Goolgule.com: ኮንሶ – የግፍ ምድር! “የሚሆነው ሁሉ የሚታመን አይደለም” የኮንሶ ተወላጆች

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sat, 3 Dec 2016 12:24:06 +0100

ኮንሶ – የግፍ ምድር!

“የሚሆነው ሁሉ የሚታመን አይደለም” የኮንሶ ተወላጆች
konso
 

አንደኛዋ ባለቤታቸው ሶስት ጊዜ ቀዶ ጥገና አድርጋለች። ሌላኛዋ ባለቤታቸው ከአንድ ልጇ ጋር ሁሉም እስር ላይ ናቸው። እመጫትም ከእርጥብ ልጇ ጋር ታስራለች። እነዚህ ማሳያ እንጂ በኮንሶ ከእስር የተረፉ ተሰደዋል።  በወረዳው ያሉት 43 ትምህርት ቤቶች እስር ቤቶችና የወታደሮች ካምፕ ሆነዋል። ወደ አጎራባች ቀበሌ ወይም ጫካ የመሸጉ ሰዎች ህይወታቸውን የሚገፉት በመከራ ነው። ይህ ሁሉ ምሬት ሲሰማ ክልሉ ምንም ነገር እንደሌለ ነው የሚናገረው – ኮንሶ ግን ፍጹም ግፍ የሚፈጸምባት ሆናለች!

ህዳር 27 ቀን 2016 ቪኦኤ ያናገራቸው ሁለት የኮንሶ ነዋሪዎች “ኮንሶዎች የሚኖሩት በሌላዋ ኢትዮጵያ ነው” ይላሉ። በኮንሶ መተንፈስ አይቻልም። መቃወም አይፈቀድም። ጥያቄ ማቅረብ ክልክል ነው። የሚማርበትን ዩኒቨርሲቲና የራሱን ስም ለጥንቃቄ ሲል በመደበቅ አጭር ቃለ ምልልስ ያደረገው የኮንሶ ተወላጅ “የሚረዳኝ የለምና ትምህርት አቁሜያለሁ። በኮንሶ የሚሆነውን ለመናገር ቃል የለኝም። መግለጽም አልችልም። ተጨንቄያለሁ…” በማለት ተናግሯል።

“እህቴ ታስራለች፤ አባቴ ታስሯል፤ አጎቶቼ ታስረዋል፤ ኑሯችን ዝቅተኛ በመሆኑ የሚረዱኝ እናቶቼና አባቶቼ ሁሉም እስር ላይ ናቸው” የሚለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ጨክኖ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንዳይሄድ የሰጋበትን ሌላም ምክንያት ተናግሯል። ጋዜጠኛዋ ለምን ወደ ትምህርቱ እንደማይመለስ ጠይቃው “የኮንሶ ልጆች እየታደኑ ይታሰራሉ” ሲል ነው የመለሰላትkonso14-people

በኮንሶ አገልግሎት የለም። ሰራተኞች ደሞዝ ቆሞባቸዋል። ማሳ ላይ የሚገኙ ይታሰራሉ። አንድ የህክምና ጣቢያ ሲቀር ሁሉም ተዘግተዋል። ትምህርት ቤቶች ስራ አቁመዋል። የቻለ ተሰድዶ አገር ለቋል። የጨከኑም ጫካ ናቸው። አቅም ያጡ እስረኞች ሆነዋል። በኮንሶ ህይወት እንዲህ ሆናለች። ለዚህም ነው “የምንኖረው ሌላዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው” የሚሉት።

ግፍ እየተንተከተከባት ካለችው ኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የሚሰማው ምሬት ነው። የዩኒቨርሲቲው ተማሪም ያለው ይህንኑ ነው። “ለምን ሰውን እንደዚህ ያሰቃዩታል፤ ያማርሩታል?” በኮንሶ የሚደርሰውን በደል ይፋ ለማድረግ የመገናኛ ችግር መኖሩን ያስታወቀው ይህ ተማሪ ጫካ ውስጥ የመስተጋብር (ኔትወርክ) ችግር መኖሩ፣ ስልክን ቻርጅ ለማድረግ ኤሌክትሪክ መጥፋቱ፣ አብዛኛው ህዝብ ሸሽቶ ጫካ መኖሩ የግንኙነት መረቡን በጥሶታል።

ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ለምን አነሳችሁ” በሚል ህዝብ የመረጣቸውን የአካባቢው ተወላጆች  በማሰር የተጀመረው የኮንሶ ችግር ቅጥ ያጣ ስለመሆኑ መረጃ መውጣት ከጀመረ ቢቆይም አስተዳዳሪ ነን የሚሉት ክፍሎች መፍትሔ ሊፈለጉ አልቻሉም ወይም አልፈለጉም። አሁን የሚፈራው ድርቅ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ነው። ቪኦኤ ያነጋገራቸው ሁለት ወገኖች እንዳሉት ያረሰ፣ የዘራ የለም። ሰብል የለም። ምን ሊበላ ይሆን?

የክልሉ ቃል አቀባይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢደወልላቸው ሊገኙ አልቻሉም። የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነርም በተመሳሳይ ስልካቸውን አይመልሱም። ሃይለማሪያም ደሳለኝ “ያልተመለሰ የማንነት ጥያቄ የለም” ሲል የኮንሶን ጉዳይ ማጣጣሉ አይዘነጋም።

konso10-flagበኢትዮጵያዊነታቸው ስለማይደራደሩት ኮንሶዎች ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መስከረም 6፤ 2009 (September 16, 2016)“ህወሃቶች – ምንድነው የሚፈልጉት? ደም አይጠግቡም?” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና የኮንሶን ሕይወት በተመለከተ ከዓይን እማኞች በማግኘት ያተመው መረጃ እንዲህ ይነበባል፤

“እኔ እስከማውቀው ድረስ የመንግስት ኃላፊነት ህግን ማስከበር፣ ሰላምን ማስፈን እንዲሁም ግጭት ሲፈጠር እንደ ገለልተኛ ሆኖ ለየትኛውም ወገን ሳያዳላ የማረጋጋት ሥራን መስራት ነው። አሁን አሁን በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ግን ከዚህ የተቃረነ መሆኑ ባያጠያይቅም በኮንሶ ምድር ከጳጉሜ 5 ጀምሮ እስካሁኑ ደቂቃና ሰከንድ ድረስ እየሆነ ያለው ግን እጅግ የሚዘገንን ከአንድ መንግስት ቀርቶ በሀገር ጠላት ላይ እንኳን ለመፈፀም የሚከብድ የአንድን ብሔር ዘር ማጥፋትን ኢላማ ያደረገ ዘመቻ በፈደራል ፖሊስና በደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ቅንጅት በኮንሶ ህዝብ ላይ እየተካሔደ ይገኛል።

“እንደሚታወቀው የኮንሶ ህዝብ ከሰገን ዞን ወጥቶ ራሱን በራስ ማስተዳደር ይችል ዘንድ ራሱን ችሎ በዞን ለመደራጀት ከዓመት በፊት ኮሚቴ አዋቅሮ ደረጃ በደረጃ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የኢህአዴግ እህት ድርጅቶችና ለውጭ ኤምባሲዎች ጭምር ማሳወቁ ይታወቃል።

“ይህ ጥያቄ ከዓመት በፊት ቀርቦለት የቃል መልስ ለመስጠት እንኳን ዓመት ሙሉ የፈጀበት የደቡብ ክልል መጀመሪያውኑ ጥያቄውን ተቀብሎ በህገ መንግስቱ መሰረት ከመመለስ ይልቅ ጥያቄውን በጉልበት እንደሚቀለብስ በተደጋጋሚ እየዛተ “ኮንሶ የሲኒ ውስጥ ማዕበል ነው፤ በአንድ ዘር ማጥፋት ይቻላል” ምናምን በማለት ለዓመታት ያቀደውን እቅድ አሁን ተግባር ላይ በማዋል ላይ ይገኛል።

“ዕቅዳቸውን ከግብ ለማድረስም በመጀመሪያ ከፌዴራል መንግስት ፍቃድ በማግኘት ጳጉሜ 5 ቀን 2008 አንድ የሰገን ዞን ተላላኪ አቶ ከተማ ካሽለ ከአጋሮቹ በምሥጢር የሰማውን የደቡብ ክልል የኮንሶ ብሔርን ከምድረ ገፅ የመገርሰስ ጥማት የፈደራል መንግስት መፍቀዱ ብቻ ሳይሆን አጋርነቱን እንደገለፀላቸው በመተማመን ሀላኮ (ታራ ማንጋሻ) የሚባል መንደር ማምሻውን ሄዶ እናቃጥላችሁሃለን፣ እንጨርሳችኋለን፣ በታቀደው መሰረት ዘራችሁን ከምድር ላይ እናጠፋለን በማለት ከደነፋ በኋላ ወዲያው ተሰወረ። ይህን የሰማው ሰላማዊ ህዝብ ውሸቱን ነው በማለት ተዘናግቶ እንዳለውም ምሽት ላይ ከሻላሎ በኩል ኮንሶን በከዱ ከሃዲዎች አማካኝነት መተረየስ ተጥምዶ ተኩስ ተከፈተባቸው። የሀላኮ ህዝብም ተደናግጦ ልጆችን ወደ ኋላ እያሸሹ መከላከል ጀመሩ ጠብ ጫሪዎቹም ከህዝቡ ጋር እስከ ሌሊቱ 8፡00 ተዋጉ በዚህ ሁሉ ግን ህይወት ሳይጠፋ ህዝቡ 3 ቀበሌዎችን አልፎ ቢያባርራቸውም ከ3 ቤት ቃጠሎ ውጪ ምንም ጉዳት በንብረትም ሆነ በሰው አካል ላይ ሳይደርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።konso6

“በ01/01/2009 የመጀመሪያ ንድፋቸውን ያሳኩት የሰገን ዞንና የደቡብ ክልል አመራሮች ኮንሶ ጦርነት ቀስቅሷል በማለት በርካታ ልዩ ሃይልና የፌዴራል ፖሊሶችን ወደ ሰገን ዞን አስገቡ። ከዚያም ማታ ላይ ወደ ሻላሎ ስራዊቱን አስገብተው የኮንሶ ገሃዲ የሻላሎ ነዋሪዎች በሻላሎ ውስጥ ያሉትንና የኮንሶ ጥያቄን የሚደግፉትን ቤቶች በፌዴራልና ልዩ ኃይል ታግዘው ሙሉ በሙሉ አቃጠሉ።

“ምሽት ላይ ቤቱን ካስቃጠሉ በኋላ ሰራዊቱ ወደ ሰገን ከተማ ሲመለስ ገሃዲዎቹ ብቻቸውን አቅም እንደለላቸው ቢያውቁም በታዘዙት መሰረት በሀላኮ መንደር ላይ ዳግም ተኩስ ከፈቱ። ህዝቡም ተነስቶ ገጠማቸውና በምሽቱ እንደገና ብዙ ቤቶች ተቃጠሉ።

“በ02/01/09፤ በዚህ ዕለት የሰገን ዞንና የደቡብ ክልል ኮንሶን ለማጥፋት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደደረሱ በመተማመን የዞኑን የበላይ አመራሮች ወደ ሀዌሳ ሲያስኮበልሉ የበታች አመራሮችን በምስጢር ቤተሰቦቻቸውን እንዲያስጠነቅቁ መልዕክት አስተላለፉና ቁጥሩን ለመገመት የሚከብድ አጋዚን በመንገድ ላይ ሌላው ህዝብ አይቶ ይሸበራል በማለት መሰለኝ ወታደሩን በሶስት አቅጣጫ ከፋፍለው ግማሹን በፕለን በጅንካ፣ ግማሹን በአርባምንጭ እንዲሁም ግማሹን በያቭሎ በኩል በማስገባት አይሎታን ከበቧት። ከሰዓት በኋላ ከተማ ገለቦ የሚባል የሰገን ዞን አመራር (አሁን አርባምንጭ ኤፍ ኤም ላይ መረጃ እንዲያቀባብል በዞኑ የተቀመጠ) ወደ እፋዮ መንደር ለቤተሰቦቹ ስልክ ደውሎ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው ዛሬ ማታ ስለምከናወን ሸሽታችሁ አሁኑኑ አካባቢውን ልቀቁ ሲላቸው ዕለቱ የሙስሊም በዓል የሚከበርበት ስለነበር ደግሞ በዓል ባይሆንም መንግስት የገዛ ህዝቡ ላይ እንዲህ ዓይነት Genocide ያውጃል ብሎ ስለማያስብ ውሸቱን ነው ብለው ዝም አሉ።

“ይህን ተከትሎ ነው እንግዲህ ማታ በሞያለ በኩል የገባው የአጋዚ ሃይል በብርብርና ሻራንካ በኩል ገብቶ በጋማ ዳራ ከፍብሎ አንተና ያለበት አካባቢ ህዝቡን ከበው በከባድ መሳሪያ ታግዘው የውትድርና ብቃታቸውን ለማሳየት በቁም ህብረተሰቡ ላይ ተኩስ የከፈቱት። ህዝቡ ፌዴራል ሊያገላግላል እንጅ አይፈጀንም የሚል እምነት ስለነበራቸው ተኩስ አቁመው ቢያፈገፍጉም የአጋዚ የጥይት እሩምታን የሚያቆም አልተገኘም እንዲሁም ወዲያው 6 ሰው ገድለው ሬሳ እንኳን ለመውሰድ በከባድ መሳሪያ የታገዘው የአጋዚ ሃይል ፋታ ስላልሰጣቸው የአንዱን ሬሳ ብቻ እንደምንም ወስደው ካልጠበቁት ጥቃት ሰው ህይወቱን ለማትረፍ እየፈረጠጠ ስለነበር ከዚያ በኋላ የሞቱ ሰዎች ስንት እንደሆኑ እንኳን ከፈጣሪ በቀር ማንም በማያውቀው ሁኔታ ለሊቱን ሙሉ ህዝቡን እየጨፈጨፉ አደሩ።konso12-displaced

“03/01/2009፤ ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀላኮ በኩል ምንም ተኩስ ሳይሰማ በሰላም ያደረ ህዝብ ጠዋት በማለዳ ከየት በኩል እንደመጡ እንኳን ህዝቡ ሳያውቅ በአርባምንጭ በኩል የገባው የአጋዚ ሃይል የሀላኮን መንደር ከብቦ የጥይት እሩምታ ሲለቁባቸው ከእንቅልፍ ገና በደንብ ያልነቃው ህዝብ ፈዴራሎች ስለሆኑ አይነኩንም ብለው ሲሸሹ አከታትለው በማጥቃት ህዝቡን አሳድደው ከኋላ ባስከተሉት ልዩ ሀይል ቤቶቻቸውን እያቃጠሉ እነሱ ከፊት እያሳደዱ ብታምኑም ባታምኑም አሁን የሀላኮና የጎጫ መንደሮችን ሙሉ በሙሉ አመድ አድርገው መሮጥ ያልቻሉ ህፃናትና አዛውንቶች ጨፍጭፈው ጨርሰዋል ከዛን ወደ ሉልቱ ቀበሌ በመጓዝ ላይ ይገኛሉ።

“አሁን ህዝቡ እንዳለ ሸሽቶ ስለሆነ ከዚህ ድርጊት የሚመልሳቸው ማንም የለም። ከኮንሶ ያለው ህዝብ እንኳን መጥቶ እንዳይከላከል ተዋጊው አጋዚ ከመሆኑ ባሻገር በጅንካ በኩል የገባው ሃይል ከተማውን ከብቦ መንገድ ዘግቷል።

“እንግዲህ ከተጠየቀ ዓመታትን ያስቆጠረው የኮንሶ ህዝብ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በፅሑፍ ከቀረበ ከዓመት በላይ ዕድሜ ቢሆነውም ዛሬ መልሱ የ ኮንሶን ዘር ከምድረ ገፅ የማጥፋት ዘመቻን በደቡብ ክልልና በአጋዚ ቅንጅት ሆኗል። የሚገርመው ISIS እንኳን ለማጥፋት ዘመቻ ሲደረግ ልክ አለው፤ ዛሬ ግን የኮንሶን ህዝብ በሀገር ጠላት ላይ እንኳን በማይፈፀም የዘር ማጥፋት ዘመቻ ህዝቡን የሚታደግ ከፈጣሪ በቀር ያለ አይመስልም።konso15

“በመጨረሻም ቤተሰቦቼን የጨረሱ አርመኔዎች እኔንም ይምሩኛል የምልበት እምነት የለኝም ከዚህ በኋላ የምኖረው ህይወት የራሴ አይደለም እኔም ዛሬ ሞቻልለሁ። ቢሆንም ግን ይህን በእንባ እየታጠብኩ የፃፍኩትን የምታነቡ ወገኖች ሁሉ በፀሎት ከጎናችን በመሆንና ይህን ግፍ ለዓለም ሚዲያዎች በማሳወቅ እንድትረዱን በነበረኝ ኢትዮጵያዊ ወንድምነት እማፀናችኋለሁ።”

Received on Sat Dec 03 2016 - 06:24:06 EST

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved