Goolgule.com: “የጣዕር ጊዜ አዋጁ” እና ኢትዮጵያ "ምንድነዉ የሚደብቁት? ... በብሔራዊ ደረጃ የመጣ ጥፋት ነዉ"

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 19 Oct 2016 23:43:28 +0200

“የጣዕር ጊዜ አዋጁ” እና ኢትዮጵያ

"ምንድነዉ የሚደብቁት? ... በብሔራዊ ደረጃ የመጣ ጥፋት ነዉ"
tplf-agazi-emergency
 

የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ህወሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ስላወጀው “አትኑሩ” አዋጅና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ስለሰጡት አስተያየቶች ያቀናበረውን ከዚህ በታች እንዳል አስፍረነዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና ኢትዮጵያ
* “በብሔራዊ ደረጃ የመጣ ጥፋት ነዉ”

የኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ የደነገገዉን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የሚያጠናክሩ ማብራሪያዎችን ይፋ ከተደረጉ ወዲህ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ስጋታቸዉን መግለጽ ጀምረዋል።

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፤ ይደረጋሉ የተባሉት መሻሻሎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትንታኔ ይፋ ሲደረግ በተቃራኒዉ መንገድ የሚጓዝ ነገር መኖር እንደሚያመላክት ነዉ የተጠቀሰዉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከዉጭ የሚሰራጩ የሽብርተኛ ድርጅቶች ልሳን ያላቸዉን መገናኛ ብዙሃን ማዳመጥ ያግዳል፤ የዉጭ ሃገራት ዲፕሎማቶችም ከዋና ከተማ አዲስ አበባ ዉጪ ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ሳያሳዉቁ እንዳይወጡም ገድቧል።

ባልተጠበቀዉ የተቃዉሞ ማዕበል ምክንያት የተደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንድ ወገን የሲቪሉን ኅብረተሰብ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ወንጀል ለማድረግ የሚሞክር መሆኑን የተጨቆኑ ሕዝቦች መብት የሚሟገተዉ የጀርመኑ ገዜልሻፍት ፉዩር በድህሮተ ፎልከር ባልደረባ ዑልሪሽ ዴሊዩስ ይናገራሉ።

«በአንድ ወገን በኦሮሚያ የሚገኘዉን ሲቪል ሕዝብ ማንኛዉንም ዓይነት ተቃዉሞ ወንጀል ለማድረግ የሚሞክር ሲሆን ይህ ደግሞ የፖለቲካ ቀዉስን የሚፈታ ጥሩ መንገድ አይደለም። በዚያም ላይ ለምንድ ነዉ ተቃዉሞዎቹ የቀጠሉት፤ በቅርቡስ የተፈጠረዉ ምንድነዉ፣ እነዚህ ሰዎችስ እስካሁን ለምን በቁጣቸዉ ቀጠሉ፤ ለምንስ በአዲስ አበባ አቅራቢያ የሚገኙ ኩባንያዎችን አቃጠሉ ለሚለዉም ተገቢ ትንታኔ አይሰጥም። አሁን የምናየዉ ባለስልጣናት በገጠሩ አካባቢ የሚደረገዉን ነገር ለመደበቅም በዋና ዋና ጎዳናዎች አካባቢ የ25 ኪሎ ሜትር አደገኛ ቀጠና ተደንግጓል፤ ስለዚህ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቶች በየአካባቢዉ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ ለጋዜጠኞች ረዥም ጊዜናት ተቆጥረዋል ተንቀሳቅሰዉ መመርመር እንዳይችሉ ከተገደበ። ስለዚህ እራሳችንን ምንድነዉ የሚደብቁት ብለን እንጠይቃለን። ጋዜጠኞችም ሆኑ የመብት ተቆርቋሪዎች በገጠሩ አካባቢ ምን እንደተፈጠረ መነሻዉን እንዳይመረምሩ እንዲህ ያለ ጠንካራ ገደብስ ማድረግስ ያስፈልጋል ወይ እንላለን።»

መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሀገሪቱን ሰላም እና ፀጥታ ስጋት ላይ የጣሉ ፀረ ሰላም ኃይሎችን ለመቆጣጠር የታለመ መሆኑን ይናገራል። በተቃዉሞ እንቅስቃሴዉ ወቅት የንፁሐን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል፤ የግል ንብረቶችም በተቃዉሞ አድራጊዎቹ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ለመሆኑ ፀረ መንግሥት ተቃዉሞዉ ምን ያህል ሀገሪቱን ወደ ትርምስ ይከታታል ብሎ መገመት ይቻላል? እንደገና ዴሊዩስ፤

«ቢያንስ የእርስ በርስ ጦርነት አፋፍ ላይ ናት የሚል ስሜት አለን ። ነገር ግን መንግሥት  የተደራጀ አሸባሪ ቡድን የሚያካሂደዉ እንቅስቃሴ ነዉ፤ ወይም ደግሞ የዉጭ ኃይሎ እንደ ኤርትራ ወይም ግብፅ ከጀርባዉ አሉ እንደሚለዉ ነዉ ብዬ አላስብም። ጉዳዩ ወደ ዓለም አቀፍ ግጭትነት ይሻገራል ብዬ አልገምትም። ምክንያቱም በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ብሔራዊ ግጭት፤ ብሔራዊ ችግር ነዉ። ለምን እነዚህ ሰዎች ጎዳና ላይ ወጥተዉ ይቃወማሉ የሚለዉን ማሰብ አለባቸዉ። ከመንግሥት በኩል ለምን እነዚህ ሰዎች እንደተቆጡ የሚያስረዳ ተጨባጭ ትንታኔ ያለ አይመስለኝም። እናም ይህ ሀገሪቱን በቀጣይ ወራት እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ ሁኔታ ላይ ሊጥል የሚችል በብሔራዊ ደረጃ የመጣ ጥፋት ነዉ።»Ulrich Delius (Gesellschaft für bedrohte Völker)

ዑልሪሽ ዴሊዩስ እንደሚሉት ይህን መፃኢ ችግር ከወዲሁ ለማስቀረት አስፈላጊ የመፍትሄ መንገዶችን መፈለግ፤ የተመድም ሆነ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ምን እየተካሄደ እንደሆነ ጉዳዩን እንዲመረምሩ ማድረግ ወሳኝ ነዉ። ለምድነዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዉሞን ፈፅሞ የሚጠላዉ፤ በተለይ ደግሞ የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች የሚያካሂዱትን? ለሚለዉ ጥያቄ የዑልሪሽ ዴሊዩስ ምላሽ እንዲህ የሚል ነዉ፤

«ባለፉት ቀናት በተለይ በዋና ዋና የአማራ አካባቢዎች ኦሮሚያ ዉስጥ የተከሰተዉን በተመለከተ የመተባበር እንቅስቃሴዎች አይተናል። እናም ከዚህ ጠንካራ ገደብ ጀርባ ያለዉ ስጋት በእነዚህ አካባቢ የተነሳዉ ተቃዉሞ ወደሌላዉም የአማራ ክፍል ሊስፋፋ ይችላል የሚል ይመስለኛል። አሁን እኛ በምንነጋገርበት ሰዓት በአማራ ክልል ተፈላጊ በሆነችዉ ጎንደር ከተማ ላይ የሶስት ቀናት የስራ ማቆም አድማ መኖሩ ተሰምቷል። እናም ለዚህ መንግሥት በጣም አስቸጋሪ ነዉ። ምክንያቱም በየጊዜዉ ለዓለም ፀጥታችን የተረጋጋ ነዉ እያለ ባለወረቶችን ለሚጋብዘዉ ለዚህ መንግሥት አስቸጋሪ ነዉ። አሁን መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በተጠንቀቅ ላይ ናቸዉ፤ ከኢትዮጵያ ስለመዉጣትም እየተናገሩ ነዉ፤  እናም መንግሥት እጠብቀዋለሁ ብሎ በሚሞክረዉ ኤኮኖሚዉ ላይም ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል።»

ኢትዮጵያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስጋት
«የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመሪዎቹ በላይ ሆኗል?»

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ለስድስት ወራት የደነገገዉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወትሮም በቋፍ የነበረዉን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋግረዉ እንደሚችል እያሳሰቡ ነዉ።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግሥት የሚቀርቡበትን ተቃዉሞዎች ለማቀዝቀዝ የሚወስዳቸዉ ርምጃዎች ይበልጥ አባባሽ እየሆኑ መሄዳቸዉን ትናንት ባወጣዉ መግለጫዉ አመልክቷል። ቻተም ሃዉስ የተሰኘዉ የብሪታኒያዉ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ምርምር ተቋም ለሩብ ምዕተ ዓመት በትረ ሥልጣን ጨብጦ የሚገኘዉ ገዢ ፓርቲ ሚናዉን እና ኅብረተሰቡን የሚረዳበትን ሁኔታ ዳግም ሊያጤን ከሚገባዉ ደረጃ ላይ መድረሱን አሳስቧል።

ከ25 ዓመታት የስልጣን ዘመን በኋላ ገዢዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በምህጻሩ ኢህአዴግ፤ በጣም ወሳኝ ለዉጥ ማድረግ የሚገባዉ ወቅት ላይ ደርሷል ያላል፤ ቻተም ሃዉስ። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የሀገሪቱን ምክር ቤት ወንበሮች ከነአጋር ድርጅቶቹ የተቆጣጠረዉ ኢህአዴግ፤ በሀገሪቱ ሥርዓት ማስከበር አለመቻሉን መቀበሉን እንደሚያመለክትም ቻተም ሃዉስ ትናንት «የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመሪዎቹ በላይ ሆኗል?» ሲል ይፋ ያደረገዉ ጽሑፍ ይዘረዝራል። ጽሑፉ አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ የምርጫ ሂደቱ ላይ ማሻሻያ እና ከተቃዉሞ ፖለቲካ ኃይሎች ጋርም ዉይይት ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዉ እንደነበርም ያስታዉሳል።

መረዳት የሚገባዉ ዋናዉ ነገርም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ ተቃዉሞ የተነሳዉ የትጥቅም ሆነ ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ኃይሎች ሳይሆን ከተራዉ ሕዝቡ መሆኑንም ቻተም ሃዉስ ያመለክታል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በሀገሪቱ ተቃዉሞዉ የተባባሰዉ መንግሥት ገንቢ በሆነ መንገድ ተቃዋዉን ማስተናገድ ስላልቻለ እንደሆነ በመግለጫዉ ገልጿል። የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍሰሃ ተክሉ እንዴትነቱን ይናገራሉ።

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu (REUTERS/File Photo/T. Negeri)አምነስቲ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ የማሠር እና የተሃድሶ ርምጃዎች ከዚህ ቀደም ሲወሰዱ፤ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች በዘፈቀደ እየታሰሩ ቤተሰብም እና ጠበቆቻቸዉ በማያገኟቸዉ ሩቅ በሆኑ ወታደራዊ ጣቢያዎች እንዲታሰሩ ማድረጉን በመግለጫዉ ጠቁሟል። ለስድስት ወራት የሚዘልቀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እጅግ ሰፊ እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ስጋት ላይ የሚጥል መሆኑን አመልክቷል። በአንድ ሀገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የመናገር፣ የመፃፍ እና መረጃዎችን በነፃነት የማግኘቱ መብት ሊገደብ እንደሚችል ያመለከቱት አቶ ፍሰሃ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረገዉ ግን ካለዉ ሁኔታ ጋር የተመጠነ አይደለም ነዉ የሚሉት። አክለዉም ካለፈዉ ዓመት ኅዳር ወር አንስቶ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚካሄደዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ መንግሥት በኃይል ፀጥ ለማድረግ የሚወስደዉ ርምጃ ያባብሰዋል እንጂ አይፈታዉም ብለዋል። (ሁለቱንም ዘገባዎች ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ያቀናበሩት ሸዋዬ ለገሠ እና ኂሩት መለሰ ናቸው)
Received on Wed Oct 19 2016 - 16:22:33 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved