Goolgule.com: የ11ኛው ሰዓት አዋጅ እና ሕዝብ "ለመኖር ብቸኛው አማራጭ ሌላው እንዲኖር መፍቀድ ነው"

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 11 Oct 2016 13:51:37 +0200

የ11ኛው ሰዓት አዋጅ እና ሕዝብ

"ለመኖር ብቸኛው አማራጭ ሌላው እንዲኖር መፍቀድ ነው"
tplf military agazi
 
 

ስለ አስቸኳይ ግዜ አዋጁ የጠየቅኩት አንድ የአዲስ አበባ ወጣት ምላሽ አስገረመኝ። “የምን አዋጅ?” ነበር ያለው።

“ትላንት የታወጀው።”

“አቦ መስሚያችን ጥጥ ነው። … ሚሰማ የለም” አለኝ።

ሃይለማርያም ደሳለኝ ዝም ብለው ኖሯል የደከሙት!

“ለመኖር ብቸኛው አማራጭ ሌላው እንዲኖር መፍቀድ ነው።” ብለው ነበር የህንዷ ማህተመ ጋንዲ። እነሱ እየኖሩ ሌላው እንዳይኖር ለሚሹ ራስ ወዳዶች ትልቅ መልእክት ነበረው። ማስተዋል የተሳናቸው ግን “እኛ ብቻ እንኑር” ይህንን የማይቀበል በሙሉ ይጥፋ የሚለውን ጭፍን አመለካከት እንደ ብቸኛ ምርጫ ይዘውታል።

ይህ የ11ኛው ሰዓት አዋጅ “አለሁ፤ አልሞትኩም” ለማለት ካከልሆነ በስተቀር ምንም የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖረው እንገነዘባለን። አንድ በነፍስ ዉጪ፤ ነፍስ ግቢ ሁኔታ ያለ አካል ከገባበት የፖሊቲካና ወታደራዊ አጣብቂኝ ዉስጥ ለመዉጣት መፍጨርጨሩ ግድ ነው። በመጨረሻ በራሳቸው ሰንሰለት ተጠፍረው ከዚያ እስር ለመውጣት የሚወስዱት እርምጃ  አጣብቂኝ ውስጥ አሰመጣቸውና በአጭሩ የተነፈሱበት ንግግር ነው። ከዚያ አያልፍም።

አዋጁ የሚገድባቸው መብቶች እና የሚያከናውናቸው ተግባራት ገና በዝርዝር ይፋ አልሆኑም። ግን ተግባሩ ከአዋጁ በረጅም ርቀት ቀድሟል። ሰራዊቱ ህዝቡን እንዲያረጋጋ ሳይሆን ይልቁንም ሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ ማንኛውንም የሃይል እርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ ከተሰጠ አንድ ወር አልፎታል።

በቅርቡ በቱርክ እንደተደረገው – አለም አቀፍ ህግ ያሰፈራቸውን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ለመጣስ አንባገነን መንግስታት የሚጠቀሙበት መሳርያ ነው – አስቸኳይ ግዜ አዋጅ። እኛ ጋ ግን እነዚህ ድንጋጌዎች አንጻራዊ ሰላም በነበረበት ግዜ እንኳን አላየናቸውም። አዋጁ ወጣም አልወጣ አሁን ባለው ውጥንቅት እና በፖለቲካ አየሩ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይታይም። የጅምላ ግድያውን ሕጋዊ ሽፋን ሰጡትም አልሰጡት ዘር ከማጥፋት እና ሰብአዊነት ላይ ከሚፈጽሙት ወንጀል ራሳቸውን አያነጹም።  ችግሩ ከእጅ ወጥቷል።

ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሏቸው የነበረው የማህበራዊ ሜዲያው ነበር። ከቁጥጥር ውጭ የሆነውን ይህንን ጉዳይ እየዘጉ መክፈቱ በምእራቡ አለም አስወቀሳቸው እንጂ እነሱ እንዳሰቡት አንዳች አልፈየደም። ኢንተርኔትን ጨርሶ ለመዝጋትና ለዚህም ሕጋዊ ሽፋን መስጠት ተብሎ ይጠቅም ይሆናል ይህ አዋጅ። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንኛውንም ዓይነት የመገናኛ ዘዴ የመዝጋት ስልጣን አለው!” ብለውናል። አስተዋይ ቢሆኑ ኖሮ ከስልክ እና ከኢንተርኔት  ይልቅ ህዝብ ላይ የደቀኑትን አፈሙዝ ነበር መዝጋት!

አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የአዋጁን ዜና ሲዘግቡ “ተቃውሞውን ለማስቆም”  ብለውታል። 100 ፐርሰንት የመረጣቸው ሰው ላይ እንዲህ አይነት አዋጅ ለምን እንዳወጡ የሚጠይቅ ግን የለም። በጥይት እና በመርዝ ጭስ ያልቆመው አመጽ እንዴት ሆኖ በአዋጅ ይቆማል የሚልም አልተገኘም?… አዋጅማ ተለመደ። ሕወሃቶች ጥርሳቸውን የነቀሉበት ጉዳይ ነው። “አስቸኳይ” የሚለው ሃረግ ከፊቱ ገባበት እንጂ ሃገሪቷ ላለፉት ሁለት አስርተ-አመታት በህግ ሳይሆን በአዋጅ ነው እየተገዛች ያለችው። የፕሬስ አዋጅ፣ የጸረ-ሙስና አዋጅ፣ የጸረ ሽብር አዋጅ፣ የግብረሰናይ ተቋማትን የሚያግድ አዋጅ፣ … የሰው ልጅ መብት በሙሉ እነሱ በሕዝብ በሚጭንዋቸው አዋጆች ታስረዋል። ይህንን አዋጅ ከሌሎቹ አዋጆች የሚለየው ሃይለማርያም ደሳለኝ በቴሌቭዥን ወጥተው ምጥ እንደያዛት ሴት አዋጁን መንበባቸው ብቻ ነው።

አረፋፍዶ የተነገረው ይህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልሰማውም። ሕዝቡ የህወሃት ፕሮፓጋንዳ ጣብያዎችን ከዘጋ ሰነባበተ። በማህበራዊ ሜዲያ እንዳይሰማው የኢንተርኔት አገልግሎቱን ቆርጦታል። አዋጁ ለማን እንደተነገረ ግልጽ አይደለም።

እንደማንኛውም አንባገነን ገዥ እነሱም ዘላለም እንቆያለን ብለው ያስቡ ነበር። ግና ነገሮች ሁሉ ፈጠኑ።  ሕዝብ በረጅም ቀደማቸው።እጃቸው ላይ የህዝብ ሃብት እና ደም አለ። ከዚህ አምልጦ ለመውጣት ግዜ መግዛት ግድ ነው። አንድም ቀን ዕድሜ ነው ይላሉ አበው። ግዜ እንደ ጉቶ ሲያጥርባቸው፣ ትንሽ ግዜ ለመግዛት መፍጨርጨር ግድ ነው። ሰአታቸው አልቆ በባከነች ደቂቃ ውስጥ እንዳሉ ተገንዝበዋል። ግን ስልጣን ለመልቀቅም ሆነ ሃገር ጥሎ ለመጥፋት አልተዘጋጁም። በራሳቸው ሰንሰለት ተጠፍረው ከዚያ እስር ለመውጣት የሚያደርጉ አጣብቂኝ ሁለት አማራጭ ሲኖር ለምርጫ የሚከብድ አጣብቂኝ ይኖራል።

እንደዚህኛው ጫን ያለው ባይሆንም ምርጫ 97 ወቅትም ተመሳሳይ አዋጅ ወጥቶ ነበር። ሟች ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በቴሌቨዥን ቀርበው የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና ሌሎች ተያያዥ መብቶች ለአንድ ወር የተገደቡ መሆናቸውን ተናገሩ። ይህንን እና አዲሱን አዋጅ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር አለ። ሁለቱም ራሳቸው ያወጡትን ህገ-መንግስት የሚጥሱ ህገ-ወጥ አዋጆች ናቸው። ሀገሪቱን እያስተዳደርን ያለንበት የሚሉት ህገ-መንግስት በአንቀጽ 93 ያሰፈረውን ድንጋጌ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ውጭ ወረራ አልያም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት  በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደንግጎ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኝላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ ሲጸድቅ ነው።

ከህዝብ ጋር እየተላተሙ ወደማይፈታ ችግር ውስጥ ራሳቸውን እየዘፈቁ ሽንፈትን ሲከናነቡ – የራሳቸውን ህግ እየጣሱ ሕዝብን ለመጨረስ የተነሱ እነዚህ ሃይሎች አንባገነን የሚለው ቃል አይገልጻቸውም። ካምቦዲያን አንቆ ይዞ የነበረው የፖልፖት ካመር ሩዥ እንኳን እነዚህ የሚያደርጉትን አላደረገም። ቺሊን እና ሕዝቧን የገደለው አውግስቶ ፒኖሼም አይደርስባቸውም። የመካከለኛው አፍሪካ ቦካሳ እና ከኢድያሚን ዳዳ የሚለዩት እነዚህ እስካሁን የሰው ስጋ መብላት አለመጀመራቸው ብቻ ነው።

ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል። ይህንን የጋለ ፍላጎት ለውጥ እንጂ ሌላ ሃይል አይመልሰውም! 25 ዓመት በአንድ የዘረኛ ፖሊሲ መገዛት ሰልችኦታል። ጥሩም ነገር ቢሆን ከመጠን ካለፈ መጥፎ ነው። ይሉናል ከበደ ሚካኤል።

ክንፉ አሰፋ

Received on Tue Oct 11 2016 - 06:30:41 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved