Ethsat.com: በኦሮምያ አፈናው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ በርካታ ዜጎችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጫካ እየገቡ ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 18 Oct 2016 23:21:12 +0200

በኦሮምያ አፈናው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ በርካታ ዜጎችና የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጫካ እየገቡ ነው

October 18, 2016

Watch these:

ESAT DC Morning News Tue 18 Oct 2016

http://video.ethsat.com/?p=29628

ESAT Daily News Amsterdam October 18, 2016

http://video.ethsat.com/?p=29625

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከክልሉ የሚደርሱን መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለይ በአርሲ  እና በምስራቅና ምእራብ ጉጂ ዞኖች አፈናው በእጅጉ ተጠናክሮ ቀጥሎአል። የአጋዚ ወታደሮች ወደ አካባቢው በስፋት በመሰማራት መንገድ ላይ ያገኙትን ወጣት ከማፈስ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ድርጅት አባላትም እየታሰሩ ነው። እስር ቤቶች እየሞሉ ፣ መኖሪያ ቤቶች ወደ እስር ቤት እየተለወጡ ነው።

ከቢሾፍቱ እልቂት በሁዋላ በአካባቢው ተነስቶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ የሼክ ሙሃመድ ሁሴን አላሙዲ ንብረት የሆነው ዳዋ ኦኮቴ የወርቅ ማውጫ ኩባንያ ተቃጥሎ ወድሟል። ኩባንያውን ያቃጠሉትን ለመያዝ ነው የሚል ሰበብ የሚሰጡት አጋዚዎች፣ ሴት ወንድ ሳይሉ ሁሉንም በገፍ እየያዙ ማሰራቸውን ተከትሎ የሚችሉት ጨካ ውስጥ ተደብቀው እያንዳንዷን ቀን በርሃብ  እያሳለፉ ነው።

አጋዚዎች በግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እየገቡ ዲሽ መነቃቀላቸውንም ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በአርሲም ባለሃብቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና መምህራንን ማሰር የቀጠለ ሲሆን፣ የሮቤ  ጄና  ሁለተኛ ደረጃ  ትምህርት ቤት  መምህር  የሆኑት  መምህር ሙሐመድ  ቡልቡሊ  ከቤታቸው  በምሽት ከተወሰዱ በሁዋላ  በጥይት ተደብድበው መገደላቸው ታውቋል፡፡ በዚሁ ዞን  በአርሲ ሮቤ ጄና ገደምሳ ቀበሌ ገ/ማህበር ውስጥ  70 ሰዎች በጅምላ የታሰሩ ሲሆን፣ አቶ ፈዮ ገለቴ  እና  ቃሶ ሁሴን በማንኛውም ሰአት ሊገደሉ ይችላሉ የሚል ፍርሃት መኖሩን ምንጮች ገልጸዋል፤፡

በሻሸመኔ የቢሸን ሰላም ውሃ ባለቤት የሆኑት ባለሃብቱ አቶ ተሾመ ጉዱ አጋዚዎች ወደ መኖሪያ ግቢያቸው በመሄድ ከፍተኛ ድብደባ ከፈጸሙባቸው በሁዋላ፣ ሆስፒታል ገብተው እየታከሙ ነው። በከተማዋ ተደርጎ የነበረውን ተቃውሞ ተከትሎ ወጣቶች ራሳቸውን ለመከላከል ወደ መኖሪያ ግቢያቸው መግባታቸውን ተከትሎ፣ አጋዚዎች ልጆቹን በራስህ መኪና ጭነህ ወደ እስር ቤት ውሰድ ብለው ሲያዙዋቸው፣ አቶ ተሾመ “ ልጆቹ ወንድሞቼ ናቸው፣ ግቢውም የእኔ ነው “ በማለት መመለሳቸውን፣ “የጦር መሳሪያ አለህ?” ተብለው ሲጠየቁም ፣ “ህጋዊ ፈቃድ ያለው የጦር መሳሪያ አለኝ” ብለው ሲመልሱ አጋዚዎች ዱላቸውን በጭካኔ አሳርፈውባቸዋል።

የፓራዳይዝ ቫሊ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ባለቤትን ጨምሮ ሌሎች ባለሀብቶች ወደ አዲስ አበባ ተወስደው ታስረዋል።

****************************************************************************

በጎንደር የሚደረገው የሥራ ማቆም አድማ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎአል።

October 18, 2016

ጥቅምት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- አስተባባሪዎች እንደገለጹት  ሱቆች፣ ሆቴሎች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለሁለተኛ ቀን ተዘግተው ውለዋል። ከትናንት በበለጠም የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ሲያስገድዱ ውለዋል። የገዢው ፓርቲ ደጋፊ ነጋዴዎች ወይም እየተጠሩ ድርጅቶቻቸውን ካልከፈቱ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተነግሮአቸው ለይስሙላ ከከፈቱት በስተቀር በአብዛኛው የከተማ ክፍል የስራ ማቆም አድማው በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል።

“ የሥራ ማቆም አድማ ማድረግ ክልክል ነው” የሚል አፋኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣ በሁዋላ፣ አዋጁን ከምንም ባለመቁጥር በክልሉ የሥራ ማቆም አድማ ሲደረግ ከባህርዳር ከተማ አድማ ቀጥሎ የጎንደሩ አድማ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ  ነው። የአሁኑ የስራ መቆም አድማ የባህርዳር ህዝብ በቢሾፍቱ ያለቁ ወገኖችን በማሰብ ያካሄደውን የሥራ ማቆም አድማ በመደገፍ አጋርነትን ለመግለጽ እንዲሁም አፋኙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለመቃወም ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን አስተባባሪዎች ተናግረዋል።

ሰኞ እለት የስራ ማቆም አድማውን ተከትሎ  የንግድ ድርጅቶችን በጉልበት ለማስከፈት በተደረገ ሙከራ ወታደሮች በሰዎች ላይ የተኮሱት ጥይት አንድ አህያ ተመትታለች። በርካታ ነጋዴዎችም ተይዘው ታስረዋል። በከተማዋ ዲሽ ለማውረድ የተንቀሳቀሱ ካድሬዎች በድንጋይ መመታታቸውም ታውቋል።

በባህርዳርም ህዝቡ ዲሽ እንዲያወርድ በቀበሌዎች አሰተዳደር በኩል ሚሊሻዎች አሰሳ  እያደረጉ ነው፡፡

 
Received on Tue Oct 18 2016 - 16:00:17 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved