Dehai News

Goolgule.com: “የፌዴራል መንግሥት በትግራይ የሆነ ዕርምጃ እወስዳለሁ ካለ ራሱ ያደርገዋል”

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Friday, 31 July 2020

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በፋና ቴሌቪዥን በትግርኛ ቋንቋ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። ከተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ለውጡና የትግራይ ክልል ሁኔታ፣ የድምፂ ወያነና የትግራይ ቴሌቪዥን መዘጋት፣ ምርጫን በተመለከተ፣ የኤርትራ ጉዳይና የፌዴራል መንግሥት ትግራይን ሊያጠቃ ነው ስለመባሉ ይገኙበታል። በማብራሪያቸው የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው ተጠናቅረዋል።

ለውጡና የትግራይ ክልል ሁኔታ

“የትግራይ ሕዝብ የማይሳተፍበት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ በአሁኑ ወቅት ሦስት ችግሮች አሉ። እነዚህ ሦስት ችግሮችን በግልጽ መገንዘብ ያስፈልጋል። የመጀመርያው ችግር ከለውጥ ጋር የተያያዘ  ነው። አገራችን ከለውጥ ጋር በተያያዘ ፈተና ውስጥ ነው ያለችው። ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ ሁሉም ሰው ያውቃል። በርከት ያሉ የውስጥም የውጭም ፈተናዎች አሉ። በዚህ ሰዓት የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብና ሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፈተና ላይ ነው ያሉት። የትግራይ ሕዝብም የራሱ ፈተናዎች አሉበት።

“ፈተናዎቹ የየራሳቸው የሆነ ባህሪያዊ ምክንያት አላቸው። የሁሉንም ሕዝብ ፈተና አንድ ላይ ጠቅልለህ ልትመለከተው አትችልም። ይህ ሁሉ የሚሆነው በለውጥ ሒደት ውስጥ ስለምንገኝ ነው። ለውጡ የራሱ የሆነ ባህሪያት አሉት ብለህ ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል። ለውጥ ደግሞ በባህሪው መልካም ቢሆንም እንኳን የተወሰነ ሥቃይ አለው። ልክ እንደ የወሊድ ሒደት ለውጥም ሕመም አለው። ቢሆንም ግን ከሕመሙ በኋላ የሚኖረው ተስፋ ጥሩ ስለሆነ፣ ልክ ወላድ እናት የወሊድን ሕመም እንደምትቋቋመው እኛም እያስታመምነው ነው። በለውጥ ሒደት ውስጥ በመሆናችን የሚመጡ ችግሮችን በቅርቡ መፈታታቸው እንደማይቀር አምናለሁ። ቀስ እያሉ ሊፈቱ ይገባል ይቻላልም የሚል እምነት አለኝ። ይህን ወስደህ እንደ ቋሚ ችግር ልትመለከተው አይገባም።

“ሁለተኛው ችግር በብልፅግናና በሕወሓት መካከል ባለው ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው። በብልፅግናና በሕወሓት መካከል ያለው ግንኙነት ልዩነት መኖሩ ገሃድ ነው። ይህን የለም ልትል አይቻልም። በፌዴራልና በክልሉ ያለው ልዩነት በትግራይ ላይ ተጨማሪ ችግር መፍጠሩ ግልጽ ነው። እንደፈለግከው ተገናኝተህ ተመካክረህ በአንድ ላይ መሥራት ካልቻልክ፣ ተጨማሪ ችግር መፈጠሩ የሚቀር አይመስለኝም። ስለሆነም በለውጥ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በድርጅቶቹ መካከል ያለው ልዩነት ሌላ ችግር ሆኗል ተብሎ ሊወሰድና ችግሩም ሊፈታ ይገባል ቢባል ትክክል ይመስለኛል።

“በብልፅግና በኩል ሁሉን ነገር በመረዳዳት (በመግባባት)፣ በግምገማና በመነጋገር የመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን። ሁልጊዜ ቁጭ ብለን በትዕግሥት በመነጋገር ብቻ በመካከላችን ያሉ ችግሮች ይፈታሉ የሚል እምነት አለን። በሕወሓት በኩልም ቢሆን ያለውን ልዩነት በመግባባት የመፍታት ፍላጎት ያላቸው አመራሮች እንዳሉ የማይካድ ሀቅ ነው። ሁሉንም ሰው አንድ አድርገህ ልትመለከተው አትችልም። አንዳንዶቹ ሌላ ሊፈልጉ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ ልዩነቱ በሰላማዊ መንገድ ይፈታል የሚል እምነትና ፍላጎት እንዳላቸው አስባለሁ።

“ይሁን እንጂ በሕወሓት በኩል ያለውን ልዩነት በግጭት የመፍታት ፍላጎት ያላቸው ጥቂት አመራሮች መኖራቸው ለሁሉም ግልጽ መሆን አለበት። ሁሉም ሰላም ይፈልጋል፣ ሁሉም ተነጋግረን ጉዳያችንን እንጨርስ የሚል እምነት አለው ብሎ መውሰድም ተገቢ አይደለም። ስለሆነም በግሌ እኔ የትግራይ ሕዝብ ወደ ግጭትና ሁከት የሚገፋፉትን አካላት፣ እንደ ልማዱ ተው ማለት አለበት የሚል እምነት አለኝ። ይህን የማድረግ የሞራልም ይሁን የብቃት ችግር እንደሌለበት አሳምሬ አውቀዋለሁ። በአንፃሩ ደግሞ ሰላም የሚፈልጉትን አመራሮች ሊደግፋቸው ይገባል። ሰላም የሚፈልጉት አመራሮች የሕዝብ ድጋፍ ካገኙ አብዛኛው ችግር ይፈታል ብዬ አምናለሁ። ይህንንም ለማድረግ የትግራይ ሕዝብ ዝግጁ መሆኑን እረዳለሁ።

“ሦስተኛው ደግሞ በሁለቱ መሀል ያለውን ልዩነት ለማስፋት የሚፈልጉ አካላት የሚፈጥሩት ችግር ነው። ይህ የለም የሚል ግምገማ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ስላለና ስለሚታይ። እነዚህ ሦስት ጊዜያዊ ምክንያቶች ከሚፈጥሩት ችግር ውጪ ትግራይን የመጉዳት የሚባል ሐሳብ ፈጽሞ የለም ብዬ ነው የማምነው። እንዲህ ያለ ሐሳብ ያለው ግለሰብ በመንግሥት ውስጥ ካለም በችግር ውስጥ ስላለ ሊታገዝ፣ ሊገመገምና ባህሪውን እንዲመለከት ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ። ከዚህ ውጭ ያለውን የፖለቲካ ጨዋታ ግን ወስደህ ከሕዝብ ጋር ደባልቀህ ማየት ተገቢ አይደለም።

የድምፂ ወያኔና የትግራይ ቴሌቪዥን መዘጋት

“ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ፍላጎት እንደነበረን በግልጽ በአገር ደረጃ የታየ፣ እንዲሁም ተጨባጭ ዕርምጃ የወሰድንበት ሥራ እንደሆነ ዓለም ሁሉ ያውቀዋል። ከለውጡ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች አንዱ የመገናኛ ብዙኃንን ክፍት ማድረግ ነው። ለትግራይ ይሁን፣ ለኦሮሚያ ይሁን፣ ለአማራ ይሁን አሁን ላይ ያለን የመገናኛ ብዙኃን ዓይነት በአገር ደረጃ ኖሮን አያውቅም። ይህ ሁሉም ሰው የሚያውቀው ሀቅ ነው። የትግራይ ሕዝብ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን አማራጭ በጣም ውስን ነበር።

“እንደሚታወቀው ከለውጡ በፊት ድምፀ ወያኔና ትግራይ ቴሌቪዥን ብቻ ነው የነበረው። በአሁኑ ወቅት ከሁለቱ በተጨማሪ በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞችም አማራጭ ሐሳቦች ለመግለጽ የሚያስችሉ ዕድል እንዳለ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚታወቅ እውነታ እንደሆነ ሁላችንም ልናምን ይገባል። ይሁን እንጂ በአገራችን ያሉ መገናኛ ብዙኃን በአጠቃላይ ችግር እንዳለባቸው የታወቀ ነው። የመንግሥት ይሁን፣ የግል ይሁን፣ የሃይማኖት ይሁን በተለያየ ምክንያት ችግር አለባቸው። አንዳንዱ ከአቅም ማነስ የሚመጣ ችግር ነው ያለበት። አንዳንዱ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃንን ሥነ ምግባር ካለመረዳት የሚመጣ ችግር ይታያል። በሌሎች ደግሞ ከክፋት የሚመጡ በርካታ ችግሮች አሉ። ሆነ ብለው የውሸት ወሬ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ችግር ውስጥ እንዲገባ የሚሠሩ የውሸት ዜና (Fake News) እየፈጠሩ የሚሠሩ በርካታ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉ የሚታወቅ ነው። ይህን ችግር ለሌሎች ክልሎች ሰጥተህ በትግራይ የለም ልትል አትችልም። የትግራይ መገናኛ ብዙኃንም ቢሆኑ ከዚህ ድክመት ነፃ አይደሉም። ይህ በአገር ደረጃ የምናየው ችግር እዚያም አለ።

“ችግሩን ለፌዴራል መንግሥት ሰጥተህ ራስህን ነፃ ልታደርግ አትችልም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ በብሮድካስት ባለሥልጣን የተወሰደው ዕርምጃ ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ፣ ከተፈጠረው ሁከትና ግርግርን የማባባስ ድርሻ ስለነበራቸው ነው። ሁኔታውን በድንገት ነው የሰማነው። ኃላፊነት የሚሰማው የመገናኛ ብዙኃንም ሆነ የክልል መንግሥት ሰላም እንዲወርድና ሰው እንዳይጎዳ ነበር ከሁላችንም የሚጠበቀው። ባህላችንም እንዲህ ነበር። ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃን ሲሠሩት የነበረው ሥራ ፈጽሞ የማይጠበቅና መልካም ያልሆነ ነበር። ይሁን እንጂ ዕርምጃው ጊዜያዊ ነው። ዕርምጃው የትግራይ ሕዝብ አፍ እንዳይኖረው ተብሎ ነው የተወሰደው ብሎ መውሰድ ተገቢ አልመሰለኝም።

ምርጫን በተመለከተ

“በምርጫ አስፈላጊነት ላይ ልዩነት ያለን አይመስለኝም። ሁሉም እንደሚያውቀው ለምርጫ ቀጠሮ ይዘን እየተዘጋጀን እያለን ነው ሳናስበው የኮሮና ፈተና የመጣው። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫ እስከሚደረግ ሥልጣን ላይ ያለው እንዲቀጥል ወስኗል። ይህ ደግሞ የሚሠራው ለብልፅግና ስለሆነ ሕወሓት መቀጠል አትችልም የሚል አልነበረም። ይህ ማለት ሕወሓት በክልልም ሆነ በፌዴራል የሕዝብ ውክልናውን ይዞ እንዲቀጥል ተወስኗል ማለት ነው። ለምን ተወሰነ? እንዴት አድርገን ይህን ውሳኔ ተቀበልን? የሚለውን ሒደት ለሁለትና ለሦስት ወራት የተመለከትነው በመሆኑ፣ ራሱን ተመልሼ ልናገር አልፈልግም። ብልፅግና ፍላጎቱ ምርጫ ማድረግ ነበር። ምርጫ ቦርድ በኮሮና ምክንያት ምርጫ ማድረግ አልችልም ጊዜ ያስፈልገኛል በማለቱና ፓርላማ በመቅረቡ፣ ፓርላማውም በመወሰኑ ሒደቱን ብልፅግናም ይሁን ሕወሓት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተቀብሎ እንዲሠራ እጠይቃለሁ፣ እንደዚያ መሆኑም ጥሩ ነው የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም ምርጫን ከዓመት በኋላ የማድረግ ጉዳይ ሆኖ ሳለ የትግራይ ክልል መንግሥት በሚሊዮኖች የሚቆጠር በጀት መድቦ ክልላዊ ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ የሚገርም ነው። በአንድ ወገን ኮሮና በትግራይ ሥጋት አልሆነም ማለት ነውን? ሰው ኮሮና አይዘውም አይገለውም ማለት ነው? ወይስ ዘመናዊ የሆኑ ሆስፒታሎችና መድኃኒቶች ስላሉን ችግር የለውም ማለት ነው? በሥነ አመክንዮ (Logically) ስትመለከተው ለመረዳት ትንሽ አስቸጋሪ ነው።

“በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ክልል መንግሥት ሚሊዮኖችን አውጥቶ ምርጫ ከሚያደርግ ሁለትና ሦስት የውኃ ጉድጓዶችን ለምን አይቆፍርም? በትግራይ ውኃ ምን ያህል ችግር እንደሆነ ይታወቃል። ወይም ደግሞ አንድ ሆስፒታል አይሠራም? ለምን አንድ ትምህርት ቤት አይሠራም ብለህ ለመጠየቅ ትገደዳለህ። የልማት ጥያቄ እያለ፣ ገንዘብ የለም እያልንና የፌዴራል መንግሥት ገንዘብ አልሰጠም እያልን ለምርጫ ግን ችግር የለብንም ሚሊዮኖች አውጥተን ልናደርገው እንችላለን የሚለው እንዴት ያለ ሐሳብ ነው ብለህ ስትመለከተው፣ ለመቀበል አስቸጋሪ ነው። ሐሳቡ ምንድነው የሚለው አይገባህም። እንደሚታወቀው ምርጫውን አንድ ዓመት ታግሰን በጋራ ማድረግ የማይቻለው ለምንድነው? ቢረዝም አንድ ዓመት ነው። ለአንድ ዓመት ብለህ ይህንን ሁሉ ገንዘብ ከማጥፋት ለምን በአገር ደረጃ ያለውን ሥርዓት አክብረህና የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ወስደህ አትሠራም የሚል ጥያቄ ማንኛውም ግለሰብ ሊያስብበት ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።

“በሌላ በኩል ደግሞ ሕወሓት ለሌሎች ፖለቲካዊ ድርጅቶች ከልቡ ለማስረከብ ስለሚፈልግ ነው ምርጫ ማድረግ የፈለገው? እነዚህ ጥያቄዎች በቅጡ ሊመለሱ ይገባል። ከዚያ ውጪ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጉዳይ እጁን አስገብቶ አያውቅም፣ ወደፊትም አያደርገውም። ይህን ስል ግን የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱንም አሳልፎ አይሰጥም። በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለው የፌዴራል ሥልጣን ፌዴራል መንግሥቱ የሚያከናውነው ነው የሚሆነው። እኛ ኃላፊነታችንን አሳልፈን አንሰጥም በሌሎች ኃላፊነትም እጃችን አስገብተን የሆነ ነገር አናደርግም።

በኤርትራ ጉዳይ

“የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከመራራ ጦርነት በኋላ ለሃያ ዓመታት ያህል እንቅልፍ ላይ የቆየ ነበር። ስለሆነም ከረዥም እንቅልፍ በኋላ የባነነ ግንኙነት ብለህ ልትወስደው ትችላለህ። በዚህ ወቅት መልካም የሆነ ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ ግንኙነት አለን። በኢኮኖሚውም ከተመለከትነው የስልክ ግንኙነት አለን፣ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት አለን። ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ነገሮችን በጋራ መሥራት ጀምረናል። ይህ ደግሞ ቀስ እያለ ከፍ ወዳለ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል አምናለሁ። ይደርሳል የሚል ተስፋም አለኝ። የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከፍላጎት ተነስተህ ግንኙነቱ እንዲፋጠን መመኘት የተቀደሰ ፍላጎት ነው የሚመስለኝ። ጤና ያለው ኢትዮጵያዊ ሊያስበው የሚችል ሰናይ ፍላጎት ነው ብሎ መውሰድ ይገባል። ግን ችግሩን ሊፈቱ እየቻሉ ለሃያ ዓመታት ያህል ያልቻሉ ሰዎች፣ በሁለት ዓመት ያገኘነውን ድል ማሳነሳቸው ተገቢ አይመስለኝም።  

“ይህ ውጤት በሥራ ነው የመጣው። አንተ ያልቻልከውን ነገር ሌላ ሠርቶት እያየህ አሳንሰህና ምንም እንዳልተደረገ አድርገህ መናገር ተገቢ አይደለም። ሌላኛው ነጥብ ደግሞ ግንኙነቱ የሁለት አገሮች ግንኙነት እንደ መሆኑ የፌዴራል ሥልጣን መሆኑ መታወቅና ሊሰመርበት ይገባል። በአጭሩ ከግንኙነቱ የሚገኘው ማንኛውም ጥቅም ለሁለቱም ሕዝቦች፣ አገሮችና መንግሥታት እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ብቻ አይደለም። ሁላችንም ከሰላምና ከልማት ጥቅም አለን። የንግድ ልውውጡም ይጠቅመናል የሚል እምነት ይዘህ ጉዳትም ቢኖር ሁሉንም የሚጎዳ እንጂ፣ ለይተህ ለትግራይ ልትወስደው የሚቻል አይደለም። የሆነ ሆኖ ግንኙነቱ በተቃና መስመርና ደረጃ ላይ እንዳለና እየተሻሻለ እንደሚሄድ ላረጋግጥ እወዳለሁ።

የፌዴራል መንግሥት ትግራይን ያጠቃል?

“ማን ነው ማንን የሚያጠቃው? የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልልን የሚያጠቃው ለምንድነው? ይህ የዕብዶች ንግግር ነው። ‘ከተናገረው ደጋሚው’ የሚለውን የትግርኛ አባባል ያስታውሰኛል። የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልል መንግሥትንም ሆነ የትግራይ ሕዝብን ሊወጋ ይችላል ብለህ ማሰብ፣ በራሱ እንዴት ያለ ሐሳብ እንደሆነ ለመረዳት ለእኔ በጣም ያስቸግረኛል። ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመሆን ትግራይን ሊያጠቁ ነው? በመሠረቱ ውጊያ ለማድረግ የሚያስብ ማንኛውም አካል ካለ በቂ የሆነ ምክንያት ሊኖረው ይገባል። ምክንያቱ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሕዝቦችም እንዲቀበሉት ያስፈልጋል። አጀንዳ ብፈጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት ነው የሚቀበለኝ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ለምን ብሎ ነው የትግራይ ሕዝብ ሊጠቃ ይገባል ብሎ የሚያምነው? የሚለውን ነገር ለመገምገም ፖለቲከኛ መሆን አይጠይቅም። ማንኛውም ተራ ሰው ሊረዳው ይችላል።

“በአገራችን በተለይ በአሁኑ ሰዓት ጦርነት ለማካሄድ የሚያስችል ምክንያት አለ ብዬ አላምንም። ወጣ ወጣ ያሉ የፖለቲካ ጨዋታዎች እዚህም እዚያም ሊታዩ ይችላሉ። ይህን ግን እንደ በቂ ምክንያት ወስደህ ወደ ውጊያ ለመሄድ አይገባም፣ ሊሆንም አይችልም። መንግሥት ውጊያ አይፈልግም። ሕዝብም ውጊያ አይፈልግም። በዚህ ምክንያት ውጊያ አናስብም አይኖርምም። የኤርትራ መንግሥትን ከኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ ሆነን ኢትዮጵያን እንውጋ ብሎ ሊጠራው ይችላል ብሎ ማሰብ በራሱ ኃጢያት ነው። ይህ በአገራችን ታሪክ አልታየም፣ ወደፊትም ይኖራል የሚል እምነት የለኝም።

“በአሁኑ ወቅት የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ጋር ያላትን አንዳንድ ችግሮች ለመፍታት የተለየ ድርሻ እየተጫወተ ነው። የኤርትራ መንግሥት ፍላጎት ኢትዮጵያ ከሌሎች ጋር ሰላም ሆና ከኤርትራም ጋር ያለው የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ሥራ ከፍ ብሎ በአንድነት እንጠቀማለን የሚል እንጂ፣ ውጊያን የኤርትራ ሕዝብና መንግሥት አይፈልግም። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትም አይፈልግም። በግሌ ይህ ክስ ከሁሉም ክሶች የከፋ ነው። የፌዴራል መንግሥት በትግራይ የሆነ ዕርምጃ እወስዳለሁ ካለ ራሱ ያደርገዋል። ይህን ማድረግ ምን ችግር ኖሮት ነው ሌሎችን እባካችሁ ኑ በጋራ ሆነን እንዲህ እናድርግ የምንለው? እውነት ለመናገር በዚህ ወቅት የኤርትራ መንግሥት የሰላም ኃይል መሆኑ፣ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓለም ያወቀው ጉዳይ ነው። የትኛውም ዓለም ብትሄድ የኤርትራ መንግሥት ለሰላምና ለልማት ነው የሚሠራው እምነት ነው ያለው።” (ምንጭ፥ ሪፖርተር)

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events