Ethsat.com: የህወሃት አባላት ያልሆኑ የደህንነት አባላት በጥርጣሬ እየታሰሩ ነው

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 29 Jun 2016 01:35:23 +0200

የህወሃት አባላት ያልሆኑ የደህንነት አባላት በጥርጣሬ እየታሰሩ ነው

June 28, 2016
Watch this: http://video.ethsat.com/?p=25297

ሰኔ ፳፩ ( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት አባል የነበሩና በደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ በተለይም በሶማሊያ በሚካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ቁልፍ ሚና ነበራቸው የተባሉ 3ቱ ነባር የደህንነት አባላትና አስተባባሪዎች ከተገደሉ በሁዋላ፣ ከግድያው ጀርባ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል ተብለው የተጠረጠሩ የህወሃት አባላት ያልሆኑ የሌሎች ብሄረሰቦች የደህንነት አባላት እየተያዙ ነው። እስካሁን ከተያዙት መካከል አብዛኞቹ የኦሮሞ ተወላጅ የደህንነት አባላት ሲሆኑ፣ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጠበቂዎችም ይገኙበታል።

በአልሸባብ ተይዘው የነበሩትን የኢትዮጵያን ወታደሮች እና አንድ የፈረንሳይ የስለላ አባል ለማስለቀቅ ተልእኮ ተሰጥቷቸው የነበሩና ተልእኮዋቸውን በስኬት የተወጡ ኮማንዶችም ታስረዋል።  ኮማንዶዎቹ ታጋቾችን ሲያስለቅቁ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚከፈላቸው ቃል ተግብቶላቸው የነበረ ሲሆን፣ ተልእኮዋቸውን ከፈጸሙ በሁዋላ ግን አብዛኛውን ገንዘብ ወታደራዊ አዛዦች እንደነጠቁዋቸው፣ ይህንንም በመቃወማቸው ለእስር ተዳርገው እንደበሩ ታውቋል። ከአሁኑ ግድያ ጀርባ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል በሚል የተወሰኑት ተይዘው በድጋሜ ታስረዋል።

ምንም እንኳ ግድያዎችን በመመርመር ላይ ያለው ኮሚቴ፣ 9ኙን የደህንነት አባላት ማን ገደላቸው በሚለው ዙሪያ ድምዳሜ ላይ ባይደርስም ፣ ከግድያው ጀርባ የውጭ እጅ አለበት ከሚለው መላ ምት ይልቅ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ከሚታዬው የብሄር ልዩነትና ጸብ ጋር የተያያዘ ነው የሚለውን መላ ምት ወደ መቀበል እያዘነበሉ ነው ። በደህንነቱ ውስጥ የተፈጠረው ክፍተት በተለይ ለአልሸባብ እየጠቀመው መምጣቱን የሚገልጹት ምንጮች፣  ሶስቱ ወሳኝ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ በሶማሊያ ያለው የመከላከያ ሰራዊት ጨለማ ውስጥ መውደቁን ይናገራሉ።

የደህንነት አባላት እንደሚሉት ሰሞኑን ደግሞ ጥርጣሬው እየሰፋ ሄዶ ከህወሃት አባላት ውጭ ያሉ የሌሎች ብሄረሰቦች የደህንነት አባላት አንድ በአንድ እየተጠሩ በመመርመር ላይ ናቸው።

ምንጮቻችን ከህወሃት ውጭ ያሉ የደህንነት አባላት በሞላ  ከአጋዚ ገዳይ ስኳድ ራሳቸውን ለመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ በተለይም መሳሪያቸውን እንዲያስረክቡ ሲጠየቁ ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ለጓደኞቻቸው ምክር ያስተላልፋሉ። መርማሪዎች በሚጠሩዋቸው ጊዜም መሄድ እንደሌላበቸው ይመክራሉ።

ቁልፍ የደህንነት አባላት መገደላቸውን ተከትሎ በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ ፍርሃት መንገሱን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል። ግድያውን የሚፈጽሙት የተለያዩ የውጭ ሃይሎች ሊሆኑ ይችላል የሚሉ መላምቶች ቀርበው ምርመራ ሲደረግ ቆይቷል። አሁን የሚታዬው የሌሎችን ብሄረሰብ አባላትን ከድህነት መስሪያ ቤቱ ሙሉ በሙሉ የማስወጣቱ እርምጃ ከቀጠለ ፣ የእርስ በርስ መጠፋፋቱ ሊቀጥል እንደሚችል ምንጮች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።

******************************************************************************************

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ አሜሪካን አዲስ ህግ አጸደቀች

Watch this: http://video.ethsat.com/?p=25309
June 28, 2016

ኢሳት (ሰኔ 21 ፥ 2008)

የአሜሪካ መንግስት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ስጋቱን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ከቆየ በኋላ S.RES432 የተሰኘ የሰብዓዊ መብቶች ህግ በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ አማካኝነት አጸደቀ።

ሰኔ 16 ቀን 2008 ዓም በሜሪካን ህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) አባል በሆኑት የሜሪላንድ ግዛት ሴናተር ቤንጃሚን ካርቲን አቅራቢነት በውጭ ጉድዮች ቋሚ ኮሚቴ የጸደቀው ህግ የኢትዮጵያ ህግ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት አያያዝ የመረመረ ሲሆን፣ የሰብዓዊ አጠባበቅ ሊሻሻል ይገባል ያላቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በህጉ እንዲካተት አድርጓል። ከእነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ከመጠን ያለፈ ሃይል በመጠቀም በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያ፣ አፈና እና እስር መቆም እንዳለበት፣ በኦሮሚያ የተፈጸሙ ግድያዎችን መመርመር እንዳለበት፣ ተቃውሞ በማሰማታቸው ብቻ የታሰሩ የተቃዋሚ አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጋዜጠኞችን መፈታት እንዳለባቸው ያስገነዝባል። አሜሪካን ለኢትዮጵያ መንግስት የምትሰጠው የሰብዓዊ እና ወታደራዊ ድጋፎች እንድትመረምር እና ቁጥጥር እንዲደረግም ያዛል።

የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና የአሜሪካን ተራድዖ ድርጅት (USAID) አሜሪካ ለኢትዮጵያ መንግስት የምትሰጠውን እርዳታ ክትትል እንዲያደርጉና እንዲመረምሩ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴው ያወጣው ህግ ይጠይቃል።

Received on Tue Jun 28 2016 - 18:14:28 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved