Ethsat.com: “ህዝቡ ከኢህአዴግ መሪዎች ይልቅ በውጭ ለሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች እውቅና እየሰጠ ነው” ሲል የደህንነት መስሪያ ቤቱ አስታወቀ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Fri, 27 May 2016 20:06:27 +0200

“ህዝቡ ከኢህአዴግ መሪዎች ይልቅ በውጭ ለሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች እውቅና እየሰጠ ነው” ሲል የደህንነት መስሪያ ቤቱ አስታወቀ

May 27, 2016
http://ethsat.com/

ግንቦት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢህአዴግ 25ኛ አመት በአሉን እያከበረ በሚገኝበት ወቅት እያደረገ ባለው ግምገማ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ለስርአቱ አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ ያላቸውን ጉዳዮች ለውይይት ከማቅረብ ባሻገር ፣ ህዝቡ በአገር ውስጥ ላሉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ከሚሰጠው እውቅና ይልቅ በውጭ አገር ለሚገኙ የተቃዋሚ መሪዎች እየሰጠ በመምጣቱ የስደት መሪዎችን እስከመሾም ተደርሷል ብሎአል ።

የደህንነት እና መረጃ ክፍል ባቀረበው ጥቅል ግምገማ የኤርትራ መንግስት የሚካሄደውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስልክ ጠልፎ በማዳመጥ በኩል ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጿል። “ይሁን እንጅ” ይላል ሪፖርቱ “በሰሜን ጎንደር እና በሱዳን ድንበሮች አካባቢ ብዙ ስራዎችን ለመስራት ቢታቀድም ብቃት ያለው ስራተኛ ባለመገኘቱ የታቀደውን ያህል ስራ መስራት ሳይቻል ቀርቷል፡፡”

“አርበኞች ግንቦት ሰባት በመከላከያ ሰራዊታችን ውስጥ ሰርጎ ገብቷል የሚል በተለይም ተመላሽ የሰራዊት አባላት ድርጅቱን ለመቀላቀል ፍላጎት እያሳዩ ነው የሚል ማስረጃ አልባ መረጃዎች አሉ” የሚለው የደህንነት መስሪያ ቤቱ፣ አሳሳቢው ጉዳይ ህዝቡ በውጭ ለሚኖሩ የፖለቲካ መሪዎች እውቅና እየሰጠ በመምጣቱ የስደት ፖለቲካ መሪዎችን እስከመሾም ደርሷል ብሎአል።

በሀገር ውስጥ በህጋዊነት ተመዝግበው በውጭ ከሚገኙ ተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት እየፈጠሩ ረብሻ የፈጠሩ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ቢቻልም፣ አሁንም የሚቀሩ ስራዎች አሉ ይላል። ችግሩን ለመቋቋም ውስጥን ማጥራት ተገቢ መሆኑንም አስጠንቅቋል።
የደህንነት ክፍሉ ለኢህአዴግ ፈተና ይሆናሉ የሚላቸውን አምስት ጉዳዮችን በማንሳት ለውይይት አቅርቧል።ኢህአዴግን ፈተና ላይ ሊጥሉት ይችላሉ ተብለው በኢንፎርሜሽን መረብ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሻለቃ ቢኒያም ተወልደ የቀረቡት መላምቶች-
“የመከላከያ ሠራዊት መፈንቀለ መንግስት ለማድረግ ከተደራጀ፣ የተራዘመ የገጠር የትጥቅ ትግል ከተካሄደ ፣ ነጋዴው እና ህዝቡ ግብር ለመክፈል ፈቃደኛ መሆን ካልቻለ እና ባለሃብቱ በገንዘቡ ተቃዋሚዎችን ከደገፈ፣ ማህበረ ቅዱሳን እና የእስልም ድርጅቶች በተመሳሳይ ሰዓት ውስጥ ወደ አመፅ ከገቡ እንዲሁም የታጠቁ ሐይሎች ወደ ህቡዕ አደረጃጀት ገብተው መምራት እና ሃይላቸውን ማሰመራት ከቻሉ” የሚሉት ናቸው።

“የውጭ ሃይሎች ለተደራጁ ኃይላት የገንዘብ እና የመሳሪያ ድጋፍ ካደረጉ እንዲሁም የተደራጁ የሲቪክ ማህበራት ለፖለቲካዊ ለውጥ ከሰሩ” የሚሉ ተጨማሪ መላምቶች የማዳበሪያ ሃሳቦች ሆነው ቀርበዋል።

ምንም እንኳ የደህንነት መስሪያ ቤቱ ስጋቶችን ለይቶ ያስቀመጠ ቢሆንም፣ ስጋቶቹ ምን ያክል ተጨባጭነት እንዳላቸው ወይም ምን ያክል ተግባራዊ ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘርዝሮ አላቀረበም። ኢህአዴግ በማድረግ ላይ ባለው የአመራር ግምገማ ደግሞ ነባሩን አመራር የሚተካ ብቁ አመራር አለመፈጠሩን ገልጿል።

“የኢህአዴግ የትግል ዘመን ታጋይ እና አታጋዮች ጊዜ እያለቀ ነው፡፡ በትውልድ የመተተካት ስርዓት ውጤታማነት እየቀጠለ አይደለም” በማለት ነባር ታጋይ አመራሮች በውይይቱ ላይ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

“ትግሉን በጎጥ እና በቀበሌ አስተዳደር ለመምራት የተሄደው እርቀት እጅግ ስኬታማ ቢሆንም፣ ስርዓቱን ለማስቀጠል እንጅ፣ ከታጋዮች ዘመን በኃላ የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር ምቹ መደላድል አልተሰራም” የሚል አስተያየተም በታጋዮች ቀርቧል፡፡

የጠ/ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጉዳይ አማካሪው አቶ አባይ ፅሃየ በበኩላቸው “አዳዲስ ታጋዮችን የማምጣት እና የማስተዋወቅ ስራ ባለመኖሩ ፤ ተተኪ የማፍራቱ ጥረት የከሸፈ ነው “ ያሉ ሲሆን፣ ከዩኒቨርስቲ ጀምሮ እስከ ቀበሌ እና ከፍተኛ የፖለቲካ አስተዳደር ድረስ ሰዎች በተወለዱበት አካባቢ እንዲመሩት መደረጉ ለሀገሪቱ እድገትም ሆነ ለኢኮኖሚያዊ ለውጥ አስተሳሰብ መዳከም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል” ሲሉ አክለዋል።

አንድ ነባር ታጋይ “ ለምሳሌ ሳሞራ ቢሞት ማን ሊተካው ነው? ሰራዊቱን ሊያፀናው የሚችለውስ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ አንስተው የመተካካቱ ሂደት ችግር እንዳለበትና ለወደፊቱ ፈተና መደቀኑን ገልጸዋል።

*********************************************************************************

ኢህአዴግ “ህዝቡን በመልካም አስተዳደር ማወያየታችን አመጽ እንዳይፈጠር አድርጓል” አለ

Listen:
http://video.ethsat.com/?p=24215

ግንቦት ፲፰ (አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 25ኛ ዓመት የስልጣን ዘመኑን በማክበር ላይ ያለው ኢህአዴግ፣ ከፍተኛ አመራሮቹን ይዞ ግምገማ በማድረግ ላይ ነው። በግምገማው ኢህአዴግ ባለፉት 25 አመታት የተጓዘባቸው መንገዶች እና ያጋጠሙት ችግሮች በነባር አመራሮቹ ውይይት ተደርጎባቸዋል። ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሁዋላ የኢህአዴግን የርእዮት አለም አቅጣጫ በማብራራት ግንባር ቀደም ሆነው የወጡት በሁዋላም ከጤና ጋር በተያያዘ የመድረክ እንቅስቃሴያቸውን የቀነሱት አቶ በረከት ስምኦን በግምገማው መሪ ተዋናይ ሆነው ወጥተዋል።

በግንባሩ ሊ/መንበር አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በተመራው በዚህ ግምገማ አቶ በረከት ያቀረቡት ሪፖርት አወንታዊና አሉታዊ አስተያየቶችን አስተናግዷል። አቶ በረከት “ ኢህአዴግ ህዝቡን በመልካም አስተዳደር ችግሮች ዙሪያ ማወያየታችንና መድረክ መፍጠራችን ብሶቱን እንዲተነፍስ እና ወደ ተራዘመ አመጽ እንዳያመራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጎአል” ብለዋል።

የህዝብ ብሶት ማክሸፊያ ተደርጎ የቀረበውን የመልካም አስተዳደር ተግባቦት ስትራቴጂ የነደፉት አቶ በረከት ስምኦን በኢህአዴግ የምክር ቤት አባላት ውዳሴ ተችሮአቸዋል።

አቶ በረከት ባቀረቡት ግምገማ “ በከፍተኛ ደረጃ ያልተሰበሩ፣ ለወደፊቱ ብቅ ሊሉ የሚችሉና ጠንካራ ክንድ የሚሹ ችግሮች አሉ” ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአዲስ አበባ መስተዳደር ያለው የመሬት ችግር፣ የቦታና የንብረት አስተዳደር እንዲሁም የህወሃት ነባር አባላት የሃብት ክምችት ማእከል ሆነው መገኘታቸው” የሚሉትን ጠቅሰዋል።

አቶ በረከት ነቀፋቸውን በመቀጠል፣ “በኢህአዴግ ውስጥ ፖለቲካዊ ነጻነት አልተረጋገጠም፣ አሁንም በራሳቸው የሚወስኑ ሚኒስትሮች እና የክልል መስተዳድሮች አልተፈጠሩም”፣ ያሉ ሲሆን፣ በወረዳ ደረጃ በተደረገው የህዝብ የማወያየት እንቅስቃሴ 350 አይነት የኢህአዴግ አመራሮች የፈጠሩዋቸው ችግሮች መነገራቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ያክል ጸረ- ዲሞክራሲን መሸከም የማይችል ጫንቃ እንደፈጠረ የሚያሳይና የኢህአዴግን አስቻይ ጸረ-ዲሞክራትነት የሚያረጋገጥ ነው ብለዋል።

“ህዝቡ ግማሹ ትከሻው ቢረገጥም፣ ግማሹን የሚችልበትን ስርዓት ገንብተናል “ ያሉት አቶ በረከት፣ የዚህ አይነቱን ስርዓት አደጋም አስቀምጠዋል። “ ይህ ሃምሳ ሃምሳ የሆነ፣ ሃምሳ የበደል ሃምሳ የካሳ ስርዓት አንድ ፕርሰንት ጨምሮ ወደ በደል ካመራ፣ ስርዓቱን ገደል ይከተዋል” ያሉት አቶ በረከት፣ ነገር ግን ይላሉ “ ህዝቡን በማስተንፈስ ስትራቴጂ ቀጥለን በአንድ ፐርሰንት ልዩነት በደሉን የሚችልበትን ትከሻ ከፈጠርንለት በስልጣን ላይ የመቀጠላችን እድላችን መቶ ፐርሰንት የተሻለ ነው።” ሲሉ ያረጋግጣሉ።

“ከመልካም አስተዳደር ውይይት” በተጨማሪ ህዝባዊ አመጾች እንዲራዘሙ ያደረጉ ምክንያቶችም ተዘርዝረው ቀርበዋል። አንደኛው ምክንያት የኢሳት ታፍኖ ለወራት መቆየት ሲሆን፣ ኢሳትን ያለ የሌለ ሃይላችንን በመጠቀም በጊዜው ታፍኖ እንዲቆይ ባናደርግ ኖሮ በተለይ የኦሮምያ አመጽን ተከትሎ አደጋው ስርዓቱን እስከማጥፋት በተለይም ታማኝ አመራሮችን በማጥፋት ትግሉ ወደ መሃል አገር እንዲስፋፋ የማድረግ እድሉ ከፍተኛ ነበር ተብሎአል።

ሰማያዊ ፓርቲ መከፋፋሉና አመራሩ እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖረው መደረጉ እንዲሁም አርበኞች ግንቦት7 ተጠናክሮ ወደ መሃል ሀገር መግባት አለመቻሉ ግንባሩን ከአደጋ መታደጉም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

አቶ በረከትን በድፍረት መንቀፍ የቻሉት የህወሃት ነባር የአመራር አባል የነበሩት አቶ ስብሃት ነጋ ብቻ ነው። አቶ ስብሃት ለአቶ በረከት ግምገማ በሰጡት አስተያየት “ አንተ የምታቀርበው ሪፖርት ሁሌም ሞት ጠሪ ነው፤ ችግርህ ምንድነው? አንተ ከአመራርነት ለመውጣት የቀረህ ጊዜ አጭር ስለሆነ ነው?” ካሉ በሁዋላ፣ በአንተ ሪፖርት ኢህአዴግን ደርግ ሆኖብኝ ነው ያገኘሁት፤ እኛ ነጻ አውጭዎች እንጅ ጨቋኞች አይደለንም” ብለዋል።

በአቶ ስብሃት የሰላ ትችት የተበሳጩት አቶ በረከት “ አንተን ደስ እንዲልህ ፣ መብራቱ ሲቆም የሚቆም የባቡር ሃዲድ ተሰራ ብዬ ሪፖርት አላቀርብም። ኢህአዴግ ደርግ ሆነ ላልከው አንተ ብለኸዋል። ብትችል የእኔን ሰነዶች እያነበብክ ተቃውሞ ከምታደራጅ፣ ከእኔ የተሻለ ሰነድ መጻፍ ብትችልና ብታቀርብ ጥሩ ነበር። እኔም ከዚህ የስልጣን ዘመን በሁዋላ ብትለምነኝም አታገኘኝም ያውም አንተ ከቆየህ” በማለት ዱላ ቀረሽ ምልልስ አድርገዋል።

ሰብሳቢው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ “የበረከት የመልካም አስተዳደር ውይይት እቅድና ውጤት ራሳችንን እንድናይ መስታውት ሆኖናል” በማለት አሞግሰው፣ ህዝቡ ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር እንዳያብር አድርጎታል ብለዋል።

Received on Fri May 27 2016 - 14:06:28 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved