Zehabesha.com: ግንቦት ሃያ ሲመጣ… | አስቂኝ እና አሳዛኝ ገጠመኞቻችን! (ድንቁርና ኣባላት ወያነ ዝሰረቱ ዘሕዝንን ዘገርምን ፍጻሜታት ኣብ ኣዲስ ኣበባ 1991)

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sun, 5 Jun 2016 20:35:49 +0200
ግንቦት ሃያ ሲመጣ… | አስቂኝ እና አሳዛኝ ገጠመኞቻችን!

 በዳዊት ከበደ ወየሳ

(ይህ ጽሁፍ ዛሬ አዲስ አበባ ታትሞ ለህዝብ የቀርበው አዲስ ገጽ መጽሄት ላይ የወጣ ነው)
ግንቦት ሃያ ሲመጣ የኢህአዴግ የሚዲያ ፍጆታ ይጨምራል። በቴሌቪዥን የሚቀርቡት ዝግጅቶች… ኢህአዴግን  የሚቆልሉ፤ ከዚያ በፊት የነበሩትን መንግታት የሚኮንኑ ይሆናሉ። ከኢህአዴግ በፊት የነበሩት መንግስታት ኋላ ቀር እና እንደሆኑ፤ የኢትዮጵያም ህዝብ ቀን የወጣለት በኢህአዴግ መሆኑን ሳይፈሩናሳያፍሩ ይነግሩናል። እንዲህ እንዲህ እያሉ በየአመቱ መጀመሪያውና መጨረሻው የሚታወቅ አይነት የህንድ ፊልም ይሰራሉ። ተዋናዮቹ ጥቂት የቀድሞ የወያኔ አባላት ወይም ግዜ የሰጣቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ዛሬ ስለነሱ የቲቪ ተውኔት ሳይሆን፤ የራሳችንን የግንቦት ሃያ ገጠመኝ በማውጋት እለቱን እናስታውሳለን።

ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ዜናውን የሰማነው በሬድዮ ነበር። “…ደርግ ይጠቀምበት የነበረውን የሬድዮ ጣቢያ ለህዝብ ጥቅም ተቆጣጥሮታል።” ይህን አባባል ተከትለን፤ “እውን… እነዚህ ሚዲያዎች ለህዝብ ጥቅም እየዋሉ ነው ወይ?” ብለን ብንጠይቅ መልሱን የ3ኛ ክፍል ተማሪም ሊነግረን ይችላል።

ከጨዋታችን በፊት ግን ሁሌ ፈገግ የሚያሰኘን ሌላ ገጠመኝ አለ። የዚያኑ ቀን አዲስ አበባ ስቴድየምን ተቆጣጠሩት። እናም ስቴድየሙን ከተቆጣጠሩት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል አንደኛው እንዲህ የሚል መል’ክት አስተላለፈ “…ደርግ ይጠቀምበት የነበረውን፤ የማይንቀሳቀስ ትልቅ መርከብ ለህዝብ ጥቅም ተቆጣጥረነዋል” ብሎ ነበር። እነዚህ ነገሮች አሁን ሲወሩ ቀልድ ሊመስሉ ይችላሉ። ለ’ኛ ግን የግንቦት ወር ሲመጣ የምናስታውሳቸው ገጠመኞቻችን ናቸው።


ግንቦት ሃያ ሲመጣ… (አስቂኝ እና አሳዛኝ ገጠመኞቻችን)

(በዳዊት ከበደ ወየሳ – አትላንታ)

ያው ትግል ስለሆነ፤ ወያኔዎች በትግል ወቅት ሌቱን ድንጋይ ተንተርሰው፤ ጠዋት ጤዛ ልሰው አዲስ አበባ ደረሱ። አዲስ አበባ እስከሚገቡ ድረስ ለሊቱን የሚተኙት፤ አፈር አቧራውን ‘እፍ እፍ’ ብለው በየጥጋጥጉ ነበር። ከተማ ከመግባታቸው በፊት ግን አስፋልት ላይ መተኛት ጀመሩ። (ይሄ ሃሰት አይደለም። እያንዳንዱ በትግል ውስጥ ያለፈ ወያኔ የሚናገረው ነው።) ደግሞም የግንቦት ወር ጸሃይ ያረፈበት አስፋልት፤ ምሽት ላይ ሙቀቱን እንደያዘ ይቆያል። አዲስ አበባ ከመግባታቸው በፊት እና ከዚያ በኋላ አስፋልት ላይ የሚተኙ ወያኔዎች በዝተው ነበረ። ምክንያቱም የአስፋልቱ ሙቀት እና ልስላሴ ከሞዝቮልድ ፍራሽ ያልተናነሰ በመሆኑ… ለ’ነሱ።

Ginbot 20
የፍራሽ ነገር ከተነሳ ይህን ሳንጠቅስ ማለፍ የለብንም። ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ ከሌባ ጋር ድርድር አላደረገም። በየተገኙበት ይገድላቸው ነበር። ከሰንጋተራ ማዶ፣ ከሜክሲኮ በላይ ወዳለው ዲ አፍሪክ ሆቴል እንውሰዳቹሁና የፍራሹን ታሪክ እንጨዋወት። በዘረፋው ግዜ ዲ’አፍሪክ ሆቴልም ተዘርፎ ነበር። ታሪኩን ያጫወተን የዚያ ሰፈር ልጅ ኮሜዲያን ደረጄ ኃይሌ ነው። ዲ አፍሪክ ሲዘረፍ አንዳንዱ አንሶላ ሌሎች ደግሞ ትራስ ይዘው ይሮጣሉ። አንደኛው ሌባ ግን የስፖንጅ ፍራሽ ነበር የደረሰው። ያገኘውን የስፖንጅ ፍራሽ ተሸክሞ ትንሽ እንደሮጠ ከፊት ለፊቱ የሚመጣው ወያኔ ተኮሰበት። ሌባው ፍራሹን እንደተሸከመ ወደ ኋላ ወደቀ። በህይወት እያለ ባልተኛበት ስፖንጅ ፍራሽ ላይ ለዘላለሙ አሸለበ።

ከሌብነት ነገሮች ሁሌ የሚያስቀኝ እና የሚያሳቅቀኝ አራት ኪሎ ዩኒቨርስቲ የተሰረቀ ግዜ የሆነው ነገር ነው።

አራት ኪሎ የሚገኘው ዩኒቨርስቲ ሲዘረፍ በአካባቢው ነበርን። ተማሪዎቹ ወደ ብላቴን ስለዘመቱ አካባቢው ጭር ብሏል። ሆኖም የሌቦቹ ግርግር ጩኸት እና ጋጋታውን አደመቀው። ዝርፊያው ሲጀመር… ሌቦቹ የሄዱት ወደ ዩኒቨርስቲው ምግብ ቤት ነበር። ብዙም ሳይቆይ… አራት ኪሎ ተተረማመሰች። ከዩኒቨርስቲው የሚወጡት ሌቦች… አንዳንዱ ቡሃቃ፣ ሌላው ጭልፋ ሌሎቹ ደግሞ ባዶ ድስት ወይም ወጥ ያለበት ብረት ድስት ወይም ዘይት በጄሪካን ወይም ሰሃን፣ ሹካ፣ ማንኪያ በብዛት ተሸክመው በሁሉም አቅጣጫ ይሮጣሉ። ሌሎቻችን ከውጭ ሆነን የሚሆነውን ነገር እንደትእይንት እናያለን።

ከነዚህ ሌቦች መካከል አንዱ እድለ ቢስ ሌባ ቅቤ ሰርቆ፤ አናቱ ላይ ተሸክሞ ወደ ታች ሲወርድ፤ ልክ ጆሊ ባር ጋር ሊታጠፍ ሲል ከሩቅ ተኩሰው የቅቤውን ገረወይና ከአናቱ ላይ ጣሉበት። ጥሎት መሄድ ሲችል፤ የወደቀውን ገረወይና ቅቤ እንደገና አንስቶ ከመሸከሙ በፊት፤ ሌላ ጥይት አናቱን በስታ ወጣች። እሱም ከቅቤው ጎን እንደወደቀ፤ ዘረፋው ጋብ እስከሚል ድረስ ለግማሽ ቀን ያህል የሚያነሳው አጥቶ እዚያው ቆየ።

አሁን እየተረሳ መጣ እንጂ ኢህአዴግ እንደገባ ለሊት ለሩጫ ልምምድ ተነስተው የሚሮጡ ሰዎችን ጭምር ይገድል ነበር። “ምነው?” ሲሏቸው፤ “ያለምክንያት የሚሮጥ ሌባና እብድ ብቻ ነው። ምን በለሊት ያስሮጣቸዋል?” ብለውናል። በገቡ በአመቱ ባርሴሎና ላይ ፋጡማ ሮባ በማራቶን ለኢትዮጵያ ወርቅ ስታስገኝ፤ ለሩጫ ያላቸው አስተሳሰብ ተስተካከለ እንጂ፤ ከሰንጋ ተራ እስከ እንጦጦ ጋራ ድረስ ብዙ ሯጮች ገድለውብናል።

ይሄ ታሪክ እውነት ለመሆኑ የጨርቆስ ልጆችን ምስክር እናደርጋለን። ሃሰት ከሆነም የጨርቆስ ልጆች ይታዘቡን። ጨርቆስ ሰፈር ፖፖላሬ የሚገኘው የመኮንኖች ግቢ ሲዘረፍ፤ በዘረፋው ላይ ባይሳተፍም ቆሞ ያልተመለከተ ወይም ስለዘረፋው ያልሰማ የዚያ ሰፈር ሰው አልነበረም። የደርግ መኮንንኖች ቤቶቹን ጥለው ሲሄዱ፤ ኢህአዴግ ገና አዲስ አበባ አልገባም ነበር። መኮንኖቹ ግቢውን ለቀው የመውጣታቸው ወሬ ሲሰማ ግን… ግቢው በዘራፊዎች ተወረረ። ከቲቪ እና ከሶፋው በተጨማሪ፤ ሽጉጥ እና ጠመንጃ በሽ በሽ ነበር… አሉ ። ጥይት እንደቆሎ ነው የተለቀመው። አንዳንዱ የጨርቆስ ልጅ መተኮሻው አልነበረውም እንጂ፤ ኪሱ ሲፈተሽ ጥይት የማይገኝበት የለም ነበር። የሆነው ሆነና ፖፖላሬ መኮንንኖች ግቢ ሲዘረፍ ቤቱ ውስጥ የተገኘ የጥርስ ብሩሽ፣ ጫማና ሳሙና ጭምር ተዘረፈ።

ማታ ሲሆንሌላ ሰፈር አምሽቶ የመጣ ሌላ የጨርቆስ ልጅ ቀን ላይ ስላመለጠው ጸጋ ሲነገረው በጣም ተቆጨ። በንጋታው ወደ ፖፖላሬ መኮንኖች ግቢ በመሄድ እያንዳንዱን ቤት ቢፈትሽ ኦና ሆኗል። በኋላ ግን አንድ ሃሳብ መጣለት። “የሚከራይ ቤት” ብሎ በትልቁ በመጻፍ ቤቶቹን ለብዙ ግዜ ማከራየቱን የዚያ ሰፈር ልጆች አጫውተውናል። እንግዲህ ግንቦት ሃያ ሲመጣ ድንገት ትዝ ያሉንን ነገሮች ጣል ለማድረግ ያህል ይሄን አነሳሳን እንጂ፤ ሌላም ሌላም ገጠመኝ አለን።

ኢህአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ በጣም የቆጨው ነገር የኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም ወደ ዙምባብዌ መሄድ ነበር። ወያኔዎቹ እዚህ ዙምባቤ የሚባል ሰፈር ሄደው መንግስቱ ኃይለማርያምን ይዘው፤ ስጋውን ቢቆራርጡት ደስ የሚላቸው ይመስል ነበር። እናም አንድ ቀን ወያላው፤ “ሜክሲኮ ሜክሲኮ” እያለ ሲጮህ የሰሙት ወያኔዎች፤ “ከሜክሲኮ በቀር ሌላ አገር አትሄዱም እንዴ?” ቢለው፤ ተሳፋሪ አጥቶ ተቸገሮ የነበረው ወያላ… ነገሩ ገብቶት፤  “ዙምባቤ ዙምባቤ” እያለ መጣራት ሲጀምር ወያኔዎቹ ከነመሳሪያቸው ገብተው ሞሉት… ይባላል። ታክሲው አስነስቶ ከሄደ በኋላ መጨረሻቸው ምን እንደሆነ ባናውቅም፤ በወቅቱ ይሄን ሰምተን ፈገግ ማለታችን አልቀረም።

ሜክሲኮ አደባባይን አለፍ እንዳልን ደሞ ይሄ ገጠመን። አንዱን ወያኔ መንገደኛው ከቦ በጥያቄ ያዋክበዋል። “የኤርትራን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?” አንዱ ይጠይቃል። “ኤርትራ መገንጠል የለባትም” ሲል ሌላኛው አስተያየት ሰጠ። ወያኔው ግን አይኑን  የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ህንጻ ላይ እንደተከለ ነው። የህንጻው መስኮቶች አራት መአዘን ሆነው፤ በላዩ ላይ እንደዘመናዊ ቁም ሳጥን መስታወት ተለብጦባቸዋል። ወያኔው ስለኤርትራ የሚጠይቁትን ሰዎች ገሸሽ አደረገና… “አሁን ወሬውን ተዉና የዚህን ተደራራቢ ቁም ሳጥን ቁልፍ ማን ጋር እንዳለ ንገሩን” አላቸው። ይህን እውነት በስፍራው የነበረ አብዱራህማን የሚባል ጓደኛችን ነው የነገረን።

ወያኔ ግንቦት ሃያ ከገባ በኋላ የሰአት እላፊ ታወጀ። የሰአት እላፊው ደግሞ እስከ ለሊት ሳይሆን እስከ ምሽቱ ሁለት ሰአት ድረስ ነበር። የሆኑ ልጆች አምባሳደር አካባቢ ተዝናንተው ሲወጡ፤ በመከላከያ ወታደሮች ተከበቡ። አንበረከኩና ያናዝዟቸው ጀመር።

“የት ነበራቹህ? ወዴት ነው የምትሄዱት?” ብዙ ከጠየቋቸው በኋላ ወዴት ሰፈር እንደሚሄዱ ሲጠይቋቸው፤ አንዱ… “አራት ኪሎ” አለ። ሌላኛው “ስድስት ኪሎ” አላቸው። ሶስተኛው ሰፈሩ ወደ ጥቁር አንበሳ ስለሆነ፤ “እኔ ጥቁር አንበሳ…” ብሎ ሳይጨርስ አንደኛው ወያኔ በጥፊ አለውና “እንደነሱ በኪሎ ተናገር” አለው። አሁን ስናወራው ፈገግ ያሰኝ ይሆናል እንጂ በወቅቱ ከዚህ የባሰም ነገር ያጋጠማቸው ይኖራሉ።

ከሁሉም ግን ብዙ አስቂኝ ነገሮች ያጋጠሙን ኢህአዴጎች አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ትንሽ ቆይተው ደሞዝ ተብሎ መቶ መቶ ብር ለመጀመሪያ ግዜ ሲሰጣቸው ነው። ደግነቱ በዚያን ግዜ መቶ ብር ልብስ፤ እንደገና ሌላ ልብስ፣ ጫማ እና ነጠላ ጫማ ጭምር ይገዛ ነበር። አንዳንዶች መሸታ ቤት መግባት የጀመሩት ያኔ ነው። ሴቶቹን እየጎተቱ መታገል የጀመሩትም የመጀመሪያ ደሞዛቸውን እንዳገኙ ነበር።

እናም መቶ መቶ ብር ደሞዝ ከተከፈላቸው ወያኔዎች ውስጥ ሻል ያሉት ሂልተን ሆቴል ሄዱ። እዚያ ሄደው አስተናጋጅ በአይናቸው ሲፈልጉ ወንድ አስተናጋጆች በዙባቸው። እነሱ የሚያውቁት የቡና ቤት አስተናጋጅ ሴት ነው። ጭራሽ እነሱንም ‘ሸርሙጣ’ (ለቃሉ ይቅርታ) ይሏቸዋል። እናም ሂልተን ሆቴል ገብተው ወንድ አስተናጋጅ አጋጠማቸውና… “አንታ ወንዱ ሸርሙጣ ለኛም ታዘዘን እንጂ” ብለው፤ አንዳንድ ቦክሰኛ ኬክ አዘዙ።

ቦክሰኛውን ኬክ እንደገመጡ፤ ከውስጡ ነጭ ክሬም ሲወጣ፤ “እንዴት ያልበሰለ ኬክ ከነሊጡ ትሰጠናለህ?” ብለው ካቀባበሉ በኋላ በስንት ገላጋይ ነገሩ በርዷል።

የሊጥ ነገር ከተነሳ አንድ ገጠመኝ ታወሰንና ወደ ቦሌ ልንወስዳቹህ ነው። አብዛኛውን የደርግ ባለስልጣናት የነበሩበትን ዘመናዊ የቦሌ ቤቶች የወያኔ ሰዎች የገቡበት መሆኑን እናስታውሳለን። ለነገሩ አሁንም ድረስ እዚያ የሚኖሩ ስላሉ ምስክር መጥራት አያስፈልግም። (ጣልያን ኢምባሲ የገቡት የአቶ ሃይሉ ይመኑን ቤት ይጠቅሷል) ከ’ነዚህ ቤቶች መካከል በአንደኛው እንዲህ ሆነ። ወያኔዎቹ በዚህ የሚያምር ቤት ውስጥ ገብተው ብዙ አስደናቂ ነገሮችን ተመለከቱ። ምግብ እና የምግብ ማብሰያ ኩሽና ግን ሊያገኙ አልቻሉም። ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ የያዙትን በሶ የሚበጠብጡበት ውሃ አጡ። በዚህ መሃል ከነሱ ሻል ያለው በመገረም ጠራቸው።

“ቡሃቃውን አገኘሁት።” አላቸው። በሶ ለያዘው ሌላኛው ወያኔ በፍጥነት ወደ ባኞ ቤቱ መጣ።

ግር ብለው ወደ ባኞ ቤት ሲገቡ ሁሉም ነጭ ሆኖ ከሚያምር ክፍል ውስጥ ራሳቸውን አገኙት። ነጩ የገላ መታጠቢያ ገንዳ፤ ትልቅ የሊጥ ማቡኪያ ቡሃቃ ስለመሰላቸው ሁሉም በመገረም፤ “እዋይ…በዚህ ሙሉ ሊጥ ያቡኩበት ነበር? እውነትም ደርግ ይህን ያህል ሆዳም ነበር ለካ!?” ብዙ ያልተመለሰላቸውን ጥያቄዎች ከመገረም ጋር ሰነዘሩ። (ለነገሩ ይሄን ስናወራ ለአሁን ግዜ ልጆች ያጋነንን ሊመስላቸው ይችላል። ግን አይደለም።)

ባኞ ቤቱ ውስጥ እንደገቡ የሁሉም አይን በነጭ እምነ በረድ በተሰራው ገንዳ ላይ አረፈ። ይሄኛው ቡሃቃ መሰል ገንዳ ለነሱ እፍኝ በሶ ስለሚተልቅ፤ ሌላ አማራጭ ሲፈልጉ… አሁንም ሻል ያለው ወያኔ ትልቁን ፖፖ በስህተት ከፈተው። ሁሉም ደስ አላቸው። ቢያንስ ይሄኛው ነጭ ቡሃቃ፤ መክደኛ ብቻ ሳይሆን ከታች ውሃ አለው። ለነሱም በሶ የሚበቃ ሊሆን እንደሚችል ገመቱ። ከስር ያለውን ውሃ አይተው፤ በዚያ የምትበጠበጠውን በሶ አስበው ረሃባቸው ተባባሰ። በከረጢት የያዙትን በሶ እነሱ ቡሃቃ በመሰላቸው መጸዳጃ ፖፖ ውስጥ ጨመሩት። ውሃ አነሳቸውና… ውሃው እንዴት እንደሚከፈት ሲመራመሩ ውሃ መልቀቂያውን ገመድ አንደኛው ጎተተው። እናም ውሃው ፎለል እያለ ሲወርድ፤ ከረሜላ እንደተገዛለት ልጅ ሁሉም በደስታ ፈነደቁ።

የተለቀቀው ውሃ እየተሽከረከረ ሲያዩት አንደኛው ወያኔ፤ “በሶውን ራሱ እየበጠበጠው ነው።”   ሲል ሌላኛው ተከትሎ “Mixer’ኮ ኢዩ!” አላቸው። በ’ንግሊዘኛና በትግሪኛ። በአማርኛ ‘መበጥበጫ ነው’ አለ።

ይሄን አውርተው  ከመጨረሳቸው በፊት ውሃው እየተሽከረከረ በሶውን ይዞት ነጎደ። የጓጉለት በሶ ባልታሰበ ምትሃታዊ ሃይል ወደታች ሄደና ተሰወረ። በጣም የተናደደው ወያኔ ያለምንም ማቅማማት በሶውን ከታች ምጥጥ አድርጎ የወሰደበት ደርግ መሆኑን ጮክ ብሎ ተናገረ።

“ከዚህ በታች ደርግ አለ ማለት ነው” አለ።

“ደርግ ነው የጠጣብን?” ሌላኛው ጠየቀ።

“አዎ ደርግ እንጂ፤ ሌላ ሊጠጣብን አይችልም።” አለ የተሻለው ወያኔ።

በጣም የተናዳደው ባለ በሶ፤ “ምን ትጠብቃለህ? ሃደ ራሽያ ቦንቢ አጉርሰው እንጂ!!” አለው።

እውነትም አንዱን ቦንብ ላጥ አደረገና… ከታች ተደብቆ በሶውን በጠጣባቸው ወይም የጠጣ በመሰላቸው ደርግ ላይ የ’ጅ ቦንቡን ጣለበት። ተራራውን ያንቀጠቀጠው ወያኔ እንዲህ አደረገና የአቶ ኃይሉ ይመኑን ባኞ ቤት በቦንብ አፈራረሱት።

ያንን ዘመን ያላለፉ ሰዎች የፈጠራ ቀልድ ሊመስላቸው ይችላል። የነሱን ለነሱ ትተን አንድ ገጠመኛችንን እናጋራቹህ። ወያኔዎች አዲስ አበባ ሲገቡ መስኮት መስኮት ያለው ሸበጥ አድርገው ነው የገቡት። (እንዲያውም ለዚህ ጫማ አስመራ ይሁን ትግራይ ሃውልት ተሰርቶለታል) እናም የአንዱን ባለስልጣን ቤት ከተቆጣጠሩ በኋላ እዚያው ያድራሉ። ማቀዝቀዣው ቁም ሳጥን ስለመሰላቸው፤ ልብሳቸው ከዚያ… ጫማቸውን በረዶ መስሪያ ውስጥ አሳደሩት። ጠዋት ላይ ታዲያ እነዚያ ባለመስኮት ላስቲክ ጫማዎች በሥስ በረዶ ተሸፍነው ነበር። እናም አንዱ ቀልደኛ ወያኔ፤ “እዋይ ለኔስ ባለመስኮት ሸበጥ መስታወት ገባለት።” እያለ ድፍን ወያኔዎችን ለብዙ ግዜ ያስቃቸው ነበር። ይሄም አልፈ።

ከመሰናበታችን በፊት ግንቦት ሃያ ሰባት የሆነውን ነገር እንጨዋወት። ኢህአዴግ አዲስ አበባ በገባ በሳምንቱ ከኛ ሰፈር በላይ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤት ለሊት ላይ ፈነዳ። የአካባቢው ሰዎች አይተን በማናውቀው  ፍንዳታ ተደናግጠን አካባቢውን ለቀን ሄድን። ቀን ሲሆን ፍንዳታው በረድ በማለቱ አንዳንድ የሰፈር ልጆች ተመለሱ። ይሄ በአንድ የአርባ ቀበሌ ልጅ ላይ የሆነ ታሪክ ነው። የ40 ቀበሌው ልጅ የአርባ ቀን እድሉ ሆነና ወደ ሰፈር ተመልሶ መጣ። አካባቢው በወያኔዎቹ እየተጠበቀ በመሆኑ ወደ ቤት ለመግባት አልቻለም። እናም ከበድሩ ሱቅ ዳቦ ገዝቶ ኪሱ ከተተ።

ትንሽ ካዘገመ በኋላ ያቺን ዳቦ ለመብላት እጁን ወደ ኪሱ ሰደደ። ሁኔታውን ትንሽ ራቅ ብለው ሲከታተሉ የነበሩ አንድ ወንድ እና ሴት ወያኔ እንዲህ ይባባላሉ። “እጁን ኪሱ ውስጥ ከተተ።”

“ቦምብ ሊያወጣ መሆን አለበት።” ሴቷ ወያኔ ናት እንዲህ ያለችው። ሴት ድሮም ጠርጣራ ናት።

ልጁ… የ’ጁን መዳፍ የምትሞላ ዳቦውን ከኪሱ እንዳወጣ፤ “አወጣው!” አላት፤ መሳሪያ አቀባብሎ ከርቀት የሚመለከተው ወያኔ።

የአርባ ቀበሌው ልጅ፤ የአርባ ቀን እድሉ የሆነችውን ያቺን ዳቦ ሊገምጣት ወደ አፉ አስጠጋ። ይሄን የተመለከተው ወያኔ አብራው ላለችው ተጋዳላይ፤ “ቦንቡን ሊነቅለው ነው” አላት።

“ምን ትጠብቃለህ?” ብላ ጀመረች ሴቷ፤ “ምን ትጠብቃለህ? ሳይነቅል ንቀለዋ!” ከማለቷ ተኩሶ ልጁን ጣለው።

የአካባቢው ወጣቶች በፍንዳታው ፍንጥርጣሪ ተመትቶ የወደቀ ነበር የመሰላቸው። በኋላ ግን ወያኔዎቹ ተሯሩጠው መጥተው ሊነቅል የነበረውን ቦንብ ለማየት፤ መሬት የወደቀውን ልጅ ገልበጥ ሲያደርጉት፤ ዳቦ እንደጎረሰ አዩት። እናም ምን ቢሉ ይገርማል? “ይሄ ንቃት የጎደለው፤ መንገድ ለመንገድ ዳቦ ይበላል እንዴ?” ብለው ጭራሽ ስለ ልጁ ንቃተ ህሊና ማነስ በማውራት ይወቅሱት ጀመር።

ከሰፈራችን ሳልወጣ እኛ ሰፈር ቴሌው ጋር የሆነውን ተጨዋውተን እንሰነባበት። ያኔ ቴሌ በራፍ ላይ የህዝብ ስልክ ነበር። (አሁን ይኑር አይኑር አላውቅም።)  እንዳሁኑ ሞባይል ስልክ ከመብዛቱ በፊት ህዝቡ ተሰልፎ የህዝብ ስልክ ይጠቀማል። አንዱ ወያኔ የኛን ሰፈር ልጆች ጠየቃቸው። “የምን ሰልፍ ነው?” አለ።

“ስልክ ለመደወል ወረፋ ይዘው ነው” አሉት። ወያኔው ከጓደኛው ጋር በመሆን ወደ ቴሌ በራፍ ተጠጉ። ተጠግተው… በጣም ጠጋ ብለው ሲያዩ እውነትም ‘የህዝብ ስልክ’ የሚል ጽሁፍ ተለጥፎበታል። በዚያ ላይ ህዝቡ ሳንቲም እየጨመረ ስለሚደውል፤ ያቺን ሳንቲም ሌባ እንዳይሰርቃት፤ መሳሪያቸውን አቀባብለው ይጠብቁ ጀመር። ያው እንደሚታወቀው ኢህአዴግ እንደገባ፤ ለሌባ ምንም ምህረት ሳያደርግ ይገድል ነበር። እናም ጥበቃውን አጠናከሩት።

አንድ ሁለት ሰው ሳንቲም እየጨመረ ከደወለ በኋላ፤ የፈረደበት ሶስተኛው ሰው ወረፋው ደርሶት የስልኩን እጀታ አነሳ። ሳንቲም ጨመረ። ሆኖም የደወለበት ቦታ የመያዝ ምልክት ስለሰጠው፤ ያስገባውን ሳንቲም መልሶ ለማውጣት እጀታውን በንዴት ሲጫነው፤ ሳንቲሙ ከታች ወረደ። እናም እነዚያን ሳንቲሞች ወስዶ ከመሄዱ በፊት… ወያኔዎቹ ተነጋገሩ። “ይሄ ሌባ። የህዝቡን ሳንቲም ወሰደ እኮ።” አለው አንደኛው።

“ታዲያ ምን ትጠብቃለህ?” ይቺን ቃል ይወዷታል። “ታዲያ ምንትጠብቃለህ?” አለው። ‘በሌባ ላይ የሚወሰደውን እርምጃ አትወስድበትምን?’ ከማለቱ በፊት የተኩስ ድምጽ ተሰማ። ልጁ ሃያ ሳንቲሙን እንደያዘ ወደቀ። ይሄ ሰፈራችን ውስጥ የሆነና ለምን እንደተኮሱበት ራሳቸው በአንደበታቸው የነገሩን በመሆኑ፤ ‘እውነት አይደለም’ ብላቹህ እንዳትጠራጠሩ።

ለነገሩ እኛ ከዳር ሆነን ያየነውን አወራን። ከዚህ በላይ ብዙ ያዩ እና የሰሙ ይኖራሉ። እኛ ስለአዲስ አበባ አወራን እንጂ በየገጠሩ የሆነውን ቤቱ ይቁጠረው። ደግሞም የድርጊቱ ፈጻሚዎች፤ ከዛሬው ጉራ ይልቅ ራሳቸው ብዙ ሊነግሩን የሚችሉት ገጠመኝ እንደሚኖር ልንገምት እንችላለን። በዚያም ተባለ በዚህ ግንቦት ሃያ ሲመጣ እነዚህ እነዚህን ነገሮች እናስታውሳለን።

ነገሩ በጣም በሚገርም የታሪክ እሽክርክሪት አለው። ድሮ ሌባ የማይወደው ወያኔ ወይም ኢህአዴግ፤ አሁን ራሱ ሙልጭ ያለ ሌባ ሆኖ አረፈውና ጠቅላይ ሚንስትሩ ሳይቀሩ፤ ትላልቆቹን ወያኔዎች ጠርተው “ሙስናን መዋጋት አለብን። ይህንን ከራሳችን እንጀምር።” አሏቸው። እናም የግንቦት ወር ሲመጣ… ኢህአዴግ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ያጠፋቸውን ነፍሶች እናስባለን። ያጠፋቸውን ስህተትቶች እያሰብን ደግሞ ፈገግ እንላለን።

እነሱ ተራራውን አንቀጠቀጥን” እያሉ ይደነፉብናል። እኛ ደግሞ፤ “እሱን ተዉትና… ምነው ከጎናቹህ ያለውን ዘመናዊ ሌባ ተዋግታቹህ ማሸነፍ አቃታቹህ?” እንላቸዋለን። እንዲህ እንዲህ እያልን… የድሮው ጉንቦት ሃያ አልፎ ሌላ ግንቦት  ይመጣል። እኛም ‘ፈገግ የሚያሰኙንን ገጠመኞች እያሰብን ዘና ፈታ የምንልበት ምክንያት አናጣም’ እናም የድሮውን እያሰብን ፈገግ እንላለን።

ብዙ የሚባል ነገር እያለ፤ ጨዋታችን ሳያልቅ አለቀ።

Received on Sun Jun 05 2016 - 14:35:50 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved