Ethsat.com: በምስራቅ ሸዋ ሆራ ፈጀሶ የተባለ ወጣት አንድ የአጋዚ ወታደር ገድሎ ሌላ አንድ የፌደራል ፖሊስ ካቆሰለ በሁዋላ ተገደለ።

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 17 Aug 2016 21:43:46 +0200

በምስራቅ ሸዋ ሆራ ፈጀሶ የተባለ ወጣት አንድ የአጋዚ ወታደር ገድሎ ሌላ አንድ የፌደራል ፖሊስ ካቆሰለ በሁዋላ ተገደለ።

August 17, 2016

Watch this news: ESAT Daily News Amsterdam August 17, 2016

http://video.ethsat.com/?p=27231

ነሃሴ  ፲፩ ( አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከሌሊቱ 10 ሰአት ላይ ወታደሮቹ  “የጦር መሳሪያ አለህና አውጣ” ብለው  የቤቱን በር በሃይል ሰብረው ሲገቡ፣ ወጣት ሆራ እጄንማ አልሰጥም ብሎ አንዱን ግንባሩ ላይ በሽጉጥ መትቶ ሲገድለው፣ ሌላውን ደግሞ ሆዱ አካባቢ መትቶ ጥሎታል። የአጋዚው ወታደር ወዲያኑ ህይወቱ ሲያልፍ፣ የፖሊስ አባሉ ደግሞ ሆስፒታል ገብቷል። በዚህ የተበሳጩት ወታደሮች ወጣቱን ከገደሉት በሁዋላ በአስከሬኑ ላይ ደጋግመው በመተኮስ ንዴታቸውን ለመወጣት ሞክረዋል። ባለቤቱና የአንድ አመት ልጁም ወደ እስር ቤት ተወስደዋል።

የከተማው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ የሆነው ከድር ገመዳ፣ ወጣት ሆራ የጦር መሳሪያ ያለው እና መንግስትን የሚቃወም መሆኑን በመጠቆም ሊያስይዘው ቢሞክርም ወጣቱ ግን እጄን ለእናንተ አልሰጥም በሚል ተኩስ በመክፈት እርምጃ ወስዷል።

በወጣቱ ላይ የተተኮሰው የጥይት ብዛት አስገራሚ ነው የሚሉት የአይን እማኞች ፣ ወጣቱ ከተገደለ በሁዋላ አስከሬኑ መጎተቱን ባለቤቱም መደብደቡዋን ተናግረዋል ።

“የከተማው ነዋሪዎች ተቃውመንም ዝም ብለንም መገደላችን አልቀረም፣ ወያኔ ብዙ አመት ከፋፍሎ ገዝቶናል እባካችሁ በአንድነት እንነሳ የሚል ጥሪ አቅርበዋል።”

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ በኦሮሚያ ክልል በመንግስት የሚፈጸመው ወታደራዊ የሽብር ተግባር ተባባሶ መቀጠሉን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች በጣሰ መልኩ በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ የጅምላ ግድያ ተባብሶ መቀጠሉንና አፋጣኝ እልባት ሊበጅለት እንደሚገባ ሊጉ በሪፖርቱ ጠቁሟል።

የአጋዚ ወታደሮች ኦገስት 6 ቀን 2016 የሕክምና  ባለሙያ የሆኑትን ዶክተር ገበየሁ ጃለታን በግፍ በጥይት መምታታቸውን የገለጸው ሊጉ፣  ዶ/ሩ በነቀምት ከተማ የግል ክሊኒክ ባለቤት ሆነው ሲሰሩ  በአጋዚ ታጣቂዎች በጥይት ተመተው የሚመጡ ቁስለኞችን በማከም አስተዋጾ ሲያደርጉ እንደነበሩ ገልጿል። ዶክተር ገበየሁ ጃለታ በወቅቱ በጥይት ተመትተው ነቀምት ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው የቆዩ ቢሆን ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

በቅርቡ ከኦገስት 6 ቀን 2016 ጀምሮ በተካሄደው የመላው ኦሮሚያ ሕዝባዊ አመጽ ላይ ብቻ ቁጥራቸው ከ70 በላይ የሚሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ተገለዋል። በሽዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች በጅምላ ታስረው ሰቆቃ እየተፈጸመባቸው ይገኛል። በአጠቃላይ የኦሮሚያ ሕዝባዊ ማእበል ከተጀመረ ከኖቨምበር ወር 2015  ጀምሮ በመላው ኦሮሚያ ክልል የተገደሉ ሰላማዊ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ቁጥር ከ700 በላይ መድረሱን  የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ በሪፖርቱ አመላክቷል።

በምስራቅ ሃረርጌ ዞን በአወዳይ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት፣ በምእራብ አርሲ ዞን አዳባና ዶዶላ፣ በባሌ፣ በአዲስ አበባ፣ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማና ዝዋይ ከተሞች ሰላማዊ ሰልፉን ተከትሎ  ሰላማዊ ዜጎች ተገለዋል። ወደ እስር ቤትም በገፍ ተወስደው ታሰረዋል። ኦገስት 6 ቀን 2016 የተገደሉትን ቁጥራቸው 65 የሚሆኑትን ስምና አድራሻቸውንና ጨምሮ በምስል የተደገፈ መረጃ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ ይዞ ወጥቷል።

በኦሮሚያ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚያጣራ ገለልተኛ አካል እንዲሰየም ሲል የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሊግ ጥያቄ አቅርቧል።

*****************************************************************************************

የብአዴን የክፍለ ከተማ አመራሮች ተቃውሞአቸውን አሰሙ

August 17, 2016

ነሃሴ  ፲፩ ( አሥራ አንድ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነሃሴ 11 ቀን 2008 ዓም በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስም በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የክፍለ ከተማ አመራሮች ስብሰባ የተጠሩ ቢሆንም፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት የህውሃት አመራሮች ሆነው መገኘታቸው ውዝግብ አስነስቷል።

ሰብሳቢው “ በወልቃይት ላይ የሚነሳው የአማራነት ጥያቄ ወቅቱን ያልጠበቀ መሆኑንና ጉዳዩን ሊመለከቱት የሚገባቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የክልል አንድ አመራሮች በመሆናቸው ህብረተሰቡ ጉዳዩን ረስቶ የሚረጋጋበትን መንገድ መፈለግ ከሁሉም አመራር ይጠበቃል “ የሚል መልእክት እያስተላለፉ ባለበት ወቅት፣ በባለስልጣኑ ንግግር የተበሳጩት ተሰብሳቢዎች  በጩኸትና ፉጨት ንግግሩ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

የክልሉ ህዝብም ሆነ አመራሩ የህውሃት ፕሮፖጋንዳ እንደበቃው የታየበት ስብሰባ እንደነበር የገለጹት የክፍለ ከተማ አመራሮች፣  ‹‹ ስብሰባውን ለምን በአቶ ገዱ ስም ተጠራ ?በእሳቸው ስም ከተጠራስ ርዕሰ መስተዳድሩ የት ናቸው? ›› በማለት ከአዲስ አበባ መጥተው ስብሰባውን የመሩትን የህውሃት ባለስልጣን በጥያቄ አፋጠዋል።

አቶ ገዱ ስብሰባውን እንዲጠራ ማድረጋቸውን የገለጹት ባለስልጣኑ ‹‹እኛም እንደ እናንተ በወልቃይት ጥያቄ ዙሪያ ውስጣችን አሯል!›› በማለት የክፍለ ከተማ አመራሮችን ለማረጋጋት ቢሞክሩም ፣ አመራሮቹ ግን ተቃውሞአቸውን ደጋግመው በጩኸትና በፉጨት በመግለጽ ሳይቀበሉዋቸው ቀርቷል።

ሰሞኑን የባህርዳር ከተማ የልዩ ልዩ መስሪያ ቤት አመራሮችን፣ የየመስሪያ ቤቱ የስራ ሂደት ኃላፊዎችንና በዙሪያ ወረዳ የሚገኙ የሁሉም ጽህፈት ቤት አመራሮችንና አስተዳዳሪዎችን በመሰብሰብ በወልቃይት ዙሪያ የተነሳውን ህዘባዊ እንቅስቃሴ ለማክሰም ሙከራ ቢደረግም፣ ታች ያሉ  አመራሮች ግን  ‹‹ወንድሞቻችንን ተገድለዋል፤የብአዴን አመራርም በዝምታ እያየ ነው፤አሁንም የሕውሃት አገዛዝ ይብቃ ያለን ህዝብ እንዴት እናስቆመዋለን? ባዶ እጁን የወጣውን ህብረተሰብ የገደሉ የአጋዚ ወታደሮች ለምን በንጹሃን ላይ እንደተኮሱ አይጠየቁም?…››የሚሉ ጥያቄዎችን በማቅረብ በታላቅ ድፍረት ጥያቄዎችን በማቅረብ፣ የላይ አመራሩ የሚሰጠውን መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም።

በአማራ ክልል የሚገኙ አብዛኛው የብአዴን አመራሮችና አባላት ሰሞኑ በተለያዩ ከተሞች በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ እንደሚደግፉት በተዘዋዋሪ ሲናገሩ መሰማታቸው ለህውሃት ስርዓት አልገዛም ባይነቱ በብአዴን ዘንድም እየጎላ መምጣቱን ተሰብሳቢዎች ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት በባህርዳር ዩኒቨርስቲ በክረምቱ መርሃ ግብር የሚማሩ የትግራይ ተወላጆች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ እያደረገ ነው። የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ተማሪዎቹ በትግራይ ዩኒቨርስቲዎች ገብተው እንዲማሩ ለማድረግ ማቀዱን ምንጮች ገልጸዋል። ተማሪዎቹ የአየር ትኬት ተገዝቶላቸው ከባህርዳር ወደ አዲስ አበባ ከዛም ወደ መቀሌ እንዲሄዱ እየተደረገ ነው። በጎንደር ዩኒቨርስቲ የሚገኙ ተማሪዎችም በተመሳሳይ መልኩ እንዲወጡ ተደርጓል።

ህወሃት ሆን ብሎ ህዝባዊ ተቃውሞውን የብሄር ግጭት ያለ ለማስመሰል የሚሄድበት እርቀት ትችት እያስከተለበት ነው።

 
Received on Wed Aug 17 2016 - 14:22:50 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved