Date: Monday, 09 July 2018
አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 9 ፣ 2018 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት ወደ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የሚመልሱ ስምምነቶችን ተፈራረሙ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተለያዩ ስምምነቶችን በዛሬው እለት ተፈራርመዋል።
የስምምነቶች መፈረምም በሃገራቱ መካከል የጥላቻን በር በመዝጋት አዲስ የትብብር ምዕራፍ እንደሚከፍት ይጠበቃል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ታሪካዊ የተባለውን ጉብኝት ለማድረግ ትናንት አስመራ መግባታቸው ይታወሳል።
በወቅቱም ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ጨምሮ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና እና የአስመራ ከተማ ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ምሽት ለክብራቸው የእራት ግብዣ አዘጋጅተው ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ለሠላምና ልማት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ድንበር በፍቅር ፈርሷል ብለዋል።