Basic

Goolgule.com: “ድንቁርና እና ዘረኝነት ሲደባለቅ እሳት ነው፤ አገር ያፈርሳል”

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Wednesday, 07 August 2019

 

ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ እንዲያስፈራ ተደርጎ ተሰርቷል

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚገኙት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ሐምሌ 26/2011ዓም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋዜጠኛ ምህረት ሞገስ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል። “ድንቁርና እና ድህነት እሳት ነው፤ አገር ያቃጥላል” በሚል ርዕስ የወጣውን ቃለምልልስ ከዚህ በታች አስፍረነዋል። በዚህ ጥያቄና መልስ አቶ ኦባንግ ወሳኝ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መልሶችን ሰጥተዋል፤ ጎሰኝነትን፣ ብሔረተኝነትን፣ ኢትዮጵያዊነት፣ ወዘተ በመሳሰሉ ርዕሶች ላይ ሊነበብ የሚገባው መልሶችንና ዕምነታቸውን ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን፡– የካናዳ የትምህርት ህይወት እንዴት ነበር?

አቶ ኦቦንግ፡– ከአስተማሪዎቼ ውጪ ማንንም አላነጋግርም ነበር። በሂደት ግን ጓደኛ ለማፍራት ጥረት በማድረግ የነበረውን መገለል በማለፍ እስከቤተሰብ ድረስ ተዋወቅኩ። ጓደኛ ለማፍራት በቃሁ። ነገር ግን፤ መጀመሪያ ጓደኛዬ ሌሎች ጓደኞቹን እና ቤተሰቡን ፈርቶ ነበር። አልለቅህም ጓደኛዬ ሁን በማለቴ ሌሎቹ “ጓደኞችህ አንሆንም” ቢሉትም ከእኔ ጋር አብሮ ሆኗል። ለቤተሰቦቹም “የመጨረሻ ጥቁር ልጅ ወደ ቤት ላመጣ ነው” ሲላቸው ከማንም ብሔር ስለተወለድኩ ሳይሆን ሰው በመሆኔ ብቻ “መምጣት ይችላል” ተብዬ ተቀባይነት አግኝቼ ጓደኛ አፍርቼ ብቸኛ ከመሆን ተገላግያለሁ።

በተወለድኩበት ገጠር አቅራቢያ የማንም ብሔር ባለመኖሩ “ወንድ ልጅ ተወለደ” ተባለ። ወደ ጋምቤላ ዋና ከተማ ስሄድ የእኔ ማንነት ተለየ። ምክንያቱም በዋናው ከተማ ከመሃል አገር የመጡ የተለያዩ ብሔሮች ስላሉ “አኝዋክ” ተባልኩኝ። ከጋምቤላ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ስሄድ “የጋምቤላ ሰው” ተባልኩኝ። ካናዳ ደግሞ “አፍሪካዊ፤ ኢትዮጵያዊ” ተባልኩ። ሰው እንደአካባቢው ማንነቱ ይለወጣል። ወንድ ነኝ፤ ጥቁር ነኝ፤ መላጣ ነኝ፤ የአንድ ሰው ልጅ ነኝ፤ አባት ነኝ። የተለያየ ማንነት አለኝ።

የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ እ.ኤ.አ በ2000 ከካናዳ ወደ ጋምቤላ ስመለስ ሁሉ ነገር ከጠበቁት በታች ሆነብኝ። ምንም የተለወጠ ነገር የለም። እንደበፊቱ ሽንት ቤትም ሆነ መብራት የለም። ከ16 ዓመታት በኋላ ጋምቤላ እንደነበረች መቆየቷ ስላሳሰበኝ በራሴ የገንዘብ ርዳታ እንደማትለወጥ አምኜ “የጋምቤላ ልማት” የሚል አንድ ድርጅት አቋቋምኩ።

አዲስ ዘመን፡– ከካናዳ ከመምጣቶ በፊት እዛው አገር ምን ይሰሩ ነበር?

አቶ ኦቦንግ፡– ለካናዳ መንግስት የፖሊሲ ትንተና አካሂድ ነበር። በዩኒቨርሲቲ ውስጥም እሰራ ነበር። ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ጋምቤላን ለማየት እንጂ ለሥራ አልነበረም። ያየሁት ግን ሁሉንም ነገር ለወጠው። ለሶስት መቶ ስልሳ ሺ ህዝብ አንድ ሃኪምና አንድ ሆስፒታል ብቻ ነበር። ንፁህ ውሃ የለም። ወደ ካናዳ ስሄድ በወቅቱ ድርቅ ስለነበር ሰዎችን ለማስፈር መንገድ ይሰራ ነበር። ከዛ በኋላ ግን ምንም የተቀየረ ነገር ባለመኖሩ የልማት ድርጅቱ ተቋቋመ።

ድርጅቱ ከካናዳ መንግስት ድጋፍ ለማግኘት እና በጋምቤላ ልማት ለማምጣት ሲሆን፤ ፈቃድ ለማግኘት አዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ከነጮች ጋር አብረን ሄድን። እርዳታው የካናዳ ድጋፍ ሲሆን ማልማት የምንፈልገው ጋምቤላን ነው አልን። ምክንያቱም እዛ ንጹህ ውሃ የለም፤ ትምህርት ቤትም ሆነ ሆስፒታል ባለመኖሩ የምናለማው እዛ ነው ብንልም “ትግራይ ክልል ሄዳችሁ ለምን አታለሙም? እዛም ንፁህ ውሃ የለም” የሚል ጥያቄ ቀረበ። ጋምቤላ ማልማት ካልቻልን ወደ ካናዳ እንመለሳለን የሚል ምላሽ ሰጠን። እኔ የጋምቤላ ተወላጅ መሆኔን ስናገር፤ይቅርታ ተጠየቅኩኝ። ንግግራችን በእንግሊዝኛ ስለነበር ኢትዮጵያዊ አልመሰልኳቸውም ነበር። ከስድስት ወር በኋላ ፈቃድ አገኘን። ነገር ግን፤ እ.ኤ.አ በ2003 ጋምቤላ ላይ ግጭት ነበር።

በአኙዋክ ጭፍጨፋ ዋንኛ ተዋናይ የሆኑት ህወሓቶችና ተላላኪዎቻቸው

አዲስ ዘመን፡– ምን አይነት ግጭት ነበር?

አቶ ኦቦንግ፡- ጋምቤላ ከደቡብ ሱዳን ጋር በድንበር የሚገናኝ ሲሆን፤ በጋምቤላ አካባቢ የማሌዢያ የዘይት ካምፓኒ ነበር። የማሌዢያው ካምፓኒ ምርመራ ፈልጓል። የክልሉ መንግስት እምቢ ብሏል። ነገር ግን የመጨረሻ ውሳኔ የሚያስተላልፉት አማካሪ ተብለው የተቀመጡት ሰዎች እንጂ የክልሉ ባለስልጣናት አልነበሩም። በዚህ ላይ ባለስልጣናቱ በመወሰናቸው ከፌዴራል መንግስት ጋር መቃቃር ተፈጠረ። በሚያዚያ 2003 የጋምቤላ ክልል 44 አመራሮች ታስረው ቃሊቲ ገቡ።

ከዛ በኋላ በፌዴራል መንግስትና በክልል መንግስት መካከል ግጭት ከረረ። በኋላ ከአዲስ አበባ የሄደ የደህንነት ቡድን አባላት የሆኑ ዘጠኝ ሰዎች በማን እንደሆነ ሳይታወቅ ተገደሉ። እዛ የነበሩ የመንግስትን የፀጥታ ሃይል ሃላፊዎች የገደሉት አኙዋኮች ሳይሆኑ አይቀሩም በማለት የአጻፋ ርምጃ እንውሰድ ብለው 424 የአኙዋክ ሰዎች ተገደሉ። በኋላ ግን ችግሩን ለመሸፈን ጉዳዩ የብሔር ግጭት ነው ተባለ። ገዳዮቹም ከሌላ ቦታ የመጡ መሆናቸው ታውቋል።

በዕለቱ ብዙ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ዘንድ ስደወል እንዴት እናረጋግጥ? እያሉ ችላ አሉ። በኋላ ግን ግድያው ሲፈፀም ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ወደ አሜሪካን ውጭ ጉዳይ በመደወል በመንግስት ታጣቂዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጋምቤላ በሚባል ክልል ብዙ ሰዎች እየተገደሉ ነው ብልም ስልኩን ያነሳችው ሴት “አፍሪካ ውስጥ ሁሌም ብዙ ሰው ይሞታል” ብላ ስልኩን ዘጋች።

ሁለቱም ለፍርድ ሳይቀርቡ ሞተዋል

ከሶስት ደቂቃ በኋላ ደውዬ “ከተገደሉት መሃከል የአሜሪካን ፓስፖርት የያዙ የአሜሪካ ዜጎች አሉ፤ ስላት ግን፤ “እነማን ናቸው? መች ወደዛ መጡ? አሜሪካን የት አካባቢ ይኖሩ ነበር?” ብላ ተከታታይ ጥያቄዎችን ስታቀርብ በኋላ ልደውል ብላትም አይ በየትኛው ቁጥር አገኝሃለሁ? እኔ ልደውልልህ ብላለች። ሶስት አሜሪካዊ በዛ አካባቢ መኖራቸውን ሙሉ መረጃ በማግኘቴ ስትደውል ተናገርኩ። ወዲያው ከአዲስ አበባ 16 የአሜሪካን የደህንነት ሰዎች አሜሪካውያኑን ለማዳን ወደ ጋምቤላ መጡ።

ፈጣሪ የሰው ልጆችን እኩል ቢፈጥርም፤ የሰዎች ህይወት በፓስፖርት ተመዘነ። ሰዎቹ ምንም እንኳን የጋምቤላ ተወላጅ ጥቁር ቢሆንም፤ የአሜሪካ ፓስፖርት ስላላቸው የእነርሱ ህይወት የተለየ ሆነ። ወዲያው የአሜሪካ መንግስት የውጭ ዜጎች ወደ ጋምቤላ መሄድ የለባቸውም፤ የደህንነት ችግር አለ አለ። ዱሪዬዎች የፈጠሩት ችግር ነው። የብሔር ግጭት ነው ተብሎ ቢዋሽም የወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት ኦኬሎ አልዋሽም በማለቱ ሁሉ ነገር ታወቀ።

አዲስ ዘመን፡– ይህ ሁሉ የተፈጠረው ጋምቤላን ለማልማት በመጡበት ወቅት ነው?

አቶ ኦቦንግ፡– አዎ! በትንሿ አውሮፕላን ወደ ደቡብ ሱዳን ሄድኩ። ከዛ ወደ ኬንያ፤ ከኬንያ ወደ ኖርዌይ አቀናሁ። ከዛ በኋላ ሁሉ ነገር ገባኝ። ከሁለት መቶ ሺ በላይ አበሾች በአሜሪካ ዋሽንግተን ላይ በመኖራቸው እዛው ከነበሩ ስድስት የጋምቤላ ልጆች ጋር በመተባበር ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን በመሞታቸው ለመቃወም ሰልፍ እንውጣ በማለት ለአንድ ሳምንት በበራሪ ወረቀት፤ በሬዲዮ ጭምር ጥሪ ቀረበ። በዕለቱ ከ200 ሺ ኢትዮጵያውን ውስጥ ሶስት ሰው ብቻ ሰልፉ ላይ ተገኘ። ከስድስቱ ጋምቤላዎች ጋር የነበረው ዘጠኝ ሰው ብቻ ነበር። ለካ እኩል ኢትዮጵያዊ አይደለንም በማለት ልባችን አዘነ።

አዲስ ዘመን፡– ታዲያ ከዚህ ሁሉ በኋላ እንዴት ኢትዮጵያዊ ነን አሉ?

አቶ ኦቦንግ፡– ልክ ነው። በወቅቱ እኔ ብቻ ሳልሆን በቦታው ያሉት የጋምቤላ ልጆች በሙሉ እጅግ በጣም አዘኑ። ስለዚህ ራሳችን መደራጀት አለብን። ከኢትዮጵያ ኋላ ቀር የሆነው ጋምቤላ ነው። ይህ የሆነው በድንገት አይደለም። ታስቦበት ነው። ጋምቤላ ለም መሬት አለ። በትክክል በመሬቱ ማልማት ቢቻል ኢትዮጵያን ቀርቶ ሌላውንም መመገብ ይቻላል። ነገር ግን በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግስት ግድ የለውም ተባባልን። ስለዚህ ለአኙዋኮች ፍትህ የሚባል ተቋም አቋቋምን። ነገር ግን አኙዋኮች 100 ሺ እንኳን አይሞሉም። ወደ ዓለም አቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች ሄድን።

ከግፍ ከተጨፈፉት 424 አኙዋኮች ጥቂቶቹ

የአሜሪካን ባለስልጣናት ጋብዘውኝ ስሄድ ግን አንድ ነገር ተማርኩ። ታክሲ ስሳፈር ሹፌሩ ኢትዮጵያዊ ነበር። ወሬ ስንጀምር በፍፁም ኢትዮጵያዊ ነው ብሎ መገመት አልቻለም። ታዲያስ እንዴት ነህ? አካም ነጋ? ደሃን ’ዩ? ብዬ ሳናግረው ሊያምን አልቻለም። እኛ በኢትዮጵያ ያልታወቅን ሰዎች ብቻችንን ብንታገል ለውጥ አይመጣም። መጀመሪያ መላው ኢትዮጵያዊ ፍትህ ማግኘት ካልቻለ አኙዋክ ብቻውን ፍትህ ሊያገኝ አይችልም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ።

ስለዚህ ለድርጅቱ አባላት ስብሰባ በመጥራት እኛ የምንታገለው ለአኙዋክ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን ነው አልኩ። አኙዋኮቹ በሰልፉ ቅር ስለተሰኙ “አበድክ እንዴ?” አሉ። ብዙ ክርክር ተደርጎ በድምፅ ብልጫ ሲባል፤ የድርጅቱ አባል የነበሩት ነጮቹ ደገፉኝ። ከዛ በኋላ ከ11 ዓመት በፊት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚል ድርጅት ተፈጠረ።

ትልቁ የኢትዮጵያ ችግር የአመለካከት ነው። ይህን ነገር ለመለወጥ ትምህርት ያስፈልጋል። ከብሔር፤ ከቋንቋ ይልቅ የሰው ልጅ ክቡር ነው። ለመተማመን እንነጋገር፤ ኦሮሞ ወይም አማራ ብቻቸውን ከሚነጋገሩ እርስ በእርሳቸው ይነጋገሩ። ሁላችንም እንነጋገር።

አዲስ ዘመን፡– መጀመሪያ ያሉት የልማት ተግባር ቀረ?

የጋምቤላ ልማት ማኅበር፤ አቶ ኦባንግ በስተግራ የሚታዩት ናቸው

አቶ ኦቦንግ፡- አዎ! ቀረ። ምክንያቱም በዛ ጊዜ እኔ የምሰራላቸው ሰዎች እየሞቱ ናቸው። ቦታው ጥሩ አልነበረም። ለመስራት የተዘጋጁ ልጆችም ሞቱ። ከዛም በ1997 ከነበረው ምርጫ ጋር ተያይዞ ቅንጅት ወደ ምርጫው በመምጣቱ የቅንጅት አመራሮች በመታሰራቸው እና አዲስ አበባ የሞቱ ሰዎች ስለነበሩ በአሜሪካ ኮንግረስ ላይ ተጋበዝኩኝ። ምክንያቱ ደግሞ ከሁለት ዓመት በፊት አኙዋክ ውስጥ የተገደሉትን ሰዎች አስመልክቶ እንድናገር ነበር።

ስለዚህ መድረኩን አገኘሁ። ብዙ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ‘ራሳችንን እናክብር፤ የመጣሁት ስለአኙዋክ ብቻ ሳይሆን ስለመላው ኢትዮጵያ ነው’ አልኩ። አጥፊው አንድ ብሔር ብቻ ሳይሆን ከንባታውም፤ ኦሮሞውም፤ አማራውም፤ ሌላውም ጭምር ነው ስል ሁሉም አወቀኝ። ነገር ግን በሶማሌ ስም ስብሰባ ሲጠራ አዳራሹ ይሞላል፤ በአፋር፣ በኦሮሞም ሆነ በሌላው ብሔር ስም ስብሰባ ሲጠራ አዳራሹ ይሞላል። በኢትዮጵያ ስም ሲባል ግን አንድም ሰው አይመጣም። ሰዎች በብሔር ተከፋፍለዋል። ስለዚህ ይህን ነገር ለመስበር ሌሎችንም ኢትዮጵያውያን በማሰባሰብ ድርጅቱን በድጋሚ አቋቋምን።

“ሰው መሆን በቂ ነው” የሚለውን አስተሳሰብ ብዙ ሰው ይወደዋል። “አንድ ሰው ብቻውን ነፃ መሆን አይችልም። አንድነት ያስፈልጋል” የሚለውን ሃሳብ ብዙ ሰው ይደግፈዋል። ከዛ ሥራ ጀመርን በ2010 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ለሩጫ ጃፓን ሄደው የታሰሩ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ። ቪዛቸው ቀን ስላለፈበት ታሥረው ነበር። እስከ ጃፓን ድረስ በመሄድ ከውጭ ጉዳዩ ጋር በመነጋገር ወደታሰሩበት ጫካ ድረስ ሄጄ አይቼ እንዲፈቱ አደረግኩ። ሜክሲኮ፣ ጓቲማላ፣ እስራኤል፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካም ሄድኩ።

አዲስ ዘመን፡– ሄደው ምን አደረጉ፤ የሄዱት ድርጅትዎን በመወከል ነበር?

አቶ ኦቦንግ፡– አዎ! ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን የታሰሩት እንዲፈቱ ስናደርግ ነበር። ሊቢያም ሄጄ ብዙ ሰዎች ተፈትተዋል።

አዲስ ዘመን፡– ያስፈታችኋቸው ሰዎች ቁጥር ስንት ነበር?

አቶ ኦቦንግ፡- የሄድነው ወደ 21 አገር ነው። በአንዳንድ ነገር ላይ ደግሞ የበለጠ ስኬታማ ነበርን። አንዲት ኢትዮጵያዊ ቤይሩት ሄዳ በአሜሪካዊ ቀጣሪዋ በመደፈሯ ጃፓን እንድትሄድ ሲደረግ ተከታትለን ልጅቷን በማማከርና በመደገፍ በአሜሪካ አምባሳደር እንዲታወቅ በማድረግ ምርመራ ተደርጎ፤ ተረጋግጦ አሜሪካ እንድትሄድ ተደረገ። በኋላም አሜሪካን ሄዳ በመክሰሷ ከሁለት ዓመት በኋላ ፍርድ ቤት ደርሳ ሶስት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ ተከፈላት።

በአቶ ኦባንግ አማካኝነት ከሜክሲኮ እስር ቤት የተፈቱት

በየመንም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሮ ጥቃት የተፈፀመባት ልጅ ወደ ኢትዮጵያ ብትመጣም ምርመራ ተደርጎ ሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተከፈላት። በእስራኤል ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ኢትዮጵያውያን እየተሰቃዩ ነው ተብሎ መረጃ ሲደርሰን በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት ተችሏል። ሜክሲኮም በመሄድ ለውጥ መጥቷል።

አሁን ግን አገሪቷ ውስጥ ሰላም በመስፈኑ መጀመሪያ በአስተሳሰብ ላይ እንስራ በሚል ወደ ኢትዮጵያ መጥተናል። ባለፉት ዓመታት ለመምራት በሚል የተሰራው የመከፋፈል ሥራ ችግር ፈጥሯል። በልጅነታችን የጓደኛችንን ብሔር አንጠይቅም ነበር። በብዛት ያስተማሩን ሰዎች የመሃል አገር ሰዎች ናቸው። ብሔራቸውን አናውቅም ነበር። የምንለው “እውቀት እያስጨበጡን ነው” ብቻ ነው።

ከአንደኛ እስከ 4ኛ ክፍል ስማር አጠገቤ የነበረው ልጅ ብሔሩን አላውቀውም ነበር። አባቱ ከመሃል አገር መጥቶ ሱቅ የነበረው ሰው ነው። አሁን ሳስፈልገው ያለው ወልቂጤ ነው። አፈላልጌ ሳገኘው “ጉራጌ ነኝ” አለኝ። መቼ ጉራጌ ሆንክ? አልኩት ያን ጊዜ ጉራጌ ነበርክ እንዴ? ስለው አላውቅም ነበር አለ። አሁን በተደረገ ጥናት ከ110 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ውስጥ 30 ሚሊዮን የሚሆኑት ከሁለት በላይ ብሔር የተወለዱ ናቸው። አገር ለመምራት የራሳቸውን ፍላጎት በመጫን ሰብአዊነትን ረስተውታል።

የዚህ ምክንያቱ ፖለቲካ በአገራችን ውስጥ እንጀራ ነው። ይህ ደግሞ አደገኛ ነው። ሁሌም የበላይ መሆን ያለበት ህግ እንጂ ብሔር መሆን የለበትም። በዓለም ድንበር በብሔር እንዲከፋፈል የተደረገው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። የሰው ልጅ በክልል አይታጠርም፤ እንዳይጠፋ በክልል የሚታጠረው አውሬ ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፡– በእርግጥ ሰው በብሔሩ ሳይሆን በሰውነቱ እንዲከበር ማድረግ እንችላለን?

አቶ ኦቦንግ፡- ሰዎች በብሔር እንዲያስቡ የተሰራውን ያህል እኛ ደግሞ ሰዎች ሰው በመሆናቸው ሰብአዊነትን እንዲያስቡ ማድረግ እንችላለን። ለምሳሌ፤- ህገመንግስት መቀየር ካለበት መቀየር አለበት። የትምህርት ሥርዓታችን መቀየር አለበት። ስንወለድ ሰዎች ብቻ መሆናችንን ማሳወቅ ይቻላል። እንዲያውም ከብሔርተኝት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን መስበክ ቀላል ነው።

ኢትዮጵያዊነት ስሙ ሲጠራ ክፉ ስሜት እንዲሰማ ተብሎ ህፃን ልጅ ጅብ ሲባል እንደሚፈራው ሁሉ ኢትዮጵያ የሚለው መጠሪያ እንዲያስፈራ ተደርጎ ተሰርቷል። ስለዚህ በየእምነት ተቋማት፣ በየትምህርት ቤትም ሆነ በየትኛውም ቦታ ስለኢትዮጵያዊነት መነገር አለበት። በተረፈ አንድ ሰው የብሔር ማንነት ብቻ አይደለም። የፆታ (ወንድ፣ ሴት)፤ የሃይማኖት፣ የወላጅነት፣ የሙያ እና ሌሎች ማንነቶችም አሉት። ይሄን መንገር በራሱ ለውጥ ያመጣል።

ማንም ሰው ልጁን ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚልከው እንዲሞት ሳይሆን ዲግሪ እንዲይዝለት ነው። ይህ ማንም ቢሆን በልጁ ላይ እንዲፈፀም አይፈልግም። በተጨማሪ፤ አንድ ልጅ ሲሞት ‘ሰው ሞተ’ ሳይሆን ‘የዚህ ብሄር ልጅ ሞተ’ ይባላል። ይህ ትክክል አይደለም። እኛ ትምህርት ሚኒስቴርን፣ የሰላም ሚኒስቴርን ምክትል እና ጠቅላይ ሚኒስትሮችንም አነጋግረናል።

በተረፈ የነበረው ሴራ ያለንን ሀብት መጠኑን ባለማወቅ የተፈፀመ ነው። ቢገባን ለሌሎች የሚካፈል ሀብት አለን። ስለዚህ ሀብቱን በአግባቡ ተጠቅመን ለማደግ ክፍፍላችንን እናቁም።

በአንድ ቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ እንደተተከለው ሁሉ በመቶ ሚሊዮኑም ህዝብ ውስጥ በዘመቻ የፍቅር፤ የሰብአዊነት ችግኝ እንትከል። ክብር ለሰው እንጂ ለብሔር መሰጠት የለበትም። በምኒልክም ሆነ በኃይለስላሴ ጊዜ የነበረው የውጭ ጠላት ነው። አሁን ግን ጠላት የሆንነው ራሳችን ለራሳችን ነው። እያንዳንዳችን በመገናኛ ብዙሃን፣ በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን በጋዜጣም በደንብ መሰራት አለበት። ደርግ በዘመቻ መሰረተ ትምህርት ብሎ በመስራቱ እናቶቻችን መፈረም ችለዋል።

አዲስ ዘመን፡– የብሔር ፖለቲካ ይቅር ብለን ከተነሳን አይከብድም? ብዙዎች ደስ አይላቸውም?

አቶ ኦቦንግ፡– ደስ የማይላቸው ለምንድን ነው? እንጀራቸው ስለሆነ ነው። ክልል ክልል የሚሉ ሰዎች ለራሳቸው ጥቅም ነው። ቀይ መብራት ከበራ መኪና አይሄድም ህግ ነው ግዴታ ነው። ህግ ካለ ወደደም ጠላ ማክበር ግዴታ ነው።

አዲስ ዘመን፡– አሁን አማራነት ወይም ኦሮሞነትም ሆነ ጋምቤላነት ተገንብቷል። ያንን ማፍረስ ቀላል ነው። በዛ ላይ በመደፍጠጥ እንጨቆናለን የሚሉ አሉ?

አቶ ኦቦንግ፡- ተጨቁነናል ብሎ ነገር ምንድን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጨቆነ ብሔር የለም። ህገመንግስት መለወጥ የለበትም የሚሉም አሉ። ራሳችንን አገራችንን ለማዳን ህገመንግስት መለወጥ ካለበት መለወጥ አለበት። እኛ እንደሶሪያ፣ እንደሊቢያ፣ እንደየመን እና እንደኢራቅ እንዳንሆን ከተፈለገ ከዚህ በፊት የተሰራውን ሥራ መቀየር ያስፈልጋል። ራሱን ያልወደደ ሌላውን መውደድ አይችልም።

ራሱን ያላከበረ ሌላውን አያከብርም። ህዝቦች ብሎ ነገር የለም። ህዝብ ነው። የትም አገር ቢኬድ የብሔር መብት የሚባል ነገር የለም። የሚባለው የሰው መብት ነው። በዛ ላይ መፈረጅ አለ። አማራ ጨቋኝ ነው ይባላል። አፋር ነፃ አውጪ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ፣ የአማራ ነፃ አውጪ ማን ነው ከማን ነፃ የሚያወጣው? ተጨቋኝ ከተባለ ሁሉም ህዝብ ተጨቋኝ ነው።

በልዩነት ውስጥ አንድነት የሚለው አገላለፅ ልክ አይደለም። መባል ያለበት በአንድነት ውስጥ ልዩነት ነው። አንድ ሰው ሰው ይባላል። ከዛም በውስጡ እጅ፣ እግር፣ ጭንቅላት፣ አይን እያለ ይከፋፈላል። በሙሉ ሲጠቃለል አንድ ሰው ይሆናል። ኢትዮጵያም እንደዛው በውስጧ የተለያዩ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እና ሌላም እየተባለ የተለያየ አካል አለ። ስለዚህ በልዩነት ውስጥ አንድነት ሳይሆን በአንድነት ውስጥ ልዩነት ነው ያለው። ይህ በህገመንግስት ውስጥ ተቀምጧል። ይህ ልክ አይደለም።

ድሬዳዋ ውስጥ ብዙ አማራዎች አሉ። ነገር ግን የአማራ ድምፅ የለም። የስልጣን ክፍፍሉም 40/40/20 ሶማሌ፣ ኦሮሞ እየተባለ ተከፋፍሏል። ስልጣንና ሥራ እንዴት በብሔር ይከፋፈላል? መሆን ያለበት በብቃት ነው። ይህ አካሄድ ትክክል አለመሆኑን ማመን፤ መናገርና ማስተካከል ይገባል።

ሩዋንዳ ሄጄ ነበር። በሩዋንዳ አንድ ሰው ብሔሩ ሲጠየቅ የሚሰጠው መልስ ‘የሰው ልጅ ነኝ’ የሚል ነው። የሰው ልጅ ነኝ ለማለት እንደነሱ አንድ ሚሊዮን ህዝብ እስኪያልቅብን መጠበቅ አለበት? የፖለቲካ ፓርቲ በብሔር ከመቋቋሙ አልፎ፤ ቤተዕምነት እና ባንክ ሳይቀር በብሔር ስም ተቋቁሟል። ይህ አደገኛ ነው። አንዱ ነዋሪ ሌላው ሰፋሪ እየተባለ የሚነገረው ትክክል አይደለም። አሜሪካ ሄደን ስንኖር ከሌላው ጋር አንድ አይነት ዜጋ ሆነን ፓስፖርት እናገኛለን። ደግሞ ነዋሪ የተባለውም አያቱ ወይ ቅድመ አያቱ ከሆነ ቦታ የመጡ ናቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰፋሪ ነው። ክፍፍል መቆም አለበት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ችግኝ ተከላውን በዘመቻ እንዳደረጉት ችግኙን የሚጠቀምበት ኢትዮጵያዊ እንዲኖር የሰብአዊነት እና የፍቅር ዘመቻ ያስፈልጋል። በጣም አደገኛው ነገር ድንቁርና እና ዘረኝነት ሲደባለቅ እሳት ነው፤ አገር ያፈርሳል። ድንቁርና ስለሰው ልጅ ስለሰብአዊነት አለማወቅ ነው። ዘረኝነት ውስጥ በጥላቻ መሞላት አለ። ዶሮ ወጥ ለመስራት በርበሬና ሽንኩርት፤ ቂቤና ዘይት እንደሚሟላለት ሁሉ እርስ በእርስ ለመተላለቅ መሰረታዊ አቅርቦቶች ተሟልተዋል። ይህን ለማጥፋት ስለሰብዕና ማስተማር ይገባል። ማንም ቢሆን ለልጁ የሚመኘው ሰላምና ዕድገት ነው። ለራሳችን እሱን ተመኝተን የጎረቤታችንን ልጅ መግደል፤ ማፈናቀል ትክክል አይደለም።

አንድ ሰው ሥራ ማግኘት ያለበት በብሔሩ መሆን የለበትም። ፈጣሪ የሰጠን 86 ብሔር አለ። ይህ ትክክል ነው። ውበት ነው። ይህ ውበት መፍረስ የለበትም፤ ለትውልድ መተላለፍ አለበት። አይናቸው የተንሻፈፉ ደንቆሮዎች የሌላው ብሔር ውበት አይታያቸውም፤ ውስጣቸው በጥቅም ስለተያያዘ ነው። ድሃ ሰው እንደጅብ ዘመዱን ይበላል። አይምሮውና አይኑ አይገናኝም። ስለጎዳና ተዳዳሪዎች፤ በአረብ አገር ስለሚሰቃዩ ዜጎች ማሰብ ይገባል። ብዙ ለዓለም የሚሆኑ ገጣሚዎች፤ ብዙ ያልተሰሩ ጥሩ የባህል መድሃኒቶች አሉ፤ በዛ መጠቀም አለብን እስከመች ወደ ኋላ ቀርተን እንኖራለን?

አሁን እየከፋፈለ ያለው ሰው ከ30 እና ከ40 ዓመት በኋላ በህይወት አይኖርም። ጥፋት ለየትኛው ዕድሜ ነው? ውስጣችንና በልባችን ውስጥ ያለውን ማስተካከል አለብን። ይህን ማሰብ ካልቻልን መንግስት ወንድሞቻችሁን አትግደሉ እቀጣለሁ ካለ ሁሉም መስተካከል አለበት። ግማሹ ወንድ በጫት፤ ሌላው በቃና፤ ማንበብ ቀርቶ መደንዘዝ በዝቷል።

 አዲስ ዘመን፡– ዓለም የሚመራው በመከፋፈል ማለትም በፌዴራሊዝም ነው። ክፍፍሉ ታዲያ እንዴት ይሁን?

አቶ ኦቦንግ፡– የፌዴራሊዝም አወቃቀሩ በመልከአ ምድር አቀማመጥ ይሁን። ክልል 1 እንደማለት ትግራይ፣ አማራ እየተባለ ነው። ሶማሌ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ያላደጉ ይባላል። ይህ ለምን ይሆናል። በነገራችን ላይ ጋምቤላ ብሔር አይደለም መልክአ ምድር ነው። ማንም ሰው ሊኖርበት ይችላል። ሶስት ሚሊዮን ህዝብ የተፈናቀለው በድንቁርና እና በዘረኝነት ፖለቲካ ነው። ደቡብ ክልል ደግሞ የተከፈለው በአቅጣጫ ነው። የፌዴራሊዝም አወቃቀሩ ራሱ ድብልቅልቅ ያለ ነው። መንግስት እውነት ሃቀኛ ከሆነ ህዝቡ በሰላም እንዲኖር ህገመንግስቱን ማሻሻል አለበት።

ከዚህ በኋላ ያለአግባብ ሰው መፈናቀል መሞት የለበትም። ሁሉም በሰላም እንዲኖር መሰራት አለበት። ይህንን ህዝብ መደገፉ አይቀርም። ኢትዮጵያውያን በህግ አምላክ ሲባል የሚሰሙ ናቸው። ነገር ግን ህጉን ማስተካከል ይገባል፤ ከዛ ደግሞ ህግ ይከበር። ስለብሔር ከምናስብ ለሙን መሬት በአገር ፍቅር ስሜት ከሰራንበት ምስራቅ አፍሪካን መመገብ ይቻላል። ነገር ግን፤ ህግ አይሻሻልም ማለት ሆዳምነት ነው።

የአገራችንን የፍቅር እሴት በማሳደግ በዘመቻ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል። መንግስት በዚህ ላይ ማሰብ አለበት። ኢትዮጵያውያን ከሌላው ዓለም በተለየ መልኩ ከአፋቸው ላይ ነጥቀው ያጎርሳሉ። ማንም አገር የማጉረስ ባህል የለውም። ኢትዮጵያውያን ልዩ ናቸው። ይህን ማጉላት አለብን። የሰላም የፍቅር የአንድነት መንገድ መሰራት አለበት።

አዲስ ዘመን፡– አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሚለው ድርጅታችሁ ከመንግስት ባሻገር እናንተስ በቀጣይ ምን ትሰራላችሁ?

አቶ ኦቦንግ፡- ዕቅድ አውጥተናል። የወጣቶችን አስተሳሰብ ለማሳደግ እንሰራለን። የሃይማኖት አባቶች እና ሽማግሌዎች እንዲሁም በትምህርት ቤት አካባቢ ያሉትን የእኛ ልጆች አስተሳሰባቸው ላይ ለመስራት አስበናል። ኢትዮጵያዊነት አንድ ያደረገን ስም መሆኑን በማሳወቅ የሶማሌ ልጅ ትግራይ ሄዶ እንዲያይ፤ የደቡብ ልጅ ኦሮሚያ ሄዶ እንዲያይ የጋምቤላ ልጅ ጎንደር ሄዶ ፋሲልን እንዲያይ በማድረግ ኢትዮጵያ ያሏትን ታሪኮች እንዲያውቁ ለማድረግ አቅደናል።

የአክሱምን ሃውልት እንዲያዩ አስበናል። ትኩረታችን በዚህ ላይ ነው። ከዚህ በፊት የሚያጋባው ፍቅር ነበር። ሽማግሌ ዘር አይጠይቅም ነበር። አሁን ሽማግሌ ተዉ ከማለት ይልቅ በሉ ፍለጡ እስከማለት ደርሷል።

በብዛት ኢትዮጵያውያን መፍትሄ የሚያገኙት ዛፍ ስር ነው። እስከዛሬ ያቆየን የመንግስት ፍርድ ቤት ሳይሆን በዛፍ ጥላ ስር የሚሰጥ ፍርድ ነበር። ሽማግሌዎች ወደዛ እንዲመጡ እንሰራለን።

አዲስ ዘመን፡– ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን!

አቶ ኦቦንግ፡– እኛም በጣም እናመሰግናለን!


EmbassyMedia - ራብዓይ ግንባር!

Dehai Events