Ethsat.com: በክልሎች ሲካሄዱ የቆዩ ተቃውሞዎችን ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ሲያገናኝ የቆየው መንግስት ችግሩ ከአገልግሎት አሰጣት ችግር የመነጨ ነው አለ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam.1_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Tue, 23 Aug 2016 18:45:08 +0200

በክልሎች ሲካሄዱ የቆዩ ተቃውሞዎችን ከሽብርተኛ ቡድኖች ጋር ሲያገናኝ የቆየው መንግስት ችግሩ ከአገልግሎት አሰጣት ችግር የመነጨ ነው አለ

August 23, 2016

ኢሳት (ነሃሴ 16 ፥2008)

በተለያዩ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በጸረ-ሰላም ሽብርተኛ ቡድኖች የተዘጋጀ ነው ሲል የቆየው የኢትዮጵያ መንግስት የአገልግሎት አሰጣት ችግሮች ለተቃውሞ ምክንያት ሆኗል በማለት ሰኞ አስታወቀ።

በሃገሪቱ ስላለው የጸጥታ ጉዳይ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮችና ተወካዮች ማብራሪያን የሰጠው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች እየተነሱ መሆኑን ለአምባሳደሮቹ መግለጹን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በሃገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት ተቃውሞ ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ ሊዛመት ይችላል በማለት ዜጎች በእንቅስቃሴያቸው ላይ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አርብ ማሳሰቢያን ማውጣቱ ይታወሳል።

የአሜሪካ መንግስት በተጨማሪ መቀመጫቸውን በሃገሪቱ ያደረጉ የተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎችና አለም አቀፍ ተቋማት ተመሳስይ ማሳሰቢያን ሲያሰራጩ መሰንበታቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ የመለክታል።

እነዚሁ አካላት ሲያሰራጩ የቆዩትን ማሳሰቢያ ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአምባሳደሮቹ ጋር ሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር ሲያካሄድ መዋሉ ታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ምክንያታዊ የሆኑና ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች በህዝቡ ዘንድ መነሳቱን ለልዑካኖቹ አስረድተዋል። የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ በሽብረተኛ ቡድኖች የተዘጋጀ ነው በማለት ለአለም አቀፍ አካላት ምላሽን ሲሰጡ ቢቆዩም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አግባብነት ያላቸው ናቸው ያላቸውን ችግሮች ለመፍታት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይቶችን እንደሚያካሄድ ገልጿል።

የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት መንግስት የሚወስደውን የሃይል እርምጃ በማቆም ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ሰላማዊ መፍትሄን እንደሚያፈላልግ ሲያሳቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

Received on Tue Aug 23 2016 - 11:24:13 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved