Goolgule.com: “[እምቢ ካሉ] አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን የሚያሽመደምድ ስልት አለን”

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Sat, 4 Jun 2016 13:13:33 +0200

“[እምቢ ካሉ] አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን የሚያሽመደምድ ስልት አለን”

የኢህአዴግ “ኦሮማይ” ነጸብራቅና ድርጅታዊ መሰነጣጠቅ
students exam

ህወሃት ኦህዴድን ለማጽዳት በሚል ከ800 የሚበልጡ ሃላፊዎችን በየእርከኑ ቢያሰናብትም ለውጥ የሚታይ አልሆነም። ይልቁኑም የተጠኑ በሚመስሉ ማህበራዊ ጉዳዮች መናጡ እየተባባሰ ነው። አቶ ጃዋር መሐመድ ኢህአዴግ የቀረበለትን “የምክር ሃሳብ” የሚሰማ ካልሆነ አጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱን የሚያሽመደምድ ስልት አለን ማለታቸው “እንዴት” የሚል ጥያቄ ቢያስነሳም ጆሮ ያገኘ ወሬ ሆኗል። ይህንኑ ተከትሎ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ጉዳዩን ከተወዳጁ ደራሲ በአሉ ግርማ ትንቢታዊ ድርሰት ጋር በማያያዝ “የኢህአዴግ ኦሮማይ እየተቃረበ ነው” ሲሉ በድፍረት ተናግረዋል።

በትላንትናው እለት የቪኦኤ አማርኛ ክፍለ ጊዜ ካቀረበው ቃለ ምልልስና ካጠቃላይ እውነታዎች ለመረዳት እንደተቻለው ኦሮሚያ ውስጥ የተጀመረው “ሰላማዊ” ትግል እየበሰለ የሄደ ይመስላል። ቀደም ሲል በተደረጉ የድርጅትና የውስጥ ግንኙነቶች የኦሮሞዎች ትግል አንድ ደረጃ ከፍ ሊል ያልቻለው “ኦሮሚያን የሚያስቀድም ሚዲያ ባለመኖሩ ነው” ከሚል ድምዳሜ ተደርሶ ነበር። በዚህ ውሳኔ መነሻ ይሁን በሌላ አቶ ጃዋር መሐመድ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ የተሰኘውን ሚዲያ በሃላፊነት በመምራት ይፋ ወጡ።jawar m

አቶ ጃዋር የሚመሩት ይህ ሚዲያ ለስድስት ወራት ያህል በኦሮሚያ ሲካሄድ የነበረውንና አሁን ድረስ እሳቱ ያልተዳፈነውን ተቃውሞ ዝርዝር ጉዳዮችን በማቅረብ፣ ትኩስ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን በማሰራጨት ግንባር ቀደም ሆኖ ታይቷል። ኦሮሚያ ላይ ሲካሄዱ የቆዩትን ተቃውሞዎች በማስተባበር ግንባር እንደሆኑ በመግለጽ ፊት መስመር የወጡት አቶ ጃዋር፣ “ጽንፈኛ፤ አክራሪ” በሚል የሰላ ተቃውሞ ቢሰነዘርባቸውም የዚያኑ ያህል ደጋፊና ተከታይ ስለማፍራታቸው ብዙም ክርክር የማያስነሳ ሃቅ ሆኗል።

በኦሮሚያ ፖለቲካው ግልጽ ያለ አቋማቸው ምን እንደሆነ በውል የማይታወቀው አቶ ጃዋር በሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ያላቸው ተቀባይነት እንዲሁም ኦሮሚያን መሰረት ካደረጉ ፖለቲከኞች ጋር አሁን የደረሱበት የግንኙነት ደረጃም የጠራ አይመስልም። ለዚህ ይመስላል አካሄዳቸውን በጥንቃቄ የሚመለከቱ የሚበረክቱት። ከዚህም በላይ የ“ሜንጫ” ስም ጠርተው የተናገሩት ዛቻ አዘል ንግግር ደግሞ በተዛተባቸው፣ የጎሳንና የቂም ፖለቲካን በሚጠየፉ ወገኖች ዘንድ የሚጠሉ አድርጓቸዋል።

ምንም ይሁን ምን ግን ኦሮሚያ ላይ ከወትሮው በተለየ የጋለና ረጅም ጊዜ የቆየ አመጽ መቀጣጠሉን ተከትሎ የተከሉት ስም ጃዋርን አጉልቶ አውጥቷቸዋል። አሁን ደግሞ የኦሮሚያን ተማሪዎች የወደፊት ህይወት ለመታደግ በሚል የተወሰደውን ብሔራዊ ፈተናን አስቀድሞ ይፋ የማድረግ ዘመቻ የመሩት እሳቸው መሆናቸውን በማስታወቅ ሃላፊነት መውሰዳቸው ጃዋርን ለጉዳዩ ፊትአውራሪ አድርጓቸዋል። እሳቸው እንደሚሉት የጉዳዩ ባለቤት ሙሉ በሙሉ እሳቸውና የሳቸው ኔትዎርክ ከሆነ፣ ድርጊቱ የሌሎች የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎችን ሚና እንዳያቀጭጨውና ጥያቄ ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል “ተግባር ናፈቀን” የሚሉ ይጠቁማሉ።

ከሁሉም በላይ የትምህርት ሚኒስቴር የፈተናውን መሰረዝና፣ ፈተናው እንደገና የሚሰጥበትን ቀን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አቶ ጃዋር “ምክረ ሃሳብ” ለኢህአዴግ ሃላፊዎችና ለትምህርት ሚኒስትሩ መላካቸውን ሲናገሩ “ከእንግዲህ እምቢ ብለው የሚቀጥሉ ከሆነ ለሚመጣው ማንኛውም ዓይነት ኪሳራ ተጠያቂ ይሆናሉ” በሚል ማሳሰቢያ ሰጡ። ቀጥለውም “የትምህርት ስርዓቱን ሙሉ በሙሉ የሚያሽመደምድ ታክቲክና ስትራቴጂ አለን። አሁን እዚያ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም” ሲሉ አስጠነቀቁ። ይህንን ብልት ጉዳይ በተከታይ ጥያቄዎች ከማጠናከር ይልቅ የተኛችበት የቪኦኤ ቃለምልልስ አድራጊ ቢያንስ ለወደፊት በዚህ ጉዳይ ላይ እንደምትመለስበት ፍንጭ ሳትሰጥ ራስዋን አዳማጭ አድርጋ አልፋዋለች።

oromo1አቶ ጃዋር በዚህ አላበቁም በትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን ቁጥጥር ሙሉ በሙሉ ሽባ የማድርግ ስራ እንደሚሰሩም ነው የዛቱት። “እንዴት” የሚለው ጉዳይ አሁንም የበርካቶች ጥያቄ ቢሆንም “በጎ ምላሽ እንጠብቃለን፤ እኛ በእልህ የምናደርገው ነገር የለም” ሲሉ ውሳኔ ሰጪዎች ራሳቸውን ከእልህ እንዲያጸዱና ተጨማሪ ውድመት ከማስከተል እንዲታቀቡ ተለሳልሰው ጥሪ አድርገዋል።

ከቪኦኤ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት አቶ ጃዋር በተደጋጋሚ ከፈተና አዘጋጆች ወይም ከፈተናዎች ኤጀንሲ፣ ከዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ከባለሙያዎች፣ ከትምህርት ቢሮ ሰዎች ጋር በመመካከር ሃሳቡን እንዳቀረቡ ጠቁመዋል። በጥቆማው መሰረት ተማሪዎች የሁለት ወር ተጨማሪ ጊዜ ቢሰጣቸው እንደሚበቃ የማሳመን ስራ ተሰርቷል። እናም ይህ እሳቸው በጥናት ተሰርቶ እንደቀረበ ያመለከቱት ምክረ ሃሳብ ተቀባይነት ካላገኘና ፈተናው ለሁለት ወር ካልተራዘመ ቀጣዩ ስትራቴጂ ተግባራዊ ይሆናል። ኢህአዴግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝብ አመጽ አዋጅ መሻር፣ መመሪያ መቀየር፣ ህግን መገደብ፣ ወዘተ እየቀናው ስለሆነ ውሳኔው በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል። ፈተናው የሚሰጥበት ቀን የኢድ በዓል ዋዜማን ማግስት መሆኑም ሌላው ትኩሳት መሆኑ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

በኦሮሚያ በአማካይ አራት ወራት ትምህርት አለመሰጠቱ፣ መጠነኛ ሰላም አለባቸው በሚባሉት አካባቢዎች ተማሪዎችና መምህራኖች መታሰራቸውን፣ መምህራን የማስተማሪያ መጽሃፍትን ግማሽ ድረስ እንኳን አለማስተማራቸው፤ ተማሪዎች የጠየቁት የአራት ወር ጊዜ ቢሆንም፣ ጃዋር “ከእኛ ጋር የሚሰሩ” ያሏቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለእረፍት ሲመለሱ የማካካሻ ክፍል ትምህርት እንደሚሰጧቸው ከመግባባት ላይ ተደረሶ ሁለት ወር እንዲጨመር መስማማታቸውን በቃለ ምልልሱ ወቅት ተነግሯል። dagnachew a

እዚህ መሃል አዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ በፖለቲካ ውሳኔ ያባረራቸው ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ አስተያየት ሰጠተዋል። እየሳቁና መገረማቸውን እየገለጹ ነበር የተናገሩት። የተማረና ያልተማረ አንድ ማዕድ ላይ እንዲቀርቡ ማድርግ ፍትሃዊ እንዳልሆነ አመልክተው “…አንድ አስተማሪስ እንዴት ያላስተማረውን ይፈትናል?” ሳቁና “ያሰቃል እኮ” ሲሉ ግርምት አሳዩ። ከዚያም የማይሆን ውሳኔ ተላልፎ ሲያበቃ “ፈተና ጠፋ ተባለ” ሲሉ ጉዳዩን የፖለቲካው ነጽብራቅ እንደሆነ ጠቆሙ።

“የኃይለሥላሴ ኦሮማይ ነበር፤ የደርግ ኦሮማይ ነበር፤ አሁን ተራው የኢህአዴግ ኦሮማይ ነው” በማለት ጉዳዩ የፖለቲካ ጥያቄ ስለመሆኑ አሰመሩበት። “ኢህአዴግ ቅንጅት ነው” ካሉ በኋላ ቅንጅቱ በመሰነጣጠቅ ላይ መሆኑን የሚያሳይ የሂደት ነጸብራቅ እንደሆነ በማከል “የኢህአዴግ ኦሮማይ” ሲሉ የጠሩት ጊዜ ስለመቃረቡ አስረዱ። አክለውም “አንድ ፈተና እንኳን ተቀናጅተው መፈተን አልቻሉም። አንድ ስርዓት ተቀናጅቶ በቀድሞ መልኩ መሄድ ካልቀጠለ ኦሮማይ ነው” ብለዋል፡፡

የተዘጋጁ ተማሪዎችና ቤተሰቦቻቸው የስነልቦና ችግር ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በማመልከት ሁሉንም አቻችሎ ማስኬድ እንደሚገባ የጠቆሙት ዶ/ር ዳኛቸው “እኛ የተናገርነው አይቀርም የሚለው አባባል ትክክል አይደለም” በማለት ነገሮችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማየት አስፈላጊ እንደሆነ መክረዋል።

አስተያየት ሰጪ ተማሪዎች የፈተናው ቀን እንዲራዘም መደረጉ እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፣ አሁንምም በተመሳሳይ በቀረበው የምክር ሃሳብ መሰረት ተግባራዊ ሊሆን እንደሚገባ ለቪኦኤ ሲናገሩ ተሰምተዋል። በሌላ በኩል ለፈተናው ዝግጅት ያደረጉ ደግሞ ሁኔታው የፈጠረባቸውን ኪሣራ በሕይወታቸው ላይ መቼም ሊስተካከል የማይችል ጉዳት ማድረሱን ይናገራሉ፡፡ የእንዲህ ዓይነቶቹን ተማሪዎች ምሬት በማጉላት የህወሃት ቅጥረኞች ድርጅታቸውን በከፍተኛ የሞራል ማማ ላይ ሰቅለው የሥነምግባር ጥያቄ ሲያነሱ መደመጣቸውን ተከትለው አስተያየት ሰጪዎች “ለረሃብተኛ በተላከ ገንዘብ መሣሪያ የሚሸምተው ድልድይ አፍራሹ ህወሃት ምነው ሃውዜንን ረሳው” ብለዋል፡፡

ኦህዴድ ለማፈንገጡ ዋና ምልክት መሆኑ የተነገረለት ይህ ክስተት ማቆሚያው የት እንደሚሆን ባይታወቅም “ህዝብ ለምን ይገደላል በማለት የጠየቁ ተባረዋል። እነዚህ ወገኖች ጥፋት የለባቸውም። የህዝብ ወገኖች ናቸው” በማለት ኦፌኮ የተባረሩትን የኦህዴድ አባላት ማወደሱ አይዘነጋም። OFC_Merera_Bekeleበተመሳሳይ ህወሃትን ከህዝባቸው በላይ በማስቀደም የሚያገለግሉትን መንቀፉ ይታወሳል።

ቀደም ሲል 23 የአስረኛ ክፍልና 12 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የፈተና ጊዜ እንዲራዘም ሲወሰን ድርጊቱን የተቃወሙ እንደነበሩ ተሰምቷዋል። ሙሉ በሙሉ በአገር አቀፍ ደረጃ ፈተናው ሊቋረጥ እንደሚገባ አቋም የያዙ ክፍሎች “ዝም በሉ” እንደተባሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሌላ በኩል በድጋሚ የሚሰጠው ፈተና በልዩ ግብረሃይል ጥበቃ እንደሚከናወን ሪፖርተር ባለስልጣኖችን ጠቅሶ ረቡዕ እለት ዜና ሲያስነብብ “ልዩ ግብረኃይል” የማስፈተኑን ተግባር ተማሪዎችን በሜካናይዝድ ብርጌድ በማጀብ ወይም ብረት በማስለበስ ወይም የትምህርት ተቋማትን opdoበታንክ በማጠር እንደሚከውነው ያለው ነገር የለም። ሪፖርተር አቅለስልሶ ወሬ ያደረገው ይህ ዜና ሌሎች እያቀረቡ ስላለው የተጨማሪ ጊዜም የሰጠው ሃተታ የለም። ጉዳዩን ፖለቲካ ነው የሚሉ ወገኖች “ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የኦህዴድ ሰዎች ከተባረሩ በኋላ ህወሃት አሁንም ኦህዴድ ውስጥ ያለውን መዋቅር ካላመነ ፈተናው ሊከናወን አይችልም የሚል ስጋት አለን፤ 25 ዓመት ሙሉ ሁሉንም ነገር በራሱ መነጽር ሲይይ የኖረው ህወሃት ቢያንስ አሁን እንኳን ቆም ብሎ ቢያስብ ይሻለዋል” ብለዋል።

“ሁሉን ትወዳለህ፣ በመጨረሻም ሁሉን ታጣለህ! ሴላቪ ኦሮማይ!”?

Received on Sat Jun 04 2016 - 07:13:33 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved