Dehai

(ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠ/ሚ ዐቢይ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጅማ ዞን ጉብኝት አደረጉ

Posted by: Semere Asmelash

Date: Monday, 12 October 2020

ጠ/ሚ ዐቢይ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጅማ ዞን ጉብኝት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የስራ እንቅስቃሴን ጎበኙ።

መሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው የሚያካሂዳቸውን የምርምርና የግንባታ እንቅስቃሴዎች መጎብኘታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በጅማ ዞን ጎማ ወረዳ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ስኬታማ የሆነ አርሶ አደርን የቡና ማሳ ጎበኝተዋል፡፡

አርሶ አደር ሳቢቅ አባመጫ ቡናን በማሳቸው በማምረት በቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ስኬታማ የሆኑ አርሶ አደር ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጉብኝቱ በኋላ እንዳሉት እንደ ሌሎች ሰብሎች ሁሉ ቡናን ኩታ ገጠም በሆነ የግብርና ዘዴ በመጠቀም ምርታማ ለማድረግ ይሰራል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የተመለከቱትን የቡና ግብርና ዘዴ በሃገራቸው ለመተግበር ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ለማድረግ ጠዋት ላይ ጅማ ከተማ መግባታቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዚዳንቱ ጅማ አባ ጅፋር አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ከፕሬዚዳንቱ በተጨማሪ የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እና አማካሪያቸው የማነ ገብረዓብ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብን ጎበኙ፡፡

በስፍራው እየተሰራ ያለውን የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት አካል የሆነውን የሰው ሰራሽ ሐይቅ ግንባታንም ጎብኝተዋል፡፡

በተጨማሪም በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችንም ጎብኝተዋል፡፡

በዚህም በዳውሮ ዞን እና ኮንታ ልዩ ወረዳ እስከ ንጉስ ሃላላ ኬላ ድረስ የሚገኙ የተፈጥሮ ሃብቶችን ነው የጎበኙት፡፡

በገበታ ለሃገር ይፋ በተደረገው የኮይሻ ፕሮጀክት ዙሪያ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ዛሬ ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ጠዋት በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events