የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሁለት እጅግ ሞገደኛ ሲል በጠራቸው የስደተኛ አስተላላፊ ኤርትራዊያን ላይ ማዕቀብ ጣለ። ግለሰቦቹ በሺህ ለሚቆጠሩ ስደተኞች እንግልትና ሞት ምክንያት ናቸው ብሏል።

የጸጥታው ምክር ቤት በግለሰቦች ደረጃ እንዲህ ያለ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ይህ የመጀመርያው ነው ተብሏል።

ስደተኛ አስተላላፊ ግለሰቦች ሰፊ የደላላ መረብ እንዳላቸው ይታመናል። እነዚህ የስደተኛ አስተላላፊዎች ዋና መቀመጫቸውን ሊቢያ በማድረግ ስደተኞችን ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ የማሻገሩን ንግድ አጧጡፈውት ቆይተዋል።

ከሁለቱ ኤርትራዊያን ሌላ አራት ሊቢያዊያንም ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ይገኙበታል። ከነዚህ መሐል አንዱ ደግሞ የሊቢያ የጠፈር ጠባቂ ብርጌድ ኃላፊ ነው።

ስደተኛ አስተላላፊዎቹ በሊቢያ ያለውን አለመረጋጋት እንደ መልካም አጋጣሚ ይመለከቱታል።

በሁለቱ ኤርትራዊያን ላይ የተጣለው ማዕቀብ የጉዞ ዕቀባና ንብረታቸው እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርግ ነው።

ሐሳቡን ለተባበሩት መንግሥታት ያቀረበችው ኔዘርላንድስ እንደሆነች ተዘግቧል።

የተባበሩት መንግሥታት በግለሰቦች ደረጃ ለመወሰን ያስገደደው የሲኤንኤን ቴሌቪዥን በ2017 በሠራው አንድ ኅቡዕ ዘገባ በሊቢያ የባሪያ ንግድ እንደሚካሄድ ካጋለጠ በኋላ ነው።

በጸጥታው ምክር ቤት የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ እንደተናገሩት “ስደተኞች እንደ ባሪያ ሲሸጡ ማየት ሕሊናችንን ረብሾታል። የተባበሩት መንግሥታት ይህን ለመቀልበስ እንደሚሰራ ቃል ይገባል” ብለዋል።

ከስድስቱ ማዕቀብ ከተጣለባቸው ሰዎች ውስጥ ኤርሚያስ ግርማይ ይገኝበታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ኤርሚያስ ከሰሀራ በታች እጅግ ሞገደኛው የሰው አስተላላፊ ከበርቴዎች ቀንደኛው ነው።

ከኤርሚያስ ሌላ የአገሩ ልጅ ፍትዊ አብዱረዛቅ እና ሌሎች አራት ሊቢያዊያን ይገኙበታል።

የዓለም የስደተኛ ጉዳዮች ማኅበር እንደሚለው ባለፈው ዓመት ብቻ 3100 ሰዎች ሜዲትራኒያንን ለማቋረጥ ሲሉ ውሃ በልቷቸዋል።