World News

DW.com: ኢትዮጵያ: በሕወሓት ውስጥ "የሕግ የበላይነት የለም" -ተቺዎች

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 30 November 2017

ኢትዮጵያ: በሕወሓት ውስጥ "የሕግ የበላይነት የለም" -ተቺዎች

ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አንድ ወር ገደማ "በር ዘግቶ" ካካሔደው ግምገማ በኋላ ሊቀ-መንበሩን አቶ አባይ ወልዱን በዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ተክቷል። ፓርቲው ባወጣው መግለጫ "አመራሩ ከገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቅቶት ሲዳክር" ነበር ብሏል። የደረሰበት መደምደሚያ ግን መሰረታዊ ለውጥ ይጠብቁ ለነበሩት አመርቂ አይመስልም።

ቀን 30.11.2017
እዚህ ታች ያዳምጡ፡
 

ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሥቅልቅል ተጠያቂ እየተባለ የሚወቀሰው በአደባባይ ተቃውሞዎችም የሚብጠለጠለው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ለ35 ቀናት ግምገማ ላይ ከርሟል። ከፓርቲው በጡረታ የተሰናበቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች ጭምር መሳተፋቸውን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን በጉዳዩ ላይ በሰሯቸው ዘገባዎች የተካተቱ ምስሎች ይጠቁማሉ። የሕወሓት መሥራቹ እና ዛሬም ድረስ ከፍ ያለ ተጽዕኖ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ ሥብሐት ነጋ አንዱ ናቸው።  ፖለቲከኛ እና ፀሐፊው አቶ አስራት አብርሐም ፓርቲው ባካሔደው ሹም ሽር "አሁንም አንድ ቤተሰብ ተደራጅቶ ስልጣኑን" ተቆጣጥሯል የሚል ዕምነት አላቸው። "የአቦይ ስብሐት ቤተሰቦች አካባቢ ወይ ደግሞ የአድዋ አውራጃ አካባቢ ልጆች የሚበዙበት አመራር ነው አሁን እየመጣ ያለው።" ሲሉ ያክላሉ።

መቐለ ወይስ አዲስ አበባ

Äthiopien Debretsion Gebremichael (DW/Tesfalem Waldyes)

ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል

ከግምገማው በፊት ሕወሓት የመቐለ እና የአዲስ አበባ የሚባሉ ሁለት አንጃዎች አሉት የሚሉ ጭምጭምታዎች ነበሩ። ፓርቲውን በቅርበት የሚከታተለው አስፋው ገደሙ አለ የሚባለውን ክፍፍል "ችግር የለብንም የተወሰኑ ማስተካከያዎች አድርገን እንዳለ እንቀጥል" እና "አይ አይደለም ተበላሽተናል፤ በስብሰናል ስለዚህ በጥልቅ መታደስ አለብን።" በሚሉት መካከል አድርጎ ይገልጸዋል። እንደ አስፋው አባባል ሁለቱ ወገኖች "በር ዘግተው ማንም በማይሰማበት እርስ በርስ ተፋጭተው አንዱ ሌላኛውን አሸንፎ" ከውሳኔ ደርሰዋል።

በውሳኔው ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ሊቀ-መንበር፤ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረአግዚአብሄር ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው ተመርጠዋል። የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መሥተዳድር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ አባይ ወልዱ ከሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ተነስተው ወደ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዝቅ ተደርገዋል።

አቶ አስራት አብርሐም "ከአባይ ወልዱ አመራር ይልቅ የአሁኑ አመራር ጠንካራ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ይመስለኛል።" ሲሉ ይናገራሉ። "አንደኛ ኃይላቸውን ወደ አዲስ አበባ እየሰበሰቡ ነው። ለፌድራል ከፍ ያለ ትኩረት የተሰጠ ይመስላል። ከአነ አባይ ወልዱ አመራር ይልቅ የአሁኑ አመራር በአቅምም በመናበብም በኩል ጠንካራ አመራር እንዳመጡ ነው የማየው።" ሲል ያክላሉ።

Äthiopien Addisalem Balema (DW/Tesfalem Waldyes)

ዶ/ር አዲስ ዓለም ባሌማ

በኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ ዶ/ር አብርሐም ተከስተ፣ የቀድሞው የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒም የፓርቲውን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተቀላቅለዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ምኒሥትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ከሥራ አስፈፃሚም ሆነ ከማዕከላዊ ኮሚቴዎቹ አግዷል። አስፋው  "በዴሞክራሲያዊ አግባብ ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ ሳይሆን የቡድኑ አንዱ አውራ በፈለገው መንገድ ነው እያስኬዱት ያለው ማለት ነው" ሲል ይተቻል።

የአመራር ለውጡ የትግራይ ወጣቶች እና ልሒቃን ከሚሹት ወቅቱም ከሚጠይቀው አኳያ ግን አመርቂ አይመስልም። ወጣቱ ፍፁም ብርሐነ የሕወሓት ፖለቲካ አሳታፊ አይደለም የሚል ትችት አለው። "አጠቃላይ ሲጠበቅ የነበረው ለውጥ አሳታፊነት ነው። አሁን ብዙ ችግር ያለበት የሕወሓት ችግር አሳታፊነት ነው። ባለፈው እንደገመገሙት ራሳቸው መጠቃቃት ላይ የተመሰረተ ነበር። ወይም ደግሞ በቡድን በዝምድና ላይ የተመሰረተ አካሔድ ይሔድ እንደነበረ አምነው መግለጫ አውጥተዋል። ይኸን የሚፈታው አሳታፊነት ነው። አሳታፊነት ማለት ፓርቲው የሕዝብ እንደመሆኑ መጠን ወጣት መሳተፍ መቻል አለበት።" ሲል ይናገራል።  

ፓርቲው ኅዳር 21 ቀን ባወጣው መግለጫ "ከገባበት አዙሪት ውስጥ መውጣት አቅቶት ሲዳክር" መቆየቱን ገልጿል። መሰረታዊ ለውጥ ሊያደርግ ይገባል የሚለው ትችት ከቀድሞ አባሎቹ እና የአዲሱ ትውልድ ዘንድ ጎልቶ ሲሰማ ከርሟል። አስፋው ገዳሙ አሁን ፓርቲው አደረኩ የሚለውን ለውጥ ከዚህ ቀደም ከነበሩት የተለየ አይደለም ሲል ይተቻል።

"ሙስና አለ። በቡድን ተደራጅተህ እርስ በርስ መጠቃቃት አለ። ሥልጣን ለሕዝብ ማገልገል ከመጠቀም ይልቅ ለግል ማበልጸጊያ መጠቀም አለ። እነዚህ ምልክቶች ናቸው። ምንጩ ምንድነው የሕግ የበላይነት የለም። ተጠያቂነት የለም። ግልፅነት የለም። ግልፅነት ከሌለ ተጠያቂነት ከሌለ የሕግ የበላይነት ከሌለ የቡድኖች እና የግለሰቦች የበላይነት ከነገሰ ምንድነው የሚሆነው? ሕግ ይጣሳል። ሥልጣኑ ለግላቸው ነው የሚጠቀሙበት ማለት ነው። ከድሮ የመጣው ችግር እንደ ማበረታቻ ነው። ስልጣን ከያዝክ ተጠቃሚ ትሆናለህ። ራስህ ብቻ ከነ ቤተሰብህ አንዳንዴም አካባቢህ እንጂ እንደ ሀገር ማሰብ እንደ ሕዝብ ማሰብ እየቀረ ነው።"

ወጣቱ ፍጹም ብርሐነ በበኩሉ በሕወሓት ዘንድ የታየው የግለሰቦች መቀያየር ለውጥ ያመጣል የሚል ዕምነት እንደሌለው ፈርጠም ብሎ ይናገራል። ፓርቲው የሚከተለውን ፖሊሲ ሊቀይር ይገባል የሚለው ፍጹም ሕወሓት የሚከተለውን መንገድ የጥፋት ነው የሚል ሥጋት ጭምር አለው።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events