Ethsat.com: በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመቆየት ወይም ለቆ ለመውጣት በሚሉ አማራጮ ላይ እየመከሩ መሆኑ ተገለጸ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Thu, 27 Oct 2016 00:01:03 +0200

በኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአውሮፓ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመቆየት ወይም ለቆ ለመውጣት በሚሉ አማራጮ ላይ እየመከሩ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (ጥቅምት 26 ፥ 2009)

Watch these:

ESAT DC Morning News Wed 26 Oct 2016

http://video.ethsat.com/?p=29816

ESAT Daily News Amsterdam October 26,2016

http://video.ethsat.com/?p=29827

በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የአውሮፓ ኩባንያዎች በሃገሪቱ ለመቆየት ወይም ለቆ ለመውጣት የሚሉ አማራጮ ላይ እየመከሩ መሆኑ ተገለጠ።

ኩባንያዎቹ በተለያዩ የክልል  ከተሞች ያለው ፖለቲካዊ ውጥረትና በቅርቡ በአንዳንድ ኩባንያዎች ላይ የተቃጣው ጥቃት በኢንቨስትመንት ስራዎቻቸው አማራጮችን እንዲመለከቱ እንዳስገደዳቸው ዘጋርዲያን ጋዜጣ ረቡዕ ዘግቧል።

መቀመመጫውን በኔዘርላንድ ያደረገው የአፍሪካ ጁስ ሃላፊ የሆኑት አያን ዴሪ ባለፈው ወር በፋብሪካቸው ላይ የደረሰውን ጉዳት በአግባቡ ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ለጋዜጣው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ በተካሄዱ የመሬት ቅርምት ላይ ጥናትን ሲያካሄድ የቆየው የኦክላንድ ኢንስቲትዩት በበኩሉ በመንግስት ተግባራዊ ሲደረገ የነበረው ይኸው ፕሮግራም በአርሶ አደሮች ዘንድ ቅሬታን እንዳስነሳ ለዘጋርዲያን ጋዜጣ ገልጿል።

ላለፉት አራትና አምስት አመታት በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ የነበሩ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራሞች የአርሶ አደሮችን በምግብ እራስን የመቻል ተስፋ አደጋ ውስጥ እንደከተተው በኢትዮጵያ የመሬት ይዞታ ላይ ጥናትን ያካሄደው ተቋም ምላሽን ሰጥቷል።

በአርሶ አደሮቹ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በመንግስ በኩል ምላሽ ባለማግኘታቸው ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሊቀሰቀሱና ስጋትን ሊፈጥሩ መቻላቸውንም ኦክላንድ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በዚሁ ህዝባዊ ተቃውሞ ጥቃት ደርሶባቸው የነበሩ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ተቋማት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

በቅርቡ ጥቃት የተፈጸመበት የአፍሪካ ዱሽ ኩባንያ ከመንግስት ጋር በሽርክና የሚሰራ ሲሆን፣ 10 በመቶ የሚሆነው የድርጅቱ ድርሻ የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን ከዘጋርዲያን ጋዜጣ መረዳት ተችሏል።

ሬንሰን የተሰኘ ሌላ የአትክልት አምራች ኩባንያ ለመንግስት ቅርበት ባለው አንድ ግለሰብ የሚተዳደር እንደነበርና የጥቃቱ ሰለባ መሆኑን ጋዜጣው በጉዳዩ ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት አስነብቧል።

ይሁንና የጥቃቱ ሰለባ የነበሩት የውጭ ኩባንያዎች ነዋሪው በመሬት መብት ዙሪያ ያለውን ቅሬታ በአግባቡ እንደሚያውቁ እና ከመንግስት ጋር በሽርክና መስራታቸው ለጥቃቱ ሊዳርጋቸው እንደሚችል መገንዘብ አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በጉዳዩ ላይ ምላሽን እንዲሰጥ ቢጠየቅም መልስ አለመስጠቱን የገለጸው የብሪታኒያው ጋዜጣ የኔዘርላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ከመንግስት በኩል የጥበቃ ደህነት እንደተሰጠው አስታውቋል።

የኢንቨስትመንት ባለሙያዎች በበኩላቸው  አለመረጋጋቱ ገና ዕልባት ያላገኘ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው የጸጥታ ሃይሎች የሚያደርጉት ጥበቃ ዘላቂ ዋስትናን እንደማይሰጥ አስረድተዋል።

የኦክላንድ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አኑራዳህ ሚታል በበኩላቸው የውጭ ኩባንያዎች ሃገሪቱን በትክክለኛ መንገድ ለመደገፍ ፍላጎት ካላቸው ዜጎችን የሚጨቁን መንግስት የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ስለማይችል ከሃገሪቱ ለቀው መውጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

*******************************************************************************

ወታደራዊ ምዝገባ ለማካሄድ ቅስቀሳ እየተካሄደ ነው

ኢሳት (ጥቅምት 26 ፥ 2009)

ጥቅምት ፲፮ (አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የመከላከያ ሰራዊቱ የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም እየጠፋ በመምጣቱ የሃይል መሳሳት ያጋጠመው አገዛዙ፣ ወጣቶችን ወደ ውትድርና ስልጠና ለመውስድ አዲስ ማስታወቂያ እያስነገረ ቢሆንም፣ ጥሪው ተቀባይነት አላገኘለትም። በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ ወጣቶች እንዲመዘገቡ የሚያሳስቡ ማስታወቂያዎች እንየተነገሩ ነው። ቀደም ብሎ በግልጽ ይወጣ የነበረው የወታደር የቅጥር ማስታወቂያ ተቀባይነት ማጣቱ በሚዲያ ከተዘገበ በሁዋላ፣ አገዛዙ ቅጥሩን በተለዬ መንገድ ለማስፈጸም እንቅስቃሴ ጀምሯል። ወጣቶቹ የትምህርት ስልጠና እንደሚሰጣቸው እየተነገራቸው እንዲመዘገቡ በማድረግና ስልጠናውን በአዋሽና በሌሎችም ቦታዎች እንዲካሄዱ በማድረግ፣ ወጣቶችን ወደ ውትድርና የማስገባት እቅድ መነደፉን ምንጮች ገልጸዋል።

የህወሃት ኢህአዴግ አገዛዝ አዲስ ባወጣው አዋጅ ፣ አዋጁ እስከሚነሳበት ጊዜ ድረስ ወታደሮች የስራ መልቀቂያ ወይም የእረፍት ፈቃድ መጠየቅ አይችሉም። በዚህ ውሳኔ ከ7 ሺ ያላነሱ 7 አመታት አገልግለው የስራ መልቀቂያ የጠየቁ ወታደሮችን አግቶ ለመያዝ እንዳስቻለው ምንጮች ገልጸዋል። የ7 አመታት ግዴታቸውን ፈጽመው የስራ መልቀቂያ የሚያቀርቡ ወታደሮች መበራከቱን ተከትሎ ገዢው ፓርቲ በአዳዲስ ምልምል ወታደሮች ለመተካት ቢያልምም ይህም እቅዱ አልተሳካም።

ሰራዊቱ በህጋዊ መንገድ ስንብት ሲጠይቅ “በኢትዮጵያ ሰንደቃላማ እና በመለስ አጽም” እየተባለ ይለመን የነበረው አሰራር ዋጋ አልባ መሆኑን ተከትሎ፣ የመልቀቂያ ጥያቄያቸውን በድፍረት ሲያቀርቡ የነበሩ በርካታ ወታደሮች ታስረዋል። በሁለቱ ክልሎች የተፈጠረውን ተቃውሞ ተከትሎ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች የጠፉ ሲሆን፣ ብዙዎች መሳሪያቸውን እየሸጡ ከህዝብ ሲቀላቀሉ ሌሎች ደግሞ የነጻነት ሃይሎች ተቀላቅለዋል።

በሌላ በኩል አገሪቱን የሚገዛው ወታደራዊ እዙ ወይም ኮማንድ ፖስቱ ከ800 በኦሮምያና አማራ ክልሎች ከወታደሮች የተቀሙ ከ 513 ጠመንጃዎች ከ300 በላይ የሚሆኑትን አስመልሻለሁ ብሎአል።

የተባለው አሃዝ ትክክል ይሁን አይሁን ማረጋጋጥ ባይቻልም፣ ወታደሮች አሁንም ድረስ መሳሪያቸውን እየያዙ እንደሚጠፉ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱን መረጃዎች ያሳያሉ። የሚጠፉ ወታደሮች የተሻለ አቀባባልና አያያዝ እንደሚደረግላቸው የአርበኞች ግንቦት7 ሊ/መንበር ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ መገልጻቸው ይታወሳል።

*******************************************************************************

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በቱሪዝም እንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያመጣ ነው

ኢሳት (ጥቅምት 26 ፥ 2009)

ጥቅምት ፲፮ (አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የተከሰተው ህዝባዊ ተቃውሞና ተቃውሞውን ተከትሎ የታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በእያመቱ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገቢ የሚያስገኘውን የቱሪዝም እንዱስትሪ ክፉኛ እንደጎዳው ፋይናንሻል ታይምስ ዘግቧል።

ምንም እንኳ ገዢው ፓርቲ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ችግር የሌለባቸው በመሆኑ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደሚችሉ ቢናገርም፣ የውጭ አገር የአስጎብኝ ድርጅቶች አማካሪዎች ግን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም በሁዋላ ሁኔታው አስፈሪ በመሆኑ ቱሪስቶች እንዳይጓዙ መክረዋል።

አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ ፣ እንግሊዝና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ ያወጡት ማስጠንቀቂያ ገዢውን ፓርቲ በእጅጉ ያበሳጨው ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቱሪስቶችን አይመለከትም የሚል መግለጫ አውጥቷል። ማንኛውም ዜጋ ዋና ዋና በሚባሉት መንገዶች እንዳይጓዝ ታግዶ ባለበት ወቅት እንዲሁም ቱሪስቶች ጉዳት ሲደርስባቸው እርዳታ ለመስጠት የሚችሉ የኢምባሲ ሰራተኞች ከአዲስ አበባ 40 ኪሎሜትር ውጭ እንዳይወጡ ታግደው በሚገኙበት ወቅት አዋጁ ቱሪስቶችን አይመለከትም መባሉ ግራ አጋብቷል።

የቨርሲክ ማፕል ክሮፍት የአደጋ ተንታኝ የሆኑት ኢማ ጎርዶን ፣ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ካለፉት ሳምንታት ጋር ሲነጻጸር ጸጥ ያለ ቢመስልም፣ ተቃውሞው ግን አልቆመም ብለዋል። የስራ ማቆም አድማ፣ ከተሞችን ሰው አልባ ማድረግ፣ እና ሌሎችም ሰላማዊ ትግሎች አሁንም ድረስ እየተካሄዱ መሆኑን የገለጹት ተንታኟ፣ እነዚህን ድርጊቶች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ሆነ በፖሊስ ለማስቆም እንደማይቻል ገልጸዋል።

ተቃውሞውን የሚያካሂዱ ወገኖች እንዴት አድርገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደሚቋቋሙት መላ ከዘየዱ በሁዋላ፣ በተለይም ማህበራዊ ሚዲያ መዘጋቱን፣ የፖለቲካ ውይይት መከልከሉንና ስብሰባ ማከሄድን አለመቻሉን አስመልክቶ መፍትሄ ከፈለጉ በሁዋላ አመጹ እንደገና ሊካሄድ ይችላል ብለዋል።  የውጭ አገር ኩባንያዎች ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ በአገር ውስጥ በመቆየትና በመልቀቅ መካከል እየዋዠቁ ነው።

 

Received on Wed Oct 26 2016 - 18:01:03 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved