Ethsat.com: በኦሮሚያና አማራ ክልልሎች ከተፈጠረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጀርባ የውጭ ሃይል አለበት ሲሉ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam59_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 31 Aug 2016 00:20:37 +0200

በኦሮሚያና አማራ ክልልሎች ከተፈጠረው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጀርባ የውጭ ሃይል አለበት ሲሉ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ

ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)

August 30, 2016

Watch this news:

http://video.ethsat.com/?p=27741

http://video.ethsat.com/?p=27744

የኢህአዴግ ም/ቤት ያደረገውን የ15 አመት ግምገማ ተከትሎ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከተነሱት ግጭቶች ጀርባ የውጭ ሃይል አለበት” በማለት ውንጀላ አሰሙ።

በወቅታዊ  የአገሪቱ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በአገሪቱ የሚስተዋሉትን ግጭቶች በማባባስ ጀርባ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷን እንዳትጠቀም የሚፈልጉ አገራት አሉ በማለት ተናግረዋል። አያይዘውም፣ “ሁከቶችን በገንዘብ እየደገፉ የሚገኙት እነዚህ የውጭ አገራት ለጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ገንዘብ በገፍ እየረጩ መሆናቸውን መንስግስታቸው ተጨባጭ መረጃ እንዳለው አስታውቀዋል።

በአቶ ሃይለማሪያም ደሳኝ ንግግር ላይ ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ የዲፕሎማቲክ ሙያተኞች እንደገለጹት ከሆነ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በቀጥታ የሚያያዘው ከግብፅና ሱዳን የመሳሰሉ አገሮች ጋር ነው። ለዚህም እማኝ አድርገው ያቀረቡት ሰሞኑን በአሜሪካን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማት በኢንባሲው ድጋፍ በሚደረግላቸው ሚዲያዎች ላይ በመቅረብ ግብፅ እጇ እንዳለበት በግላጭ ተናግረዋል።

አቶ ሃይለማሪያም ተጨባጭ ማስረጃ አለን ካሉ ለምን ተጠያቂው ነኝ ከሚሉት የኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ አያደርጉም የሚሉት አስተየየት ሰጪዎች ይልቁንስ ችግሩን የራስ አድርጎ መፍትሄ ማፈላለግ እንደሚበጅ ምክራቸውን ለግሰዋል።

አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ በተያዘው ፓርላማ ቀርበው በአገሪቱ የታዩት ችግሮች በተለይም በኦሮሚያ ክልል የተወሰደው እርምጃ መንግስት በማንም ሳያሳብብ ሃላፊነቱን በመውሰድ ህዝቡን ይቅርታ ይጠይቃል ማለታቸው የሚታወስ ነው።

******************************************************************************

የቀድሞ ከፍተኛ የአጋዚ ክ/ጦር አዛዥ ጦሩ አፈሙዙን ወደ አዛዦቹ እንዲያዞር ጠየቁ

ኢሳት (ነሃሴ 24 ፥ 2008)

August 30, 2016

በአማራና በኦሮሚያ ክልል በተቀጣጠለው ህዝባዊ እምቢተኝነት በመንግስት የግድያ ትዕዛዝ የተሰጠው የአጋዚ ጦር ወደ ህዝቡ እንዳይተኩስ እና መሳሪያውን ወደ አዛዦቹ እንዲያዞር አንድ የቀድሞ ከፍተኛ የአጋዚ ክ/ጦር አዛዥ ጠየቁ።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተነሳውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ተከትሎ መንግስት ያሰማራቸው የጸጥታ ሃይሎች ህዝቡን በመግደል ላይ መሆናቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳዘናቸው ለኢሳት የገለጹት የቀድሞ አጋዚ ክ/ጦር መስራችና አመራር ኮሎኔል አለበል አማረ፣ የክ/ጦሩ አባላት ከህዝቡ ጋር በመወገን ታሪክ የመስሪያው ጊዜ አሁን መሆኑን ተናግረዋል።

የአጋዚ ክ/ጦር መስራች የሆኑት ኮሎኔል አለበል አማራ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ወደ ኋላ በመሄድ በምርጫ 97 የተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን አስታውሰዋል። በምርጫ 97 በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ህዝቡን ለመጨፍጨፍ በአሮጌው አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ ዋና የማዘዣ ጣቢያ ተቋቁሞ እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን የማዘዣ ጣቢያ የሚመሩት ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች እና 12 የህወሃት አባል የሆኑ ጄኔራሎች እንደነበሩ አስታውቀዋል።

ማዘዣ ጣቢያውን የመሩት የፖለቲካ አማራሮች አቶ መለስ ዜናዊ፣ አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ እና አቶ ሙሉጌታ አለምሰገድ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ከፖለቲካ መሪዎች ትዕዛዝ እየተቀበሉ ግድያውን ሲያስፈጽሙ የነበሩት 12 ጄኔራሎች በስም ዝርዝር የገለጹት ኮሎኔል አለበል አማረ፣ ሁሉም ጄኔራሎች የትግራይ ተወላጆች መሆናቸው በሰራዊቱ ውስጥ ጥያቄ አስነስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

የቀድሞ የአጋዚ ክ/ጦር ከፍተኛ መሪ የነበሩት ኮሎኔል አለበል አማረ፣ አሁን በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ እምቢተኝነት ለመቀልበስ ተመሳሳይ የሆኑ አደረጃጀቶችና ማዘዣ ጣቢያዎች እንዲሚቋቋሙ የገለጹ ሲሆን፣ ምስኪኑ ተራ ወታደር ወደህዝቡ መተኮሱን አቁሞ በቅምጥል ህይወታቸውን እየመሩ ወዳሉት አዛዦች አፈሙዙን ማዞር ይኖርበታል በማለት ተጽዕኖአቸውን አቅርበዋል።

ተራው የአጋዚ ወታደር እንደሌላው ኢትዮጵያው በድህነት ውስጥ የሚኖር፣ ከህዝቡ አብራክ የወጣ እና በህዝቡ ውስጥ የሚኖር በመሆኑ እየተካሄደ ያለውን የህዝብ ቁጣ ይገነዘባል ያሉት ኮሎኔል አለበል፣ ሰራዊቱ በህዝቡ ድጋፍ ከተደረገለት አፈሙዝ  በዘረኝነትና የቅንጦት ህይወት ወደ ሰከሩት የጦር አዛዦች እንደሚያዞር ጥርጥር እንደሌላቸው አስታውቀዋል።

 
Received on Tue Aug 30 2016 - 16:59:41 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved