Zehabesha.com: ዞኖች ተቀላቀሉ፤ ቀበሌዎች ተጨናነቁ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 11 Oct 2016 23:05:36 +0200

 ዞኖች ተቀላቀሉ፤ ቀበሌዎች ተጨናነቁ  

 ማስተዋል በለጠ (ከአዲስ አበባ)

“ሰላም ባይኖርም ሰላም ልበላችሁ” ይላል ያ ኪሩቤል በቀለ የተባለ ወዳጄ፤ እናም ‹ሰላም ለኩልክሙ› ብዬ ዘመነ ዲቁናየን በእግረ መንገድ ላስታውስ፡፡

ሰሞኑን ቀበሌዎች በሰው ብዛት እየተጥለቀለቁ እንደሆነ በቅርብ የማውቃቸው ነግረውኛል፡፡ ቀበሌዎቹ በሰው የሚጨናነቁባቸው ብቸኛ ምክንያትም ትግሬ ወያኔዎች መታወቂያቸው ላይ ያለውን ብሔር ከትግሬነት ወደ ኦሮሞነትና አማራነት ለመለወጥ ነው ተብሏል፡፡

Demonstrators chant slogans while flashing the Oromo protest gesture during Irreecha, the thanksgiving festival of the Oromo people, in Bishoftu town, Oromia region, Ethiopia, October 2, 2016. REUTERS/Tiksa Negeri

Demonstrators chant slogans while flashing the Oromo protest gesture during Irreecha, the thanksgiving festival of the Oromo people, in Bishoftu town, Oromia region, Ethiopia, October 2, 2016. REUTERS/Tiksa Negeri

አንድ ከቀበሌ መጣሁ ያለኝ የማይዋሸኝ ትልቅ ሰው – ትልቅ ፈጣሪ ብቻ መሆኑ በታሳቢነት ተይዞልኝ – እንደነገረኝ ከሆነ እጅግ በርካታ ትግሬዎች በሰሞኑ የኦሮሚያና የዐማራ ግርግር ከመደናገጣቸው የተነሣ መታወቂያቸውን ወደሌሎች ዘውጎች እየቀየሩ ነው፡፡ በዚህ የመታወቂያ ለውጥ ሰበብ የአዲስ አበባ ቀበሌና ወረዳ ጽ/ቤቶች ቅጥረ ግቢ ጠጠር ቢወረወር ማረፊያ የለውም ይባላል፡፡

“ፊቱን ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ…” ይባላል፡፡ ቀና ቀናውን ደጋግሞ ማሰብ ቀድሞ ነው፡፡ አንድ ነገር ከሆነ በኋላ መሯሯጥ ብዙም አይጠቅምም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ መረን የለቀቀ ጠባይን በጊዜው ማረምና ማስተካከል ይገባ ነበር፡፡ በፊት “እዩኝ እዩኝ” ከማለትና ኋላ ላይ አሁን እየታዬ እንዳለው “ደብቁኝ ደብቁኝ” ከማለት አስቀድሞውኑ በትክክለኛ አቅጣጫ መጓዝ ይቻልና ይገባም ነበር፡፡ አሁን በጣም የመሸ ይመስለኛል፡፡ ለ25 ዓመታት እላዩ ላይ ሲጨማለቁበት የከረመ ሕዝብ አሁን ሲብስበትና ሞትና ስደቱ፣ ስቃይና እንግልቱ ሲበዛበት የመከራና የስቃይ ምንጮቹን ሀብትና ንብረት ማቃጠል ይቅርና እነሱ ራሳቸውንም በዘነዘና አናት አናታቸውን ቢጨፈልቃቸው አይፈረድበትም – የደረሰበት ግፍ ወደር የለውምና፡፡ ሕዝቡ ተናግሯል፤”በምታምኑት ይሁንባችሁ ማሩን፣ ድሃም ሆነን በቀያችን እንድንኖር ፍቀዱልን፣ ሀብትና ንብረታችንን ግዴለም ውሰዱት – በሕይወት የመኖር መብታችንን ግን እባካችሁ አክብሩልን” እያለ ግማሽ ምዕተ ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ፈሪና ቦቅቧቋ ተብሎ እስኪሰደብና መሣቂያ መሣለቂያ እስኪሆን ድረስ ተንበርክኮ ወያኔ ትግሬዎችን ለምኗል፤ አስለምኗልም – ስለዚህም በዚህ በአሁን እርምጃው “አይዞህ፤ በርታና ግፋበት! ለነዚህ የሲዖል ትል ወያኔዎችና ደጋፊዎቻቸው ይህም ሲያንሳቸው ነው!” ብሎ ሊያደፋፍር የሚቃጣ ወገን አይኑር እንጂ “ለምን እንዲህ አደረግህ” ብሎ ማንም ሕዝቡን ሊወቅሰው አይገባም፤ እንኳንስ በጨዋ ደንብ እየመረጠ ለሚያወድመው የመዥገሮች ንብረት ከዚህ በላይ ቢሄድም የግፈኞቹ ጥጋብ ያስከተለው መርገምት ስለሆነ ማንም በሕዝ መፍረድ አይችልም – ጎርጉረህ ጎርጉረህ ለምታወጣው ግማት ተጠያቂው አንተ ራስህ እንጂ ሌላ ወገን አይሆንም – በምን ዕዳው? በጊዜው ሰሚ አጣን እንጂ እኛም ብዙ ጩኸናል፡፡ አንጎላቸውን ሞራ የሸፈነባቸው ጥጋበኛ ወንድሞቻችን ይሠሩትን አጥተው ሕዝብና ሀገር ላይ ያን ያህል የበደልና የግፍ ደለል ሲከምሩ መቆየታቸው ምን ሊያስከትል እንደሚችል ለነሱ ቢሰወር ለኛ ግልጽ ነበር – ማንኛውም ጨለማ ሌሊት ሳይነጋ እንደማይቀር የማወቅን ያህል ቁልጭ ብሎ የሚታይ ሃቅ ነበርና፡፡

አሁንም የግፍ ብድሩ መከፈል ተጀመረ እንጂ አላለቀምና እግዜሩ በቀላሉ ይማረን፡፡ ደግሞም አንድ አይደለም 30 ዐዋጅ ቢያውጁ ከላይ የታዘዘን መቅሰፍት ሊያስወግዱት አይችሉም – ብቸኛው የመዳኛ መንገድ የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስና እውነተኛ ድርድር ማድረግ ነው – ከወያኔ ጋር ድርድር ሊኖር እንደማይችል ግን ነጥብ ይያዝልኝ – እንዲህ የምለው በየዋህነትና ምናልባትም በተዘዋዋሪ አንዳች ዘዴ ካለ ብዬ ነው – ለምሣሌ ለነገብሩ አሥራትና ለነአረጋሽ አዳነ ጉዳዩ ተላልፎ የሚሰጥና በነሱ አማካይነት ምናምን ነገር…፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው የኃይልም በሉት ጊዜ ለመግዛት የሚደረግ የማጭበርበር ሥልት ሁሉ ለበለጠ መላላጥና ለሕዝብና ሕዝብ መቃቃር በር ከመክፈት ባለፈ ፋይዳ የለውም – መጽሐፍ ምን አለ? “ኢይድኅን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ” – ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም – ሌላስ? “ቦዕ ጊዜ ለኩሉ” – ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለዚህ ለዚህማ ቁጥር ሥፍር የሌለው የደርግ ሠራዊትስ ያን ሁሉ ዘመናዊ መሣሪያ ይዞ መች እግር አውጭኝ ይፈረጥጥ ነበር? ቀን አያዘምብልብህ – ካዘነበለ አዘነበለ ነው፤ መመለሻም የለው፡፡ ለማንኛውም በወያኔ የደረሰው ጭቆና ዓለም የማታውቀው እጅግ ከባድ ነበር – የሚደርሰው የዕዳ ክፍያም እንዲሁ ዓለም የማታውቀው እጅግ አሰቃቂ ይሆናልና ይህን የድሃ ምክር የሚሰማ ይስማ!! ሳይቃጠል በቅጠል ከተቻለ ደግ ነው፡፡ አለዚያ በኔና በናንተ ይቅር እንጂ “እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን፤ ያመዱ ማፍሰሻ ሥርፋው ወዴት ይሆን” እያለ የጎንደርና የጎጃም ገበሬ እየፎከረ መሆኑን ሹክ ያለኝ ሰው አለና የወደፊት ጉዟችን እሾሃማ ነው፤ እንዲያውም የዚህ ፉከራ የኦሮምኛ ትርጉም በኦሮሞው ገበሬ መሀልም ተስፋፍቶ እንደቀጠለ ሰምቻለሁ፡፡

መታወቂያን በሚመለከት እኔ እንኳን በቅርብ ጊዜ የጻፍኩት አንድ አቤቱታ አለ፡፡ “በመታወቂያ ላይ ብሔራዊ ማንነት ይጻፋል እንጂ ጎሣና ነገድ አይጻፍም፤ እንዲያ ከተደረገ ለዘረኞች ጥቃት ግማሽ ሥራ እንደመሥራትና እነሱን እንደመርዳትም ነውና ዜጎችን በቀላሉ ለጥቃት መዳረግ ነው…” ብዬ አቤት ብያለሁ፡፡ ይሄውና ጊዜው ደረሰ፤ ዕብሪተኞቹ የዘሩትንም ማፈስ ጀመሩ፡፡ ግን ማን ተጎዳ? ማንስ ተጠቀመ? በመሠረቱ በዚህ ሂደት የሚጎዳ እንጂ የሚጠቀም የለም፡፡ በወረት ፍቅር የታወሩ፣ በዘረኝነት ዛር የሚያጎሩ፣ በጎጠኝነት የስሜት ስካር የደነዘዙ ቆሻሻ ሰዎች በተከሉብን የብሔር ፖለቲካ ምክንያት እየተላለቅን ነው፤ አሁን ከመሸ በኋላ መታወቂያ ቢቀየር አንደበት አይለወጥም፤ መታወቂያ ወረቀት ቢቀየር እውነት አትሰረዝምና ማንም ቢሆን ዘርቶ ካሳደገው ጌሾና አርሞ ኮትኩቶ ለመኸር ካበቃው እንክርዳድ የተዘለለ ጠላ መቃመሱ አይቀርም፡፡ ወዮ ለምሥኪን ዜጎች! ወዮ ምንም ጥቅም ሳይደርሳቸው መከራና ፍዳው በስማቸውና በዘውጋቸው ምክንያት ለሚደርስባቸው! ለኢትዮጵያ ወዮ በሉ ወገኖቼ፡፡

በልማድ ዞን ዘጠኝ  ይባል የነበረው የብዙዎቻችን ትልቁ እሥር ቤት ከትናንትናው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ በኋላ ወደ ስምንቱ ዞኖች ተቀላቀለ፡፡ በቃሊቲው ዘብጥያ ስምንት ዞኖች እንዳሉና እኛ ከጠባቦቹ እሥር ቤች ውጪ የምንኖረው ዜጎች በዘጠንኛው ዞን መመደባችን የሚታወስ ነው – እንደቀልድ ግን እውነት የሆነ እውነት፡፡ አሁን ግን ሁላችንም እኩል የምንሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይህም ከአሁን በኋላ እስካሁን ጭል ጭል ትል የነበረችው በአንጻራዊ አነጋገር እንደመልካም አጋጣሚ የምትጠቀስ ትንሽዬ በነፃነት የመንቀሰቅ መብት በዚህ ዐዋጅ መሠረት ድራሽዋ ጠፍቷል፡፡ ከእስካሁኑ በከፋ ሁኔታ የምንገደልበት፣ የምንሰቃይበት፣ የምንታሰርበት፣ የምንበረበርበት፣ እንደዐይጥ በየተገኘንበት ሥፍራ የምንጨፈጨፍበት፣ ያለችን ሀብትና ንብረት በጠራራ ፀሐይ የምትዘረፍበት … አዲስ ዐዋጅ ታውጆ ለተግባራዊነቱ አጋዚዎች ነቅተው የሚጠባበቁበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

ብቻ ለማንኛውም እግዚአብሔር ይሁነን፡፡ ኢትዮጵያዊቷ አርማጌዴዎን ሰተት ብላ እየመጣች ነው፡፡ ሀገርና ሕዝብን በገንዘብ የምትለውጡ ሁሉ ወዮላችሁ! ለእውነት ያልቆማችሁ ወገኖች ሁሉ የምትበጠሩበት፣ ያጠራቀማችሁትን ገንዘብ የማትበሉበት የመከራ ዘመን እየመጣ ነው፡፡ አስታውሱ – ይሁዳ በዘመኑ አንቱ የተባለ ትልቅ ክፍያ – 30 ዲናር – ከክርስቶስ ጠላቶች ከጻፎች ፈሪሣውያንና ሰዱቃውን ተቀብሎ ጌታውን በመሳም አሳልፎ ሸጠ፡፡ ኋላ ላይ ግን ተፀፀተና ከገንዘቡ አምስት ሣንቲም እንኳን ሳያጎድል ራሱን ሰቅሎ ገደለ፡፡ ያም ገንዘብ በአይሁዶች እጅ ገባና መሬት ተገዛበት – የደም መሬት ተባለ – አኬልዳማ! አለቀ፡፡ ተበልቶ ዕዳሪ፣ ተጠጥቶ ሽንት ለሚሆን ምድራዊ ሀብት ብለን ዘላለማዊት የሆነች ነባቢት ነፍስን፣ በአርአያ ሥላሤ የተገነባ ተክለ ሰውነትን አለጊዜው ብናጠፋ ወይም ለመጥፋቱ ምክንያት ብንሆን ጌታ በቀላሉ የሚለቀን ወይም ሂሳባችንን ሳናወራርድ እንዲሁ የሚምረን እንዳይመስለን፡፡ የጌታ መሐሪነት የማይቀጣጠቡት ሆኖ ነገር ግን የእጃችንን የማግኘቱን ጉዳይ ማናችንም ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ጌታ ሌላ ምን ሥራ አለው? ሥራው ይሄው ነው – መፍረድ፡፡

ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውንን በመሸጥ በሀብት የከበራች አሁኑኑ ንስሃ ግቡና ወደሕዝብ ተመለሱ፡፡ ይህችን ጠባብ ዘመን የሚያልፍ እጅግ ጥቂት ሰው ነው – ያም የታደለና ከወንጀልና ከክፉ ሥራ ራሱን የገታ ነው፡፡ ወደ ሆድ ወርዶ የመሸገ ጭንቅላት በአስቸኳይ ወደቦታው ይመለስ – የሰማ ያሰማ፡፡ ይህን መልእክት በቻላችሁት መንገድ ሁሉ ለሁሉም አዳርሱልኝ፡፡ ይህ መልእክቴ ራዕይ ወይም ንግርትና ሟርት ወይም ትንቢት አይደለም – ማንም የዋህ ልቦና ያለው መሬት ላይ በጉልኅ ቀለማት ተጽፎ ሊያነበው የሚችል ግልጽ አውነት ነው፡፡ አጉሊ መነጽር ሳያስፈልገን በግልጽ በምናየው አደጋ መጠቃት የለብንምና ለሁላችንም አስተዋይ ልቦና ይስጠን፡፡

 
Received on Tue Oct 11 2016 - 15:44:40 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved