Goolgule.com: የኦሮሚያ ሰነድ – አዲሱ ቃል ኪዳን? አማራ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ … እንዴት?

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Mon, 10 Oct 2016 15:24:48 +0200

የኦሮሚያ ሰነድ – አዲሱ ቃል ኪዳን?

አማራ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ … እንዴት?
charter

ጊዜ ገድቦ መናገር ይከብድ ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ አይቀሬ ስለመሆኑ ክርክር የለም (አንዳንድ የወያኔ አንጋሽ ምዕራባውያን ባለሙያዎች በጥቂት ወራት ይተምኑታል)። ይህ እውነት ቢሆንም አንዳንድ “የፖለቲካ መክለፍለፎች” ሊወድቅ የተቃረበውን አገዛዝ እንዲውተረተር ዕድል ሊሰጠው ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ወገኖች ከያቅጣጫው ብቅ እያሉ ነው። የስጋታቸው መንስኤ ደግሞ በዋናነት የግልጽነት፣ ያለመተማመን፣ የውድድርና “ጊዜን” የመጠቀም ተራ እሽቅድምድም እንደሆነ እነዚሁ ስጋት የገባቸው ክፍሎች ይናገራሉ

ከየአቅጣጫው የሚሰሙት የ“ሽግግር” ዜናዎች፣ ዳር ዳሩን በለሆሳስ ይሰማ የነበረው “የሃሜት በሽታ” ገልጠውታል። በዚሁ መነሻ ይመስላል ለኦሮሚያ የሽግግር ሰነድ እንደሚዘጋጅ ይፋ መሆኑንን ተከትሎ ሰፊና ግልጽ ያለ መልስ ከሚመለከታቸው የእነ በቀለ ገረባ ወኪሎች ህዝብ እየጠበቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ “የቱ መቀደም ነበረበት?” የሚሉ አሉ።

የኢትዮጵያን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሰንደቅ ይዞ የሚታገለው “አማራ”፣ በብሔር ደረጃ ወይስ በብሔራዊ ደረጃ ቻርተር ሊያረቅ? በሚል ግራ የተጋባ ጥያቄ የሚያቀርቡ ክፍሎች፣ “ሁሉም ብሔረሰቦች በግል ሊሮጡ?” ሲሉ ይጠይቃሉ። ሁሉንም የሚያገባባ ሰነድ ማዘጋጀትና ውሳኔውን ለህዝብ መተው እንደሚሻል በመጠቆም ያገባናል የሚሉ ወገኖች በአንድነት መክረው አንድ የመሸጋገሪያ ሰነድ ለማዘጋጀት አለማሰባቸው ያስገረማቸውም አሉ። ሁሉም ያለውን ቢል አሁን ይፋ የሆነው የኦሮሚያ የሽግግር ቻርተር ጉዳይ አንኳር ጉዳይ ለመሆን በቅቷል።

ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ቢቢኤን ያነጋገራቸው በኬተሪንግ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሕዝቅኤል ገቢሳ ግልጽ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል። እንደ እሳቸው አባባል ዛሬ “አማራ የለም ለምን ትላላችሁ?” የሚሉ ክፍሎች ተነስተዋል። “የጎንደር ትግል” እየተባለ ትግሉን የማሳነስ ጉዳይ አግባብ እንዳልሆነ የሚናገሩት ክፍሎች “ትግሉን የአማራ ትግል” እንዲባል እየወተወቱ ነው። ዶ/ር ሕዝቅኤል አያይዘውም “ተወደደም ተጠላም አሁን ውጤት እያመጣ ያለው በብሔር እየተደራጁ ያሉ ሃይሎች ናቸው። ስለዚህ በብሔር ደረጃ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ግድ ነው” ሲሉ ቀዳሚው ተግባር ሁሉም በ“የቤቱ” ስራውን ሰርቶ በአገር ደረጃ አንድ ማዕድ ላይ መቅረቡ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንዲህ ያለውን ዝግጅትና ውይይት ማድረግ አግባብነት ያለው፣ ዴሞክራሲያዊና ህጋዊ የሆነ መሆኑንን ያመለከቱት ሕዝቅኤል በኢትዮጵያ ደረጃ የሚደረግ ውይይት ስለመኖሩም ጠቁመዋል። ይህ አካሄድ ስርአት የጠበቀ ሆኖ ሳለ የተለያየ ስም መስጠት፣ ጥርጣሬን፣ አለመተማመንን ማንገስና መፈራራትን መስበክ አግባብ አለመሆኑንን አስረድተዋል። አያይዘውም አሁን በተቀጣጠለው የሕዝብ ትግል “ኦሮሚያ ትገንጠል” የሚል አላማ የሚያራምዱ ሃሳቦች ጭራሹኑ እንደማይሰሙ ነው ያመለከቱት።

የታሪክ ምሁሩ ሕዝቅኤል ገቢሳ ኦሮሞ የኢትዮጰያ መሰረት መሆኑን፣ ከጣሊያን ወረራ ጀምሮ ኦሮሞዎች አገርን ከወራሪ ሃይል ለመታደግ ህይወታቸውን መከስከሳቸውን፣ በኤርትራ፣ በሶማሌ ወረራና አሁን በቅርቡ በባድመ ህይወታቸውን መክፈላቸውን አንስተው እንዴት ይህ ህዝብ አይታመንም የሚል እንደምታ ያለው ማሳያ አቅርበዋል። እሳቸው እንደሚሉት ተራ ጥርጣሬና አለመተማመን ካልሆነ በስተቀር ተከባበሮ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አይቸግርም።

በዚሁ ቃለ መጠይቅ ላይ ሌላ ተጋባዥ የነበሩት አቶ ጃዋር መሐመድ በበኩላቸው “ቅድመ ዝግጅት ካልተደረገ አደገኛ ነው” ሲሉ ግብጻውያን አብዮት ካካሄዱ በኋላ ሌላ አምባገነን እጅ ላይ መውደቃቸውን፣ የቱኒዚያ የለውጥ ሃይሎች አስቀድመው ዝግጅት በማድረጋቸው የተሳካ ሽግግር ማድረጋቸውን ዋቢ ያደርጋሉ። ሊቢያ መተራመሷንም ያወሳሉ። ስለዚህ ሁሉም፣ አማራዎችን ጭምር የራሳቸውን ዝግጅት አድርገው ስምምነቱ “በብሔራዊ ደረጃ መሆን አለበት” የሚሉት ጃዋር፣ በአገር ደረጃ ያለውና በብሔር ደረጃ ያለው አስተሳሰብ መጥራት እንዳለበት ማሳሰቢያ አዘል ሃሳብ ሰንዝረዋል።

ከለውጡ መጋጋል ጋር ግንባር የሆኑት ጃዋር መሐመድ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ሃላፊ ከመሆናቸው በዘለለ የትኛውን ተቋምና የፖለቲካ ድርጅት ወክለው መግለጫ እንደሚሰጡ ግልጽ አይደለም። አቶ ጃዋር ራሳቸውን ስልጣን የማይፈልጉ አክቲቪስት መሆናቸውን በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ በወሳኝነትና በሙሉ ስልጣን የሚሰጧቸው መግለጫዎችና አስተያየቶች ብዙ ጊዜ አነጋጋሪ ናቸው።

በርካቶች ሲሉ እንደሚሰማው አንዳንዴ ሰፊ ምክክርና ማስተዋል የሚሹ ጉዳዮችን ጃዋር መሐመድ እንደ ቀላል ጉዳይ ይናገራሉ። እነዚሁ ክፍሎች ጃዋር አሁን ያላቸውን የነቃ ተሳትፎ ባይነቅፉም እንደ በሰለ ሰው ንግግራቸውና አቀራረባቸው የሰሚዎችንና የጉዳዩን ባለቤቶችን ቀልብ ሊስብ ይገባል ባይ ናቸው። እንዲያውም አካባቢያቸው ያሉ ፖለቲከኞች በቁልፍ ጉዳዮች ላይ እሳቸው ስለሚሰጡት መግለጫዎች ምክክርና ጥንቃቄን እንዲያደርጉ ይመክራሉ። እንደ መሪም ማብራሪያቸውን በተዋበ መንገድ እንዲያስተላልፉ እንዲመክሯቸው የሚያሳስቡም አሉ። ጃዋር ከስሜት በራቀ መልኩ በግልጽ የቀረበላቸውን ምክር ቢቀበሉ የእነ በቀለ ገርባን አሻራ ሊከተሉ የሚችሉ ሰው እንደሚሆኑም ያመለክታሉ።

ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት እሳቸው በሚመሩት ሚዲያ የሚቀርቡ የኦሮሞ ምሁራን በርጋታና በፍጹም ሊደመጥ በሚችል መልኩ የሚያቀርቡት ገለጻ የተዛነፉ የሃሳብ ሚዛኖችን እያስተካከሉ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ ህዝብ ወደፊት መክሮና ዘክሮ ውሳኔ በሚሰጥባቸው ጉዳዮች ላይ አስቀድሞ በስልጣን መናገር አድሮ ከውስጥም ከውጭም አደጋ ሊጋብዝ እንደሚችል አስተያየት እየተሰጠ ነው። ለህወሃት የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ የሚዳርግና ጅምራቸው መልካም የሆኑ አካሄዶችንም የሚጎዳ ሊሆን እንደሚችል ግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባ የሚያሳስቡ ጥቂት አይደሉም።

በቅንጅት የፖለቲካ ወቅት ሁሉም አመራሮች እንዳሻቸው መግለጫ እንዲሰጡ መፈቀዱ መጨረሻ ላይ ለህወሃት ቅስቀሳ ተጋላጭ እንዳደረጋቸው፣ ሚዲያዎችም አጀንዳ ከማስያዝ፣ ሁኔታዎችን ከመዘገብ፣ ከመተቸትና ሚዛናዊ ዘገባ ከማቅረብ በዘለለ የትግሉ ስትራቴጂ ነዳፊ የመሆን ጣለቃገብነት ማሳየታቸው ትግሉን እንደጎዳው ያስታወሱ ክፍሎች፣ አሁንም ተመሳሳይ ጥፋት እንዳይሰራ ይፈራሉ። ፍርሃቻቸውንም ሲገልጽ የሚዲያ መሪዎች “ከመክለፍለፍ ፖለቲካ” ራሳቸውን በማግለለ የፖለቲካ ውሳኔዎችን ለፖለቲከኞች እንዲተውና የህዝብን ሃሳብ በነጻነት እንዲያራምዱ ይመክራሉ። ክርክሮችን በማዘጋጀት ህዝብን ግራ የሚያጋቡ ጉዳዮችን  ማጥራት ላይ ቢያተኩሩ እንደሚሻል ይጠቁማሉ። በሌላም በኩል  ጃዋር እንዳሉት የሰዎችን ወይም የድርጅቶችን ሃሳብ ካለመረዳት ውስን ሃረጎችን በመምዘዝ ማጸጽ አደጋው የከፋ ስለሚሆን ጥንቃቄ ሊወሰድበት የሚገባ አቢይ ጉዳይ ስለመሆኑ ይናገራሉ፤ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዳለ ሆኖ አስተያየት ሰጪዎችም ይህንኑ አመለካከት ይጋራሉ!!

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ውክልና ሳያገኙ አገርና መጪውን ትውልድ ችግር የሚያወረሱ ልሂቃኖች እንደሆኑ ባለፉት የለውጥ ሂደቶች ላይ ታይቷል። ሁሉንም ወደኋላ ብንተወው እንኳን ህወሃት የቅርብ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። በራሳቸው የልደት ታሪክ ህወሃት ዱር ቤቴ ያለው ደርግ ወደ ስልጣን በመጣ በዓመቱ አካባቢ ነበር። ደርግ አዲስ አገዛዝ ሆኖ ሳለ እነሱ “የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር” ብለው በረሃ ሲገቡ ህዝብ ስለመገንጠል ጉዳይና አጀንዳ የሚያውቀው ነገር አልነበረም። የራሳቸው አባላት በተለያዩ ጊዜያት እንደመሰከሩት ሁሉም የሆነውና የተጠነሰሰው ህዝብ ውክልና ሳይሰጥ፣ ህዝብ ሳይጠየቅ፣ ከጥቂት ቅጥረኞች በስተቀር የሸፈቱት ራሳቸው በቂ ግንዛቤ ሳይዙ ነበር። ዛሬም ለዚህ ነው ያለፈውን ስህተት ላለመስራት ጥንቃቄ ሊወሰድ ይገባል የሚባለው። ሁሉንም ጉዳይ በጥቅሉ በአገር ደረጃ አዘጋጅቶ ቀሪውን ጉዳይ ለህዝብ መተው ከታሪክም፣ ከኪሳራም፣ በተለይም ከኅሊና ህመም ያድናል በሚል ርጋታና ማስተዋል እንደሚያሻ በስፋት እየተነገረ ነው።

የኦሮሚያ ቻርተር – መሠረታዊ ሃሳቦች

አሁን በኦሮሚያ ትግሉ ያመረረበት ደረጃ ደርሷል። ይህ ትግል መሰባሰብና ወደ አንድ የዕዝ ቋት /ኮማንድ ፖስት/ መግባት እንዳለበት ታምኗል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ አንድ ሁሉንም በኦሮሚያ ክልል ላይ ያገባኛል የሚሉትን ድርጅቶች ሊገዛና ሊመራ የሚችል ቻርተር ማዘጋጀት ግድ ሆኗል። ጥያቄው ያለው ይህ ቻርተር ከሌሎች ህብረ ብሔር ድርጅቶች ጋር ግንባር/የጋራ መድረክ ፈጥረው የሚሰሩትን የኦሮሞ ድርጅቶች እንዴት ያስተናግዳቸዋል? የሚለው ነው። ምክንያቱም ለጎልጉል መረጃ እንዳቀበሉ ክፍሎች ግርድፍ ሃሳብ፤ ቻርተሩ ማንም ድርጅት በቻርተሩ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ፣ በግሉ ከማዕቀፉ ውጭ ካሉ የፖለቲካ ተቋማት ጋር ስምምነት ማድረግን በተመለከተ ድርጅታዊ ነጻነቱ ላይ ገደብ የማድረግ ሃሳብ ስላለበት ነው።

የቻርተሩ “ነፍስና ልብ” የሚባሉትን ሁለት ጉዳዮች እንያቸው። ለጎልጉል መረጃ የሰጡና ከጉዳዩ ጋር ቅርብ ግንኙነት ያላቸው የብሔሩ ተወላጅ እንዳሉት መሳሪያ ያነገቡና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ድርጅቶችን በሁለት ከፍሎ የሚያየው ቻርተር ሁለቱንም ዓይነት ሃሳቦችን እንደ ፍጥረታቸው በጋራ ይገምዳቸዋል። አገር ውስት በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት ህወሃት እንዲታዘዙ ከሚያስገድዳቸው አንጻር ጉዳያቸው በልዩ መንገድ የሚታይ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት ግን በአጠቃላይ የኃይል አማራጭ በመያዝ ትግል ሜዳ ያሉትን በአንድ፣ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉትን በሌላ ከፍሎ የሚገምዳቸው ይህ ቻርተር ጊዜያዊ ይሆናል።

