Ethsat.com: በሰሜን ጎንደር ዳባት የተከሰተው ተቋውሞ እስካሁን እልባት አላገኘም

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sat, 11 Jun 2016 11:16:29 +0200

በሰሜን ጎንደር ዳባት የተከሰተው ተቋውሞ  እስካሁን እልባት አላገኘም

June 11, 2016

ኢሳት (ሰኔ 3 ፥ 2008)

Watch the special news:

http://video.ethsat.com/?p=24714

ሰሞኑን በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ከተማ የኤሌክትሪክ ሃይል ማሰራጫ መነሳት ጋር የተቀሰቀሰው ተቃውሞ አርብ ድረስ እልባት አለማግኘቱንና የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ከተማዋን ለቀው ወደጎንደር ከተማ መሰደዳቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጡ።

በሃይል ማሰራጫው ማሽን መነሳት ተቃውሞ ሲያቀቡ የነበሩ ነዋሪዎች የወልቃይት ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ሲሉ አዲስ አስተዳደራዊ ጥያቄን ማቅርብ መጀመራቸው ታውቋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዳባት ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በርካታ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ መሆናቸውን ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

ከቀናት በፊት የከተማዋ ነዋሪዎች ከ25 አመት በፊት የኤሌክትሪክ ሃይል እንዲያሰራጭ ታስቦ የተተከለ ማሽን ወደ መቀሌ ሲወሰድ ነው በማለት በተሽከርካሪ ላይ ተጭኖ የነበረውን ማሽን በማውረድ ተሽከርካሪውን ማቃጠላቸው ይታወሳል።

በከተማዋ የተቀሰቀሰን ይህንኑ ግጭት ተከትሎ የዞን ባለስልጣናት ከነዋሪዎች ጋር ለመወያየት ጥረት ቢያደርጉም ከነዋሪው ጋር አለመግባባት መፈጠሩንና ውጥረቱ አርብ ድረስ መቀጠሉን እማኞች ለኢሳት አስታውቀዋል።

በአሁኑ ሰዓትም በከተማዋ ነዋሪዎች የፌዴራል ፖሊስ ብቻ ተፋጠው እንደሚገኙ የሚናገሩት ነዋሪዎች የከተማዋ አስተዳዳሪዎች ወደ ጎንደር ከተማ መሰደዳቸውን አክለው ገልጸዋል።

በከተማዋ ዙሪያ በሚገኙ አርሶ አድሮች የከተማዋ ነዋሪው ያነሳውን ተቃውሞ የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ አዲስ አስተዳደራዊ ጥያቄ ማቅረብ መጀመራቸው ታውቋል።

ነዋሪዎቹ የወልቃይት ጉዳይ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝ በመጠየቅ “ወልቃይት አልተመለሰም” በማለት ተቃውሞ እያሰሙ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

የመንግስት ባለስልጣናት የወልቃይት ጉዳይ እልባት አግኝቷል ቢሉም ነዋሪዎች ጥያቄው አሁንም ድረስ እልባት አለማግኘቱን ይገልጻሉ።

በዳባት ከተማ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘግተው የሚገኙ ሲሆን፣ በጸጥታ ሃይሎች የተደበደቡ ወጣቶች መኖራቸውን እማኖች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።

በዳባት ከተማ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ወደ አጎራባች ወረዳዎች በመዛመት አስተዳደራዊ ጥያቄ ማስነሳት መጀመሩን ከነዋሪዎች ጋር ከተደረገው ቃለምልልስ ልመረዳት ተችሏል።

 
Received on Sat Jun 11 2016 - 05:16:29 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved