Dehai News

(ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት) በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አራት የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎች ሊከፈቱ ነው

Posted by: Semere Asmelash

Date: Wednesday, 16 January 2019

በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አራት የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎች ሊከፈቱ ነው

ጥር 16 ፣2019

አዲስ አበባ (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ህጋዊ የድንበር ላይ ንግድ ልውውጥ ለማስጀመርና ለመቆጣጠር አራት የንግድ ማስተላለፊያ ኬላዎችን ለመክፈት የልየታ ስራ ማጠናቀቁን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።

ከሚከፈቱት ኬላዎች መካከል ሁለቱ በዛላምበሳና ራማ የሚገኙ ናቸው።

በአገሮቹ መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ ምጣኔ ኃብትን ጨምሮ አጠቃላይ ግንኙነታቸው ተቋርጦ ለሁለት አስርት ዓመታት ቆይቷል።

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤርትራ ድንገተኛ ጉብኝት በማድረግ ግንኙነቱን ወደነበረበት ለመመለስ የሚያስችል የሰላም ስምምነት በአገሮቹ መካከል ተፈርሟል፤ ከዚሁ ጋርም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ በይፋ ተጀምሯል።

ሆኖም በአገሮቹ ዜጎች መካከል ድንበር ላይ የተጀመረው የንግድ ልውውጥ የጉምሩክ አሰራርን ጨምሮ ህጋዊ ስርዓት እንዳልተበጀለት ሲነገር ቆይቷል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም የዛልምንበሳ ድንበር፤ የጉምሩክና ተያያዥ ስርዓቶች እስኪስተካከሉ ተብሎ በቅርቡ መዘጋቱ ይታወሳል።

እናም ይህንን ሁኔታ በመለወጥ የአገሮቹን የምጣኔ ኃብታዊና የንግድ ግንኙነት ህጋዊ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ዛሬ ያስታወቀው።

በዚህም መሰረት በጉምሩክ ኮሚሽን አማካኝነት የንግድ ማስተላለፊያ (ትራንዚት) ፕሮቶኮል የተዘጋጀ ሲሆን ሰነዱም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሚመራው አገር አቀፍ ኮሚቴ መቅረቡን በኮሚሽኑ የህግ ማስከበር ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ለኢዜአ ገልፀዋል።

የንግድ ማስተላለፊያ (ትራንዚት) ፕሮቶኮሉ በቅርቡ በአገራቱ ፀድቆ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

በፕሮቶኮሉ መሰረትም በአገሮቹ መካከል የገቢና የወጪ ዕቃዎችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችሉ አራት የንግድ መተላለፊያ ኬላዎች በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ ለመክፈት ዝግጅቱ ተጠናቋል።

ከሚከፈቱት አራት የትራንዚት ኬላዎች ውስጥ ራማና ዛላምበሳ ተጠቃሽ ናቸው።

እንደ ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ማብራሪያ በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ የሚከፈቱት አራቱ ኬላዎች ጊዜያዊ ሲሆኑ የንግዱ እንቅስቃሴ ስፋትና ህገ ወጥነትን ለመቆጣጠር እንደአመቺነቱ ተጨማሪ ኬላዎች ይከፈታሉ።

ለኬላዎቹ የሚያስፈልጉ የሎጀስቲክና የሰው ኃይል ምደባ ስራ መጠናቀቁን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ ገልጸዋል።

የአገሮቹን ምጣኔ ኃብታዊ ግንኙነት ለማጠናከር የጉምሩክ ኮሚሽን በምፅዋና በአሰብ ሁለት ቢሮዎችን እንደሚከፍትም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለውን ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር በነባር ኬላዎች ላይ የማሻሻያ ስራ መሰራቱን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉጌታ አክለዋል።

በኢትዮጵያ 55 የመቆጣጠሪያ ኬላዎች ያሉ ሲሆን በመንገድ መስፋፋትና በአዳዲስ የንግድ መስመሮች መከፈት ሳቢያ ተገቢነት የሌላቸውን ኬላዎች የማንሳትና አዳዲስ ኬላዎችን የመክፈት ስራ እየተከናወነ ነው።

የጅቡቲ ወደቦችን ዋነኛው የወጪና ገቢ ንግድ ማስተናገጃ አድርጋ የምትጠቀመው ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የኤርትራ ወደቦችንም ለመጠቀም እየተዘጋጀች ነው።

ይህንን ማቀላጠፍ ይቻል ዘንድም የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በምፅዋና አሰብ ሁለት ቢሮዎችን ይከፍታል ተብሏል።

ምንጭ ፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events