Basic

Goolgule.com: ከኦነግ የተገነጠለው ኦዴግ ከኦዴፓ ጋር መቀላቀል ኢህአዴግን እና ግንቦት 7ን ወዴት ያመራቸዋል?

Posted by: Berhane.Habtemariam59@web.de

Date: Friday, 30 November 2018

“አዲሲቷን ኢትዮጵያ በጋራ ለመመስረት ተነስተናል። የቀድሞው የትግል ስልት አያዋጣም” በማለት “የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር” (ኦዴግ) ODF የሚባል አዲስ ግንባር መጋቢት 22፤2005ዓም (ማርች 31/2013) ያቋቋሙት የቀድሞው የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች የቀድሞውን ኦህዴድ የአሁኑን ኦዴፓን ተቀላቅለዋል። ከኦነግ ተገንጥሎ ኦዴግ የሆነው የሌንጮ ለታ ፓርቲ ኦዴፓን መቀላቀሉና በኢህአዴግና በግንቦት 7 ላይ የሚያስከትለው የፖለቲካ ተጽዕኖ ገና አልጠራም። ከዳውድ ኢብሣ ኦነግ ጋር እቀላቀላለሁ ያለው የመረራ ጉዲና ኦፌኮም መጨረሻው አልታወቀም።

የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ከብሪታንያ፣ ከስዊትዘርላንድ፣ ከካናዳ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከጀርመንና ከተለያዩ አገራት የተሰባሰቡ ቁጥራቸው 400 የሚጠጋ ተሰብሳቢዎች ባካሄዱት ውይይት ላይ ስለ ኦዴግ ማብራሪያ የሰጡት ሌንጮ አስፈላጊ የተባሉ ጥያቄዎች ተጠይቀው ነበር። ኢትዮጵያን “ኢምፔሪያሊዝም፣ ቅኝ ገዢና ጠላት” አድርገው በመሳል ጥያቄ የሰነዘሩትን ጨምሮ ስለ ቀጣዩ ትግል ትግበራና ስለ ኦሮሞ ህዝብ ነጻነት መከበር በስፋት ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ ሌንጮ ለታ አስገራሚ መልስ ሰንዝረው ነበር።

“ያለፈውን በመውቀስ የትም አንደርስም። አሁን ማየትና ማሰብ ያለብን ወደፊት ነው። ሌሎች ወገኖችን አግልለን ብንታገል የትም አንደርስም። ያለፈው የትግል መንገድ ስህተት ነበር” ብለዋል። ስለ ኦሮሞ ህዝብ ነጻነት መከበር ሲናገሩ “የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ካልተከበረ የኦሮሞ መብት ብቻውን ሊከበር አይችልም” በማለት መመለሳቸውን ለማወቅ ተችሏል።

የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር ከፍተኛ አመራርና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ አዲስ ያቋቋሙትን ድርጅት ይዘው አዲስ አበባ እንደሚገቡ የዚያን ጊዜ አስረግጠው ተናግረው የነበሩት አቶ ሌንጮ ድርጅታቸው ኢትዮጵያ ገብቶ ለመታገል መወሰኑ ለምን ወሬ እንደሚባል እንዳልገባቸውም የዚያን ጊዜ አመላክተው ነበር።

ቀጥሎም በ2006ዓም ጥር 5 ቀን ከጀርመን ድምጽ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት አቶ ሌንጮ “ኖርዌይ ተቀምጠን ምን እናደርጋለን? ሃገር ቤት ገብተን እንታገላለን” ሲሉ ወደ አገር ቤት ለመመለስ መወሰናቸውን ግልጽ አድርገዋል። “ይሳካል?” በማለት ጠያቂው ላቀረበው “ይሳካል አይሳካም ተብሎ ወደ ትግል አይገባም” በማለት አቶ ሌንጮ ማምረራቸውን በሚያሳብቅ ሁኔታ መልስ መስጠታቸው ይታወሳል።

በቀጣይም ወደ አገርቤት ከገቡ በኋላ ህወሓት/ኢህአዴግ በጠበቁትና በፈለጉት ልክ አላንቀሳቅስ ስላላቸው ጥለው ወጥተው ነበር። የዛሬ ሰባት ወር አካባቢ እንቁላሉን ከውስጥ በሰበሩት የለውጥ ኃይሎች በውጭ አገራት ለሚገኙት ተቃዋሚ ኃይሎች በሙሉ ባቀረቡት ጥሪ መሠረት ኦዴግ አዲስ አበባ ገብቷል

ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት አገባቡ አብሮት ጥምረት ከፈጠረው አርበኞች ግንቦት 7 በፊት በመሆኑ ለወደፊቱ ከግንቦት 7 ጋር የሚኖረው ግንኙነት እንዴት እንደሚሆን የድርጅቱ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅቱ ቃል አቀባይ አቶ ሌንጮ ባቲ ቢቢሲ አማርኛ ለጠየቃቸው ምላሽ ሰጥተው ነበር። “ለሃገር ግንባታ እና ዴሞክራሲ ዕድገት ከሚሠራ ማንኛውም ፓርቲም ሆነ ግለሰብ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን። ከማንኛውም ቡድን ጋር መሥራታችን ይቀጥላል። አቋማችንን የሚቀይር ነገር የለም” ብለዋል።

ዛሬ ህዳር 19፣ 2011 የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ተዋህደው መቀጠል የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። ፋና እንደዘገበው ስምምነቱን የኦዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳና የኦዴግ ሊቀ መንበር አቶ ሌንጮ ለታ ተፈራርመዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ ሁለቱ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የራሳቸው ታሪክና አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ተበታትኖ መጓዙ ለህዝቡም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ አድካሚ በመሆኑም እንደየፓርቲዎቹ የአስተሳሰብ ቀረቤታ በመጣመርና በመዋሃድ ለሃገር ግንባታ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት። የፓርቲዎቹን ውህደት ህዝቡ ሲጠይቅ እንደነበር ያነሱት አቶ ለማ፥ ፓርቲዎቹም ተወያይተው ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን አውስተዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያን ፌዴራሊያዊ ስርዓት ዴሞክራሲያዊ በማድረግ የተረጋጋና ሰላማዊ የአፍሪካ ቀንድን መገንባት እንደሚቻል ገልጸዋል። አቶ ሌንጮ አያይዘውም የኦሮሞ አንድ መሆን ለሃገር ግንባታም ቢሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ነው ያሉት።

የኦዴፓ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ስምምነቱን አስመልከቶ በሰጡት መግለጫ፥ ሁለቱ ፓርቲዎች የኦሮሞ ህዝብ አንድ እንዲሆኑ ባቀረበላቸው ጥሪ መሰረት በዛሬው እለት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የውህደት የመግባቢያ ስምምነት እንደተፈራረሙ አንስተዋል። አያይዘውም ኦዴፓ ከኦዴግ ጋር የህገ ደንብ፣ የስትራቴጅ እና የፕሮግራም ልዩነት የሌለው በመሆኑ በጋራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። በቀጣይም ከሁለቱ ፓርቲዎች የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ብለዋል። በጋራ ለመስራት የሚደረገው የውህደት ሂደት እንደሚቀጥል ያነሱት አቶ አዲሱ፥ አሁን ላይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተጀመሩ ውይይቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በሁሉም ዓይነት መስክ እታገላለሁ ሲል የነበረው ግንቦት ሰባት ሰሞኑን ከአርበኞች ግንባር ጋር ተፋትቷል። ከሌንጮ ለታ ኦዴግ ጋር የመሠረተው ፈዛዛ ጥምረትም እስካሁን ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳያሳይ አሁን ደግሞ ኦዴግ ከኦዴፓ ጋር በመቀላቀል ብቸኛ አድርጎታል። ግንቦት 7 ከኢህአዴግ ጋር መቀላቀል የሚችልበት የርዕዮት መስመር የለውም። ከዚህ ሌላ ግንቦት 7 ፓርቲ ሳይሆን ወደ ፓርቲ ምሥረታ የሚሄድ ንቅናቄ ነው። ኦዴግ በዚህ ከኦዴፓ ጋር ባደረገው ስምምነት ግንቦት ሰባትን ጥሎ የሄደ ይመስላል፤ ምክንያቱም ግንቦት 7 ከኦዴግ ጋር ጥምረት ሲፈጥር ለኦዴግ ኅብረብሔራዊ ቁመና ለመስጠት በምላሹ ደግሞ ለራሱ የኦሮሞን ድጋፍ ለማግኘት የታሰበ እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። በመሆኑም ግንቦት 7 የአቋምና የአስተላለፍ አካሄዱን በማሳመር በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ከሚገኙ ፓርቲዎች ጋር መቀላቀል የግድ ይሆንበታል። ይህ ደግሞ አስቀድሞ ከቅንጅት ጋር ውኅደት ሲፈጠር ፓርቲዎቹን ለከፍተኛ ችግር የዳረገው ዓይነት የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ እንዳያስገባው ካሁኑ ፍርሃቻ አለ።

ከላይ “በጋራ ለመስራት የሚደረገው የውህደት ሂደት” ይቀጥላል በማለት የተናገሩት አቶ አዲሱ፥ “አሁን ላይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተጀመሩ ውይይቶች መኖራቸውን” መጥቀሳቸው ኦዴፓ በኦሮሞ ስም የተደራጁ ሌሎች ፓርቲዎችን እየጠቀለለ ግዙፍ የኦሮሞ ፓርቲ ይሆናል የሚል ግምት እንዲሰጠው አድርጓል። ከዚህ አኳያ በርዕዮት፣ በፖለቲካ ፕሮግራም፣ ወዘተ ከሌንጮ ኦዴግ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የመረራ ጉዲና ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ከዳውድ ኢብሣ ኦነግ ጋር ውኅደት ለመፍጠር በመሥራት ላይ እንደሆኑ በመስከረም ወር ላይ አስታውቀው ነበር። እስካሁን ግልጽ ባይሆንም ይህ አካሄድ ኦዴፓን ያገዝፈዋል፤ ወይም ኦፌኮንና ኦነግን በጥምረት የኦዴፓ ግምባር ቀደም ተፎካካሪ ያደርጋቸዋል።

በሌላ በኩል ይህ የኦዴግና የኦዴፓ ውህደት በግንቦት 7 ላይ የሚስከትለው የፖለቲካ ጫና ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ ምን እንደሚሆን ገና አልጠራም። ኦዴግ ኢህአዴግን በመቃወም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮት የተለየ አካሄድ ሲከተል የቆየ ፓርቲ ነው። ኦዴፓ ደግሞ በቅርቡ ካካሄደው የስምና መሰል ለውጦች አኳያ ኢህአዴግን በስም ብቻ የተሸከመ እንጂ በገሃድ የኢህአዴግ ካባውን አሽንቀጥሮ የጣለ ፓርቲ ሆኗል። ይህ ውህደት ደግሞ ኦዴፓ በጣም ራሱን ከኢህአዴግ አግልሎ እየሄደ ለመሆኑን እንደማሳያ ሆኖ ቀርቧል። ከዚህ አንጻር የኢህአዴግ መጻዒ ዕድል “በክብር” ወደ ሙዚየም መግባት ወይም የህወሓት ወንበዴዎች “ታላቁ መሪ” እንደሚሉት መለስ ወደ ከርሰ መቃብር መውረድ ይሆናል። ሁሉም ጉዳይ በቅርቡ መስመር የሚይዝ ይሆናል።


6ይ ክፋል: ማዕበል ስርሒት ፈንቅል - የካቲት 1990 - ሰነዳዊት ፊልም| sirihit fenkil 1990 - part 6 - ERi-TV Documentary

Dehai Events