Dehai News

Satenaw.com: የህወሓት መከፋፈል እና በጌታቸው ረዳ ላይ የደረሰው ዘለፋ!

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Thursday, 12 July 2018

ስዩም ተሾመ

ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት እያየለ መጥቷል። ባለፈው ሳምንት በአውስትራሊያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የሆኑት፣ የአቶ አባይ ወልዱ ባለቤት ወ/ሮ ትርፉ በሀገሪቱ እየታየ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ፣ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ከተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ እና ከደረሰው የቦንብ ፍንዳታ ጋር አያይዘው የሰጡት አስተያየት ፀረ-ለውጥ አቋም ከሚያራምዱት የህወሓት መስራቾችና አመራሮች ፍፁም የተለየ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ባወጣሁት ፅሁፍ ለመግለፅ እንደሞከርኩት፣ አስተያየቱ ከአምባሳደሯ ይልቅ በእነ አቦይ ስብሃት ቡድን የተመታው የእነ አባይ ወልዱ አቋም ነው። ከዚህ አንፃር የእነ አቦይ ስብሃት ቡድን ከዶ/ር አብይ ጋር ወደ ለየለት ግጭት እየገቡ መሆኑ እርግጥ ነው። በተለይ ከሰኔ 16/2010 በኋላ የኃይል ሚዛኑ ወደ ዶ/ር አብይ ማመዘኑን ተከትሎ የእነ አባይ ወልዱ ቡድን ወደፊት እየመጣ እንደሆነ መገመት ይቻላል።

ከአምባሳደሯ መግለጫ በመቀጠል የህወሓትን መከፋፈል በግልፅ ያጋለጠው ዶ/ር አብይ በኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ነው። በተደጋጋሚ እንደታዘብነው ዶ/ር አብይ በጎረቤት ሀገራት በሚያደርጓቸው ጉብኝቶች የአዋሳኝ ክልል ፕረዜዳንቶችን ያሳትፋሉ። ለምሳሌ ጠ/ሚኒስትሩ ኬኒያን በጎበኙበት ወቅት የኦሮሚያ ፕረዜዳንት ኦቦ ለማ መገርሳ አብረዋቸው ተጉዘዋል። በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት ደግሞ የአማራ ክልል ፕረዜዳንት አብረዋቸው መጓዛቸው ይታወሳል። በተመሳሳይ ወደ ኤርትራ ሲጓዙ ደግሞ የአፋር ክልል ፕረዜዳንት አብረው ተጉዘዋል።

ነገር ግን ከኤርትራ ጋር ሰፊ አዋሳኝ ድንበርና ችግር ያለው ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ እንደመሆኑ የክልሉ ፕረዜዳንት ከጠ/ሚ አብይ ጋር ወደ አስመራ መጓዝ ነበረባቸው። ስለዚህ የትግራይ ክልል ፕረዜዳንት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ወደ አስመራ አብሮ እንዲሄድ “ወይ አልተጋበዘም” ወይም ደግሞ “ግብዣውን አልተቀበለም’። የአፋር ክልል ፕረዜዳንት ተጋብዞ የትግራይ ክልል ካልተጋበዘ አይን ያወጣ መድሉና መገፋት ነው። ጠ/ሚ ስለ ፍቅርና ይቅርታ እየተናገሩ እንዲህ ያለ አድልዎ ያደርጋሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። በሌላ በኩል “የኢትዮ-ኤርትራ ግጭት መቋጫ ባለማግኘቱ ምክንያት የትግራይ ክልል ክፉኛ ስለተጎዳ የፌደራሉ መንግስት የተለየ ድጎማ ሊያደርግለት ይገባል” እያሉ ሲከራከሩ የነበሩት ህወሓቶች “የሰላም ስምምነቱ አካል መሆን አይፈልጉም” ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። ይሁን እንጂ፣ ጉዳዩን ለማጣራት ባደረኩት ጥረት ለማሰብ የሚከብደው ነገር በእውን መደረጉን ለመረዳት ችያለሁ።

ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አስመራ ከመሄዳቸው በፊት ለአፋርና ትግራይ ክልል ፕረዜዳንቶች አብረዋቸው እንዲጓዙ ጠይቀዋል። የአፋር ፕረዜዳንት እና የትግራይ ክልል ምክትል ፕረዜዳንት ጥያቄውን በደስታ ተቀብለው ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር አብረው ወደ አስመራ ለመጓዝ ተስማምተዋል። የትግራይ ክልል ም/ፕረዜዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ወደ አስመራ ለመጓዝ ቅድመ-ዝግጅት እያደረጉ ባሉበት ወቅት አክራሪ የህወሓት ቡድን ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር አብረው እንዳይጓዙ ይከለክላቸዋል። የጠ/ሚስትሩ ልኡካን ቡድንም በጅቡቲ በኩል አድርጎ አስመራ በመግባት የሰላምና ወዳጅነት ስምምነት ተፈራረሙ። ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ከምስራቅ አፍሪካ አልፎ በመላው ዓለም መነጋገሪ አጀንዳ ሲሆን አኩርፈው የነበሩት ህወሓቶች ሳይወዱ በግድ ፈገግ ብለው ድጋፋቸውን ገለፁ።

ላለፉት 20 አመታት እነ ስዩም መስፍን እውን ማድረግ ያቃታቸውን ነገር ዶ/ር አብይ መቶ ቀን ሳይሞላው ማድረጉን ባያስደስታቸውም ከመቀበል ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም። በሁለት ሀገራት መካከል የሰላም ስምምነት በመፈረሙ ያልተደሰተ አካል ቢኖር የህወሓት ባለስልጣናት እና የጦርነት አማልዕክት ብቻ ናቸው። ዶ/ር ደብረፂዮን ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር አብሮ እንዳይሄድ መከልከሉ ህወሓቶች ምን ያህል ያረጀ-ያፈጀ አመለካከት እንዳላቸው በግልፅ ይጠቁማል።

ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም! በተለይ እንደ ጌታቸው ረዳ ላሉት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አክራሪው የህወሓት ቡድን ክልሉንና ሕዝቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይዞ እየሄደ እንደሆነ በግልፅ አሳይቷል። ስለዚህ በዶ/ር ደብረፂዮን እና ጌታቸው ረዳ የሚመራው ቡድን ራሱን ከአክራሪው ቡድን ማላቀቅና ከለውጡ ጋር መደመር ይፈልጋል። በስብሃት ነጋ እና ስዩም መስፍን የሚመራው አክራሪ ቡድን ደግሞ የለውጡን እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚታትር የቀድሞ-ስርዓት ናፋቂ ነው።

ዶ/ር ደብረፂዮን ከጠ/ሚ አብይ ጋር ወደ አስመራ እንዳይሄድ መከልከሉን ለውስጥ አዋቂዎች በራሱ አንደበት አረጋግጧል። በመሆኑም ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ ነገሮች ከመበላሸታቸው በፊት የህወሓትን አመራር ከእነ አቦይ ሰብሃት ጫና ለማላቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህ ረገድ አቶ ጌታቸው ረገዳ ከዶ/ር ደብረፂዮን ጎን በመቆሙ ምክንያት የእነ አቦይ ስብሃት ቡድን የስድብና ዛቻ ናዳ እያወረዱበት ይገኛሉ። በተለይ ደግሞ አቶ ጌታቸው “የራያ” አከባቢ ተወላጅ መሆኑን በመጥቀስ እየደረሰበት ያለው ዘለፋ የሚከተለው ይገኝበታል፡-

“ድሮም ከራያ ትልቅ ሰው የለም! ዓሻ እናንተ አትታመኑም! በሚስጥር የብአዴን አጀንዳ ታራምዳለህ! ለራሳችን የፖለቲካ ጥቅም ስንል የቀጠርንህ መሆንህን አትርሳ! እንደ ትግራዋይ “አክት” አታድርግ!”

በአጠቃላይ ህወሓት ራሱን ለማዳን እና ለማጥፋት በሚጣጣሩ ቡድኖች ለሁለት ተከፍሏል።


7ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 7 - ERi-TV Documentary

Dehai Events