Dehai News

Dahabshiil long banner 728x90
Eritrea for mobile viewing

Goolgule.com: “ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ድንበር የለም” – ህወሓት የትግራይን ሕዝብ የሚያስትበት ቅስት ሲሰበር

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Monday, 09 July 2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና አብረዋቸው የተጓዙ የኢትዮጵያ መንግሥት ልዑካን በኤርትራ የ27 ዓመታት ታሪክ የመጀመሪያ የተባለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ይህ ዓለም ከዳር እስከዳር ያዳረሰ ታላቅ ግንኙነት በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የህወሓትን ውስን አመራሮች ዕቅድና የትግራይን ህዝብ የሚያስቱበትን ቀስት ሰብሯል።

መሪዎቹ የሃገራቱን ሕዝብ የጋራ ፍላጎት፣ እኩልነትና ሉዓላዊነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ውይይት እያደረጉ መሆኑንን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገጻቸው የገለጹት ንግግሩ በተጀመረ በቅጽበት ውስጥ ነው። አቶ የማነ እንዳሉት ሁለቱ መሪዎች ፈጣንና አዎንታዊ ውጤት የሚያስመዘግብ ስምምነት ይፋ እንደሚያደርጉ ነበር ፍንጭ የሰጡት።

ይህንኑ ተከትሎ የጸብ፣ የጥላቻ ግንብ መናዱንና የ“ፍቅር ድልድይ” መዘርጋቱን ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር ተስማምተናል” ሲሉ በደማቅ ፈገግታ የተናገሩትና ያበሰሩትታላቅ ዜና “ድንበር የለም፣ ድንበር ፈርሷል” የሚለው ነው።

ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ዘመቻ የከፈተባቸው ህወሓት በትግራይ ክልላዊ መስተዳድር ስም፣ ከዚህ ታሪካዊ ጉዞና የዕርቅ ቀን አስቀድሞ ድርድሩ ግልጽነት የሌለው፣ የትግራይ ህዝብን ፍላጎት የማያስተናግድ በሚል ጥላሸት ቀብቶት መግለጫ አሰራጭቶ ነበር። ይህ ብቻ አይደለም በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ ሕዝብ እንዲነሳ በምኞት ደረጃም ቢሆን ጥሪ አስተላልፎ ነበር። በተለይም የተሟላ መረጃ እንዳያገኝ የተዘጋበትን የትግራይን ህዝብ ለማነሳሳት ያልማሰው ጉድጓድና ያልቧጠጠው የክልል አጥር አልነበረም።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ ሳይሆኑ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር “መሪዎቹ የሃገራቱን ሕዝብ የጋራ ፍላጎት፣ እኩልነትና ሉዓላዊነትን ከግምት ውስጥ ያስገባ ውይይት እየተደረገ ነው” ሲሉ ብዥታውን አከሰሙት።

ከሰዓታት ልዩነት በኋላ ራሳቸው ዐቢይ አሕመድ እንደ ፍም በሚያበራ ፈገግታ “ድንበር የለም” ሲሉ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ካሁን በኋላ የድንበር ውዝግብ እንደማይኖር ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አረጋግጠውልኛል ሲል አስተጋቡ። ኢሳያስ ራሳቸው ቃላቸው የሳቸው ስለመሆኑ አሳይተውት በማያውቁት መፍለቅለቅ አረጋገጡ።

ይህ ብቻ አይደለም። ወደብ፣ ድንበር፣ ትራንስፖርት፣ ስልክ እና ነጻ የሕዝብ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ከስምምነት መደረሱን ሲናገሩ ኢሳያስ አሁንም በጭብጨባ አረጋገጡ። ቅስቀሳው መና የቀረበት ህወሓት አድሮ ምን እንደሚል ባይታወቅም ለጊዜው የትግራይ አክቲቪስት የሚባሉትን ጨምሮ ቅርጹ ግራ የሚያጋባ ሆኗል። ህወሓት ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ እስከሚያስቸግር ድረስ ባዶ ቀርቷል።

የትግራይ ሕዝብና የአፋር ሕዝብ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ምንም ዓይነት ጸብ እንደሌለው፣ በፍቅር ጉርብትና አብሮ መኖር እንደሚፈልግ፣ ቂምና በቀል እንደሌላቸው “እመኑኝ” ሲሉ የተናገሩት ጠ/ሚ/ር ዐቢይ “ልክ እኛን እንደተቀበላችሁት ሁሉ ልባችሁን ከፈታችሁ” ሲሉ ነበር የኤርትራ ሕዝብና መንግሥት የፍቅር እጃቸውን እንዲዘረጉ የተማጸኑት።

ከጅምሩ የአልጀርሱን ስምምነት ለመቀበልና ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ አምኖ እጁን በመስቀል የተስማማው ህወሓት አድሮ ሌላ ቅስቀሳ ለማድረግ የተነሳበት አካሄድና የፖለቲካ መዛነፍ ከምን ፍርሃቻ የተነሳ እንደሆነ በርካታ አስተያየቶችና መረጃዎች እየወጡ ሲሆን ወደፊት ሁሉም ነገር ይፋ እንደሚሆን የአብዛኞች እምነት ነው።

ሃያ አራት ዓመት ሙሉ አገር በዘር መርዝ ሲያምስና ሲያፋጅ ቆይቶ ድንገት እንደ ቡሽ የተስፈነጠረው መለስ ዜናዊ ያቦካውና “ያበከተውን” ፖለቲካ በ90 ቀናት ውስጥ መስመር እያስያዙ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኤርትራ ዘልቀው በመግባት ኢሳያስን ሳይቀር ዛሬ ነጻ አውጥተዋቸዋል። በፍቅር ዝማሬ አስክረዋቸዋል። ፍቅርን ለተጠሙ እናትና አባቶች ፍቅርን አብስረዋል። ከጅምሩ ችግሩ በሕዝብ መካከል ሳይሆን በጎጥ በተደራጁ ከሃዲዎች ተጠንስሶ አስከፊ ውድመት ያስከተለ የጸብ ግንብ ዛሬ ፈርሶ የፍቅር ድልድይ ተመስርቷል።

Dm eri tv subscribe

HDRI Publishers: Book Release - ህያው ደብሪ A Book Hailed As A Game Changer in Eritrean Modern Poetry