World News

Zehabesha.com: የህወሓት ክፍፍል ወደ ሶስት ቡድን አደገ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Saturday, 25 November 2017

የህወሓት ክፍፍል ወደ ሶስት ቡድን አደገ

 

(ቢቢኤን) የህወሓት ክፍፍል ወደ ሶስት ቡድን ማደጉን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ከመቀሌ ከተማ የወጡ የመረጃ ምንጮች እንደጠቆሙት ከሆነ፣ ድርጅቱ በአሁን ሰዓት ከባድ የመፈረካከስ አደጋ ከፊት ለፊቱ ተጋርጦበታል፡፡ በመቀሌ ከተማ እየተካሔደ በሚገኘው እና አሁንም ሊጠናቀቅ ባልቻለው የህወሓት ማዕከላዊ ስብሰባ ላይ የቃላት ጦርነት ሁሉ መጀመሩን የጠቆሙት ምንጮች፣ አስቀድሞ ለሁለት ተክፍሎ የነበረው ህወሓት፣ አሁን ላይ ሶስት የተለያየ አቋም ያላቸው ቡድን እየሆነ ይገኛል ሲሉ የመረጃ ምንጮቹ ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የጀመረውን ግለ ሂስ እያካሄደ ቢሆንም፣ በግለ ሂሱ ላይ ኃይለ ቃል እስከመለዋወጥ የደረሱ አመራሮች መኖራቸው ታውቋል፡፡ አባይ ወልዱ የሚገኙበት አንደኛው ቡድን በውስጡ አባይ ጸሐዬን፣ አዲስ ዓለም ባሌማን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችን ያካተተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ በስብሓት ነጋ የሚመራው ቡድን ነው፡፡ ሶስተኛው ቡድን ደግሞ የሀገሪቱን ደህንነነት የሚቆጣጠረው ጌታቸው አሰፋ የሚገኝበት ሲሆን፣ በውስጡም አቶ አርከበ ዕቁባይን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ይገኙበታል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች አስቀድሞ ተከፋፍለው የቆዩ ቢሆንም፣ አርከበ ዕቁባይ እና ጌታቸው አሰፋ የሚገኙበት ቡድን ግን አዲስ የተፈጠረ መሆኑን ከምንጮች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ አዛዥ ሳሞራ የኑስ በበኩላቸው ከአንደኛው የህወሓት ቡድን ጋር መሰለፉን የመረጃ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ እንደ መረጃዎች ገለጻ፣ ጄኔራል ሳሞራ፣ አባይ ወልዱ እና አባይ ጸሐዬ ለሚገኙበት ቡድን ወግኗል፡፡ አዜብ መስፍንም በዚህ ቡድን ውስጥ እንደምትገኝበት ታውቋል፡፡ ጄኔራል ሳሞራን ለዚህ ስልጣን ያበቃቸው አቶ መለስ ዜናዊ መሆኑ፣ ወይዘሮ አዜብ መስፍን በማንኛውም ጊዜ ከእነ ሳሞራ ቡድን ድጋፍ እንድታገኝ እየረዳት እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ወይዘሮ አዜብ መስፍን ከአቶ ስብሓት ነጋ ጋር ክርር ያለ ጸብ ውስጥ መግባታቸውን የጠቆሙት ምንጮች፣ አዜብ ስብሰባ ረግጣ መውጣቷን ለህወሓት የማኅበራዊ ሚዲያ ካድሬዎች ያደረሱት እንኳን አቶ ስብሓት ነጋ ናቸው፡፡

ከአንድ ወር በላይ ለሆነ ጊዜ የተካሔደው የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ አሁንም ምንም ዓይነት መግባባት ላይ ሊደረስበት አልተቻለም፡፡ ግለ ሂስ በተባለው ፕሮግራማቸው ላይ፣ እርስ በእርስ ሲጎሻሸሙ እንደሚውሉም ታውቋል፡፡ ሁሉም ተቺ እና ተንታኝ በሆነበት የማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ አንድም የመፍትኤ ሀሳብ ሳይገኝ ከአንድ ወር በላይ የሆነ ጊዜ ተቆጥሯል፡፡ ህወሓት ከዚህ በኋላ ስብሰባው መጠናቀቁን ቢገልጽ እንኳን፣ በውስጡ ያለው ችግር ተፈትቶ እንደማይሆን የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ የድርጅቱ ክፍፍል ወደ ሌላ ምዕራፍ እያመራ ሲሆን፣ በቅርቡም ከዚህም የበለጠ ክፍፍል ሊፈጠር እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events