Ethsat.com: የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሰራተኞች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ ስብሰባው ተበተነ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Fri, 30 Sep 2016 23:18:01 +0200

የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሰራተኞች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ ስብሰባው ተበተነ

September 30, 2016

Watch this news:

ESAT Daily News Amsterdam September 30,2016

http://video.ethsat.com/?p=28930

መስከረም ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- የጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህራንንና ሰራተኞች ዛሬ በሳይንስ አምባ አዳራሽ ላይ ስብሰባ የተካሄደ ቢሆንም፣ መምህራኑ በጩኸት እና በፉጨት ተቃውሞ በማሰማታቸው እንዲበተን ተደርጓል።

ስብሰባውን የመሩት የቀድሞው የትምህርት ሚ/ር ዶ/ር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ሲሆኑ ፣ ንግግር ሲጀምሩ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ በጩኸት አቋርጧቸዋል። ስብሰባው መቀጠል እንደማይቻል የተረዱት ሰብሳቢዎቹ በእረፍት አሳበው ከ20 ደቂቃዎች በሁዋላ  ስብሰባውን በትነውታል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ደሳለኝ መንገሻ የስብሰባው ርዕስ እና አጀንዳ ከፓለቲካ ወደ እቅድ አፈፃፀም ዛሬ ከሰአት ይቀጥላል ቢልም  መምህራን ግን ተቃውሟቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡ ሰው እየተገደለና እየታፈነ እኛ ሰላም ያለ ለማስመሰል አንሰበሰብም በማለት ተቃውሟቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርስቲ መምህራንም ለ2 ሳምንት ሊሰጣቸው የነበረውን የፖለቲካ ስልጠና በመቃወማቸው ስብሰባው እንዲበተን ተደርጓል።

በአማራ ክልል በሚካሄደው የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግል የተቃውሞው ማእከል የሆኑት ጎንደርና ባህርዳር ዩኒቨርስቲዎች መምህራን እያሳዩት ያለው የአቋም አንድነት፣  ገዢው ፓርቲ ዩኒቨርስቲዎቹ ስራ ሲጀምሩ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ሊጀምሩ ይችላሉ የሚለውን ስጋት አባብሶታል።

የመምህራን ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን፣ በሰ/ሸዋ ዞን  መርሐቤቴ ወረዳ አለም ከተማ ፣ አለም ከተማ መሠናዶ:፣ አርበኞች አጠ/2ኛ ደረጃ እና አለም ከተማ 1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከመስከረም 18፣ 2009 ዓም ጀምሮ ለተከታታይ  6 ቀናት ሊሰጥ የነበረው ስልጠና መምህራኑ በዝምታ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ  እንዲቋረጥ ተደርጓል።

የዓለም ከተማ መሰናዶ መምህራን  ሰብሳቢዎቹን የወረዳውን አስተዳዳሪ አቶ ዘውዴ እና የብአዴን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰጠኝን “ስርዓቱ ሊለወጥ ስለማይችል ሰልችቶናል፣ ሀሳብ የለንም” ብለው የነገሩዋቸው ሲሆን፣   ሀሳብ የሚሰጥ መጥፋቱን የተመለከቱት አስተዳዳሪው “ስልጠናው ሳይሰጥ ትም/ት አትጀምሩም፣ በኛ በኩል ከአቅማቸን በላይ ነው፣ የክልሉ ወይም ከዚያ በላይ ያለው አካል ይፈታዋል “በማለት ማስፈራሪያ ቃሎችን ተናግረው ተመልሰዋል።

በላሊበላ ከተማ በሚደረገው  የመምህራን ስብሰባም መምህራን 4ቱን ቀናት ምንም ነገር ሳይናገሩ ያሳለፉ ሲሆን፣  ሰብሳቢዎቹ “ እያንዳንዳችሁን በሚስጢር እናጠናችሁዋለን” በማለት መምህራኑን ለማስፈራራት ሞክረዋል። እነሱ የመለመሉዋቸው መምህራን እንዲናገሩ ለማግባባት ቢሞክሩም እንዳልተሳካለቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ መምህራን ገልጸዋል።

በአቸፈር ወረዳ በዱርቤቴ ከተማም እንዲሁ መምህራን በዝምታ ተቃውሞአቸውን መግለጻቸውን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያመለክታል። መምህራኑ ባለፉት 25 ዓመታት ያየነው ለውጥ የለም በማለት በስብሰባው ላይ አስተያየት ላለመስጠት መወሰናቸውን መምህራን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አሁንም በጎንደር የንግድ ድርጅቶችን የማሸግ እንቅስቃሴው ቀጥሎአል። የተወሰኑ የንግድ ድርጅቶችን በመዝጋትና ቅጣት በመጣል፣ የተወሰኑትን ደግሞ በመዝለል ነጋዴውን ማህበረሰብ ለመከፋፈል የሚጠቀሙበት ስልት ነው በማለት የትግሉ አስተባባሪዎች ይናገራሉ።  አገዛዙ ሁሉም የንግድ ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲከፈቱ የማያደርግ ከሆነ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰድ ይጀምራሉ ብለዋል።

********************************************************************************

በቢሾፍቱ ከተማ ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

September 30, 2016

ኢሳት (መስከረም 20 ፥ 2009)

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ከነገ በስቲያ እሁድ በበሾፍቱ ከተማ ለሚከበረው የእሬቻ በዓል ልዩ ሃይል ተመድቦ የጸጥታ ቁጥጥር በመደረግ ላይ መሆኑን አርብ አስታወቀ።

የከተማዋ ነዋሪዎች የፌዴራልና የክልል የጸጥታ አባላት ከመቼውም ጊዜ በላይ በመሰማራት ተሽከርካሪዎችን  ጨምሮ በተለያዩ ስፍራዎች ፍተሻ በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ረቡዕ ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አርብ ባወጣው መግለጫ በከተማ የበዓሉ አከባበር በሰላም እንዲስተናገድ ለማድረግ ታስቦ ልዩ ሃይል መመደቡንና ከነዋሪዎች ጋር በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር መካሄዱን አመልክቷል።

በኦሮሚያ ክልል በበርካታ ከተሞች ለወራት ሲካሄድ የቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ በደብረ ዘይትና ዙሪያዋ ባሉ የገጠር ከተሞች ሲካሄድ የነበረ ሲሆን ተመሳሳይ ተቃውሞ በበዓሉ አከባበር ወቅት ሊነሳ ይችላል የሚል ስጋት በመኖሩ ጥበቃው ከመቼውም ጊዜ በላይ መጠናከሩን ነዋሪዎች አስረድተዋል።

ከአዲስ አበባና አዳማ ናዝሬት በኩል ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ፍተሻ እየተካሄደባቸው መሆኑን የተናገሩት እማኞች የበዓሉ ዝግጅት ከአከባበሩ በላይ አለመረጋጋት መስፈኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ህብረተሰቡ የጸጥታ ስጋት የሆኑ ነገሮችን ሲመለከት ለጸጥታ ሃይል መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል። የበዓሉ አስተባባሪዎች ወደ 3ሺ የሚተጋ ሰው በእሬቻ አመታዊ በዓል አከባባር ላይ በመታደም ወደ ቢሾፍቱ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።

*******************************************************************************

የመልቀቂያ ወረቀት ያቀረቡ በርካታ ወታደሮች በመለስ አጽም እየተባሉ እንዲቆዩ እየተለመኑ ነው

September 29, 2016

መስከረም ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በመላው አገሪቱ የሚታየውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የ7 አመታት የከንትራት ጊዜያቸውን የጨረሱ ወታደሮች መልቀቂያ በብዛት እያስገቡ ቢሆንም፣ አዛዦቹ የቀድሞውን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፎቶ እግራቸው ስር በማንጠፍ “ የመለስን ፎቶ ተራምደኸው እለፍ፣ በመለስ አጽም ይዘንሃል” እየተባሉ ኮንትራታቸውን እንደሚያራዝሙ የመከላከያ ምንጮች ገለጹ”

በአሁኑ ሰአት መከላከያው ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ወታደሮች በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የሚካሄዱትን ህዝባዊ አመጾች ፣ “በአማራ ክልል ከሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ገብቶ የህዝብ ንብረት እያወደመ ህዝብ እያተራመሰ ነው ፣ በኦሮሚያ ክልል ከሆነ ደግሞ ኦነግ ገብቶ ህዝብ እየበጠበጠ ነው ለግዳጅ ተዘጋጁ” እንደሚባሉ ተናግረዋል። ሰራዊቱ ወደ ቦታው ደርሶ ሁኔታውን አጣርቶ የራሱን ግንዛቤ እንዳይዝ ለማድረግ ኔት ወርክ እንደሚዘጉበትና ከሌላው ህዝብ ጋር እንዳይገናኝ እንደሚያደርጉት እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል። በዚህ የተሳሳተ መረጃ  ወታደሩን ከእህት፣ ወንድሙ እናት እና አባቱ ጋር እያዋጉት ነው በማለት ሰራዊቱ ስለገጠመው ፈተና ይገልጻሉ። ሁኔታውን ዘግተውም ቢሆን የተረዱ ወታደሮች መልቀቂያ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከአቀጣጠሩ ጀምሮ እየተሰራ ያለውን ደባም በዝርዝር ይናገራሉ። መጀመሪያ አንድ ወጣት ወደ ውትድርና ማሰልጠኛ ለማስገባት ሲመለምሉ ጤና ሳይንስ፡ ኮምፒውተር ሳይንስ፡ ኢንጂነሪንግ የመሳሰሉትን ትማራላችሁ ብለው በማታለል መሆኑን የሚናገሩት ምንጮች፣ በሁዋላ ላይ ትምህርቱን የሚማረውና አየር የሚያበረው ግን አብዛኛው የህወሃት አባላት ብቻ ናቸው ይላሉ።

ሰራዊቱ በመጀመሪያ የፈረመውን የ7 አመታት ኮንትራት በአነስተኛ የደሞዝ ክፍያ ቢጨርስም፣ ኮንንትራቱ ካለቀ በሁዋላ ግን አብዛኛው መልቀቂያ እንደሚያስገባ ይገልጻሉ።

ቀድም ብሎ “አንፈልግም” የሚሉትን ወታደሮች  ባንዲራ እያነጠፉ “ አልፈልግም ካልክ ባንዲራውን እረግጠኸው ሂድ” የሚል አሰራር ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን፣ አንዳንድ ወታደሮች በምሬት እና በንዴት  ወደ ቤተሰቤ መሄድ እፈልጋለሁ ብለው ባንዲራውን ተራምደው ሲያልፉ በጠላትነት ተፈርጀው ሰባት ዓመት እንዳላገለገለ ሁሉ  ወደ ወታደራዊ እስር ቤት ይወረወራል ይላሉ ፡፡

በአገሪቱ የሚታየው ችግር እየተባባሰ መምጣቱንና የስርዓቱን ባንዲራ እየተራመዱ የሚሄዱ ወታደሮች መበራከታቸው ያሳሰባቸው አዛዦች፣ ከባንዲራው የበለጠ ጉልበት ይኖረዋል ብለው የሚያስቡትን የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶ በመያዝ ፣ በመለስ አጽም እያሉ በመለመን ላይ ናቸው። በአካል ብቃት ችግር ወይም በህመም ሲሰናበቱም አንድ አመት ላገለግሉበት 1 ሺ ብር በአጠቃላይ ለ7 አመታት አገልግሎት 7 ሺ ብር ብቻ ተሰጥቷቸው እንደሚሰናበቱም ገልጸዋል።

ከወታደራዊ ማሰልጠኛ እስከ ዋናው የጦር ክፍል ድረስ የሚዘመረው ስለ ህወሓት ጀግንነት መሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ በብሄር የተነሳ የበላይነትና የበታችነት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚሰራ በመሆኑ በሰራዊቱ ውስጥ ለሚታዬው ክፍፍል አንዱ ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከዋናው ኢታማዦር ሹም ሰሞራ የኑስ ጀምሮ የ4ቱም ዕዝ አዛዦች፣ የመከላከያ ዩኒቨርስቲ የ2ቱም ካምፓስ አዛዦችና አመራሮች እንዲሁም የጦር ማሰልጠኛ ክፍሎችና የክፍለ ጦር አዛዦችና አመራሮች በሙሉ ይህን የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በንቃት እንደሚሰሩ ይገልጻሉ።

አብዛኛው ስልጣን አልባ የተደረገው ታዛዡ ወታደር ወር ሃዊ ደሞዙን እንኳ በወጉ እንዳይገኝ በሰበብ አስባቡ እንዲቆረጥበት መደረጉ ለተጨማሪ ብሶት ዳርጎታል።

አንድ ወታደር ግዴታ በ6 ወር አንድ ጊዜ የወታደራዊ ሬንጀር አልባሳትና ከስክስ ጫማ  አሟልቶ መግዛት ግዴታው እንደሆነ የሚገልጹት ወታደራዊ ምንጮች፣ ልብስና ጫማ አንድ ጊዜ ለመግዛት የ2 ወር ደመወዙን እንደሚያጣ፣ “ሰራዊት አይደለም ብሩን ህይወቱን እየለገሰ ነው” በሚል ቅስቀሳ ደግሞ ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በየዓመቱ የ1 ወር ደመወዙን እንዲከፍል መደረጉ ፣ ወታደሩ በዓመት የ7 ወር ደመወዝ ብቻ እያገኘ ህይወቱን እንደገፋ መደረጉ  እንዲሁም በውጭ ሀገር ሰላም አስከባሪ እየተባለ በዳርፉር፡ በአብይ ግዛትና በሶማሊያ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የሚያመጣው ገንዘብ አብላጫው ፐርሰንት ለመንግስት ግብር እየተባለ እየቆረጠ ለህወሓት ጀኔራሎች  ቤት መስሪያና ለመኪና መግዢያ  መዋሉ ወታደሩ በብዛት እየለቀቀ እንዲሄድ ተጨማሪ ምክንያት ነው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የትግራይ ተወላጅ የአጋዚ አባል፣ “በህዝቡ ላይ በወሰድኩት እርምጃ ተጸጽቻለሁ፣ ከዚህ በሁዋላ ግን ይህን ስርዓት አላገለግልም” በማለት ዩኒፎርሙን አውልቆ እና መሳሪያውን ለአካባቢው ሰዎች አስረክቦ ከፍኖተሰላም ከተማ መጥፋቱን ምንጮች ገልጸዋል። ወታደሩ መጥፋቱን ተከትሎ ከፍተኛ አሰሳ እየተደረገ ሲሆን፣ በአካባቢው ህዝብ እርዳታ ከአካባቢው ማምለጡ ታውቋል። ከሁለት ሳምንት በፊት አንዲት ሴትን ጨምሮ ስምንት ወታደሮች ከዚሁ ከተማ መጥፋታቸው ይታወቃል።

በብር ሸለቆ አካባቢም እንዲሁ በርካታ ወታደሮች መሳሪያቸውን ሽጠው መጥፋታቸውን ከአካባቢው የደረሰን አስተማማኝ መረጃ ያመለክታል። ለደህንነት ሲባል ስለሰዎቹ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ፍላጎት የሌላቸው ምንጮች፣ ወታደሮቹ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የነጻ አውጪ አባላት ጋር ግንኙነት መፍጠራቸው ታውቋል።

ይህን ተከትሎ በአካባቢው ባሉ ወታደሮች መካከል አለመተማመኑ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ በወታደሮች መካከል ያለው የእርስ በርስ ግንኙነትም በእጅጉ መቀዛቀዙን ገልጸዋል። ወታደሮቹ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር መገናኘት እንደሌለባቸው ትእዛዝ እንደተሰጣቸውም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

Received on Fri Sep 30 2016 - 15:57:06 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved