Goolgule.com: በኢህአዴግ ጎጆ ያልበሰበሰው ማን ነው? የኢህአዴግ የ“ገደል ማሚቶዎች” ኅሊና የት ነው?

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 27 Sep 2016 15:28:08 +0200

በኢህአዴግ ጎጆ ያልበሰበሰው ማን ነው?

የኢህአዴግ የ“ገደል ማሚቶዎች” ኅሊና የት ነው?
eprdf-supporters

ተሰብሳቢዎቹ አገሪቱን “በስብሰናል፣ ሸተናል፣ ማስተዳደር አቅቶናል …” እያሉ ራሳቸውን የሚሰድቡት የኢህአዴግ ምክርቤት አላባት ናቸው። በእነርሱ አነጋገር አንድም “ልውጥ” ሰው መካከላቸው የለም። ሰብሳቢዎቹ “ቅምጥ” የሚባሉት ታማኝ የህወሃት ታዛዦች “ጓድ ሃይለማርያም ደሳለኝና ምክትላቸው ደመቀ መኮንን” ነበሩ። የኃይል አሰላለፉ በራሱ የቤቱንና የአስተዳደሩን መብከት የሚያሳብቀው ስብሰባ ላይ ተሰብሳቢዎች ፊት የቆሙት ራሳቸው ኢህአዴጎች ነበሩ።

በፊት አውራሪዎቻቸው ፊት ቆመው ሪፖርት የሚያቀርቡት ሰዎች ኢህአዴግ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በፊት አውራሪዎቻቸው የተሾሙ ነበሩ። የተሾሙት በድርጅቱ መዋቅር ስር ባሉ አደረጃጀቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ ዘልቀው በመግባት እንዲያጠኑ ነበር። ከሙስና ጀምሮ ኢህአዴግ “ገለማሁና፣ በሰበስኩ” የሚልበትን መስመር መርምረው እንዲያቀርቡ የተሰየሙት ሰዎች “ግኝታችን” ያሉትን ሲያቀርቡ በገሃድ በቴሌቪዥን ተላልፎ ነበር።

ራሱን በራሱ ሰዎች አስመርምሮ ኃጢያቱን ሲሰማ የነበረው “የአገር አመራር” በመዋቀሩ ተብትቦ የያዘው አገልግሎት ዘርፍ ሙሉ በሙሉ መንቀዙ፣ መበስበሱ፣ መገልማቱና በሙስና የነተበ መሆኑ ሲሰማ፣ ህዝቡም “ወይ እነዚህ ጉዶች” እያለና “ማን ነው ያልበሰበሰ?” እያለ ከታዘበ ዓመት አልሞላም።eprdf haile wife

በተለይ በፍትህ አካላቱና በዳኝነት ዙሪያ “በነጻነት መስራት አለመቻሉና ከላይ ስልክ እየተደወለ ይህን ፍረድ፣ ይህን ወስን፣ እንደዚህ ብለህ በይን…” እየተባሉ መስራት እንዳልቻሉ መናገራቸውን የሚያበስረው ሪፖርት ሲቀርብ አዛዦቹ “መሪዎች” የድንጋጤም ስሜት አይታይባቸውም ነበር። ይልቁኑም የራሳቸውን ኃጢያት በራሳቸው ሰዎች ሲያዳምጡ “የቀለጠው መንደር” የሚለውን ቲያትር የሚመለከቱ ጥርቃሞዎች እንጂ ኅሊና የሚባል ነገር የፈጠረባቸው አይመስሉም።

በማጠቃለያው ጓድ ሃይለማርያም “ካሁን በኋላ ጥናት እያልን ቻይና፣ ዱባይ፣ ቱርክ…. አንሮጥም። የተጠኑ ጥናቶች መደርደሪያ ላይ ሞልተዋል። አሁን የምንገባው ወደ ተግባር ነው። ታክስ ፎርስ (ግብረኃይል) ይዋቀርና ወደ ርምጃ እንገባለን” በማለት የ“ቀለጠውን መንደር” ተውኔት ደመደሙት። ከዚያም ውጤቱ ዝም ሆነ። ዛሬ ደግሞ ህዝብ በቁጣ ሲነድ “ጥልቅ ተሃድሶ” የሚል ነጠላ ዜማ ማዜም ተጀመረ።

ከገለማው ቤት ሲቀርቡ ከነበሩት አሳፋሪና ተስፋ አስቆራጭ የ“መበስበስ” ገድላት ውስጥ ስለ ዳኝነት የተባለውን መቆንጠር የተፈለገው ያለምክንያት አይደለም። ሰሞኑንን በተባራሪ መሰማት ከተጀመሩ በቋሚነት የማይቀጥሉ “ጊዜ ወለድ” ዜናዎችና አስተያየቶች መካከል ባለፈው ሳምንት እሁድ (መስከረም 8) በሸገር ካፌ የህግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሒጅራ “በሙያዬ የማውቀውን ልንገርሽ” ሲል ለአወያይዋ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ የተናገረው ጥልቅና ምን አልባትም ታሪካዊ ሊባል የሚችል አስተያየት ቀልብ የሚስብና አስረጂነቱ የጎላ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

eprdf haile romanዶ/ር መረራ ጉዲና “ኢህአዴግ አፍ እንጂ ጆሮ የለውም” የሚለውን አግባብ ያለው ንግግር እያሰብን አቶ አብዱን ስንሰማ ያነሳቸው ጉዳዮች አእምሮ ያላቸው የኢህአዴግ አመራሮች ቢኖሩ በበነጋው “በቃኝ” የሚያስብላቸው ነበር። ዳሩ ምን ያደርጋል ዛሬም አቶ አብዱ “እነዚህ ሰዎች” የሚላቸው ሰዎች ለማውራት እንጂ ለመስማት የሚከጅል ሞራልም የላቸውም። ወይም ደግሞ አልፈጠረባቸውም። በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ከደሃ ህዝብ ኮሮጆ አውጥቶ የደፋና ያባከነ ሰው ዛሬም ይናገራል። በሙስና የገለሙ፣ በደም የተጨማለቁ፣ የአገሪቱን ቆዳ ገፈው የለበሱ ሌቦች ዛሬም “የቀድሞ ባለሥልጣናት፤ ጉምቱ አመራሮች” እየተባሉ ስለ “ጥልቅ ተሃድሶ” አይናቸውን በጨው አጥበው ህዝብና ንጹሃን ዜጎች ፊት ቀርበው የተሃድሶ ሃይል ለመሆን ይመኛሉ። ከምኞትም አልፈው በበሰበሰው ገንዳ ውስጥ ሆነው የመበስበስን አደጋ የሚጋፈጡ አርበኛ ይሆኑብናል። ደስ ሲላቸው በስብሰናል፤ አቅቶናል ባሉበት አፋቸው “እኛ ካልገዛን” የዘር ፍጅት፣ ሩዋንዳ፣ ሶሪያ፣ … እያሉ ሕዝብ ለማስፈራራት ይሞክራሉ፡፡

አቶ አብዱ “ይኼ ነው የአገር ጀማ፣ ሸንጎ፣ መጀሊስ” ሲል አሳዛኝ መሆኑን በመጥቀስ እርቃኑንን ያስቀረው የኢህአዴግ “ፓርላማ” የመሰለው በውጭ ጨርሰው ሽማግሌ ለይምሰል እንደሚልኩ አዲስ ተጋቢዎች ነው። ቤተሰብ “እኛም ፈቅደናል …” ከማለት ሌላ በምንም መልኩ “አልቀበልም” ብሎ እንደማይመልስ ሁሉ፣ የኢህአዴግም “ፓርላማ” የተባለውን ሁሉ “የወይን አበባዬ የወይን፣ እኛም ወደናል ይሁን…” በማለት አጨብጭቦ እንደሚቀበል አቶ አብዱ ያስረዳል። መደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ የሚደግፍበት ቃልና ሃረግ ተሰፍሮ የሚሰጠው ይኸው “ፓርላማ የኅሊና ነጻነት” የሌለው ነው። ዝም ብሎ የአባልነት ካርድ ይዞ የሚበር ሳይሆን ከዛም በላይ “የልቤ” ወይም “እንደ ልቤ የሚሆንልኝ” የሚለውን መስፈርት የተጫነበት ካርድ እንደሆነም አቶ አብዱ አክርሮ ተናግሯል።

“አገር ስብዕና ላይ የከሰከሰችውን ከነቡሃቃው ደፍታዋለች” ሲል የተናገረው አቶ አብዱ፣ ኢህአዴግ ፖሊሲውን አምልኮ ማድረጉን፣ ዜጎችም ሆኑ አባላቱ ከዚህ አምልኮ ሳይወጡ ከፖሊሲው ይልቅ አፈጻጸሙን ብቻ እየተቹ እንዲኖሩ፣ ሕዝብ  አማራጭ አልባ ሆኖ እንዲሸበብ መደረጉን ያወሳል። አያይዞም በነጻ ማሰብ፣ ማወዳደር፣ መፈተሽ፣ ማንጠር፣ መለየት፣ ተከልክሎ እንዲሁ በማወደስና በማውገዝ መካከል እንድንወዛወዝ ተፈረደብን፣ ሚዲያውም ስራው ይኸው ሆነ። በዚህ እኛም መንግስትም ልናፍር ይገባል በማለት የመበስበሱና የመዝቀጡ ችግር ከኢህአዴግ አልፎ እንዴት ህዝብና አገርን እንዳወከ ያስረዳል። ይህ ብቻ አይደለም፤ አቶ አብዱ በስፋት ማሳያ ተንደርድሮ “ሕዝብ ሳይሸማቀቅ ገዢውን ፓርቲ ዘጭ አድርጎ የሚያወርድበት አስተዳደር አላለማንምና፣ የእነሱ አደጋ ውስጥ መውደቅ የአገርም ሆነ” ይለናል።former-eprdf

“ይህን አመዛዝኖ ህሊናሽ ቢፈርደኝ…” የሚለውን የፍቅር ዘፈን አስታውሶ ስለ ህሊና ያወሳው አቶ አብዱ፣ ተጠሪነታቸው ለሕገ መንግስት፣ ለሕዝብና፣ ለህሊና የሆነ ሁሉ በተለይም ለህሊናቸው ይታዘዛሉ ሲባል “በህገ ልቡና የሚተዳደሩ” እንደማለት መሆኑንን ያመላክታል። ይህ ሲባል ተገዢነታቸው ለህሊናቸው ሲሆን፣ በህሊናቸው እንዲተዳደሩ ተፈቅዶላቸዋል ማለት መሆኑንን ያሰምርበታል። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚነሳው መናገር፣ መደገፍ፣ መቃወም፣ ከበላዮቻቸው የሚሰፈርላቸው ፮ ሚሊዮን የሚሆኑ የኢህአዴግ አባላት ከገደል ማሚቶነት ያለፉ አይደሉም። ህግ አውጪው፣ ተርጓሚው፣ አስፈጻሚው፣ ከስር ያሉት ሁሉም በሌላ አነጋገር የገደል ማሚቶ ናቸው።

“ሰው ሕገ መንግስትን የሚተረጉመው ከህሊናው ጋር በጨዋነት ሲፈርድ ነው” የሚለን አቶ አብዱ በኢህአዴግ ውስጥ የፓርቲ አባል መሆን ብቻ ሳይሆን “የልቤን ያውቃል” በሚል ሹመት እንደሚሰጥ ጠቁሞ በተካነበት የዳኝነት ሙያ ዙሪያ ማብራሪያውን ያብራራ ጀመር። አወያይዋ መዐዛ በአዎንታ እያጀበችው ከወትሮው በተለየ ኢህአዴግን ጥንብርኩሱን ያወጣው አቶ አብዱ “እኔ በማውቀው የፍትህ፣ የዳኝነት ስርዓት ውስጥ ያሉትን ብናያቸው” አለ አቶ አብዱ ላፍታ እንኳን የቃላት ፍሰቱ በማይቋረጥበት ውብ ገለጻ “ከዳኝነት ስርዓት ውጪ የሆኑትን የህግ ባለሙያዎችና በዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ አሁን ያሉትን ባለሙያዎች ሲታዩ ባርሴሎናን ከአንድ በቡቱቶ ኳስ ከሚጫወቱ የመንደር ቡድን ጋር ማወዳደር ነው”

“ለምንድን ነው?” ሲል እንደ ሁሉም ዜጎች ይጠይቃል አቶ አብዱ “አገር ያንን ሁሉ ስብዕና ላይ የከሰከሰችውን ሃብት እንዲህ አድርጎ ማባከንና ከነ ቡሃቃው መድፋት ለምንድን ነው?” (ለምንስ ይሆን እነዚህ የሕግ ባለሙያዎች በመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ገብተው የማይሰሩበት ሁኔታ ያልተፈጠረው? ለምንስ ተገለሉ?) ሲል መልሱን እሱ ሊመልሰው የማይችለውን ጥያቄ ጠይቆ፣ “እየተሳሳትን እንማራለን” ይሉናል ሲል ቁጣውን ሊደብቅ በማይችልበት መልኩ ሲሞግተው የቆየውን ጉዳይ ጊዜን አንተርሶና ተነፈሰው። “እየተሳሳትን ፣ እያጠፋን እንማራለን ብሎ ነገር የለም” አቶ አብዱ እንደ ትንታግ በሚወርደው ንግግሩ “ሊስትሮዎችን በካልሲያችን የምናስተምረው ይበቃናል። ሃኪም ሰው እየገደለ ይማር የሚል ሰብአዊነት የለም” በማለት በዳኝነት ዘርፍ ያለውን ብቃትና የህሊና ታማኝነት ቡቱቶ ኳስ ውስጥ ቀርቅሮ አጀንዳውን ወደ ሌላ ጉዳይ ያዞራል።tplf eprdf

ከዚሁ ከብቃት ጋር የተያያዘውን ማብራሪያውን ከሃላፊነታቸው የተነሱትን የጠቅላይ ኦዲተር ዳይሬክተርን ጉዳይ በማስታወስ ነበር። ላፍታም የማይረሳውና ሲያስታውስ ብዥታ የማይታይበት፣ ሲያብራራ ቢውል መነሻውን የማይስተው አቶ አብዱ “ሞዴል 6 ለመበደር  የደሞዝ 1/3ኛ፣ መጀመሪያ የወሰድነውን ብድር መመለስ፣ እና ብድሩ የሚቻለው ወር በገባ በ10ኛው ቀን ነበር” /እኛ የጨመርነውበኢኮኖሚ እድገቱ ሳቢያ ሰዎች ሳይቸገሩ ወር ለሚደርሱ አሁንቀር/ ኢህአዴግ ከባንክ የተበደረው ገንዝብ በዛና ጠቅላይ ኦዲተር “ህጉን ተላልፈህ የተበደርከው በዛ” አለ። ወዲያውኑ ሁኔታው ስላላማረ ህጉ ተሻሻለ። መንግስት የሚበደረው በገንዘብ ሚኒስቴርና በብሔራዊ ባንክ መካከል በሚደረግ ስምምነት መሆኑ ታወጀ። እንደ አቶ አብዱ አባባል “ያንን የመሰለ ማነቆ፣ የ’መንግስትን’ የስልጣን መባለጊያ የሚገድብ ህግ ተሻረ። ሰውየውም ከሃላፊነታቸው ተነሱ”፡፡

አቶ አብዱ በተጠቀሰው ቀን በርካታ አሳሳቢና ወቅታዊ ጉዳዮችን የዳሰሰ ማብራሪያ የሰጠ ሲሆን ቆንጥረን ለአንባቢ እንዲመች ካቀረብነው ሌላ ያለውን አብባቢው እንዲያደምጥ እንጋብዛለን

በቅርቡ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት የቀድሞው ሚኒስትርና የኦሮሚያ አስተዳዳሪ ጁነዲን ሳዶ ይቅርታ ከሚጠይቁበት ነገሮች መካከል ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡ ከጠቃቀሱት ሁለት ይቅርታዎች መካከል በዋንኛነት ያነሱት eprdf bahir darኢህአዴግን ሲገለግሉ የኖሩበትን ዓመታት እጅግ የሚጸጽታቸው መሆኑን ነው – ይህንን ሥርዓት ለዚህን ያህል ዓመታት ማገልገሌ ይጸጽተኛል ነበር ያሉት፡፡ ከገደል ማሚቶነት በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የሚገለሉ ሰዎች በአእምሯቸው ማሰብ ይጀምራሉ፡፤ ፍቺውን የሚፈጽሙበት ምክንያት የግል ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ፍቺውን ሲፈጽሙ ሰው መሆን ይጀምራሉ፤ እንደ ሰው በኅሊናቸው ፍርድና አስተሳሰብ መመራት ይጀምራሉ፡፡

በዚሁ የሸገር ሬዲዮ የዛሬ ዓመት አካባቢ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ቃለምልልስ ባደረጉበት ጊዜ ስለዚሁ የኅሊና ጉዳይ አንስተው ነበር፡፡ በኅሊና አስተሳሰብ መመራት መጥፋቱ ያሳሰባቸው አንጋፋው ምሁር ከየእምነት ቤቱ በቀዳሚነት መገኘት የሚገባው የኅሊና ጉዳይ መጥፋት አገሪቱን ይህ ነው ለማይባል የሞራል ኪሣራና ጥፋት እንደዳረጋት መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የአቶ አብዱም ገለጻ ይህንኑ የሚያሳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ በሁሉም መስክ ከስሮ ሲያበቃ “ጥልቅ መታደስ” በራሱ ለማካሄድ ማሰቡ ራሱ ከመፍትሔው ምን ያህል የራቀ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ የሚቃወመውን ብቻ ሳይሆን የሚደግፈውን ጉዳይ እንኳን ምን ማለት እንዳለበት ተለክቶ የሚሰጠው ስድስት ሚሊዮን የሚሆነው የኢህአዴግ አባል ኅሊና ቢስ ነው፡፡ ራሱ ባጸደቀው ህገመንግሥት እንኳን ላይ የተፈቀደው በኅሊና ማሰብ ያልተፈቀደለት፤ የተነገረውን ብቻ የሚያስተጋባ የገደል ማሚቶ ነው፡፡ ይህንን ሁሉ የገደል ማሚቶ ይዞ በቀጣይ የሚሆነው ነገር “በጥልቀት መታደስ” ሳይሆን “በጥልቀት መበስበስ” ብቻ ነው፡፡

Received on Tue Sep 27 2016 - 08:07:13 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved