Ethsat.com: በጎንደር ከተማ ከቤት ላለመውጣት የተጀመረው አድማ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ

From: Berhane Habtemariam <Berhane.Habtemariam_at_gmx.de_at_dehai.org>
Date: Wed, 17 Aug 2016 00:34:38 +0200

በጎንደር ከተማ ከቤት ላለመውጣት የተጀመረው አድማ ለሶስተኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ

August 16, 2016

ኢሳት (ነሃሴ 10 ፥ 2008)

Watch this news:

http://video.ethsat.com/?p=27184

http://video.ethsat.com/?p=27172

በጎንደር ከተማ ከቤት ላለመውጣት የተጀመረው አድማ ለሶስተኛ ቀን ማክሰኞ መቀጠሉንና ሁሉም የመንግስትና የግል ድርጅቶች ተዘግተው እንደሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

ለተለያዩ አስቸኳይ ጉዳዮች ከቤት የሚወጡ ነዋሪዎች ጥቁር ልብስን በመልበስ ብቻ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያደርጉ እነዚሁ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።

በቅርቡ በጎንደርና እና በባህርዳር ከተሞች የተፈጸመ ግድያ በመቃወም ከቤት ላለመውጣት አድማ ላይ የሚገኙት የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እርምጃቸው ያላቸውን ከፍተኛ ተቃውሞ የሚያሳይ እንደሆነ አስረድተዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ባለስልጣናት ነዋሪው የተለመደ የዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴውን እንዲጀምር የተለያዩ ቅስቀሳዎችን ቢያደርጉም ነዋሪው በእምቢተኝነት መቀጠሉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በከተማዋ የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ከቆሙ ተሽከርካሪዎችና ባጃጆች ላይ ታርጋን ለመፍታት ሙከራ ቢያደርጉም የከተማዋ ነዋሪዎች የፈለጋችሁትን አድርጉ የሚል ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን እማኞች ለኢሳት አስታውቀዋል።

ለሶስተኛ ቀን የተጠራው ከቤት ያለመውጣት አድማ ቢጠናቀቅም፣ የተጀመረው ተቃውሞ በተለያዩ ስልቶች ቀጣይ እንደሚሆን ከኢሳት ጋር ቃለምልልስን ያደረጉ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ማክሰኞ ለአስቸኳይ ጉዳዮች ከቤት የወጡ ነዋሪዎች በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለማሰብ ጥቁር ልብስ መልበሳቸውን ከነዋሪዎቹ ለመረዳት ተችሏል።

በቅርቡ በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች ተካሄዶ በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ50 የሚበልጡ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን በተመሳሳይ ወቅት በኦሮሚያ ክልል ተካሄዶ በነበረ ተቃውሞ ከ50 የሚበልጡ ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ግድያው በአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ቢጠይቁም የኢትዮጵያ መንግስት ለምርመራው ትብብር እንደሚያደርግ አቋሙን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በኦሮሚያ ክልል ለወራት በቆየው ህዝባዊ ተቃውሞ ከ400 የሚበልጡ ሰዎች በተመሳሳይ የጸጥታ ሃይሎች ድርጊት ግድያ እንደተፈጸመባቸው የሂውማን ራይስት ዎች መረጃ የመለክታል።

*****************************************************************************************

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች የስራ ማቆም አድማ መጀመራቸውን አስታወቁ

August 16, 2016

ኢሳት (ነሃሴ 10 ፥ 2008)

በሳምንቱ መገባደጃ ቅዳሜ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍን ያካሄዱ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ መጀመራቸውን ነዋሪዎች ለኢሳት አስታወቁ።

የከተማዋ ነዋሪዎች ማከሰኞ ጠዋት ከዞንና ከከተማው አስተዳደር ሃላፊዎች ጋር ምክክርን በማካሄድ ለእስር የተዳረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።

ነዋሪዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ የስራ ማቆም አድማ እንደሚጀምሩ ለሃላፊዎቹ በውይይቱ ወቅት መግለጻቸውንና ከስብሰባው መጠናቀቅ በኋላ ነዋሪው የንግድ ድርጅቶችን ሙሉ ለሙሉ መዝጋቱን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ቅዳሜ ያካሄዱትን የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ በርካታ የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።

በከተማዋ የሚገኙ የጸጥታ አባላት የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ትምህርት ቤቶችንና የሲኒማ ቤቶችን በጊዜያዊ እስር ቤትነት እየተጠቀሙ መሆኑን እማኞች አስረድተዋል።

እነዚሁ እስረኞች እንዲፈቱ ጥያቄን በማቅረብ ላይ ያሉት ነዋሪዎች ህዝቡ ያነሳውን ሰላማዊ ጥያቄ አግባብ ያለው ምላሽን እስኪያገኝ ድረስ የስራ ማቆም አድማው እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በሃላፊዎችና በነዋሪው መካከል ማክሰኞ ጠዋት የተካሄደው ውይይት ያለስምምነት መበተኑን የተናገሩት እማኞች ቅዳሜ የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ህገወጥ ብሎ በመንግስት መፈረጁን ቁጣ እንደቀሰቀሰ አክለው አስረድተዋል።

ከቅዳሜ ጀምሮ ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደተለያዩ አካባቢዎች የሚጓዙ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችም አሁንም ድረስ ስራ አቁመው እንደሚገኝ ነዋሪዎች አከለው አስታውቀዋል።

በከተማዋ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ የተጀመረውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የንግድ ተቋማትን ጨምሮ የትራስፖርት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ታውቋል።

ላለፉት ሶስት ቀናቶች የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከቤት ያለመዉጣት ተቃውሞ ሲያካሄዱ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ  በጸጥታ ሃይሎች ለተገደሉ ሰዎች ሻማ የማብራት ስነስርዓት እንደሚያካሄዱ ለኢሳት የደረሰ መረጃ ያመለክታል።

Received on Tue Aug 16 2016 - 17:13:42 EDT

Dehai Admin
© Copyright DEHAI-Eritrea OnLine, 1993-2013
All rights reserved