Ethsat.com: በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የኦሮቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች መስቀልን እጅግ በተቀዛቀዘ ስሜት አከበሩ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 27 Sep 2016 21:19:24 +0200

በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የኦሮቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች መስቀልን እጅግ በተቀዛቀዘ ስሜት አከበሩ

September 27, 2016
Watch these News:

ESAT DC Morning News Tue 27 Sep 2016

http://video.ethsat.com/?p=28823

ESAT Daily News Amsterdam September 27, 2016

https://www.youtube.com/watch?list=PLKH8s2pMt15Ij8T8_O6ecDq5MpepFv-No&v=p2px7HcxcxU

መስከረም ፲፯ (አሥራ ሰባት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ዘንድ ታላላቅ ከሚባሉት ሃይማኖታዊ በአላት መካከል አንዱ የሆነው  የመስቀል በአል በመላ አገሪቱ እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት መከበሩን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በታሪካዊቷ የጎንደር ከተማ በአሉ ከዚህ በፊት ይደረግ እንደነበረው በአደባባይ ያልተከበረ ሲሆን፣ አንዳንድ የከተማዋን ታሪክ የሚያውቁ ሰዎች እንደሚናገሩት ጎንደር የመስቀልን በአል በአደባባይ ሳታከብር ስትቀር ከ100 አመት ወዲህ ይህ የመጀመሪያ ነው።

የከተማው ህዝብ በስልጣን ላይ ያለውን የህወሃት አገዛዝ በመቃወም ከአደባባይ ተቃውሞ በተጨማሪ ለ3 ተከታታይ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ አድርጓል።

በሰሜን ጎንደርና በደቡብ ጎንደር በሚገኙ ሌሎች  ከተሞችም ህዝቡ በአሉን ከዚህ በፊት በሚያከብርበት መንገድ አላከበረም። በእስቴ መካነእየሱስ ወረዳ ህዝቡ ወደ አደባባይ  ሳይወጣ የቀረ ሲሆን፣ ፖሊሶች አፍረው መመለሳቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

በቆላ ድባም እንዲሁ ምንም አይነት የመስቀል በአል ሳይከበር መቅረቱን ነዋሪዎች ገልፀዋል በባህርዳርና ዙሪያ ወረዳዎች የነበረው የመስቀል በአል በተመሳሳይ መልኩ በሃዘን የተከበረ ሲሆን፣ በባህርዳር የብጹዕ አቡነ አብርሃም የባህርዳር ፣ አዊ፣ የምእራብ ጎጃም እና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀጻጻስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በበአሉ ላይ ያስተላለፉት መልእክት የብዙ ኢትዮጵያውያንን አድናቆት አትርፏል።

“የህዝቡ ጥያቄ መልስ ማግኘት አለበት ያሉት ብጹዕ አቡነ አብርሃም፣ መንግስት ትናንት አጽም እያወጣ ልጆቻችሁን ገደለባችሁ እያለ ማላቀሱ የትናንት ትዝታ ነው ፣ አሁንም ደግሞ ይህ ታሪክ ተፈጽሞ ነገ ሌላ የታሪክ ጠባሳ እንዳይኖር ሊጠነቀቅ ይገባል” ሲሉ ምክር ለግሰዋል ።

ሁልጊዜም ችግር የመሪው እንጅ የህዝብ አይደለም የሚሉት አቡነ አብርሃም፣ የምለውን ካላደረክልኝ፣ ጩኸቴን ካልሰማሃኝ እያለ፣ የጩኸቱን ድምጽ ሰምቶ ካልመለሰ፣ ማስተባባያ ካልሰጠ ህዝብ ጩኸቱን አያቆምም ብለዋል። አቡነ አብርሃም ጋዜጠኞችንም ወቅሰዋል። እኛን ከህዝቡ ጋር የሚያጣላ እያወጣችሁ ህዝቡ ምን አባት አለን እንዲል ታደርጉታላችሁ በማለት ከፍተኛ ወቀሳ አቅርበዋል ።

ቤተክርስቲያን ጥላቻን አትሰብክም መገዛትን ታምናለች ያሉት አቡኑ፣ ቤተ/ክርስቲያን ሃይማኖቷን የሚቃወም ሲመጣ አልገዛም ትላለች ብለዋል። እኛ ክርስቲያኖች ሞትን ተማርን እንጅ መግደልን አልተማርንም፣ መሰደድን ተማርን እንጅ ማሳደድን አልተማርንም፣ እውነትን ግን ይናገራል ብለዋል።

የቤ/ክርስቲያን ድምጿ ሊሰማ ይገባል ያሉት አቡነ አብርሃም የታሰሩት እንዲፈቱ፣ ያዘኑት እንዲጽናኑ ጠይቀዋል። ሰዎችን በሌሉበት እየተወነጀሉ ነው ያሉት አቡነ አብርሃም ፣ የውስጥ ችግሮችን መፍታት አለብን ብለዋል።

ለወታደሩ ባስተላለፉት መልእክት ደግሞ ከመግደያ የጦር መሳሪያ ይልቅ የፍቅር የጦር መሳሪያን ተጠቀሙ ብለዋል።

በቡራዩ ከተማም እንዲሁ የመስቀል በአል እንደወትሮው ሳይከበር መቅረቱን ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልጸዋል።

በአገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ወጣቶች በኦሮምያና አማራ ክልሎች የሚደረጉ ህዝባዊ ተቃውሞችን መደገፋቸውን እንዲሁም በአጋዚ ወታደሮችና በፌደራል ፖሊሶች የተጨፈጨፉ ወገኖቻቸውን አስበው መዋላቸውን ለማሳየት የተለያዩ የበአል አከባበር ዘዴዎችን ተጠቅመዋል።

ወኪላችን ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በአዲስ አበባ የከተራ የመስቀል በዓል አከባበር  “የከተራ ቀን” የበዓሉን ድምቀት ከፍተኛ ድርሻ የሚወስድ ሲሆን ፣ በርካታ ቁጥር ያለው የከተማው ህዝብ ቤተ በራሱ አማራጭ በመኖርያ ቀየው ወጣቶችን መሪ በማድረግ ፈጠራ የታከለበት ከበዓሉ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ልዩ ልዩ ባህላዊ ቁሳቁሶችን በመጠቀም በየግማሽ ኪ.ሜትር ርቀት ላይ አነስተኛ ደመራዎችን፣ ሻማዎችን፣ ሰንደቅ አላማዎችን፣ባነሮችን፣ ህብረ ዝማሬ፣ ሙዚቃዎችን፣ምግብና መጠጥ ወ.ዘ.ተ በህብረት አዘጋጅቶ የአካባቢ አባቶችን ደመራ በማስለኮስ በዓሉን አክብሮአል ብሎአል።

ፖሊሶች ከዝግጅት ቦታዎች በቅርብ ርቀት ጨለማን ተገን አድርገው በመቆም ወጣቱን ለመደብደብ መሞከራቸውን፣ ታክሲዎች አመሻሽ ላይ ከጎዳና የጠፉበትና ህዝቡም ቤቱ ለመግባት ረጅም መንገዶችን በእግሩ የሄደበት አጋጣሚ በብዛት መታየቱን እንዲሁም ፣ ተንቀሳቃሹም ህዝብ በፍተሻ ብዛት የተሰላቸበት ድብልቅልቅ ያለ ስሜት የነበረባት አዲስ አበባ ሆና አልፋለች።

********************************************************************************

በጎንደር የመስቀል በዓል አለመከበሩ ተገለጸ

ኢሳት (መስከረም 17 ፥ 2009)

September 27, 2016

ከሃምሌ ወር ጀምሮ ህዝባዊ ተቃውሞ በመካሄድ ላይ በሚገኝበት የጎንደር ከተማ ማክሰኞ ሊከበር የነበረው የመስቀል በዓል አከባበር አለመከበሩን የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

በዕለቱ የዳመራ የችቦ ማብራት ስነስርዓት አለመከናወኑን የተናገሩት እማኞች በርካታ ነዋሪዎች በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ በመሰባሰብ ተቃውሞ አዘል የሆኑ መልዕክቶችን ሲያስተጋቡ እንደነበር ገልጸዋል።

የቪዲዮ መረጃን በማስደገፍ መረጃን ለኢሳት ያደረሱ አካላት የዘንድሮው የመስቀል በዓል አከባበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ውጥረትና አለመረጋጋት የታየበት እንደነበር አከለው አስረድተዋል።

የበዓሉ አከባበር በአዲስ አበባና ሌሎች የክልል ከተሞች ተመሳሳይ ድባብ ታይቶበት መዋሉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

Received on Tue Sep 27 2016 - 13:58:29 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved