Dehai News

Goolgule.com: የልደቱ፤ የትህነግ እና የነጃዋር መጨረሻ

Posted by: Berhane Habtemariam

Date: Thursday, 11 March 2021

ትህነግ ወደ ከርሰ መቃብር፤ ጃዋር ወደ ከርሱ፤ ልደቱ ወደ ዕረፍቱ

በስተመጨረሻ “መንግስት የለም” የሚለውን ትግል ተቀላቅለው የነበሩትና፣ ትህነግ ባስቀመጠው የትግል ስልት የማስተባበር ስራ ሲሰሩ እንደነበር በመግለጽ ክስና ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው የነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው በድንገት ከፖለቲካ በበቃኝ መገለላቸው ተሰማ። ውሳኔያቸው ከትህነግ ህልውና መክሰማና ከነ ጃዋር ምግብ መብላት መጀመር ጋር መያያዙ ውሳኔያቸውን የተስፋ መቁረጥ አስመስሎባቸዋል።

ልደቱ አያሌው በቅርቡ ተከሰው በነበሩበት ወቅት የተገኘባቸውን ሽጉጥ ከደህንነት መስሪያ ቤት የተሰጣቸው መሆኑንን መግለጻቸው፣ በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በሂሳብ መዝገብ ወጪ እየተደረገ ደሞወዝ ይከፈላቸው እንደነበር ይፋ መሆኑ “ቀድሞም ትህነግ ነበሩ” የሚለውን ወቀሳ አጠናክሮባቸው ነበር።

ቀደም ሲል ህግ ተጥሶም ቢሆን ምርጫ መደረግ እንደሌለበት ሲሞግቱ የነበሩት አቶ ልደቱ፤ ትህነግ መቀሌ ሆኖ “ከመስከረም 30 በኋላ ቅቡል መንግስት የለም” የሚል አዋጅ ካሰማ በኋላ “ የሽግግር መንግስት ይቋቋም” በሚል የመሃል ፖለቲካውን ለመምራት ከነ ጃዋር መሐመድ ጋር ግንባር ገጥመው እንደነበር ይታወሳል። በወራት እድሜ ውስጥ ለተቀያየረው አቋማቸው በወጉ ተጠይቀው ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ያልተሰሙት አቶ ልደቱ፣ ባሰራጩት ሰፊ ጽሁፍ ራሳቸውን ከፖለቲካ ማሰናበታቸውን አስታውቀዋል።

“በመጨረሻም ከአቅም በላይ በሆነ የጤና ምክንያት ቢሆንም ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ለጊዜውም ቢሆን ከትግል ተሳትፎዬ ለመታቀብ በመገደዴ፥ የትግል አጋሮቼንና የዐላማ ደጋፊዎቼን ሁሉ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ያሉት አቶ ልደቱ፣ ስንብቱን የመረጡት በጤና እክል የተነሳ ነው ብለዋል።

ሆኖም በእስር በነበሩ ጊዜ የልብ በሽታ እንዳልባቸውና ውድ አሜሪካ ለመሄድ እያሉ መታሰራቸው አገባብ አይደለም በማለት የፓርቲ ሰዎቻቸው መንግሥትን ሲሞገቱ ነበር። በእስር እያሉ የጤና ዕክል ቢገጥማቸው መንግሥትን ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ሲናገሩ ነበር። ሆኖም አቶ ልደቱ ከእስር ከተለቀቁ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም ለልብ ሕክምና ወደ ውጭ እስካሁን እንዳልሄዱ ይታወቃል። ከዚያ ይልቅ የሚለውን መጽሃፋቸውን በማሳተም ተጠምደው እንደ ነበር ይታወቃል።

“… ከእኔ ብዙ እንደምትጠብቁና ለእኔ ለራሴ እንደሆነብኝ ሁሉ ለእናንተም ይህ ክስተት ድንገተኛ መርዶ እንደሚሆንባችሁ ስለምገነዘብ ነው። ወደፊት የጤና ሁኔታዬ ተሻሽሎ እስከመጨረሻው በፖለቲካ ሒደቱ ለመቀጠል ለራሴ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም ፈጣሪ ዕድል እንደሚሰጠኝ ተስፋ እያደረግኹ ሀገራችን ኢትዮጵያ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማት ያለኝን ልባዊ ምኞት በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ” ሲሉ ደብዳቤያቸውን የቋጩት አቶ ልደቱ፣ እሳቸው በሚሉት ደረጃ ለኢትዮጵያ ወሳኝና ለዘመኑ ቀውስ መድሃኒት የሆኑ ዜጋ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ታሪካቸው ለማሳያነት አልጠቀሱም።

በጽሁፋቸው ኢትዮጵያ በኤርትራና በሱዳን መወረሯን አንስተው “ይህ የመበታተን ምልክት ነው” ብለዋል። የኢትዮጵያ ጦር ላይ ክህደት ተፈጽሞ በተኛበት መጨፍጨፉን አጉልተው ሲነቅፉ ያልተሰሙት አቶ ልደቱ ዛሬም ኤርትራን ወራሪ አድረገው መሳላቸው አግራሞትን ፈጥሯል።

“ከሞት የተረፈው የኢትዮጵያ ጦር እርቃኑንን በርሃብና በውሃ ጥም ተሰቃይቶ ኤርትራ ሲገባ ነብስ እንዲዘራና ሃፍረተ ሰውነቱን እንዲሸፍን ያደረጉት የኤርትራ ሰራዊትና መንግስት ናቸው” በሚል የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የደረሰባቸውን ግፍ በተናገሩት መጠንና ህዝብ ቁጣውን በገለጸበት ልክም ባይሆን አቶ ልደቱ ለትህነግ ወግነው መቆማቸው ደጋፊ አልባ አድርጓቸዋል እየተባለ ነው። በተለይ ከእስር ሲፈቱ ከእስርቤት ደጅ ጀምሮ ይሆናል ብለው የጠበቁትን የሕዝብ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ፖለቲካቸው ድጋፍ እያጣ ለመሆኑ የማነቂያ ደወል እንደሰጣቸው በቅርብ ያሉ ሰዎች ይናገራሉ።

ተወለድኩበት የሚሉት አካባቢ ሳይቀር በዚሁ ከትህነግ ጋር ያላቸው ትሥሥር ያስከተለባቸው ጥላቻ ድጋፍ እየነሳቸው መሆኑንን በመረዳታቸው ከጤና ችግራቸው ጋር አዳምረው ከፖለቲካው ዓለም ለመሰናበት መወሰናቸውን ከጽሁፋቸው ግርጌ አስተያየት የሰጡ አስታውቀዋል። “ሲሻለኝ እንደምመለስ ተስፋ አደርጋለሁ” ያሉትን አስመክልቶ “አቶ ልደቱ አሁን የደበዘዘውና የሰከነው የውስጡ ፖለቲካ ሲጋጋል እንደሚሻላቸው አመላካች ነው” የሚል ሽሙጥ ቢጤ አስተያየት ተሰጥቶበታል። በመረጋጋት ላይ ያለው ፖለቲካ ባንድ ጊዜ መጦዝ ቢጀምርና ትርምስ ቢከሰት ልደቱ በፊትአውራሪነት ብቅ እንደሚሉ በርግጠኝነት አስተያየት የሰጡም አሉ።

አቶ ልደቱ “የትግራይ ህዝብና ትህነግ አንድ ናቸው” በሚል ድምዳሜያቸው ይታወቃሉ። በዛሬ የመለያያ ጽሁፋቸው መንግስትን ለአንዴና ለመጨረሻ በሚመስል መልኩ ደብድበዋል። ህገ መንግስቱ እንዲቀየር ጥሪ አቅርበዋል። የህገመንግስት ረቂቅና አፈጻጸም መጽሃፍ እያዘጋጁ ስለሆነ ተቃዋሚዎች እንደ ሰነድ ተጠቅመውበት የመታገያ አጀንዳቸው እንዲያደርጉት ታቦት ሳይጠሩ ተማጽነዋል። በተዘዋዋሪ ቀጣዩ መጽሃፌን ግዙ ብለዋል።

የትህነግ መክሰም በኢትዮጵያ በርካታ ችግሮችን አብሮ እንደሚያከስም በፖለቲካው ዙሪያ ያሉ አስተያየት ሰጥተዋል። በርካታ ደጋፊዎቻቸውም ተስፋ እንደሚቆርጡ አመልክተዋል።

ሌላው የተነሳው ጉዳይ አቶ ልደቱ ከፖለቲካ መሰናበታቸውና የእነ ጃዋር መሐመድ ምግብ መጀመር ግጥምጥሞሽ ነው። አቶ ልደቱ “ከመስከረም ሰላሳ በኋላ መንግስት የለም” የሚለውን ዘመቻ ሲቀላቀሉ ከነ ጃዋር ጋር ገጥመው የነበረ መሆኑንን፣ በኦሮሞ ሚዲያዎች ላይ ከጃዋር ጎን በመሆን በህብረት ዘመቻውን ማራመዳቸውን ያታወሱ፣ ሁሉም ነገር ማክተሙና እነ ጃዋርም ምግብ ለመብላት መወሰናቸው አቶ ልደቱን አዲስ የሚጠበቅ ተስፋ አሳጥቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ስንበቱን ለጊዜውም ቢሆን መርጠዋል የሚሉ አስተያየቶች ተሰምተዋል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ጃዋር “የአንድነት ሃይሎች ከዱኝ” መናገሩን አስመልክቶ ከዚህ በፊት የዘገበው እዚህ ላይ ይገኛል። (ethio12.com)


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events