Dehai News

DW.com: በቁጥጥር ሥር የዋሉት በረከት ስምዖን ወደ ባሕር ዳር ተወስደዋል

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Wednesday, 23 January 2019

በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ በባሕር ዳር ከተማ እንደሚገኙ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አረጋገጠ። የአማራ ክልል የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ዝግአለ ገበየሁ "ሰዎቹ በክልላችን ውስጥ ገብተዋል በክልላችን ጊዜያዊ ማረፊያም ነው ያሉት" ብለዋል።

ዛሬ ማለዳ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) በአሁኑ ወቅት ባሕር ዳር እንደሚገኙ የአማራ ክልል የሥነ-ምግባር እና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ። የኮሚሽኑ ኃላፊ አቶ ዝግአለ ገበየሁ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በባሕር ዳር በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሁለቱ ጉምቱ ሹማምንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አረጋግጠዋል። 

አቶ ዝግአለ "ሰዎቹ በክልላችን ውስጥ ገብተዋል በክልላችን ጊዜያዊ ማረፊያም ነው ያሉት" ብለዋል። 

አቶ በረከት እና አቶ ታደሰ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በጥረት ኮርፖሬት ውስጥ ተፈጽሟል በተባለ የሐብት ብክነት ተጠርጥረው መሆኑን አቶ ዝግአለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መስራች፤ አንጋፋ ታጋይ እና ባለፉት 27 ዓመታት በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በኃላፊነት ያገለገሉት አቶ በረከት ስምኦን ከቀድሞው ብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ባለፈው ነሐሴ ወር መታገዳቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ከመንግሥታዊ ኃላፊነቶች ገሸሽ ያሉት አቶ በረከት በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።

ባለፈው ታኅሳስ ወር በመቐለ ከተማ በተደረገ የውይይት መድረክ የቀድሞው የኢሕአዴግ ጉምቱ ሰው ኢትዮጵያ ለውጭ ጣልቃ ገብነት ተጋልጣለች፤ መንግሥትም ቸልተኛ ሆኗል የሚል ነቀፋቸውን ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ የፌዴራል ፖሊስ እና የፌዴራል ጠቅላይ አቃቢ ሕግ የህዝብ ግንኙነት የስራ ሂደቶች በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመስጠት ተቆጥበዋል።

ጥረት የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ከሆነው የቀድሞው የብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የአሁኑ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ጋር ትስስር ያለው ድርጅት ነው፡፡ የድርጅቱ የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ካሳ እና የቦርዱ የቀድሞ ሰብሳቢ አቶ በረከት ስምዖን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ሆነው አገልግለዋል፡፡

የድርጅቱ ኃላፊዎች በተለያየ ጊዜ በሰጡት መግለጫ ጥረት የተቋቋመው የአሁኑ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የቀድሞው ኢህዴን በትጥቅ ትግሉ ወቅት በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ባሰባሰበው ንብረት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከ20 ዓመት በፊት የተመሠረተው ጥረት በአሁኑ ወቅት 17 በሥራ ላይ ያሉ ድርጅቶችን እንደሚያንቀሳቅስ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ዓለምነው መኮንን

እሸቴ በቀለ


Dr. Fikrejesus Amahazion at the XXIX International Rosa Luxemburg Conference in Berlin on January

Dehai Events