ለአስገድዶ ደፋሪዎች ከልብ ያዘንኩላቸው ልዩ ዕለት! (ፍርዱ ዘገዬ – ከአዲስ አባባ)

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sat, 28 May 2016 22:36:49 +0200

ለአስገድዶ ደፋሪዎች ከልብ ያዘንኩላቸው ልዩ ዕለት! (ፍርዱ ዘገዬ – ከአዲስ አባባ)

 

ፍርዱ ዘገዬ – ከአዲስ አባባ (ግንቦት 20 ቀን 2008ዓ.ፍ.)

ይህችን ማስታወሻ እጽፋለሁ ብዬ በልሜም በውኔም አላሰብኩም፡፡ ዛሬ ቀኑ በዓል በመሆኑና የተወዘፈ ሥራ ስላለብኝ ቢሮ ገብቼ ለመሥራት በማቀድ ከጧቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ወደ መሥሪያ ቤቴ መጓዝ ጀመርኩ፡፡ ጥቂት እንደሄድኩ ግን ጉዞዬ ጉዞ ፍትሓት ሆነና እንዳሰብኩት መሆን አቃተኝ፡፡ ምክንያቱም በግንቦት 20 ምክንያት የአዲስ አበባ መንገዶች በተለይም መሀል ከተማ ተዘጋግቷል፡፡ በካዛንችስ ስሄድ ዝግ ነው፤ በአራት ኪሎ ስሄድ ዝግ ነው፤ በቴዎድሮስ አደባባይ በኩል ስሄድም ዝግ ነው፤ በተክለ ሃይማኖት በኩልም ዝግ ነው፡፡ እንደምንም ብዬ ወታደሮችንና ትራፊክ ፖሊሶችን በመለማመጥ ዲአፍሪክ ሆቴል አካባቢ ደረስኩና መኪናየን እዚያ ጥዬ ከአንድ ኪሎ ሜትር የሚበልጠውን የመሥሪያ ቤቴን መንገድ በእግር ተያያዝኩት – ግንቦት ሃያን በልቤ እየረገምኩ፡፡ መንገዱን ሁሉ የሞላው ከየወራዳውና ከፍተኛው በሃይገርባሶችና በከተማ አውቶቡሶች እንዲሁም  በሌሎች ልዩ ልዩ የመንግሥትና የግል ተሽከርካሪዎች በግዳጅ እንዲመጡ የተደረጉ በዓል አክባሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህን በግዳጅና በገንዘብ ኃይል የተሰባሰቡ ዜጎች ጠጋ ብላችሁ ስትመለከቷቸውና ስትጠይቋቸው የምታገኙት ነገር ልባችሁን ይሰብረዋል፡፡ ነገረ ሥራቸው ያሳዝናል፤ ድህነት እንዴቱን ያህል እንደሚያዋርድና የጭራቅንም እጅ ሳይቀር እንደሚያስቀላውጥ ትረዳላችሁ፡፡Ethiopia May 28 celebration

እኚህ ዜጎቻችን በኑሮ እጅግ የተጎሳቆሉ መሆናቸውን በአለባበሳቸውና በሁኔታቸው ትገነዘባላችሁ፡፡ አንድም ደህና ሰው የለባቸውም – ደህና ሰው ስል ከምድራዊ የደህና ሰውነት መለኪያ አንጻር ማለቴ እንጂ በፍጡርነት ሁሉም እኩል መሆኑን ዘንግቼው አይደለም፡፡ በአለባበስ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በመልካም ስብዕና፣ በሥራና በኑሮ ወዘተ. በእጅጉ የተበሰቋቆሉ መሆናቸውንና እነዚህን ዓይነት ዜጎች ገንዘብ ካሳዩዋቸው ምንም ዓይነት የራሳቸው ዓላማና አቋም ቢኖራቸው እንኳን ለገንዘቡ ሲሉ አድርጉ የተባሉትን እንደሚያደርጉ መረዳት አይከብድም – የተማረ ሰው መቼም በዚያ መልክ ውራጅ ለብሶና ሞጋ ጫማ አድርጎ ለወያኔ ሠርግ ሲል በራሱ ሞት አይጨፍርም፡፡ ይህን ትርዒት ባይኔ በብረቱ ስመለከት በዜግነቴ አፈርኩ፤ የወቅቱ ኢትዮጵያዊነቴ ራሴን ከሰው በታች አድርጌ እንድመለከተው አደረገኝ፡፡ የት እንዳለሁም ማወቅ ተሳነኝ፡፡ “እኔ ነኝ አካባቢየ እንዲህ ቆሽሾ የሚታየኝ? እንደሀገርም ሆነ እንደማኅበረሰብ ከየት ወዴት እየተጓዝን ነው? በእነዚህ ሰዎችና በኔ መሀል ምን ልዩነት ቢፈጠር ይሆን ያለሁበት ሥፍራ  በመጥፎ ጠረን ተበክሎ ኅሊናየን የሚያሰቃየው?” በሚል በሃሳብ ናወዝኩ፡፡ ዙሪያ ገባየን ተፀየፍኩት፤ እሱም ተጠየፈኝ መሰለኝ ገፈታትሮ ከዚያ አካባቢ አስወጣኝና ወደቢሮየ አስገባኝ፡፡

እንዲህና እስከዚህ የተዋረድነው ለምን ይሆን? ፈጣሪን ምን ብንበድለው ይሆን ወደዚህ የዘቀጠ ደረጃ አውርዶ የፈጠፈጠን? ምንድነው በሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው? እናስብ እንጂ!

ምስኪኖቹ ወገኖቼ የሚዘፍኑትም ሆነ ጉሽ ጠላ ጠጥቶ እንደሰከረ ሰው የሚያዱብዱት ለምን እንደሆነ የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ በየፒካፑ ተንጠልጥለው ከሞንታርቮ በሚለቀቁ ዘፈኖች ሥልት በሌለቀው ዳንስ አይሉት ጭፈራ ይንጠራወዛሉ፡፡ የአካባቢውም ሰው አፉን እየሸፈነ ሳይሞቀው ሳይበርደው በትዝብት ዐይን ይመለከታቸዋል – አንዳንዱም ስለነሱ እያፈረ፡፡ ሲዖል ውስጥ በዕረፍት ሰዓት እንዲደነክሩ ለአፍታ የተፈቀደላቸው የሚመስሉት እነዚያ የተኮነኑ በሰው አምሳል የሚንቀሳቀሱ ነፍሳት ወያኔ በጨው እያታለለ ለዓላማው ስኬት የሚጫወትባዘቸው ቀን የጣላቸው ዜጎች ናቸው፡፡

ከዚህ ወዝ የለሽ ድራማ በመነሳት እኔን የታየኝ ሌላ ነገር ነው፡፡

በዓለም ላይ እጅግ ብዙ አስገድዶ ደፋሪዎች አሉ – ሴትን ብቻ ሣይሆን ወንድንም ጭምር፡፡  ልዩ የርኩሣን መናፍስት ኃይል የተጠናወታቸው እነዚህ ሰዎች – ሰዎች ማለት እንኳን ይከብደኛል – የሚያደርጉትን ባለማወቅ ከሕጻናት እስከዐዋቂ – ከጤነኛ እስከ በሽተኛ ያገኙትን ሁሉ ይደፍራሉ፤ በዚህም ጠያፍና ወንለለኛ ድርጊታቸው ብዙዎችን ለአካላዊ፣ ለኅሊናዊና ለአእምሯዊ በሽታዎች ይዳርጋሉ፡፡ ያልተፈለገ እርግዝናም በማስከተል ብዙዎችን ለቁም ስቅል ይዳርጋሉ፡፡

በፈረንጅኛው Stockholm Syndrome የሚሉት አባባል አለ፡፡ ምን ማለት ነው – ተጎጂው ለጎጂው የሚያዝንለት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስም የሚሰቅሉትን የዚያን ዘመን ፈሪሣውያንና ሰዱቃውያን ወያኔዎችን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሲል አብ እንዲምራቸው ጸልዮላቸዋል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አይሲሶች አንዲት ሕጻን ደፍረው ሲገድሏት በሚገርም ሁኔታ “እግዚአብሔር ሆይ ይቅር በላቸው” እያለች ነፍሷ እንደወጣች አንብቤያለሁ፡፡ ይህን የሚሉ ብፁዓን ናቸው፡፡ ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን ጨምሮ ከሰው ልጆችም ውስጥ ይህ የከፍተኛ አእምሯዊና መንፈሣዊ ዕድገት ምልክት የሆነ ለጠላት ምሕረትን የመለመን መልካምነት አልፎ አልፎ ይታያል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው የሚዘገንን ኃጢኣትም እንበለው ወንጀል የሚሠራው በሆነ ኃይል ተገድዶ እንጂ በጤናው ሊሆን አይችልምና፡፡ ወያኔዎችም ይህን የመሰለ አጸያፊና ነውረኛ ተግባር የሚፈጽሙት እነዚህ ምስኪኖች ከተማ ውስጥ በግዳጅ ወጥተው ስለተንጫጩ የሚያገኙት ጠቀሜታ ኖሮ አይደለም፡፡ ሰዎቹ ጮኹ አልጮኹ የወያኔን ዕድሜ አያረዝሙ ወይ አያሳጥሩ፡፡ እርግጥ ነው ወያኔዎች እንዲህ የሚያደርጉት “ብዙ ደጋፊ አለን” የሚል ምስል በተለይ ለእስስታውያኑ የዳብል ስታንዳርድ አራማጅ የዓለም ኃያላን አገሮች ለማስተላለፍ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያረጀ ያፈጀ ሥልት ነው፡፡ ሁሉም የወያኔን ጠባይና ተፈጥሯዊ ባሕርይ ስለሚያውቀው – ማወቁንም ወያኔዎች ራሳቸው ስለሚያውቁ – ይህን ያህል በሕዝብና በሀገር ሀብት መቀለድ አያስፈልጋቸውም ነበር፡፡ ይልቁንም እንዲህ የሚጫወቱበትን የሀገር ሀብትና ንብረት ዜጎችን አለፍላጎታቸው እየዘረፉ ገሚሱን ለሙስና ገሚሱን ለግንባታ በሚል እንዳሻቸው ለሚመዘብሩበት ለዚያ መከረኛ የአባይ ግድብ ቢያውሉት ይበጅ ነበር፡፡

እኔ ግን አዘንኩላቸው፡፡ ድሆችን አስገድደው አእምሯቸውን በመድፈር ለዚህ ለኢትዮጵያ ውድቀትንና ውርደትን ላስከተለ የግንቦት 20 በዓል በማሰለፋቸው ለነሱም አዘንኩ፡፡ አስገድደው የሚደፍሩ ሰዎች በዚያ ሰዎችን እያስለቀሱና ደም እያስነቡ በሚፈጽሙት ወሲብ እንዴት እንደሚደሰቱ ለማወቅ እርግጥ ነው እነሱን መሆንን ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ደስታቸው ሰይጣናዊ እንጂ ቅዱስ እንደማይሆን መረዳት አይከብድም፡፡ ግልጽነት በተወሰነ ደረጃ መጥፎ አይመስለኝም፤ ይህን ጉዳይ በሚመለከት በራሴ ሕይወት ማረጋገጥ የምችለው አንድ ነገር አለ – እርሱም በተለይ በወጣትነት ዘመኔ ባለቤቴ ዳቦ አልሰጥም ብላ እምቢ ስትለኝና በእልኽ ተነሳስቼ ዳቦዋን አለፍላጎቷ ስቀማት፣ ከበላሁት በኋላ ምንም ያላገኘሁ ያህል ይሰማኝ እንደነበር አሁን ድረስ ትዝ የሚለኝ ልዩ ትውስታ ነው፡፡ ምክንያቱም ጉድለቱ ወደራሴ ስመለስ እየቆዬ ይሰማኛል፡፡ ፈቅዳና ወድዳ ስላልስጠችኝ ብበላም አልረካም፤ እናም የጥፋተኝነቱ ስሜት እያንገላታኝ ደስኛ አልሆንም ነበር – እንኳንስ የማታውቀውን ሰው ማስገደድ ይቅርና የራስህንም ቢሆን በፍቅር እንጂ በጠብና በእልህ አይሆንም ለማለት ፈልጌ ነው እንዲህ የራሴን ምሥጢር ፀሐይ ላይ አውጥቼ የማሰጣው፡፡ ይቅርታ ደግሞ፡፡ ሆ!

ስለዚህ ወያኔን ይቅር የሚለው ይቅር ይበላቸው፡፡ የሚያደርጉትን አያውቁምና ኅሊናቸውን ይመልስላቸው፡፡ በሽተኞችንና የአእምሮ ዘገምተኞችን ሣይቀር በየወራዳውና በየቀበሌው እንዲሁም በየከፍተኛው ከፍተኛ የኃላፊነት ሥራ ላይ እየመደቡ ሕዝብንና ሥራን እንደሚበድሉ በበኩሌ አውቃለሁ፡፡ ብዙ የተማረ ሰው እነሱ ጋ መሥራት ስለማይፈልግ አብዛኛው ሠራተኛቸው ከፊደል ዘር የተጣላ ማይም መሆኑንና  ያገኘውን አግበስበስብሶ ዘወር ለማለት የሚፈልግ እንደነሱው ወሮበላ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ በወያኔዎች መንግሥት የሥራ መዋቅር በየደረጃው የተሰገሰገው የሰው ኃይል ለሆዱ እንጂ ለሀገራዊ ጥቅምና ዓላማ እንዳልሆነም ግልጽ ነው፡፡ ብዙው ሠራተኛቸው ዛሬ ከምሞት ነገ ልሙት ብሎ ቆርጦ የተነሣና ለማንም ለምንም የማይሞቀው የማይበርደው መሆኑም የታወቀ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ በብላኔ እየተነዳች እንዳለች የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ቢሆንም ምን እያደረጉ እንዳሉ ማወቅ የማይፈልጉትን ወያኔዎች ፈጣሪ ይማርልንና የኛ የሚላቸውን ሰዎች በቶሎ ይስጠን፡፡ አሜን፡፡ (በተከበረው የበዓል ዕለት መ/ቤት የገባሁበት “ሥራ ተሠራ”ና ወደበይተይ ልመለስ ነው – ወያኔ እያለ እኮ በርግጥም መደበኛ ሥራ መሥራት አልተቻለም፡፡ ኤዲያ! ሥራ አስፈቺዎች! …)

ማሳሰቢያ፡- ዓ.ፍ  – ዓመተ ፍዳ ለማለት ነው፡፡ ዓ.ዓ. ብል ኖሮ ደግሞ ዓመተ ዓለም በሆነ ነበር፡፡

 
Received on Sat May 28 2016 - 16:36:50 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved