊነት ያስመረረው የአማራ ክልል ነዋሪ ለካድሬው በተዋረድ አስታጥቆ የላከው መልዕክት “ህወሓት ተስፋፊነቱን ያቁም”፣ ከክልላችን ጉዳይ ላይ እጁን ያንሳ የሚል ነበር። ምክንያቱ በማይገባን እና ፍጹም ልንረዳው በማንችልበት መልኩ በህወሓት በኩል ተስፋፊነትና ወራሪነት እየተካሄደብን ነው፤ ይህ ከበረሃ ጀምሮ እስካሁን ጠይቀን ምላሽ ሳናገኝ የቀረንበት ጉዳይ ነው፤ አሁን መሸከም ከምንችለው በላይ ሆኗል፤ በቃን! የሚሉ የከረሩ ጥያቄዎች ሕዝቡ አቅርቦ ነበር። ካድሬው ይህንን የሕዝቡን ጥያቄ ሥርዓቱን ተከትሎ ለበላይ አመራሩ አቅርቧል።

ከላይ ለተጠቀሱት የኦህዴድና የብአዴን “ምን ይዤ ወደ ሕዝቤ ልመለስ?” ጥያቄዎች ህወሓት/ኢህአዴግ “ከበቂ በላይ” የሆነ ምላሽ ሰጥቷል። ከየዲግሪ ወፍጮቤት በተገኘ ያለዓቅማቸው የዲግሪ መዓት ተሸክመው “ዶ/ር” እና የዚህ ዩኒቨርሲቲ ምሩቅ እየተባባሉ የሚሞጋገሱት ኢህአዴጋውያን ባወጡት መግለጫ “አመራሩ ብቃት የለውም” ብለዋል። ሲቀጥል “ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱና የድርጅትና የመንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች በተናጠልና በጋራ፣ ስትራተጅያዊና ታክቲካዊ አመራር የመስጠት ሃላፊነት” የላቸውም ብሏል። “ይሰልጥኑ” በማለት “የመፍትሔ ሃሳብ” አቅርቧል።

በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የመለስን “እስከ እንጥላችን በስብሰናል” በማስታወስ ሥራ አስፈጻሚው ራሱ ያለ አቅማቸው ስለሰየማቸው ኃላፊዎችና ሚኒስትሮች ይህንን ብሏል፤ “በዚህ ግምገማ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የመንግስት የበላይ አመራሮች ወቅቱ የሚጠይቀውን ስትራቴጂያዊ አመራር የመስጠት ጉድለታቸው ሰፊ እንደሆነ ታይቷል። ከፍተኛ አመራሩ ችግር አስቀድሞ የመለየት፣ ተንትኖ የማወቅ፣ የመፍቻ መንገዶች የመተለምና በዚሁ መሠረት የመፍታት ብቃቱ ወቅቱና መድረኩ ከሚጠይቀው ደረጃ ጋር አብሮ ባለማደጉ የተወሳሰበውን አገራዊ መድረክ በብቃት የመምራት ጉድለት እንደነበረበት የጋራ አቋም ተይዟል። በመሆኑም ለተፈፀመው ስህተትና ለደረሰው ጉዳት ከፍተኛ አመራሩ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ስምምነት ላይ ተደርሷል” በማለት “መሃይምም ቢሆን የኢህአዴግን መርህ እስከተቀበለ በሚኒስትርነት ይሾማል” የሚለውን የመለስ “የድንቁርና” አስተምህሮ በማስታወስ ሁሉም አመራርና ሚኒስትር “እንደበሰበሰ” እንዲቀጥል ስብሰባው በውሳኔው ላይ አስታውቋል።

የፌዴራል ጣልቃገብነት ይቁም፤ በክልላችን እየመጡ ግድያ የሚፈጽሙት ኃይላት ለፍርድ ቅረቡ፤ ተጠያቂዎች ናቸው፤ ወዘተ በማለት መግለጫና ዲስኩር ሲሰጡ የነበሩት እነ ለማ መገርሳም የመከላከያ ሠራዊት በክልላችን እየመጣ እንደፈለገ ይግደል በማለት አጨብጭበው ከስብሰባው ወጥተዋል። ህወሓትም “የበረሃ ልጆቹን” በማሞገስ ወደመጣችሁበት ተመለሱ ብሎ “በሰላምና በቡራኬ” ሸኝቷቸዋል። ከሽኝቱ ጋር አያይዞም ኦህዴድንና ብአዴንን “መርህ አልባ ቡድናዊ ትስስራችሁ” በተመለከተ “ሰከን በሉ” በማለት ተግሳጽ በመስጠት “ቸብ ቸብ” አድርጎ ወደመጡበት መልሷቸዋል።

የወደፊቱ!?

ህወሓት ላይ ሕዝብ ተነስቶበታል፤ ማመን ባይፈልግም ትውልድ አምጾበታል። የሕዝብ ጥያቄዎች እጅግ በርካታና ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ የመጡ ናቸው። ከግድያና አፈና ይቁም ጀምሮ እስከ እስረኞቻችን ይፈቱ! እጅግ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ … ጥያቄዎች አገሪቱን እየናጧት ነው።

በአገር ውስጥ ካለው ዘርፈብዙ ችግር ሌላ በውጭ በርካታ ችግሮች የአገሪቱን በሮች ያንኳኳሉ። ከዳያስጶራው የማያባራ ተቃውሞ እስከ አፍሪካ ቀንድ ውስብስብ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበቡት ችግሮች በህወሓት/ኢህአዴግ 17 ቀን ግም-ገማ ምላሽ የሚሰጥባቸው አይደሉም። ከዕውቀት ለጸዱት ኢህአዴጋውያን ዓቅማቸውን የማይመጥን ነው። በዚያ ላይ የህወሓት/ኢህአዴግ እብሪተኛነት፣ አልሰማም ባይነትና ጭፍንነት ሲጨመር ውስብስቡን ችግር መጀመሪያና መጨረሻ እያሳጣው መጥቷል።

በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከገጠር የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ የችግሩ ጉልላት ነው። ኢህአዴግ የአርሶአደሩ ነኝ፤ የገጠሩ ችግር የሚገባኝ የገበሬ ድርጅት ነኝ እያለ ሲፎክርና የተናጠል የበላይነት ይዞበት የቆየው የገጠር መዋቅር መበታተኑ የህወሓት/ኢህአዴግን መጨረሻ መቼ ብሎ የሚያስጠይቅ እየሆነ ከመጣ ሰንብቷል። የሥራ አስፈጻሚ መግለጫ በተባለው መሠረት ህወሓት/ኢህአዴግ ሚዲያውን ከማፈን ጀምሮ በሁሉም መስክ “የተቀናጁ ተጨማሪ እርምጃዎች” እወስዳለሁ ብሏል። ይህ የህወሓት ቋንቋ በአማርኛ ሲተረጎም “ግድያውን አፋፍመዋለሁ” ማለት ነው። ኦህአዴድና ብአዴንም ይህንኑ ውሳኔ አጽድቀው ወጥተዋል። ችግሩ ያለው ከማጽደቁ ላይ ብቻ ሳይሆን ይህንን እንደ አጀንዳ ወደየክልል ምክርቤቶቻቸውና ወደ ካድሬው እንዴት ያወርዱታል የሚለው ነው።

ይህንን በመሳሰሉ እጅግ አንኳርና ከህወሓት/ኢህአዴግ “የድንቁርና ብቃት” ያለፉ ችግሮች ውስጥ አገሪቱ እያለች በቅርብ ዓመታት መቶበመቶ የሚደፈንበት ምርጫ የማካሄድ ሃሳቡ እንደሌለ ራሱ ህወሓት/ኢህአዴግ ያመነበት ጉዳይ ሆኗል። ጥርነፋው ነትቦ፣ መዋቅሩ ፈርሶ ባለበት ባሁኑ ወቅት ምርጫ የሚሰርቅና የሚያጭበረብር ካድሬ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው። የውሸት ምርጫ እንኳን አለማድረግ ለህወሓት/ኢህአዴግን “ለምርጫ ማካሄጃ” እያለ የሚሰበስበው የውጭ ምንዛሪ ከማሳጣት ባለፈ ፖለቲካውን በእጅጉ የሚያከስርበት ይሆናል። ይህንን ክስረት መስመር ለማስያዝ የጻድቃን ገ/ትንሳኤ ህወሓት ቁጥር ሁለት “የመፍትሔ ሃሳቦች” በድጋሚ ወደ መድረኩ ብቅ ሊሉ ይችላሉ።

በዚህ ሁሉ ውስጥ ህዝባዊነታቸውን በአደባባይ በማሳየታቸውና በፊት እንዳልነበረ የውጭ አገር ዜጋ ዘግየት ብለው ኢትዮጵያዊነታቸውን በ“ሠርገኛ ጤፍ” እንጀራ ሕዝቡን ሲያበሉት የቆዩት አብይን ጨምሮ እነለማ መገርሳና ገዱ አንዳርጋቸው በቀጣይ በፖለቲካው መጥበሻ ላይ የሚቀመጡበት ሰዓት ላይ ይገኛሉ። የህወሓት “የበረሃ ልጆች” እንደመሆናቸው ወደአባታቸው ይመለሳሉ ወይስ ሕዝባዊነታቸውን በገሃድ በማሳየት የትግሉን ዙር ያከሩታል? በመቆየት የሚገለጽ እውነታ ይሆናል!   (ፎቶ: ስብሰባው ሲጠናቀቅ ሁሉም እጃቸውን በማንሳት መግለጫውን ሲያጸድቁ ENA)


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events