መሳሪያ ያነገቡ ሁሉ ጠላታቸው ወያኔ ከሆነ፣ እሱን ለማውረድ የሚታገሉ ከሆነ የማያስማማቸው ነጥብ ለኦሮሞም ሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ አይደለም። ሁሉም በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉት የኦሮሞ ድርጅቶች በሙሉ ሃሳባቸውና እምነታቸው ወያኔን በሰላማዊ መንገድ መጣልና ህዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ከሆነ እነርሱንም የማያስማማቸው ጉዳይ ግልጽ አይደለም። በዚህ መነሻ ቻርተሩ እነዚህን ሁለት ዓይነት ኃይሎች ባንድ ገምዶ ለቻርተሩ እንዲገዙ ያደርጋቸዋል። ሌላ አጀንዳ እስከሌላቸው ድረስ!

በዚሁ መሰረት ቻርተሩ አንድ ድንበር ያለው ጊዜያዊ መግባቢያ ይሆናል። ይህንን ድንበርና ገደብ የሚያበጀውን ቻርተር መቀበልና ፈርሞ አባል መሆን ማለት በተቀመጠው ገዢ ህግ መመራት ማለት ይሆናል። ቻርተሩ መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ ሲተከል ከሁሉም ድርጅቶች የሚውጣጡ አስፈጻሚ አካላት ይኖሩታል። ተግባራዊ ሲሆን ማንኛውም ዓይነት ኅብረብሔራዊም ሆነ ብሔር ተኮር የፖለቲካ ድርጅት ከኦሮሞ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመስራት ግንኙነቱ በቻርተሩ ደንብ መሰረት ቻርተሩን እንዲጠብቁ ከሚሰየሙት ክፍሎች ጋር ይሆናል ማለት ነው።

ዝርዝሩን ለጊዜው በጥልቀት መተንተን ቢያስቸግርም ይህ ቻርተር የድርጅቶችን ውስጥዊ ነጻነት እንዳያንቅ ፍርሃቻ ስለሚኖረው ሊያከራክር እንደሚችል ይገመታል፤ እንደ መረጃው ሰው ግን በአገር ቤት በ“ህግ” ተመዝግበው የሚሰሩትንም ሆኑ  ከሌሎች ኅብረብሔርና የብሔር ድርጅቶች ጋር ግንባር የፈጠሩ  የኦሮሞ ድርጅቶች ጉዳይ ባግባቡ የሚስተናገዱበት አግባብ እንደሚኖር ይጠቁማሉ። እሳቸው ይህን ቢሉም ታዛቢዎች ይህ ጉዳይ አዳጋች እንደሚሆን ከወዲሁ እየተናገሩ ነው። በዚህም መነሻ ቻርተሩ ጠብመንጃ ያነሱት ላይ ቢያተኩር እንደሚሻል ይጠቁማሉ።

ሌላኛውና ዋናው ጉዳይ አገር ቤት ያሉትም ሆነ፣ በውጪ አገር ሆነው በትጥቅ ለመፋለም የወሰኑ ክፍሎች ሠራዊታቸው ወደ አንድ የዕዝ ማዕከል /ኮማንድ ፖስት/ እንዲካተቱ መታሰቡ ነው። ጃዋር መሐመድ ለቢቢኤን እንዳሉት ተመጣጣኝ ኃይል ያላቸው ክፍሎች ወደፊት ችግር ውስጥ እንዳይገቡ አስቀድመው ሃይላቸውን ሁሉ ወደ አንድ ዕዝ ማዕከል ማስገባታቸው አደጋን ያስቀራል። ይህ አስተሳሰብ ኦሮሚያ “መከላከያ ሠራዊት የመገንባቱን ሥራ ከወዲሁ አጠጠናቅቃ፤ አለያም ወጥ ሠራዊት ማደራጀት ትጀምር” እንደማለት ይሆናል።

በዚህ ጉዳይ ላይ አስመራ የከተሙት የኦነግ /ብዙ ኦነጎች አሉ/ አመራሮች ይፋ አስተያየት ባይሰጡም ቻርተሩን ከተቀበሉ ወታደራዊ ኃይሉ ወደ አንድ ቋት ሲገባ የኃይል አሰላለፍ ላይ ስምምነት ለመድረስ ቀላል እንደማይሆን የሚገምቱ አሉ። እዚህ ላይ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ በአገሪቱ የተቀናቃኝ ፖለቲካ ደርጅቶች ዘንድ ያለው ልብ የሚያደማ ጉዳይ ይነሳል። የፖለቲካ ፕሮግራማቸው ካንዱ የተገለበጠ የሚመስለው የተቃዋሚ ድርጅቶች እርስ በእርስ ሲላተሙና ህዝብን ተስፋ ሲያስቆርጡ የመኖራቸው ምሥጢራዊ ምክንያት ለማንም ዜጋ ግልጽ አይደለም። እንደውም ተስፋ አስቆራጮች ሆነው የኖሩ አሉ። አንዳንዶቹም ቲተርና ማህተም፣ በየወቀቱ የማይታደስ ድረገጽ ይዘው ከመንከላወስ ሳያልፉ መኖራቸውን የሚያውጁት ለመስራት የሚንቀሳሰቀሱትን ሲያወግዙና ሲኮንኑ ነው።

ዛሬም ኦሮሚያ ላይ ይህን “መበታተን” ያሉትን ጉዳይ ለማስወገድ የሚዘጋጀው ጉዳይ ከወዲሁ እንከን እንዳይገጥመው ፍርሃቻ አለ። አንድም “ከመክለፍለፍ”፣ አለያም ዓላማን ግልጽ ካለማድረግ የሚነሱ ጉዳዮች ግማሹን በጥርጣሬ፣ ግማሹን በግል የሥልጣን ስካር እንዳይከፋፍሉት የሚፈሩ፣ አሁን ብቅ ያሉና የረጋ ስብዕና ያላቸው ክፍሎች ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲመሩት ይመክራሉ። በተለይም ዶ/ር ሕዝቅኤል ገቢሳ፣ ዶ/ር ጸጋዬ አራርሣ፣ ዶ/ር አወል ቃሲም አሎና እነሱን መሰል ዜጎች ጉዳዩን በጥንቃቄ እንዲይዙት የሚወተውቱ ጥቂት አይደሉም።

ከመክለፍለፍ ፖለቲካ ክስረት፣ እንዲሁም የማይነሱበት ውድቀት እንጂ ሌላ ትርፍ የለም” የሚሉ ክፍሎች ይህ አሁን እየፈሰሰ ያለውን ደም፣ የእናቶች እምባ፣ የንጹህ ዜጎች ሰቆቃ የሚያሽር ታሪክን የሚቀይር ሃሳብ ከዚህ ትውልድ እንደሚጠበቅ እምነት አለ። አገራችን በደም ታጥባለች። ትኩስ ቁስል ላይ ነች። ወገን፣ ዘር፣ ጎሣ፣ ብሔር ሳይለይ ሐዘን ሁሉንም ስብሮታል። ታላቅ የሆነ ብሔራዊ መግባባት አለ። እዚህ የተደረሰው በቀላሉ አይደለም። እንደ ህወሃት መሠሪ አሠራር ሳይሆን ባጭሩ ሊባል በሚችል ጊዜ ይህንን ዓይነት መግባባት ላይ መደረሱ እንደ ታላቅ ድል ሊቆጠር ይገባል። ከዚህ ወደ ኋላ መመለስ በሕዝብ ደም መቀለድ ነው። ውጤቱም የዜሮ ድምር ጨዋታ ነው።

ባለፉት 25 ዓመታት ለመታዘብ እንደተቻለው በኢትዮጵያ የተመሠረቱና እስካሁንም እየተመሠረቱ ያሉት ድርጅቶች (በተለይ ጎሣዊ ትኩረት የያዙት) ሕዝብ “ተመሥረቱልኝ” ብሎ ጠይቆ ወይም ከሕዝብ ጋር ተማክረው ሳይሆን “እናውቅልሃለን” በሚል አስተሳሰብ ነው ራሳቸውን ያቋቋሙት። በዚህ እሳቤ ላይ በመመርኮዝ ተመሥርተው ሃሳባቸውን በፕሮፓዳንዳ መልክ በሕዝብ ላይ በመጫን ሕዝብ ያላሰበውን እንዲያስብ፤ ያልተመኘውን እንዲመኝ፤ ያልሆነውን እንዲሆን አድርገውታል፤ ስያሜና መጠሪያም ሰጥተው አሳንሰውታል። ከመተለቅ ማነስን አጀንዳቸው በማድረግ ድብልቁን ሕዝብ መኖሪያ አሳጥተውታል፤ ኢትዮጵያዊነትን አመናምነውታል። ይህ አሁንም እየሆነ ያለ ሃቅ ነው። በዘር መደራጀት የሚሠጠው የግል ጥቅም ቢኖርም ውጤቱን ግን እንደገና መመለስ እጅግ ሲከብድ ተመልክተነዋል። ትልቅን ነገር ማሳነስ ሊቀል ይችላል፤ ያነሰን ነገር መልሶ ማተለቅ በጣም ከባድ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በሰብዓዊ ፍጡር፣ በአገር፣ በትውልድ፣ … ላይ ሲደረግ ማንነትን፣ ኅልውናን ያጠፋል።

ጎንደር ላይ በተሰማው “በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም” በሚል መፈክር ከ40 ዓመት በላይ በፓርቲዎች፣ በአርነት ንቅናቄዎች፣ በጎሣ ድርጅቶች፣ … ያልተሳካ ጉዳይ በህዝብ በቀላሉ ተፈታ። ሕዝብን ማዳመጥ አሁንም ለበርካታ ጉዳዮች መልስ ይሠጣልና የኦሮሞው መብት፣ የአማራው መብት፣ የ… መብት የሚለው አስተሳሰብ ወደ “ሕዝብ ምን ይላል” አስተሳሰብ ቢለወጥ በርካታ ችግሮች መፍትሔ ያገኛሉ።

የፖለቲካ ድርጅቶች በዓላማነት የሚያስቀምጡት፤ አመራሮቻቸው የሚናገሩትም ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ማድረግ ነው። ወደ ሥልጣን መንበር እየተቀረበ ሲመጣ ግን የትግል ዲስኩር ይቀየራል። ሕዝብ በደሙ ታሪክ እየጻፈ ድል እያስመዘገበ ሲመጣ ከጀርባ ያሉት ኃይሎች “የመክለፍለፍ ፖለቲካ” ውስጥ የመግባት ሁኔታ እያሳዩ ነው። ይህ ከቀጠለ ደግሞ ወያኔ አፈር ልሶ እንደገና እንዲነሳ በር ይከፍታልና፤ ጥንቃቄና ስክነት ያስፈልጋል። ሕዝብን ከፖለቲካ ክስረት መታደግ ያስፈልጋል። ሕዝብን ተስፋ ከማስቆረጥ መታቀብ ያስፈልጋል። ሕዝብን ውዥንብር ውስጥ አለመክተት ያስፈልጋል። ሁኔታዎች በወጉ ተመክሮባቸው ሳይበስሉ ለማኅበራዊ ሚዲያ ፍጆታ ማዋል አንዳች የሚረባ ነገር የለውም። በርን ዘግቶ፤ ጉዳይን እዚያው ወቅጦ፤ ሲያልቅ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እጅግ አዋቂነት ነው።

Received on Mon Oct 10 2016 - 08:03:53 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved